በንጉሡ “የሥነ-ጥበብ ሚኒስቴር” በሚል ስያሜ ተጀምሮ፤ ወደ “የትምህርትና ሥነ-ጥበብ ሚኒስቴር” ተስፋፍቶ፤ በደርግ ሥርአት ወደ “ትምህርት ሚኒስቴር” ተቀይሮ እዚህ የደረሰ አንጋፋ መስሪያ ቤት ሲሆን፤ የሀገሪቱን ሥርአተ ትምህርት በበላይነት እንዲመራ ሥልጣን የተሰጠው ብሔራዊ ተቋም ነው። በመሆኑም፣ እሱ እሚለው፣ እሱ የሚያደርገው፣ እሱ የሚቀርፀው፣ እሱ የሚያወጣው • • • ሁሉ፣ ከሌሎቹ የዘርፉ ባለ ድርሻ አካላት የበለጠ (ተሰሚነቱ) የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በመሆኑም “እሱ እንዳለው • • •” እያልን እንቀጥላለን።
በደርግ ሥርዓት (በዚህ ወቅት ተቋሙን ኃይለገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) ከ1966-1969፤ ተረፈ ወልደፃዲቅ (ዶ/ር) ከ1969- 1970፤ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ከ1971-1975፤ አቶ ቢልልኝ ማንደፍሮ ከ1975-1979፤ ያየህይራድ ቅጣው (ዶ/ር) ከ1979-1983 በሚኒስትርነት መርተዋል) ትምህርትን የተመለከቱ ተግባራትና ክንውኖች ያሉ ሲሆን፤ እንደ ሀገር በበጎ ከሚነሱት፣ ከዩኔስኮ ”International Reading Association literary prize” የተባለ ዓለም አቀፍ ሽልማትን በ1972 ዓ.ም ካስገኙትና የስርአቱን ስም እያስጠሩ ካሉት የትምህርትና ትምህርት ነክ እንቅስቃሴዎች መካከል ቀዳሚው መሰረተ ትምህርት ሲሆን፣ በ”መሰረተ ትምህርት ዘመቻ” አማካኝነት በርካታ ዜጎች (በተለይም እናቶች) ከማይምነት ተላቅቀዋል። ይህ ስኬት እስከ ዛሬም ድረስ እድሜ ለ• • • እያስባለና የወቅቱን መሪዎች ስም በማስጠራት እያስመሰገነ ይገኛል።
የትምህርት ጥራት (ተደራሽነት ሌላ ነው)ን ለማረጋገጥ በ2004 ዓ.ም የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬትን ያቋቋመው ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሰነድ (ሀገር አቀፍ የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን አፈፃፀም መመሪያ) በመግቢያው ላይ እንዳሰፈረው፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት በትምህርት ቤቶች የሚካሄድ ተከታታይ ኢንስፔክሽን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ [• • •] የኢንስፔክሽን የግምገማ ውጤት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጅ፤ በተለይም የትምህርት ቤት ማሻሻያ መርሀ ግብር አተገባበርን በተመለከተ መረጃ የሚሰጥ ሲሆን፤ በዚህም ትምህርት ቤቶች ቀዳሚ የትኩረት ጉዳዮችን ለመለየት እንዲረዳቸው የሚያካሂዱት ግለ-ግምገማ ተገቢውን ሂደት የተከተለ መሆኑን ለመፈተሽና የማሻሻያ ሃሳቦችን ለመጠቆም የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር አስፈጻሚ አካላትን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት ያዘጋጀው ይህ ሰነድ ትምህርት ቤቶች ያሉበትን የአፈጻጸም ደረጃ ከግብዓት፣ ከሂደትና ውጤት አኳያ ለመመዘን የሚያስችል ሀገር አቀፍ የኢንስፔክሽን ማሕቀፍ የትምህርት ቤቶች ኢንስፔክሽን መመሪያ ማሕቀፍ ማሟያ ሲሆን፣ በውስጡ የኢንስፔክሽን ሂደት፣ የአፈጻጸም ስልቶች፣ ከፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ያሉ አካላት ኃላፊነትና የሥራ ድርሻ እንዲሁም፣ የኢንስፔክተሮች ሙያዊ ሥነምግባርን በውስጡ አካቶ የያዘ መሆኑ ተመልክቷል።
በአፈፃፀም መመሪያው ትርጓሜ መሰረት “ኢንስፔክሽን” ማለት – በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችል የተቋማት ግምገማ በማካሄድ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግና የተጠያቂነት ሥርዓትን የሚያሰፍን የሥራ ዘርፍ፤ “ግብዓት” ማለት – በትምህርት ተቋማት ለመማር ማስተማር ሂደት አስፈላጊ የሆኑ የሰው፣ የገንዘብና የቁሳቁስ • • • ወዘተ ሀብትን የሚመለከት ሲሆን፤ “ሒደት” ማለት ደግሞ – በትምህርት ተቋማት ውስጥ የተማሪዎችን ውጤትና ሥነምግባር ለማሻሻል የሚከናወን ተግባር ነው። (ገጽ 3)
እንደዚሁ ሰነድ ብያኔ፣ “ውጤት” ማለት “በመማር ማስተማር ሂደትና በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ መስተጋብር የሚመጣ የተማሪዎች የእውቀት፣ ክሂሎት እና አመለካከት አወንታዊ ለውጥ” ማለት ሲሆን፤ ”የትምህርት ቤቶች ደረጃ ምደባ” ማለት ደግሞ ትምህርት ቤቶችን ከግብአት፣ ከሂደትና ከውጤት አኳያ በተቀመጡ ስታንዳርዶችና አመልካቾች መሠረት በመለካት ደረጃ የመስጠት ተግባር ነው፡፡
በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ማለትም በአጸደ ሕጻናት፣ በመጀመሪያ ደረጃ፣ በአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች፣ በአማራጭ መሰረታዊ የትምህርት ማዕከላት የመንግሥት፣ የህዝብ፣ የግልና ሌሎች የትምህርት ተቋማት ላይ ተፈጻሚ በሚሆነው በዚሁ ሰነድ ተመሳሳይ ገጽ ላይ እንደ ሰፈረው “ስታንደርድ” ማለት ደግሞ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች በአንድ አይነት ይዘት፣ አሰራር ሥርዓትና በተገኘ ውጤት ላይ ለመለካት የተቀመጠ መስፈርት ነው፡፡
ይህንን አጠቃላይ ትርጓሜ በግንዛቤ ደረጃ ይዘን የአዲስ አበባ ትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በዘርፉ ሲያከናውናቸውና እያከናወናቸው ያሉ የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ስራዎችን እንመልከት።
ባለፈው የትምህርት ዘመን “በ2016 ዓ.ም የእውቅና ፍቃድ እድሳት ከተደረገላቸው የትምህርት ተቋማት [ዝርዝራቸው ተገልጸዋል] ውስጥ በስታንዳርድ ማሟላት/አለማሟላት እና ስርዓተ ትምህርት ትግበራ በተሻለ የፈጸሙ/ያልፈፀሙ ለ2017 የትምህርት ዘመን የሚቀጥሉና የማይቀጥሉ ተቋማትን ለህብረተሰቡ ግልጽ ለማድረግ”፤ እንዲሁም “ለ2017 የትምህርት ዘመን የሚቀጥሉና የማይቀጥሉ የትምህርት ተቋማትን ለመግለጽ” የአዲስ አበባ ትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋዜጣዊ መግለጫ (ሰኞ፣ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 7:00 ጀምሮ) ሰጥቶ ነበር።
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ በጋዜጣዊ መግለጫው፣ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን መዝግበው የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች 1ሺህ 332 የማስተማር ፈቃድ የተሰጣቸው ሲሆን 43 ትምህርት ቤቶች በራሳቸው ጊዜ መቀጠል ስላልቻሉ ፈቃዳቸው ተሰርዟል፡፡ 150 ትምህርት ቤቶች ጉዳያቸው በሂደት ላይ ያለ በመሆኑ ወደ ፊት የሚገለጽ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ የገለጹ ሲሆን፤ 41 ትምህርት ቤቶች የትምህርት ፖሊሲውን ባለመጠበቅ እና ስታንዳርዱን ባለማሟላታቸው ፍቃዳቸው መሰረዙ”ን ማስታወቃቸውና እኛም መዘገባችን የሚዘነጋ አይደለም። “ዘንድሮስ?” የሚለውን ቀጥለን የምንመለከተው ይሆናል።
ዛሬን ስንሰራ ስራችን ወደ ኋላ ቢያንስ ትናንትን ያየ፤ ወደ ፊት ቢያንስ ነገን ያለመ ሊሆን ይገባዋል። ማለትም፣ 2017 ዓ•ምን ስናከናውን ወደ ኋላ 2016 እና ሌሎችንም ማንፀሪያ ማድረጋችን፤ 2018ን ታላሚ ማድረጋችን የማይቀር ጉዳይ ነው። በተለይ ስትራቴጂክ በሆነ ጉዳይ ላይ የምናወራ ከሆነ ወደ ኋላም ሆነ ወደ ፊት ሰፋ አድርጎ ማየት፤ አይቶም ማቀድ ግድ ይሆናል።
ባለፈው ወር (መስከረም) መጨረሻ ላይ የባለስልጣኑ የልደታና አዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የ2016 ዓ•ም የስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ግኝት ሪፖርት እና የ2017 በጀት አመት እቅድ ለባለ ድርሻ አካላት በማቅረብ አወያይቶ ነበር።
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የትምህርት ጥራት ማረጋገጥና ምርምር ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ ወይዘሮ እሴተ ገብረፃዲቅ የ2016 ዓ•ም የስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ግኝት ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፤ በሪፖርቱም በተጠቀሰው አመት በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በየደረጃው ከሚገኙ የትምህርት ተቋማት ለ15 በመሰረታዊ ትምህርት ተቋም፤ ለ3 ኦ (O) ክፍል፤ ለ46 ቅድመ አንደኛ፤ ለ35 የመጀመሪያ ደረጃ፤ በድምሩ 99 የትምህርት ተቋማት የኢንስፔክሽን አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። የስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ከተደረገላቸው የትምህርት ተቋማት ደረጃውን የማያሟሉ ያሉ ሲሆን፤ ተቋማቱ የኢንስፔክሽንን አላማ በአግባቡ በማወቅ እና በመተግበር ደረጃቸውን ሊያሻሽሉ የሚገባ መሆኑ ተገልጿል። (በዚህ ጉዳይ ላይ፣ በሚቀጥለው ሳምንት በዚሁ ገጽ ላይ ከባለስልጣኑ የሚመለከታቸውን የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያዎችን ይዘን እንቀርባለን።)
የ2017 በጀት አመት እቅድ፣ የሌብነትና ብልሹ አሰራር ማክሰሚያ እቅድ፤ እንዲሁም፣ የ2017 ሩብ አመት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የጽሕፈት ቤቱ ዋና ስራ አስከኪያጅ አቶ አንዋር አብዲ በእቅዱ አፈፃፀም መልካም የሆኑ ተግባራት መከናወናቸውን፤ በጋራ በመሆን የጋራ ስራዎችን መስራትና መተጋገዝ ተገቢ እንደመሆኑ፤ እንዲሁም ለህግ ተገዥ በመሆን የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ እንደሚገባ አብራርተዋል። በስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ትንተና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የትምህርት ተቋማትም የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። በሌሎች፣ በባለ ስልጣኑ ስር በሚገኙ ተመሳሳይ ጽሕፈት ቤቶችም ጉዳዩን የተመለከቱ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን፤ እንደ አስፈላጊነታቸው ወደ ፊት የምንመጣባቸው ይሆናል።
የአዲስ አበባው መማር-ማስተማር እንቅስቃሴ ከላይ ያለውን በመሰለ መልኩ እየተካሄደ ሲሆን፣ የሌሎች ክልሎችም የየራሳቸውን አሰራርና አካሄድ ባገናዘበ መልኩ እየተከናወነ ነው ተብሎ የሚታሰብ ከመሆኑ አኳያ ወደሚቀጥለው እንለፍ።
