ቋሚ ማዘውተሪያ ስፍራና የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ፈተና

ኢትዮጵያ ከሳምንት በፊት የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮናን አስተናግዳ በስኬት ከማጠናቀቋም በተጨማሪ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወሳል:: ከ16 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተሳተፉበትን ውድድር በጥሩ ሁኔታ በማስተናገድም ስኬታማ ነበረች:: የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጅምናዝየም ይህን አህጉር አቀፍ ውድድር እንዲካሄድ ትልቅ ሚና ነበረው::

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ለስፖርቱ መሰረታዊ የሆነው የማዘውተሪያ ስፍራ ስለሌለው በአካዳሚው መልካም ፍቃድና ትብብር የሀገር ውስጥና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ያከናውናል::

ስፖርቱ በኢትዮጵያ መዘውተር ከጀመረ የረጅም ዓመት ታሪክ ቢኖረውም፣ ከማዘውተሪያ ስፍራ ችግር መላቀቅ ግን አልቻለም:: ይህ ችግር መኖሩ ደግሞ ስፖርቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ እንቅፋት ሆኖ ይገኛል:: ይህም ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን በሚፈለገው መልኩ እንዳያካሂድ አድርጎታል:: ለስፖርቱ አስፈላጊ ከሆኑ ሌሎች ቁሳቁሶችም በላይ የማዘውተሪያ ስፍራ ዋነኛው ችግር እንደሆነም ፌዴሬሽኑ በተደጋጋሚ አሳውቋል::

ፌዴሬሽኑ የማዘውተሪያና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩበትም በውጤት ደረጃ የተሻለ እንቅስቃሴ እያሳየ ይገኛል:: በዚህም መሰረት ብሔራዊ ቡድኑ በዞንና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ተፎካከካሪ እየሆነ ይገኛል:: ለዚህም ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና በቡድን እና በነጠላ በሶስተኝነት በማጠናቀቅ ከ24 ዓመት በኋላ ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማሳካት መቻሉ ማሳያ ነው::

የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት የሁሉም ስፖርቶች ችግር ቢሆንም የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ከሚጠይቀው ትንሽ ሀብት አኳያ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሰራ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይችላል::

ኢትዮጵያ በቅርቡ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮናን በማስተናገዷ በርካታ ጥቅሞችን አግኝታለች:: ትልቅ ገንዘብ የሚጠይቀውን ውድ የስፖርት ቁሳቁሶች ከዓለም አቀፉ የቴኒስ ፌዴሬሽን ማግኘት ችላለች:: ፌዴሬሽኑ የራሱ የሆነ የማዘውተሪያ ስፍራና የቁሳቁስ ማከማቻ የሌለው በመሆኑ ግን ያገኘውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም እንቅፋት ገጥሞታል::

ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን የሜዳ ምንጣፍ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ የቴኒስ ኳስና እና የመጫወቻ ራኬቶችን ማግኘት ችሏል:: እነዚህን ቁሳቁሶች የሚያስቀምጥበት ቋሚ ማጣቱን የገለፀው ፌዴሬሽኑ፣ ቁሳቁሶቹን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የማይመች ወይም ለጉዳት የሚዳርግ መሆኑ እንዳሳሰበው አሳውቋል::

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ፣ በአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና በውጤትና የተሻለ ደረጃ መያዝና ጠቅላላ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ማስተናገድ እንደተቻለ አስታውሰው፣ በሁሉም ነገሮች ከዝግጅት፣ ካለው ሀብትና የስፖርት መሰረተ ልማት አንጻር ስኬታማ መሆኑን ተናግረዋል::

የተሰጠው የውድድር አመራር ስልጠናም ሁለት ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ ሆነዋል:: የስፖርቱ ትልቁ ፈተና የማዘውተሪያ ስፍራ እንደሆነና ስፖርተኞች በዚሁ ችግር ውስጥ ሆነው የተሻለ ውጤት ማምጣታቸውን የሚያስረዱት ፕሬዚዳቱ፣ ዘላቂ የማዘውተሪያ ስፍራ ቢኖር ከዚህም የተሻለ ውጤት ይመጣል ይላሉ::

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘችው ውድ የሜዳ ንጣፍ ማስቀመጫ ችግር እንደሆነ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፣ ፌዴሬሽኑ የራሱ የሆነ ቁሳቁሶች ማስቀመጫ ቦታ የሌለው በመሆኑ መንግሥት ለፌዴሬሽኑ የራሱ ቋሚ ማዘውተሪያ ቦታ እንዲኖረው መሰራት ይኖርበታል ብለዋል::

አህጉር አቀፍ ውድድሩና ጠቅላላ ጉባዔው በስኬት እንዲጠናቀቅ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ ውድድሩ የተካሄደበት አካዳሚ ካለው የስፖርት ማዘውተሪያ እጥረት አኳያ፣ ጅምናዝየሙን ካለምንም ወጪ መፍቀዱን አመስግነዋል:: የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለውድድሩ ለመጡ ሀገራት የ20 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ትልቅ ድጋፍ ማበረከቱንም ጠቅሰዋል:: አየር መንገዱ ወደ ፊት በስፖርቱ ድጋፉን ለመቀጠል፣ ከአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙንም አክለዋል::

ፌዴሬሽኑም በቀጣይ ስፖርቱን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ትኩረት ሰጥቶ ታዳጊዎች ላይ ለመስራት የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል:: ለዚህም ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ያገኘውን የቁሳቁስ ድጋፍ በአግባቡ እንዲጠቀም የማዘውተሪያ ስፍራ ጉዳይ ላይ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል::

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You