በከተማዋ ዘጠኝ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፡– በ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዘጠኝ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 50 ኢንቨስተሮች ፈቃድ መስጠቱን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ ወደውጭ ከተላኩ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርቶች ከ185 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱም ተመላክቷል፡፡

የደብረ ብርሃን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከተማዋን የኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተማ በማድረግ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡

በ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ስድስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 60  ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፤ ዘጠኝ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 50 ባለሀብቶች ፈቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡

ፈቃድ ባወጡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ለስድስት ሺህ 188 ዜጎች የሥራ እድል ሊፈጠር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ በአግሮ ፕሮሰሲንግ 27፣ በጨርቃጨርቅ ሶስት፣ በኬሚካል 20፣ በእንጨትና ብረታ ብረት 16 በአገልግሎት ዘርፍ ሰባት በድምሩ 66 ፕሮጀክቶች መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ስድስት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ወደ ግንባታ ለማስገባት ታቅዶ የ12 ፕሮጀክቶች ግንባታን በማስጀምር ከእቅድ በላይ መከናወን መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ አምስት አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መግባታቸውን እና የአምስት ፕሮጀክቶች ግንባታ መጠናቀቁንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደ ውጭ ምርታቸውን ከሚልኩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 185 ሚሊዮን 378 ሺህ ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

ገቢ ምርትን የሚተኩ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርቶችን በመለየት፣ ተኪ ምርት የሚያመርቱ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍና የምረት መጠንን እንዲጨምሩ በማድረግ አምስት ሚሊዮን 711 ሺህ 855 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል የመሬት ካሳ ከፍለው ሰባት ባለሀብቶች መሬት ያገኙ ሲሆን፤ ስድስት ነጥብ 27 ሄክታር መሬት መተላለፉን ጠቁመዋል፡፡ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውልና መሰረተ ልማት የተሟላለት 73 ነጥብ 88 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ 39 ነጥብ 72 ሄክታር ማስተላለፍ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You