የኢኮኖሚ (ኢኮኖሚያዊ) እኩልነትም ሆነ እኩል ተጠቃሚነት (Equity) መልኩም ሆነ መንገዱ ብዙ ነው። እንደየ ሀገሩ ይለያያል፤ እንደየ መንግሥታቱ ርእዮት ይቀያየራል፤ እንደ አህጉርና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችና ይዞታዎች ልዩነቶች ይስተዋሉበታል። በተለይ፣ እንደየ ሀገራቱ የእድገትና ብልፅግና ደረጃ የፅንሰ ሀሳቡ ገቢራዊነትም በዛው ልክ ዥንጉርጉር ነው። አንዳንዱ ጋ ሞልቷል፤ አንዳንዱ ጋ ሽታውም የለም።
ሀገራት (ቱጃር ግለሰቦችን ጨምሮ) ከዜጎቻቸውም አልፈው ሌሎችን “ተጠቃሚ” የሚያደርጉባቸው፤ ተጠቃሚነታቸውንም የሚያረጋግጡባቸው፤ ሀገር ያፈራው ኢኮኖሚ ደሀው ዘንድ ሳይቀር እንዲደርስ የሚያደርጉባቸው በተቋማት የተደገፉ የአሰራር ዘዴዎች ያሏቸው ሲሆን፤ አንዱም ፋውንዴሽን ነው።
ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቱጃሮች ጥቂት ግለሰቦች አለያም መንግሥት ነው። በሶሻሊስት ሀገራት ዘንድ የሀገሪቱ ሀብት በመንግሥታቱ ስር ነው። በሌላ በኩል በካፒታሊስት ሀገራት ውስጥ (በአሜሪካኖቹ በአንድ ወቅት አንድ በመቶ የሆኑትን ቱጃሮችና መንግሥት ለእነሱ የሚያደርገውን ድጋፍ በመቃወም “እኛ 99 በመቶ ነን” እንዳሉት) ደግሞ የሀገሪቱ ሀብት በጥቂቶች መዳፍ ውስጥ ነው። በመካከል ላይ ያለው (ቅይጥ ኢኮኖሚ?) ብዙም ገፍቶ በመውጣት ከፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልም ሆነ እኩልነት ጋር ትከሻ ለትከሻ ቆሞ ሲሄድ አይታይም። አንዳንዴ እንደውም ከንድፈ – ሀሳብ ደረጃ እንኳን የዘለለ አይመስልም።
ይህን ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል (የዜጎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት) በተመለከተ በርካታ ሀገራት ብዙ ሥርዓቶችን (ሲስተምስ)ና አሰራሮችን ዘርግተው ዜጎችን ተጠቃሚ ሲያደርጉ ይታያሉ። ከእነዚህ ተቋማዊ አሰራሮች አንዱ ደግሞ ፋውንዴሽን ማቋቋም ነው። ከዚህ አኳያ፣ ከሀገራቸውም አልፈው እዚህ እኛ ድረስ እጃቸውን የዘረጉ በርካቶች ናቸው። ከእነዚህም አንዱ በተለይ በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ላይ አተኩሮ የሚንቀሳቀሰው የ”ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን” (ፊላንትሮፒ) ነው።
የዓለማችን ቁጥር 1 ቱጃሩ ቢል ጌት በግብርናው ዘርፍ ላይ ከማተኮር አኳያ እጃቸው ረዘም ይበል እንጂ፣ በፋውንዴሽናቸው አማካኝነት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እጃቸውን በመዘርጋት ይታወቃሉ። ለማሳያ ያህል እሳቸውን ከጠቀስን ወደ ሀገራችን በመመለስ “ፋውንዴሽን” ያለበትን ሁኔታ እንመልከት።
በሀገራችን ፋውንዴሽኖች “አሉ” ብሎ መነሳት መቀለድ ነው የሚሆነው። በመሆኑም “የሉም” ብሎ ከመደምደምም በፊት ቢያንስ በሃሳብ ደረጃ ቦግ/እልም ይሉ የነበሩትን እንጥቀሳቸውና ወደ “መሆን ያለበት” ሃሳባችን እንመለስ።
በሀገራችን አክሊሉ ለማ ፋውንዴሽን (ከነበሩት ሁሉ እሱ ነው ነፍሱ ያለው)፣ በአሉ ግርማ ፋውንዴሽን፣ መለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ወዘተ ተብሎ “የመሰረት ድንጋይ” ከመጣል ያልተናነሰ የማስተዋወቂያ ፕሮግራሞች ይካሄዳሉ። ንግግሮች ይደመጣሉ። ጭብጨባዎች ይስተጋባሉ • • • ከዛ ወደ ቤት። ከዛ • • • ዝም፣ ጭጭ • • • በቃ።
እንደ ተነገረን ከሆነ፣ ምናልባት በቅርብ ጊዜ ውስጥና የመጨረሻው (የቅርቡ) ፋውንዴሽን “የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ፋውንዴሽን” ነው፤ ያለበትን ሁኔታ ባናውቅም እነ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋን ጠይቆ አንድ ነገር የሚለን እስኪመጣ ድረስ ይህንን ፋውንዴሽን እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው …ከማለት እንቆጠባለን።
