የአዲስ አበባን አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ

የልማት ተነሺዎችን ጉዳይ ፈጽሞ ባልተገባ፤ ባልተደረገና እየተፈጸመ ካለው ነባራዊ እውነት በተቃራኒ በማጮህ አጀንዳውን ለፖለቲካ ትርፍ እንደ መጫወቻ ካርድ መጠቀምን ጨምሮ የማህበራዊ ሚዲያ መሸቀያ ማድረግ ዜጎች ላይ ከሚያስከትለው የሥነ ልቦና ቀውስ ውጭ አንድም የሚያመጣው መልካም ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።

በሀገርም ይሁን በከተማ ደረጃ፤ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችላሉ ተብለው የተለዩ ልዩ ልዩ ተግባራዊ ርምጃዎች በሚወሰዱበት ወቅት፤ ለዘላቂ የሀገር ግንባታ የሚሆኑ ተግባራትን በጋራ መፈጸምና የድርሻን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት መቻል ከዳበረ የሀገር ፍቅር ቀናኢ አመለካከት የሚመነጭ ነው ።

የቱንም ዓይነት ስም የተሰጠው የፖለቲካ ድርጅት፤ የግለሰብ አቋምም ይሁን በምንም ጉዳይ ላይ ያለ አስተሳሰብ በጊዜ ሂደት የሚሻርና የሚለወጥ ነው ፤ በሚያንጽ አግባብ ለሀገር ግንባታ የበኩልን አስተዋጽኦ ማበርከት መቻል ደግሞ ለትውልድም ለሀገርም በታማኝነት የሚቀመጥ ዐሻራ ሆኖ ስምን ከመቃብር በላይ እንዲውል የሚደረግ እውነታ ነው።

ለዚህም ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንና ቅድም አያቶቻችን ልዩነቶችን ተሻግረው ሀገረ መንግሥትን በማጽናትና ጠብቀው በማቆየት እንዲሁም ለሀገር ግንባታ የሚበጅ በጎ ዐሻራን በአንድነት በማኖር ህያው ምሳሌ ሆነው ዛሬም ድረስ የሚታወሱ ናቸው።በሀገር ጉዳይ ያላቸውን አንድነትና ምሳሌነት መከተል ስለ ሀገር ፍቅር በቅንነት የሚከፈል ዋጋ እንጂ ለየትኛውም ስብስብና ግለሰብ ጥብቅና እንደመቆም ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በእጅጉ ዘግይቶም ቢሆን መዲናችን አዲስ አበባ፤ የሁላችንንም በጎ ዐሻራ የሚጠይቅ የኮሪደር ልማትን ያካተተ የስማርት ስቲ የከተማ ልማት ፕሮግራምን ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች። በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከአንድ ምዓተ- ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ፤ በአዝጋሚ የለውጥ ሂደት ደረጃዋን በማይመጥን ብሎም የነዋሪዎቿን ሕይወትና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በሚያከብድ ውስብስብ የመሠረተ-ልማት ችግር ተይዛ ቆይታለች።

ችግሩ ፈጽሞ ለሚቀጥለው ትውልድ መሻገር የሌለበት አፋጣኝ የማስተካከያና የእርምት ርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ተግባር ሆኖ በበርካቶች ሲጠየቅም/ ሲጠበቅ የነበረ ጉዳይ ነው።ለዚህም በወርሀ መጋቢት 2010 ዓ.ም፤ የተደረገውን የመንግሥትና የሥርዓት ለውጥ ተከትሎ በምርጫ ወቅት፤ ከተማዋን አስፈላጊ መሠረተ- ልማቶችን በመዘርጋት በሚፈለገው አግባብና ልክ ለማደስ በመንግሥት ደረጃ ቃል የተገባ መሆኑም ይታወሳል።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ርእሰ ከተማ ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗም ባሻገር ከአሜሪካ ኒዮርክና ከሲዊዘርላንዷ ጄኔቫ በመቀጠል ሦስተኛ፤ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉባት የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና አገልግሎት እየሰጠች ትገኛለች።

ይህም ሆኖ ግን ከተማዋ በመንግሥታት የለውጥ ሂደት ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ጨምሮ የነዋሪዎቿን አዳጊ ፍላጎቶች ታሳቢ ባደረገ አኳኋን መሠረተ ልማቶቿ በሚፈለገው ልክና አግባብ ባለቤት አግኝተው ሳይበጅላት ኖሯል።ችግሩ በተመሳሳይ መልኩ ለሚቀጥለው ትውልድ መሻገር የሌለበት በመሆኑ፣ የአሁኑ ትውልድ ችግሩን በልኩ ተረድቶ ደፋር የእርምት ርምጃዎችን መውሰድ ላይ ይገኛል።

