አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ የዓለም የንግድ ማዕከል ለማድረግ ከጂቡቲ ወደብ በተጨማሪ የባህር በር ባለቤት መሆን ያስፈልጋል ሲሉ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ፀጥታ ትምህርት ክፍል መምህር የኔነሽ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።
መምህር የኔነሽ ተመስገን (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ከሆነች በምሥራቅ አፍሪካ የዓለም የንግድ ማዕከል የመሆን እድሏ ይጨምራል፡፡
የእራሷ ወደብ ሲኖራት በጂቡቲ ላይ ያላት ጥገኝነት ይቀንሳል፤ በቀጣናው የሚኖራት ተጽዕኖ ይጨምራል ሲሉ አስረድተዋል። አንዳንድ አካላት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ እንዳይጨምር በተቻለ መጠን የባህር በር ባለቤት እንዳትሆን የማድረግና የቀጣናው የኃይል ሚዛን እንዳይኖራት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ጊዜ ይውሰድ እንጂ የማይቀር ጉዳይ ነው ያሉት መምህርቷ፤ የባህር በር ባለቤት መሆን ከቻለች በምሥራቅ አፍሪካ ዘርፈ ብዙ ለውጥ ይመጣል ሲሉ ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ እድገት የባህር በር አንዱና ዋነኛው መሰረት መሆኑን ጠቁመው፤ የንግድ ፍሰት ለመጨመርና የስራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ እንደሚያግዝ አመላክተዋል።
የወጪ ገቢ ንግዶችን በማሳደግ የትራንስፖርት ወጪን ለመቀነስ እንዲሁም የውጪ አልሚዎች በስፋት ለመሳብ የባህር በር አስፈላጊነት አያጠያይቅም ሲሉ አስረድተዋል። እንዲሁም ኢትዮጵያ የቀጣናው ማዕከል የመሆን እድል እንድታገኝ ያደርጋታል ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር የኔነሽ ማብራሪያ፤ እ.ኤ.አ በ2018 በኢትዮጵያ ለውጥ ሲመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደተለያዩ ሀገራት ጉብኝት አድርገዋል። የጉዞው ዋና አላማም ቀጣናዊ ውህደት እንዲኖር በተለይ ደግሞ ድንበር የለሽ አፍሪካ እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ነጻ የንግድና የሰዎች ዝውውር እንዲኖር በማድረግ የጋራ እድገትን ለማምጣት ይረዳል፡፡
ከጎረቤት ሀገራት ጋር የመንገድ ትስስር ለመፍጠር ብዙ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አስታውሰው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ የተረጋጋች ሆና የጎረቤት ሀገራትን ማስተባበር እንዳትችል ከውስጥና ከውጭ ትልቅ ተጽዕኖዎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጉዞ መቀጠል አለበት ያሉት ዶክተር የኔነሽ፤ የባህር በር ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገትና የፖለቲካ ተሰሚነት በዓለም መድረክ እንደሚጨምር አንስተዋል።
በዓለም ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ይዛ ወደብ አልባ የሆነች ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ ይህ ሊቀጥል አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ ወደብ ላግኝ አላለችም፤ የኢኮኖሚ ውህደት እናምጣ፤ ድንበር አልባ ቀጣና መፍጠር ነው ፍላጎቷ ብለዋል።
የኢትዮጵያ በጋራ የማደግ አካሄድ ያስፈራቸው ኃይሎች በቀጣናው ግጭቶች እንዲጨምሩ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ግጭት ውስጥ ብትሆንም ካለባት ችግር አንጻር መረጋጋት እስኪመጣ መጠበቅ ስለሌለባት ፊቷን ወደ ሶማሌላንድ ማዞሯን አስታውቀዋል፡፡ ከሶማሌላንድ ጋር የነበረው የባህር በር ስምምነትም ተገቢና ወቅቱን የጠበቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አንድ ሀገር ለማንኛውም አገልግሎት የሚውልን ወደብ መያዝ ይችላል፤ ይህን እድል የመወሰን ግዴታ በፈላጊው ሀገር ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያም ወደብ ያስፈልገኛል ካለች ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመነጋገር መፍትሔ የማምጣት ሕጋዊና ዓለም አቀፍ መብት አላት ሲሉ አስረድተዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም