“ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሥራዎቿን ከምንጊዜውም በላይ ማጠናከር አለባት” – የፖለቲካ ምሁር ወርቁ ያዕቆብ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሥራዎቿን ከምን ጊዜውም በላይ ማጠናከር አለባት ሲሉ የፖለቲካ ምሁሩ ወርቁ ያዕቆብ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የኢንተራክሽን ፎር ቼንጅ ኢን አፍሪካ ዋና ዳይሬክተርና የፖለቲካ ምሁሩ ወርቁ ያዕቆብ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ ከግብጽና ከተለያዩ ሀገራት የሚነሳው የፖለቲካ ጫና እያየለ በመሆኑ የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ሥራው ይበልጥ መጠናከር አለበት።

የትኛውንም ችግር በንግግር መፍታት ይገባል የሚለው የኢትዮጵያ አቋም ለዲፕሎማሲ ስራው አጋዥ መሆኑን አንስተው፤ ከወደብ ጋር ተያይዞ፣ በዓባይ ግድብ፣ በተባበሩት መንግሥታት ጉዳዮችና በተለያዩ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ሥራዎች ላይ ጠንካራ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል።

ግብጽ በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ ስትንቀሳቀስ ትስተዋላለች ያሉት የፖለቲካ ምሁሩ፤ በአሁኑ ጊዜም ይህን እንቅስቃሴዋን ከሚደግፉ ሀገራት ጋር እየሠራች መሆኑን አስታውሰዋል።

ከለውጡ ማግስት በኋላ ኢትዮጵያ ከኤርትራና ሶማሊያ ጋር የመሰረተችው ወዳጅነት በግብጽ ጣልቃ ገብነት እየሻከረ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም በቀጣናው ያለውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለመቆጣጠር የዲፕሎማሲ ሥራው ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

የግብጽ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው ሀገራት የማይጠቅም በመሆኑ ኢትዮጵያ ይህን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ በሁሉም ሚሲዮኖቿ መሥራት እንደሚኖርባት ገልጸዋል፡፡

የግብጽ መንግሥታት ፀብ አጫሪ የሆኑ እንስቃሴዎችን አደረገ ማለት ሕዝቡ ግጭትን ይደግፋል ማለት አይደለም የሚሉት ወርቁ (ዶ/ር)፤ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች አስፈላጊ መሆናቸውን አመላክተዋል።

እንደ ዶክተር ወርቁ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራት አይደለም ሀያላን ነን የሚሉ ሀገሮች እንኳን መሬቷን ተመኝተው አላገኙትም፡፡ ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጦርነቶች ማሳያ ናቸው፡፡ ሀገሪቱ ምንም እንኳን በውስጥ ግጭት ብትታመስም ለውጪ ጠላት ግን እጅ የምትሰጥ አይደለችምና የዲፕሎማሲ ሥራውም ይከብዳታል ተብሎ አይጠበቅም።

ግብጽ ኢትዮጵያን ጦርነት ገጥማ የምታሸንፍበት ምንም አይነት አካሄድ የለም ያሉት ዶክተር ወርቁ፤ ሆኖም በጦርነት ብዙ ውድመት ስለሚኖር ያለውን ችግር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመፍታት ውጥረቱን ማርገብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዘዋወር ሀገሪቷ ሰላም ወዳድ መሆኗን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳቱን መቀጠል እንዳለበት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ልታሳካቸው የሚገቡ ብሔራዊ ጥቅሞቿንም ቢሆን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንደምትፈጽም ማስገንዘብ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ዶክተር ወርቁ አክለውም፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የማጠናከር ሥራዎችን መሥራት ይኖርባታል፡፡ የዲፕሎማሲ ሥራው ፀብ ቀስቃሽ ጉዳዮች ሲነሱ የሚጠናከር ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋብ የሚል ሳይሆን ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት አድርጎ በዘላቂነት መከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You