“የናይል ትብብር ስምምነት የቅኝ ግዛት ውሎችን ግብዓተ መሬት የሚያስገባ ነው” – ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በሻህ

የዛሬ የወቅታዊ እንግዳችን ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በሻህ ይባላሉ። የቀድሞ ዲፕሎማትና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ሲሆኑ፤ በአሜሪካ ሀገር በኖርዝ ካሮላይና እና በተለያዩ ዩኒርሲቲዎች ለረጅም ዓመታት በመምህርነትና በተማራማሪነት የሠሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ናቸው ። ፕሮፌሰር ብሩክ በናይል ወንዝ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ዙሪያ ማብራሩያ ለመስጠት በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸው ምሁር በመሆናቸው በጉዳዩ ዙሪያ እንግዳችን እንዲሆኑ መርጠናቸዋል። መልካም ንባብ ፡-

አዲስ ዘመን፡- የናይል ወንዝ የትብብር ስምምነት ላለፉት አስር ዓመታት የመጣበትን በፈተናዎች የተሞላ መንገድ እንዴት ያዩታል ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- የባለፈው መንገድ እጅግ አስቸጋሪና እልህ አስጨራሽ ነበር ማለት ይቻላል። እንደውም ሰነዶች እንደሚያሳዩት የናይል ቤዝንን በጋራ ተመካክረንና ተቀራርበን እንሥራ የሚለው ሃሳብ እ.አ.አ በ1997 የዛሬ 28 ዓመት የተጀመረ ነው። ይሄ ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም በርካታ ሀገራት በናይል ቤዝን ውስጥ ተካተዋል። እነዚህም ኤርትራን ጨምሮ አስራ አንድ ሀገራት ናቸው ። ኤርትራ በዚህ ውስጥ ሙሉ አባል ሳትሆን ተመልካች (ታዛቢ) ናት። እነዚህ ሀገራት የተለያየ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የተለያየ አመራር ፣ የተለያዩ መሪዎች ያሉበት ናቸው። ሁልጊዜም ግብጽ በዓባይ ላይ የመሪነት፤ ዓባይ የኔ ነው የሚል እሳቤና አቋም ስላላቸው ነገሩን ያባብሰዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የብሉ ናይል 86 በመቶ ውሃ የሚገኘው ከኢትዮጵያ ቢሆንም፤ ውሃውን በእኩልነትና በፍትሃዊነት እንጠቀም የሚል እሳቤ አለ። ኢትዮጰያ ለብቻዬን ልጠቀም አላለችም፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም በመሆኑ በጋራ እንሥራ የሚል አቋም አላት። ይህንንም አቋሟን ጨዋነት በተሞላበት የዲፕሎማሲያዊ ሥራ ሁላችንም በፍትሃዊነት እንጠቀም ያለች ብቸኛ ሀገር ናት ።

ኢትዮጵያ ምክንያታዊ ናት። ፍትህ የምትፈልግ ሀገር ናት፤ በአብዛኛው ግብጽ ደግሞ ሁሉም የእኛ ነው የሚል ሃሳብ አላት። ሌሎቹ ዘጠኝ ሀገሮች ደግሞ መሃል ላይ የሚንሳፈፍ አቋም አላቸው። በመሆኑም ወደ ስምምነቱ ለመድረስ ንግግሩ እጅግ በጣም ከባድ ነበር። እልህ አስጨራሽም ነበር ። ሆኖም ግን ትዕግስት ጥሩ ነው፤ ከብዙ ዓመታት በኋላ ለመጽደቅ በቅቷል። እኔም እንደ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በጣም ተደስቻለሁ። የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የትግላችን ውጤት በመሆኑም ኮርቻለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ይህንን ፈተና ተቋቁሞ ጸንቶ ለመቆም በኢትዮጵያ በኩል የነበረው ቁርጠኝነት በምን መልኩ ይገለጻል?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡– በእኛ በኩል ትልቅ ቁርጠኝነት አለ። እኔ የማስታውሰው ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆኜም ፤ አውሮፓም አሜሪካም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስሠራ የማየው እና የምከታተለው ጉዳይ ነበር። የውጭ ጉዳይ ብቻም ሳይሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ባለሙያ መድበው ከአቅማቸውና ከጊዜያቸው ወደ ኋላ ሳይሉ ጽንሱ ልጅ ሆኖ እንዲወለድ የማይተካ ጥረት አድርገዋል። ከቁርጠኝነት አንጻርም ቀደም ሲል የነበሩት መንግሥታትም ሆኑ አሁን ያለው የብልጽግና መንግሥት ቁርጠኛ ሆነው ሠርተዋል። ይሄ የድል ውጤት የሁሉም ዐሻራና አስተዋጽኦ አለበት ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ የናይል ወንዝ የትብብር ስምምነት ተግባራዊ ሆኗል ፤ ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- እንግዲህ የናይል ወንዝ የትብብር ስምምነት ለኢትዮጵያ ብዙ ነገሮችን ይዞ ይመጣል። ደቡበ ሱዳን ከጥቂት ቀናት በፊት ወሳኝ ድምጽ ሰጥታ አብዛኛው የተፋሰሱ ሀገራት ስለተቀበሉ አፍሪካ ህብረትም እንዲረከብ ይደረጋል ። እናም አሁን ተግባራዊነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ለኢትዮጵያም ያለው ጥቅምን በተመለከተ ለአብነት እንጥቀስ ከተባለ በተናጥል ሳይሆን በጋራ የምትሠራበት ሁኔታ ይፈጠራል። እስካሁን የእኛን ጥረት ስናየው እ.አ.አ 2011 የዛሬ 13 ዓመት የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሠረት ሲጣል የነበረው በተናጠል እንቅስቃሴ ነበር። ይህን ስናደርግ ግን በጨለማና በደባ ሳይሆን ዓለም ያወቀው ፤ ጸሀይ የሞቀው እንደሚባለው የአፍሪካ ሀገራት ፣ ጎረቤት ሀገራት ባወቁት መልኩ ነበር። ሆኖም ግን ጥረቱ የብቻችን ነበር።

ከአሁን በኋላ ግን የሚደረገው ጥረት ለብቻችን አይሆንም። በስምምነቱ ውስጥ ትልቅ ተቋም ይቋቋማል። አሁንም “ናይል ቤዚን ኢንሸቲቭ “ አለ። ቀጥሎ የሚቋቋመው “ናይል ቤዚን ኮሚሽን” የሚባል ነው ። ኮሚሽኑ ራሱን የቻለ ቋሚ አካል ነው። የራሱ ጽህፈት ቤት ይኖረዋል ። የተለያየ አወቃቀር አለው ፤ ስለዚህ ዓባይ ላይ የሚደረገው ምንም አይነት እንቅስቃሴ በሙሉ በህብረት ተናቦ ይሆናል። ይሄ ለኢትዮጵያ የበለጠ ጥንካሬና አቅም ይሆናል። ከዚህ ቀደም ግን ይሄንን ትልቅ ጉዳይ በፊርማ መተማመኛ ማጽደቅ ስላልነበረ የምናስኬደው በራሳችን ነበር። በእርግጥ አንዳንድ ሀገሮች ተቋውሞ ባለማቅረብ ድጋፍ ያደርጉልን ነበር ።

በተለይ ከግብጽና ከሱዳን ተቃውሞ ነበር። አሁን ግን ማንኛውም የሚከወን ፕሮጀክት የሚሆነው በምክክር ነው ። በማሳወቅ ፣ መረጃ በመለዋወጥ የሚደረገው ነው። እዛ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ግዙፍ ፕሮጀክት በመሥራት ልምድ አላት ። ግንባር ቀደም ሆናም ልምዷን ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ምክር በመስጠት ፣ ባለሙያዎችን በመላክ (የግዙፍ ፕሮጀክት ልምድ ስላለን) መሪ ሀገር ሆነን በዚህ ተቋም ውስጥ እንንቀሳቀሳለን የሚል እይታ አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- የስምምንቱ መፈረም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ውጤት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል? ይህንን እንዴት ያዩታል ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አካሄድ የረቀቀ ነው። ያልተሸነፍነው በረቀቀ ሁኔታ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ስለምናደርግ ነው። ያንን ስናደርግ ብዙ ብሔራዊ ጥቅማችንን በማስቀደም ነው። ሌላው ደግሞ የአካባቢውን ሀገራት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን እሳቤ ሁሉ በመውሰድ ነው። በተለይ ብሩንዲ ፣ሩዋንዳ ፣ኡጋንዳ ፣ ታንዛኒያ ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያ የእኛ ዐሻራ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ያርፍባቸዋል። ሁሌም ስናግባባ ከምንገኝባቸው ከማንኛውም አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እስከ ሀገር መሪዎች በሳል የሆነ በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የማግባባት ሥራ ሠርተዋል። አብረን ብንሠራ በገንዘብ፣ በእውቀትና በሰው ሃይል የበለጠ ውጤት እናመጣለን በሚል መንገድ የረቀቀ የዲፕሎማቲክ ሥራ ተሠርቷል።

አዲስ ዘመን፡- ስምምነቱ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ ከማብሰር ባለፈ ፤ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብን ከአህጉሪቱ ከመንቀል አኳያ እንዴት ይታያል ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- ግብጾች የሚመኩበት ፤ ሱዳንም በተወሰነ መልኩ የሚኮሩበት እ.አ.አ የ1959 ቀደም ሲልም እ.አ.አ 929 ላይ የወጣ የውሃ ክፍፍል “አግሪመንት” አለ። ሰሞኑን የጸደቀው የናይል ትብብር ስምምነት በአንደኛነት ሁሉንም የቅኝ ግዛት ውሎች ግብዓተ መሬት የሚያስገባና የሚደመስስ ነው።

ሁለተኛም ኢትዮጵያ ለብሉ ናይል ከፍተኛውን የውሃ ሀብት እያበረከተች “የውሃ ክፍፍል አግሪመንት” አባል ሀገር ባልሆነችበትና ባልተገኘችበት ሁኔታ ብቻቸውን ተመካክረው ያጸደቁት ነው። ይሄ ውል ኢትዮጵያን አይመለከትም። ለምሳሌ የ “1959 አግሪመንት” የሚባለውን የውሃ ክፍፍል ለግብጽ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ፤ ለሱዳን ደግሞ 18 ነጥብ 5 ኪዩቢክ ሜትር ሆኖ መከፋፈላቸው ይታወቃል። ቀደም ሲልም ከእንግሊዞች ጋር በቅኝ ግዛት ነበር፤ ይሄ በጣም የሚያሳዝንና ተንኮል ላይ የተመሠረተ ነው። 86 በመቶ ውሃ የምታመነጭን ሀገር ወደ ጎን የገፋ በአንጻሩ ደግሞ ዜሮ በመቶ የውሃ አስተዋጽኦ ያላትን ሀገር የበላይነት የሰጠ ነው። ግብጽ የበላይና ባለቤት ሆና ማንም በዚህ ጉዳይ ላይ ሃሳብ መስጠትም ፣ መናገርም ሆነ መንቀሳቀስ አይችልም ብላ ቆይታለች።

አሁን የኢትዮጵያ ጥንካሬ እያየለ ሲመጣ የግብጽ እብሪት ቀነሰ እንጂ ወታደራዊ ርምጃ እንወስዳለን እያሉ በማስፈራራት የሚንቀሳቀሱብት ሁኔታም ነበር። በስምምነቱ ይሄ ሁሉ ነገር ፈራሽ ሆኗል። በተለይ ግብጾች ሁልጊዜ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤትም ሆነ በአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያን ለማስወቀስና ለማሳጣት እንደ ተበዳይ ሆነው የሚያቀርቡበት ሁኔታ ነበር። ኢትዮጵያ ለሠብዓዊነት ምንም ደንታ እንደሌላት፣ የግብጽና የሱዳንን ሕዝብ ለማጥቃት እንደተነሳች ሀገር አድርገው ሁልጊዜ ይከሱ ነበር። ይህን የሚያደርጉትና የሚመኩት ታዲያ በቅኝ ግዛት ውሉ ነበር። አሁን ይሄ ውድቅ ሆኗል። ከአሁን በኋላ ደግሞ ምን ይዘው እንደሚመጡ አይታወቅም። ይሄ ስምምነት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው የሚባለው ለዚህም ነው።

አፍሪካ ህብረት ብቻ ሳይሆን እስከ ተባበሩት መንግሥታት ድረስ ሀገራት ተሰባስበው ተፈጥሮ የሰጠንን የውሃ ሀብት በጋራ በመነጋገርና በመጠቀም የጋራ እድገትና ብልጽግና ላይ የሚያውል ስምምነት ተግባር ላይ ውሏል ። ከዚህ በኋላ የቅኝ ግዛት ውሉ ወድቋል። ከአሁን በኋላ እሱን ይዘው የሚያነሱት አቧራ አይኖርም ፤ ተቀባይነትም አያገኝም ።

አዲስ ዘመን፡- የስምምነቱን ወደ ተግባር መግባት ተከትሎ ምን ዓይነት ህጎች ሊወጡ ይችላሉ?

ፕሮፌሰር ብሩክ ፡- ስምምነቱ አራት ዋና ዋና ምዕራፍ እና አርባ አምስት አንቀጽ አለው። የውሃ ሀብቱን በተመለከተ ፍትሀዊ እና ተመጣጣኝ አጠቃቀም ላይ የተመሠረተ ነው። ይሄ ዋናውና ትልቁ አንጓ ነው። እሱ ላይ በተመሠረተ እያንዳንዱ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት አስተዋጽኦ ግንዛቤ ላይ ይውላል። የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። እንደ አስተዋጽኦው የተጠቃሚነት ነገር ይንጸባረቃል።

ሌላው ውሃውን ለማልማት የሚኖረው አካሄድ ነው። ኮሚሽኑ ዳታና መረጃ መለዋወጫ ማዕከል ይኖረዋል። ለምሳሌ ሩዋንዳ አንድ ግድብ ለመሥራት ብትፈልግ ለኮሚሽኑ ታቀርባለች። ውይይትና ምክክር ይደረግባታል። እያንዳንዱ ሀገርም ያንን ያቀርባል፤ ሁሉም በነጻነት ይወያያሉ፤ ይነጋገራሉ። በዚህ ስምምነት ውስጥ የኤክስፐርቶች ድጋፍ ይኖራል። በኮሚሽኑ ውስጥ ኤክስፐርቶቹ የማገዝ ሁኔታ ይኖራል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ጉምቱ የሆኑ በውሃ ዙሪያ በቂ ባለሙያዎች አሏት። እነዚህ ባለሙያዎች በኮሚሽኑ ስር ሆነው የሚያስፈልጉ ሙያዊ እገዛዎችን ማድረግ ይችላሉ፡፡

ለምሳሌ ብሩንዲ ግድብ ያልሠራችው አቅም ሳይኖራት ቀርታ ይሆናል። አሁን አቅም ያላቸው ሁሉ ይረባረባሉ። በህብረት ስለሚሰሩ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸከም ነው እንደሚባለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ችግሮች ያሉባቸውን በጋራ በመረዳዳት የመፍታት ባህል ይኖራል። እንደ ሀገር የሌለውን ይጠይቃል፤ ያለውን ይሰጣል። ገንዘብም፣ እውቀትም፣ ሙያም የማዋጣት ሁኔታ ይኖራል። ስለዚህ አቅም መገነባባት ስለሚኖር ደከም ደከም ያሉ ሀገራት አሁን መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል።

ሌላው ደግሞ የውሃ ሀብቱን በአግባቡ ማስተዳደር ባለመቻሉ ብዙ የሚባክን ውሃ አለ። ይሄን ብክነት በመቀነስ ሁሉም ከምንጩ ጀምሮ በአግባቡ እየተጠቀመ ውሃውን ያለማል ። ሁሉም ውሃውን እየተጠቀመ ነገር ግን ሳይገድበ እያሳለፈ ይሰጣል። የውሃው ደህንነት እየተጠበቀ ጥግ ድረስ መጠቀም የሚቻልበት ይሆናል ። የውሃው ንጽህና፣ የኬሚካል ውጤቶች በአቅራቢያው እንዳይኖር የማድረግ ሁኔታ፣ የመለስተኛ ግድብ፤ የውሃው ደህንነትና ጤንነትን የመጠበቅ ሥራ ሁሉ በኮሚሽኑ የሚሠራ ይሆናል። ለእነዚህ ሥራዎችም የባለሙያ ቡድን በየሀገራቱ ይላካሉ ፤ይሠራሉ። ውሃውንና የውሃውን አካባቢ የማልማት ሁኔታ አለ። እንዲሁም የአካባቢውን ሕዝብ የሚያነቁበትና የሚያስተምሩበት ሁኔታ አለ። እጅግ በጣም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። ይሄ የተቀናጀ ዘላቂ ልማት ውሃውን ሁሉም እንዲጠቀመው፤ የአካባቢ የውሃ ልማት ሥራ፤ የአረንጓዴ ልማት ሥራ፣ በዚህ መልኩ ኮሚሽኑ ትልልቅ መዋቅር ይኖረዋል።

ኮሚሽኑ ልክ እንደ አፍሪካ ህብረት የመሪዎች የርዕሰ ብሄርና የርዕሰ መንግሥት ካውንስል በየዓመቱ ይሰበሰባል፤ አቅጣጫ ይሰጣል። በእሱ ስር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይኖራል። እነሱ በዓመት ሁለት ጊዜ የሰበሰባሉ። ከዛ በታች የኤክስፐርቶች አማካሪ ኮሚቴ አለ። በሀይድሮሎጂ ፣ በሶይል ፣ በሜትዎሮሎጂ … ብዙ ንዑስ ኮሚቴዎች ይኖራሉ። ኤክስፐርቶቹ ኢንቴቤ ሄደው በቋሚነት የሚሠሩ ይኖራሉ፤ ከዛም በተጨማሪም የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ሠራተኛ ይኖራል። ከላይ በሚሰጣቸው አቅጣጫ ወደ ጎንና ከላይ ወደታች በተጣጣመ መልኩ ኮሚሽኑ ሥራውን ይሰራል። ይሄ በሚቀጥሉት ዓመታት ይሠራል ብለን የምንጠብቀው ነው።

አዲስ ዘመን ፡- የስምምንቱ ተግባራዊ መሆን ከፓን አፍሪካኒዝም ፖለቲካ – ኢኮኖሚ እሳቤ አኳያ እንዴት ይታያል ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡– አብነቱ ብዙ ነው። ፓን አፍሪካ “የአፍሪካ ሕዝቦች ሆይ በብዙ ሀገራት አትበታተኑ፤ አቅማችሁን፣ ገንዘባችሁንና ጉልበታችሁን ሰብሰብ አድርጉ የሚል ነው። ሰብሰብ ስትሉ ጠንካራ ትሆናላችሁ። ጠንካራ ስትሆኑ ጠላትን ትመክታላችሁ ፤ ብዝበዛውንም ትገታላችሁ፣ የእጅ አዙር ቀኝ አገዛዙን ትቀንሳላችሁ” የሚል ነው ።

ሁለተኛ አፍሪካ ህብረት በአህጉር ደረጃ እ.አ.አ በ2063 በኢኮኖሚክ፣ በማህበራዊ እና ፖለቲካል ህብረት ለመፍጠር እየሠራ ነው። በፖለቲካውም አንድ ፓስፖርት እንዲኖር ፣ ያለ ቪዛ መንቀሳቀስ መቻልን በተመለከተ እና በቀጣናው ትስስር እንዲኖር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። ይሄ ጠንካራ ሞዴል ነው።

አፍሪካ ሀብቷ የማዕድን ሀብት ብቻ አይደለም፤ የውሃ ሀብት አላት ። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በውሃ ሀብት ሁለተኛ ሀገር ናት። የውሃ ማማ የሚባለው የመጀመሪያ ሀገር ዴሞክራቲክ ኮንጎ ነው ። ሀገሩ ሰላም ከሆነ አቅም ከተፈጠረለት በውሃ ሀብቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው ። ናይል ቤዝን የአፍሪካን የቆዳ ስፋት 10 ከመቶ ይይዛል፤ የአፍሪካ ሀገራት ተባብረን ከሠራን ለውጥ ልናመጣ እንችላለን።

አዲስ ዘመን ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በጋራ የማልማትና በፍትሃዊነት የመጠቀም መብትን የሚያጎንጽፉ ተመሳሳይ ማሕቀፎች ካሉ ቢነግሩን ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- በዓለም ላይ በጋራ ማልማትንና በፍትሃዊነት የመጠቀም መብትን የሚያጎናጽፉ ስምምነቶች አሉ። ለምሳሌ ከቱርክ ብዙ ውሃ ይመነጫል፤ ቱርኮች በውሃቸው ላይ ብዙ ግድቦችን ሠርተዋል ። እሱን አልፎ ሄዶ ወደ ሲሪያ ኢራክ የሚገባ ውሃ አለ። ተጠቃሚው ብዙ ነው፤ ስለዚህ እንዲህ አይነት አሠራር ለመጠቀም ሞክረዋል።

ላቲን አሜሪካዎች በአማዞን ወንዝ አካባቢ ግድቦችን ለመሥራት እንቅስቃሴ አድርገዋል። በአውሮፓ ዳንዩብ እና ራይን የሚባሉ በርካታ ሀገራትን አቋርጠው የሚያልፉ ወንዞች አሉ፡፡ አውሮፓዎቹ የብዙ ዓመት በጋራ ወንዞችን የመጠቀም ልምድ ስላላቸው በስምምነት ያለ ምንም ጉልህ ችግር ተማምነው በጋራ ግድብ በመሥራት ይጠቀማሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የናይል ትብብር ስምምንት ተቀብለው ለማጽደቅ ፈቃደኛ ያልሆኑ የተፋሰሱ የታችኞቹ ሀገራት ስምምነቱን እንዲቀበሉ የሚገደዱበት ሁኔታ ይኖራል ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- የናይል ትብብር ስምምነትን ተቀብለው ለማጽደቅ ፈቃደኛ ያልሆኑ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት እንዲቀበሉ የሚያስገድድ ሕግ የለም። በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው። አሁን ግን ስድስት ሀገራት ስምምነቱን ፈርመዋል፤ ግብጽ ወደፊትም ብትመጣ በሩ ሁልጊዜ ክፍት ነው። በፈለጉት ሰዓት መግባት ይችላሉ። ይሄ መብት አላቸው። እንድትገባ ማስገደድ ግን አይቻልም። ስምምነቱን ያላጸደቁት አራቱ ናቸው፡፡ ኬንያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሪክ ኮንጎ ፣ ግብጽና ሱዳን ናቸው።

አዲስ ዘመን ፡- የናይል የትብብር ስምምንት በአፍሪካ ህብረት ተቀባይነት እንዳገኘ ሁሉ በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ፤ በተባበሩት መንግሥታት እና መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚኖረው ዕውቅና እና ተቀባይነት ምን ይመስላል ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- የናይል ቤዝን ኮሚሽን (ኤን አር ኤ ቢ ሲ) ይባላል። ይሄ ኮሚሽን ሲቋቋም የአፍሪካ ህብረት ኦብዘርቨር ስታተስ ወንበር ይሰጠኝ ብሎ መጠየቅ ይችላል። አፍሪካ ህብረት ስብሰባዎች ላይ ድምጽ ሳይሰጡ መታዘብ ይችላል። ድምጽ መስጠት ባይችሉም ጊዜና እድል ሲኖር የመናገር፤ በጽሁፍ ሃሳብ የማቅረብ እና የመቃወም መብት ይኖራቸዋል። በተባበሩት መንግሥታትም ልክ እንደ አፍሪካ ህብረቱ በታዛቢነት አመልክተው የሚገቡበት እድል ሊኖር ይችላል፡፡ ይሄ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል። ይሄንን መሰል ኮሚሽኖች ጋር ለምሳሌ በላቲን አሜሪካ መረጃ መለዋወጥ፣ የእውቀትና ልምድ ልውውጥ እንዲሁም መማማርን አዲስ የሚቋቋመው ኮሚሽን አብሮ ይሠራል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- ያልተዳሰሱ መነሳት አለባቸው የሚባሉ የቀሩ ጉዳዮች ካሉ እድሉን ልስጥዎት ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- ከዚህ ተሞክሮ የምንወስደው ተፈጥሮ ያደለችን ብዙ ነገር አለ። ውሃ ግን ሕይወት ነው። ከዚህ አኳያ ውሃ ውስን የሆነ ሀብት ነው። የሀገራት የውሃ ተጠቃሚዎች ቁጥር በቢሊየን እያደገ ነው፡፡ ስለዚህ ሀብቱን ደርዝና ሥርዓት ባለው ሁኔታ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አብቃቅቶ መጠቀም ያስፈልጋል። የውሃ ብክነትን ቀንሶ አብሮ መሥራት ይመረጣል። የእኛ ቀጣና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከላይ የተጠቀሱት ሀገራት ጊዜያቸውን መስዋዕት አድርገው ሰላሳ ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ ሳይታክቱ ኮሚሽኑን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ማድረግ መቻላቸው እና ውጤት ማምጣታቸው የሚደነቅ እና በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡

ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከዚህ ኮሚሽን ስኬት ትምህርት መቅሰም ይችላሉ። በጋራ እንሥራ፣ በጋራ እንደግ፣ ለሰላም ቅድሚያ እንስጥ፤ እንተባበር ፣ እንደማመጥ እላለሁ። በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያውያንን እንኳን ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ። በዚህ ሥራ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ፣ በሕይወት ያሉም ሆኑ የተለዩ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። በየዘመኑ የነበሩ የሀገር መሪዎች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረትና የቆራጥነት ውጤት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

አልማዝ አያሌው

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You