በዚህም ከአንድ ክፍለ ዘመን ለሚበልጥ ጊዜ እያለፈች ካለችበት ዝግመታዊ የከተሜነት የለውጥ ሂደት በተቃራኒ፤ ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት ፈጣንና መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ዘመን ተሻጋሪ ማዘጋጃ ቤታዊ ዓለም አቀፍ መስፈርትና ተሞክሮዎችን በተከተለ አግባብ በጥራት በ24/7 የሥራ ባሕል መሻሻል መርህ እያከናወነ ይገኛል።

በከተማዋ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራን ጨምሮ፤ በሌሎችም ከለውጡ ማግስት አንስቶ 24/7 በሚል አዲስ የሥራ ባሕል፤ ለሕዝብ የላቀ ጠቀሜታ ያላቸው የልማት ሥራዎች በአዋጭነት ጥናት እየተለዩ ተገንብተው ለሕዝባዊ አገልግሎት እንዲውሉ እየተደረጉ ነው።ይህም በስፋት በከተማዋ ሁሉም አካባቢዎች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ይስተዋላል።

በመሀል አዲስ አበባ 50 ዓመት ያለፋቸው የጭቃ ቤቶች፣ ያለ አንዳች እድሳትና ማሻሻያ፣ በዕድሜ ብዛት እየወላለቁና እየዛጉ እስከ መቼ ሊቀጥሉ ይችላሉ? ከተማዋ ገና በምትቆረቆርበት ወቅት ተዘረግተው የነበሩ የመሠረተ ልማቶች ጉዳይስ? ዘመናዊ የከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥርዓት ከመዘርጋት አኳያ ያለው እውነታስ?

ከተማዋ እንድታድግ እና እንድትዘምን፣ የነዋሪዎች የኑሮ ደረጃና የሥራ ሁኔታ እንዲሻሻል ከተፈለገ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ዘመን የደረሰባቸውን የስማርት ሲቲ ፕሮግራሞች ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ ከማድረግ በስተቀር ሌላ ሁለተኛ አማራጭ ይኖረን ይሆን?

አሁን ላይ ካለው ተጨባጭ የከተማዋ እውነታ አኳያ ሁለተኛ አማራጭ እንደማይኖረን በመንግሥት ደረጃ ታምኖበት ወደ ሥራ ተገብቷል፣ እስካሁን ባለው አካሄድም ሁኔታዎች ተስፋ ሰጭ ስለመሆናቸው በከተማዋ በጥራት እና በፍጥነት የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች እና የከተማ እድሳቶች ማሳያ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተገባደደው የ2016 በጀት ዓመት በስማርት ሲቲ የከተማ ልማት ፕሮግራሞች ማሕቀፍ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የኮሪደር ልማት ፤ በሁሉም ረገድ የሚገለጽ ዘላቂ ዕድገትና የነዋሪውን አዳጊ ፍላጎቶች ማዕከል በሚያደርግ አኳኋን የልማት ዕቅዶችን ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ ማድረግ እያስቻለ ነው።

የኮሪደር ልማት ሥራው ዋነኛ ዓላማ ከተማዋ በሁሉም ረገድ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን እንድታሟላ ማስቻልና ለነዋሪዎቿ ምቹ የመኖሪያ ከባቢ መፈጠርን የሚያረጋግጡ መሠረተ ልማቶች እንዲኖሯት ማድረግ ነው።በዚሁ አግባብ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ከተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያዋሀዱ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው።

የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት ሥራ በሚመለከት በሀገር ውስጥ የሌሉ አካላት ከተማ አስተዳደሩ በሁለቱም ዙሮች ለልማቱ ተነሽዎች እያቀረበ ካለው ካሳ ማካካሻና የማቋቋሚያ ሥርዓትን በሚቃረን አኳኋን፤ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ያለ አንዳች ካሳና ማካካሻ እየተነሱ ናቸው።የሚል ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጩ መሆናቸው ሲታይ ደግሞ የልማቱን ዓላማ ካለመረዳት አሊያም በተለመደው አግባብ ሥራዎችን ለማጣጣል ታስቦ የሚደረግ መሠረተ-ቢስ ውንጀላ ይመስላል።

በመንግሥት የሚከናወኑ የከተማ ልማት ሥራዎችን ጨምሮ ሌሎችንም የመልካም አስተዳደር ሥራዎች፤ ካለ አንዳች ተጨባጭ ማስረጃ በማጣጣል ከማህበራዊ ሚዲያዎች ለሚገኝ ሽርፍራፊ ገንዘብ ቀኑን ሙሉ ሲዋሹ የሚውሉ አካላትን ጨምሮ ፖለቲካዊ ትርፍን ከአማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ ውጭ ጊዜ ባለፈበት የማጣጣል አባዜ የሚያገኙ የሚመስላቸው አካላትም ከወዲሁ መታረም ቢችሉ መልካም ይሆናል።

የጩኸቱ መበርከት በቂ መረጃ ለሌለው ሰው ለተነሺዎች በመቆርቆር የሚደረግ ሊመስል ይችላል። እውነታው ግን እንደሱ አይደለም። ጩኸቱ ከማህበራዊ ሚዲዎች የሚገኝ ሽርፍራፊ ገንዘብና የፖለቲካ ትርፍን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት አንድ አካል ነው።ለዚህ ደግሞ ተነሺዎች በተለያዩ ወቅቶች በራሳቸው አንደበት የሚናገሩትን በቀና መንፈስ መስማት በቂ ነው።

ለሕዝብና ለሀገር የመቆረቆር ቅን ልቦና ያለው አካል በሚቻለው ሁሉ ዜጎችን በማቋቋም ሂደት ችግሮች እንዳያጋጥሙ ማድረግ፤ መንግሥት በየደረጃው ከሚያከናውናቸው የማካካሻ ተግባራት በተጓዳኝ በቡድንም ይሁን በተናጠል ቀርቦ የድርሻን ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት መቻል ፤ ሌሎችን የሚያስተምር የስልጡን ዜጋ መገለጫ መሆኑ እሙን ነው።

ከተማ አስተዳደሩ ለኮሪደር ልማት ተነሽዎች ብቻ የሚውል በጀት አስቀድሞ በማዘጋጀት ካሳ ተለዋጭ/ምትክ መሬት በየደረጃው ላሉ የንግድ ሥራዎች የሚሆኑ የመሥሪያ ቦታዎችን ጨምሮ ለከተማ አኗኗር የሚመጥኑ ቤቶችን በማዘጋጀት የልማቱ ተነሽዎችን በዚሁ አግባብ እያስተናገዱ ነው፤ ይህ በአብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ዘንድ ይታወቃል።

ሁለተኛው ዙር የከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራም ቢሆን እንደ መዳረሻዎቹ ስፋት ሁሉ በመጀመሪያ ዙር ከነበረው በሦስት ዕጥፍ የሚበልጥ ነው።እንደ አጠቃላይ የሁለተኛው ዙር የልማት ሥራው ስፋት በመጀመሪያው ዙር ለ50ሺህ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሮ ከነበረው በላይ ለበርካታ የእንጨት፣ የብረታ ብረት፣ የኤሌክትሪክ፣ የኮንክሪት፣ የአስፋልት ንጣፍና ግንበኞች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው።ይህም ወደ ሥራ ተቋራጭነት እስኪሸጋገሩ ድረስ አቅም እንዲፈጠርላቸው የሚያስችላቸው ይሆናልም ተብሎ ይጠበቃል።

በርካታ የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ አካባቢዎች የተፋፈጉ፣ ለኑሮና ለሥራ፣ ለእንቅስቃሴና ለጤናም የማያመቹ አልፎም የስጋት ቀጠና መሆናቸው እምቅ አቅማቸው እንዳይታይ ከማድረጉም በላይ ዕድገት እንዳያሳዩ አምክኗቸዋልም።ይህንን ተከትሎ የዜጎች የማደግ ፍላጎትና ኑሯቸውን የማሻሻል ጥረትም ተከርቸም የተቆለፈበት እንዲሆን አድርጓልም።

የከተማዋ የኮሪደር ልማት ለዜጎች ይዞት በመጣው መልካም ዕድል ሳቢያ፤ እጅግ የተጎሳቆሉና ለመኖር ምቹ ያልሆኑ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ የንግድ ቤቶች ውስጥ የነበሩ በርካታ የልማት ተነሺ ነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ እና መሥሪያ ቦታ እንዲያገኙም አስችሏቸዋል። በአገልግሎትና በአቅርቦት ሥራ ላይ የተሰማሩ ብዙሃን የንግዱ ማህበረሰብ አካላት በተመሳሳይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፤ በልማቱ ሳቢያ የተፈጠረው ሰፊ የገበያ ትስስር ተጠቃሚ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማን፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነትና የነዋሪዎቿን በሁሉም ረገድ የሚገለጽ አዳጊ ፍላጎቶች በሚፈለገው ልክና ፍጥነት ማረጋገጥ እንዲቻል፤ የተጀመሩ ጥረቶች አሁን ላይ እያስመዘገቡት ካለው ስኬት አኳያ፤ ከተማዋ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራት ተወዳዳሪነት ትርጉም ያለው እንደሚሆን ይታመናል።

በጋዜጠኛና ሲኒየር የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ላንዱዘር አሥራት

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You