እርግጥ ነው፣ በ1900 ዓ/ም “ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት” በሚል ስያሜ “ሀ” ብሎ የጀመረው የሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት ያልወጣና ያልወረደው የመከራና የለውጥ ሕይወት የለም። የድሮውን ለድሮው ትተን፤ በግፈኛውና እብሪተኛው፣ በኋላም በአበሻ ክንድ በተደቆሰው ፋሺዝም (ከ1928 – 1933 ዓ.ም) ምክንያት የተቋረጠውን ዘ′ለን፤ ወደ ቅርቡና “የስርአተ ትምህርት ክለሳ” (ሴክተር ሪቪው) በሚል ከሚታወቀው አወዛጋቢ የስርአተ ትምህርቱ ማሻሻያ ብንነሳ እንኳን ሴክተሩ ሁሉም በእጁ ያለውን ሁሉ ይዞ የተነሳበት፤ የመጣው ሁሉ “ካልለወጥኩት •••” በሚል ወኔ ዘገሩን የነቀነቀበት፤ አፋሽ አጎንባሹ ሳይቀር ገብቶ የዳከረበት ሴክተር ሆኖ ነው የምናገኘው።
ሴክተሩ በሀሰት የትምህርት ማስረጃ መምህር የተሆነበት ብቻ ሳይሆን፤ በሀሰት የትምህርት ማስረጃ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ እስከ መሆን ድረስ ሁሉ የተቀለደበት ጉደኛ ዘርፍ በመሆን እዚህ ድረስ የዘለቀ ተቋም ነው።
ይህ በሥርአተ ትምህርቱ ላይ እየተፈራረቀ ሲደርስ የኖረው በደል ውጤቱ ወደ ኋላ፣ ወደ ታች እየሆነ መጥቶ መጥቶ ዛሬ ወደሚቀጥለው እርከን መሸጋገሪያ በሆነው ፈተና ውጤት አማካኝነት እየታየ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ (መጻፍም ሆነ ማንበብ የማይችሉ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ሳይዘነጋ) ለብሄራዊ ፈተና ከተቀመጡት መካከል ከሶስት በመቶ በታች “አለፉ” ከሚለው አስደንጋጭ ዜና በላይ ማረጋገጫ የለውም።
ዛሬ ላይ “የትምህርት ጥራት” ችግር ሰንጎ የያዘው የሀገራችን የትምህርት ሂደት ስቃዩ ብዙ የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ስቃዮች መካከል የየክፍል ማስተማሪያ መጻሕፍት (ቴክስትስ)ን በየአመቱ እስከ መቀየር ሁሉ የተደረሰበት ጊዜ መኖሩ ለዘርፉ የከፋ ስቃይ አንዱና ተገቢው ማሳያ ነው። ይህ ደግሞ አይደለም ትውልድ ሊፈጥር እርስ በርሳቸው ሊግባቡ የሚችሉ የአንድ ትውልድ አባላትን እንኳ ማፍራት አልተቻለውም፤ አይቻለውምም። “ኢንስፔክሽን” እነዚህን ሁሉ ይመልከት ወይም አይመልከት ወደ ፊት የምንነጋገርበት ይሆናል።
ባጠቃላይ፣ በቅርቡ ባለስልጣኑ በ2017 ሩብ አመት አፈፃፀም ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት በባለስልጣኑ የእቅድና በጀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ነቢዩ ዳዊት አማካኝነት ባቀረበው ሪፖርት ላይ እንደ ገለፃው የአንደኛው ሩብ አመት የአበይት ተግባራት አፈፃፀም ከ2016 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ሲሆን፤ በድንገተኛ ኤንስፔክሽን አፈፃፀም፤ እንዲሁም፣ በእውቅና ፈቃድ እድሳት ተግባራት፤ በሙያ ብቃት ምዘና ዘርፍ ጥሩ አፈፃፀም ተመዝግቧል።
እንደ ላይኛው ሪፖርት ከሆነ በዚህ በመጀመሪያው ሩብ አመት ጥሩ አፈፃፀም ታይቷል ማለት ነው። ይህ የተሻለ አፈፃፀም በዚሁ እየተሻሻለ ከቀጠለ ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ በቀረበው ሪፖርት ከመማር-ማስተማር ተግባራቸው የታገዱ የትምህርት ተቋማት ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዘግቶ ሁሉም የልቀት ማእከል ሆነው የማናይበት ምንም ምክንያት የለም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም