አዲስ አበባ፡- በምክር ቤቱ አባላት መካከል አዋጆችንና ደንቦችን በማፅደቅ ሂደት እንዲሁም የውሳኔ ሀሳቦችን ለማስተላለፍ የሚካሄዱ ውይይቶችና ክርክሮች ዴሞክራሲያዊ ከመሆናቸው ባሻገር ምክንያታዊ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ገለፁ።
የአንድ ዓመት የምክር ቤት የሥራ እንቅስቃሴን አስመልክቶ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ትናንት ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት 67 አዋጆች እንዲያፀድቅ ቀርቦለት 62 አዋጆችንና 2 ደንቦችን ሲያፀድቅ፤ 32 የውሳኔ ሃሳቦችን አስተላልፏል። በሂደቱ የፓርላማ አባላት የክርክር ተነሳሽነት የታየባቸው ቢሆንም የሚካሄዱት ክርክሮች የፓርቲና የብሔር ቅርፅ የመያዝ አዝማሚያ የተስተዋለባቸው ነበሩ ።
የምክር ቤቱ አባላት ከየአካባቢያቸው ተወክለው የተገኙ ቢሆንም እንኳ ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ከሆኑ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካይ በመሆናቸው መከራከር ያለባቸው አጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ማዕከል አድርገው መሆን እንደሚገባ የጠቆሙት አፈ ጉባዔው፤ ክርክርና ውይይቱ በበሰለ መልኩ በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ምክንያታዊነት ላይ ትኩረት በማድረግ የአቅም ግንባታ ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
ቀደም ሲል ውሳኔዎች የሚተላለፉት በሙሉ ድምፅ ሲሆን፤ የድምፅ አሰጣጥ ላይ የተአቅቦ እና የተቃውሞ ልምድ አልነበረም የሚሉት አቶ ታደሰ፤ በዚህ ዓመት ግን አዋጆችና የውሳኔ ሃሳቦች ከሙሉ ድምፅ ይልቅ በአብላጫ ድምፅ ሲፀድቁ እንደነበር በምሳሌ አስደግፈው አብራርተዋል። ለአብነትም የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያን አስመልክቶ ክርክር በማድረግ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ እንዲተላለፍ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ክርክር በማካሄድ በሃሳብ የበላይነት ጭራሽ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ እንዳይተላለፍ የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሶ ህጉ መውጣቱን አስታውሰዋል። የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን አስመልክቶም ጠንካራ ክርክር እንደነበርም አስታውሰዋል።
ምክር ቤቱ ለአገሪቷ የሚጠቅሙ ህጎችን በማውጣት ሂደት ውስጥ ህግ ከመነጨ በኋላ ወደ ቋሚ ኮሚቴ መርቶ በዝርዝር ከማየት ባሻገር ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ በመጋበዝ የይዘት ለውጥ እስከማምጣት የደረሱ ማሻሻያዎችን በማድረግ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ላይ መሆኑን አፈ ጉባዔው አመልክተው፤ አካሄዱ ሙሉ ለሙሉ ዴሞክራሲያዊ ነው ለማለት ቢያስቸግርም በተቻለ መጠን አባላቱ ለህዝቡ፣ ለህገመንግሥቱና ለህሊናቸው ተገዝተው እንዲሠሩ መደረጉን ተናግረዋል።
እንደአፈጉባዔው ገለፃ፤ ህግ ከማውጣት ባሻገር -የምክር ቤቱ ትልቁ ሥራ አስፈፃሚውን መከታተልና መቆጣጠር ነው። በዚህ መሰረት በ10ሩ ቋሚና በ32ቱ ንዑስ ኮሚቴዎች አማካኝነት እያንዳንዱ ተቋም በየሩብ ዓመቱ የሚያቀርበውን ዝርዝር ሪፖርት ለማየት ተሞክሯል። ቦታው ድረስ በመገኘት የአካል ግምገማ በማካሄድ መሻሻል የሚገባው እንዲሻሻል ግብረ መልስ ተሰጥቷል። በልዩ ሁኔታ መታየት ያለባቸውም እንዲታዩ ተደርጓል።
ለአብነት ምክር ቤቱ ከኦዲት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ጉድለት የታየባቸውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከዔቃቤ ህግና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተሰራው ሥራ ዩኒቨርሲቲዎች የማማከርና ገቢ የሚያመነጩበትን ሁኔታ አስመልክቶ የአሰራር ስርዓት ችግር የኦዲት ጉድለት እያመጣ መሆኑን በመለየት መፍትሄ ለማበጀት እየተሠራ መሆኑን አፈ ጉባዔው ጠቁመዋል።
ምክር ቤቱ አባላቱ የተመረጡበትን አካባቢ ህዝብ ጥያቄ አምጥተው በወረዳ ደረጃ መመለስ ያለበትን ለወረዳ፣ በዞን መመለስ ያለበትን ለዞን፣ በክልል ደረጃ መመለስ ያለበትን ለክልል በፌዴራል ደረጃ መመለስ ያለበትንም በፌዴራል ደረጃ ለመመለስ ጥያቄዎችን የመለየት ሥራ መሰራቱን አመልክተዋል። በቀጣይ ዓመትም ቪዲዮ ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት በየአካባቢው ያለው ህዝብ በቀጥታ ራሱ እንዲጠይቅ በማድረግ መስራት ያለበት አስፈፃሚው አካል ተገኝቶ ጥያቄዎችን እንዲመልስና ከምክር ቤቱ ጋር በመተባበር ፈጣን ምላሽ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ አንድ ዓመት ከመደበኛ ሥራው ባሻገር የለውጥ (ሪፎርም) ሥራ ለመስራት፤ ጥራት ያለው ህግ እንዴት ይውጣ? የተቋማት ክትትልና ቁጥጥር እንዴት ይሁን? የፓርላማ የዲፕሎማሲ አደረጃጀት እንዴት መሆን አለበት? ህዝቡ በየአካባቢው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ምን አይነት የአሰራር ስርዓት ይኑር? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የለውጥ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን አፈ ጉባዔው አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 5/2011
ምህረት ሞገስ