ሥርዓት ባለው ሁኔታ፣ ሕግና ደንብን በተከተለ አካሄድ፣ ሰዎችን (ዜጎችን) ሊጠቅም በሚችል መልኩ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ እድገት ሊደግፍ (ሊያፋጥን) በሚችል አሰራር ከሚደረጉ ተቋማዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ በእውቅ ሰዎች ስም የሚቋቋም (ወይም፣ ራሳቸው በሕይወት እያሉ የሚያቋቁሙት) ፋውንዴሽን ነው።
በሀገራችን ፋውንዴሽን እና ምንነቱ በአግባቡ ይታወቃል ለማለት ድፍረትን ይጠይቃል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እከሌ ደግ ነው፣ ገንዘብ ይሰጣል፤ እንትና ንፉግ ነው፣ ምንም አይደማውም (ለምሳሌ፣ ጥያቄው “ፋውንዴሽን አቋቁሟል ወይስ አላቋቋመም?” (ያለ ማቋቋም መብቱ እንዳለ ሆኖ) መሆን ሲገባው፣ ኃይሌ ገብረሥላሴን በሬዲዮ ሳይቀር ሲወቅሱ የነበሩ ሰዎች እንዳሉ እየታዘብን ነው።
እከሌ ይሄንን ያህል ሚሊዮን ለእንትና ሰጠው/ጣት፤ መኪና ገዝቶ ሰጣት/ጠው • • • እና የመሳሰሉ አስተያየቶች ብዙ ጊዜ ከተማውን ሲያጨናንቁ (“ቶክ ኦፍ ዘ ታወን” ሲሆኑ) ይስተዋላል። እውነቱ ግን፣ ከግል ዝና በዘለለ ይህ ሁሉ የ”አባ መስጠት” ተፍ ተፍ ሀገርንም ሆነ ማህበረሰብን ሊለውጥ የሚችል ምንም ረብ የሌለው ተግባር መሆኑ ነው።
በምትኩ፣ እንትና ፋውንዴሽን አቋቋመ፤ እከሌ ወጣቶች በነፃ ስልጠና የሚያገኙበት ማሰልጠኛ ማእከል ገነባ፤ እንትን ተቋም ወጣቶችን አደራጅቶና አሰልጥኖ ወደ ስራ አሰማራ፤ እነ እከሌ ማህበረሰቡ በነፃ የፍትህ አገልግሎት የሚያገኝበትን ተቋም አቋቋሙ፤ እንትና ባንክ “ታለንት” ያላቸውን ወጣቶች አሰባስቦ፣ መልምሎና አሰልጥኖ፣ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ፣ በጀትና አማካሪ መድቦ ወደ ስራ እንዲገቡ አደረገ (ይህ በሌላው ዓለም ባሉ የግል ባንኮች እጅግ ቀላሉና ሁሌም የሚደረግ ነው) • • • ወዘተ ሲባል አይሰማም። ታዲያ ካልተሰማ እንዴት አድርጎ “በሀገራችን ፋውንዴሽን እና ምንነቱ በአግባቡ ይታወቃል” ማለት የሚቻለው?
እንደሚታወቀው፣ እኛ ሀገር “በደንብ” እንደሚታወቀው “አክሲዎን” እንጂ ሰብአዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋም አይደለም። እኛ ሀገር በሚገባ ስሙ የሚጠራና ተገቢውን እውቅና የሚያገኘው በየመንገዱ የሚመነዝርና ሻሞ የሚል እንጂ፣ እንደ አበበች ጎበና ያለው ለመታወቅ ምእተ ዓመትን ይፈጅበታል። የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የበርካታ ትምህርት ተቋማት ግንባታ ብዙም እየተወራለት ያለ ሰብአዊ ተግባር አይደለም። እኛ ሀገር ዝናው የሚናኘው መሸታ ቤት የከፈተ እንጂ ሰው ተኮር እንቅስቃሴን ያደረገ አይደለም። የእኛ ሀገር ጭብጨባ ለሚናገር እንጂ ለሚሰራ ሰው አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም። ብዙ ማለት ይቻላል።
በዚህ ጽሑፍ አማካኝነት ለማለት የተፈለገው “በሌላው ሀገር የተትረፈረፈው ፋውንዴሽን እዚህ፣ እኛ ሀገር ለምን ደብዛው ጠፋ?” የሚለው ነው። የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ፣ በጥቂቶች የተያዘ ኢኮኖሚ፣ በሙስናም ይሁን ሌላ የተግበሰበሰ ኢኮኖሚ ወዘተርፈ ወደ ደሀው፣ በገዛ ሀገሩ ያጣ የነጣው ክፍል የሚሄደው ፋውንዴሽንና እሱን በመሳሰሉ ተቋማት አማካኝነት መሆኑ ይታወቃል።
በግብረ ሰናይ ድርጅቶች አማካኝነት ነፍስ ከሞት እንደሚተርፍ ሁሌም የሚታይ እውነት ነው። ይሁን እንጂ፣ ይሄ ሁሉ “የሕፃናት • • •” ባለበት ከተማ፤ ይሄ ሁሉ “የሴቶች • • •” ባለበት ሀገር፤ ይሄ ሁሉ “የአረጋዊያን • • •” (መቄዶኒያን አይመለከትም) ባለበት ምድር መሬት ላይ ምንም አለመታየቱ እንቆቅልሽ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ ምናልባት የሀገራችን ቅን ባለሀብቶች በሚያቋቁሟቸው ፋውንዴሽኖች አማካኝነት ወደ ፊት (በቅርቡ) ለውጦችን እንመልከት፤ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍሉም ተግባራዊ፣ ሰብአዊ ድጋፉም እውን ሆኖ የምናይበት ጊዜ ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም