በዓለም የምግብ ድርጅት (FAO) ትርጓሜ መሠረት የምግብ ዋስትና ተረጋገጠ የሚባለው በአንድ አገር ያሉ ሁሉም ሰዎች ንቁና ጤናማ ሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጓቸውን በቂ፣ ጤናማና የተመጣጠነ ንጥረ ነገር ያለው የምግብ አማራጭ ለማግኘት የሚችሉበት የኢኮኖሚ አቅምና አቅርቦት ሲኖራቸው ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስምንት መቶ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ በምግብ እጥረት ችግር ወይም የምግብ ዋስትናው ባልተረጋገጠ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ፣ የዓለም የምግብ ድርጅት ሪፖርት ያመላክታል። ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚገመት ሕዝብ ደግሞ ጠቃሚ ቫይታሚኖችንና ማዕድናትን እንደማያገኝ ይገለጻል። ይህ ሁኔታ የተደበቀ ረሃብ (የምግብ እጥረት) (Hidden Hunger) መከሰቻ ተብሎ ይታወቃል።
በአፍሪካ ደረጃ የምግብ እጥረት የሚፈትነው ሕዝብ ቁጥር በጠቅላላው 21 በመቶ ሲሆን፣ ከሰሃራ አፍሪካ በታች ከሚገኙት ውስጥ ደግሞ ከሕዝቡ 25 በመቶ የሚሆነው በምግብ እጥረት ችግር ዕጦት የሚንገላታ መሆኑን አኃዛዊ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከዚህ በተጨማሪም 13 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑ ጨቅላ ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ በማጣታቸው ዝቅተኛ ክብደት ያላቸው ሲሆን፣ 30 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑ ከዜሮ እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት ደግሞ የቀነጨሩ መሆናቸው የዓለም አቀፍ የተመጣጠነ ምግብ ሪፖርት ያሳያል።
አፍሪካ ዘጠኝ ቢሊዮን ሕዝብ መመገብ የሚያስችል ለእርሻ ተስማሚ የሆነ መሬት ባለቤት እንደሆነች ቢነገርላትም፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ አገሮች ይህንን ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ሕዝቦቻቸውን ከምግብ እጥረት፣ ከተረጂነትና ከድህነት ማላቀቅና የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ መልኩ ማረጋገጥ ትልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል።
የፓን አፍሪካ ባንክ (The Pan-African Bank) ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ አኅጉሪቱ ለእርሻ ተስማሚ የሆነውን 65 በመቶ የሚደርሰውን የተፈጥሮ ሀብቷን በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል ብትችል እ.ኤ.አ. በ2050 ዘጠኝ ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ የሚገመተውን የዓለም ሕዝብ መቀለብ የሚያስችል ዕምቅ አቅም እንዳላት ያትታል። ሆኖም ግን አብዛኞቹ በአህጉሪቱ የሚገኙ ሀገሮች ዋና መለያቸው ረሃብ፣ የምግብ እጥረት፣ የምግብ ዋስትና ማጣትና የመሳሰሉት ክስተቶች ሆነው ዘመናትን ዘልቋል። ይህም አኅጉሪቱ ጤናው የተጠበቀና አምራች ኅብረተሰብ እንዳይኖራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
አህጉሪቷ የራሷን የግብርና ምርቶች በዓለም ገበያ በመሸጥ እንደሌሎቹ ሁሉ ተጠቃሚ የመሆን ሰፊ ዕድል ቢኖራትም፤ ዛሬም የምግብ ዋስትናዋ በከፊል የተንጠለጠለው በውጭ ዕርዳታና ተሸምቶ በሚገባ የምግብ እህል ላይ ነው። በዚህም ምክንያት አኅጉሪቱ ካላት ውስን ጥሪት ላይ በዓመት ወደ 75 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በማውጣት ለዚሁ ዓላማ ስታውል እንደቆየች የአፍሪካ ልማት ባንክ (African Development Bank) ሪፖርት ይጠቁማል።
ይህንን የአህጉሪቱን ችግር ማቃለል ዓላማው ያደረገና የአፍሪካ የምግብ ዋስትናን መረጋገጥ ግቡ ያደረገ የሺህ አፍሪካ ወጣቶች ጉባኤ የሚል ስያሜ የተሰጠው የወጣቶች ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በምግብ ሥርዓትና በብዝኃ ሕይወት (በአግሮኢኮሎጂ) ላይ ያተኮረው ይህ የመጀመሪያው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባኤ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ወጣቶችን ያሳተፈ ነበር።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በጉባዔው መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ አፍሪካ በምግብ እራሷን አለመቻሏ ለበርካታ ችግር አጋልጧታል። ከእነዚህም መካከል ተደራራቢ ግጭቶችና ሠላም ማጣት ዋነኞቹ ናቸው። እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም በምግብ እራስን መቻል ቅድሚያ ተሰጥቶት መሥራት ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ለግብርናው የሚገባውን ያህል ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቷል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ሀገሪቱ በምግብ እራሷን ለመቻል በግብርናው ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት፣ ሜካናይዜሽንን በማበራከት፣ ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ የግብዓት አቅርቦትን የማሳደግና በወቅቱ ተደራሽ የማድረግ ተግባር መከናወኑን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም የማዳበሪያ አጠቃቀም ከነበረበት 13 ሚሊዮን ኩንታል በ2016 የምርት ዘመን ወደ 20 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። ዘንድሮ 24 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመግዛት መታቀዱን አመልክተው፤ በኢትዮጵያ ያለው የማዳበሪያ አጠቃቀም በአምስት ዓመት ውስጥ በእጥፍ አድጓል ብለዋል። በተጨማሪም የሜካናይዜሽን ሥራውን አጠናክሮ በመቀጠል ከትራክተር ጀምሮ እስከ ወተት ማለቢያ ያሉ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በማድረግ ሀገሪቱ በምግብ እራሷን ለማስቻል ቅድሚያ ተሰጥቶት የሚሠራ መሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ጉባኤው በዋናነት የምግብ ሥርዓቱን ለማስተካከል ግብርና ላይ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ መሥራት አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር የተዘጋጀ መሆኑን ያነሱት ፍጹም (ዶ/ር)፤ የአፍሪካ የምግብ ሥርዓትና ሉዓላዊነት በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየደረሰበት በመሆኑ የአሕጉሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ግብርናው ላይ እንዴት መሥራት ይቻላል? የሚለው ላይ መፍትሔ ለማምጣት የሚመክር መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው በመዲናዋ አዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ የስንዴ እና የሌማት ትሩፋት ንቅናቄዎችን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ እየተሠራ ያለው አረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፉ ያላትን ልምድ ለማካፈል ይረዳል ብለዋል።
ጉባኤውን ያዘጋጀው አላይንስ ፎር ሶቨርኒቲ ኢን አፍሪካ (AFSA) ዋና አስተባባሪ ሚሊዮን በላይ (ዶ/ር)፤ ጉባዔው ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከ45 የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ250 በላይ ወጣቶች በአካል እንዲሁም ከሁለት ሺህ በላይ ወጣቶች በኦንላይን መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ጉባዔው የአፍሪካን ግብርና ሥነ ምሕዳርና ብዝኃ ሕይወት መጠበቅን እንደ ዋና ጉዳይ አድርጎ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረው፤ አፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ እንድትችል ሁሉም የእሴት ሰንሰለት በራስ አቅም ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
በጉባኤው ተሳታፊ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ከጋምቢያ የመጣው ፋማራ ኮንቴ አንዱ ነው። በጋምቢያ የሚገኘው የአክሽን ኤድ ኢንተርናሽናል የአካባቢ መብቶች ፕሮግራም አስተባባሪ የሆነው ፋማራ ኮንቴ በመላው አፍሪካ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ወጣቶች ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ይናገራል። በተጨማሪም የአፍሪካን የአመጋገብ ችግሮች ለመቅረፍ ቴክኖሎጂን ማላመድ እና ማስፋፋት አስፈላጊ ስለመሆኑ ይገልጻል።
“አፍሪካ በሀብት የበለፀገች ልትሆን ትችላለች። ነገር ግን ሕዝቦቿ አሁንም በድርቅ፣ በረሃብ፣ በግጭት እና በሌሎችም እየተሰቃዩ ነው። እነዚህን ጉዳዮች ለመቅረፍ ወጣቱ ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት ሊወስድና በሁሉም ዘርፍ ትብብርን ማጎልበት አለበት። ›› የሚለው ፋማራ፤ ኮንቴ ለአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብዙ ወጣቶች በግብርና በተለይም ምርትን በማሳደግ ምርታማነትን በማሻሻል ላይ መሰማራት አለባቸው ይላል።
ከመኸር በኋላ የሚደርሰውን ኪሳራ መቀነስ አስፈላጊ ስለመሆኑ የሚናገረው ፋማራ ኮንቴ፤ በምርት አሰባሰብ ሂደት ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ይባክናል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ የምርት አሰባሰብ መከተል እንደሚገባ ያስረዳል። በተጨማሪም የአፍሪካ ወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ ንቁ ርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው የሚለው ኮንቴ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአፍሪካ ስጋት እየሆነ የመጣውን ድርቅ ለመቋቋም የአካባቢ ስነ-ምህዳርን መጠበቅ ያስፈልጋል፤ ለዚህም አገር በቀል ዘሮችን መንከባከብ እንደሚገባ ይናገራል።
ወጣቱ የአፍሪካን ዘላቂ የምግብ ዋስትና ፍላጎት ወደፊት ለማራመድ ከመንግስታት ጋር በመተባበር እና ተገቢ መፍትሄዎችን በማፈላለግ አብሮ መሥራት አለበት የሚለው ኮንቴ፤ የምግብ ሉዓላዊነትን በራስ አቅም ማረጋገጥ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ይላል።
ሌላኛዋ የጉባኤው ተሳተፊ በኡጋንዳ የአሳታፊ ኢኮሎጂካል የመሬት አጠቃቀም አስተዳደር (PELUM) ከፍተኛ የፕሮግራም ኦፊሰር ጁልየት ካቱሲሜ (ዶ/ር) የአፍሪካ ወጣቶች (በአግሮ ኢኮሎጂ) ብዝኃ ሕይወት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ትናገራለች።
ብዝኃ ሕይወት ግብርናን ማዘመን ብቻ ሳይሆን አካባቢን መጠበቅ፣ የተፈጥሮ ሥርዓቶችን መረዳት እና ዘላቂነትን ማረጋገጥ መሆኑን የምትናገረው ካቱሲሜ፤ በአህጉሪቱ የምግብ ድጋፍ ለመስጠት በሚል ሰበብና በሰብአዊ ርዳታ ሽፋን የውጭ ኃይሎች እያደረጉ ያሉትን ተጽእኖና ጣልቃ ገብነት ለአፍሪካ ከጥቅም ይልቅ ጉዳቱ እንደሚበዛ ገልፃ፤ “አፍሪካ የራሷ ሃብት አላት፤ ነገር ግን በአግባቡ እየተጠቀመችበት አይደለም። ይህንን አካሄድ ለማስተካከል የአህጉሪቱ ወጣቶች ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ተናግራለች።
የአፍሪካ ወጣቶች በአህጉሪቱ የተመጣጠነ አመጋገብ የባህል ለውጥ እንዲመጣ በትኩረት መሥራት አለባቸው የምትለው ካቱሲሜ፤ ከማሳ እስከ ገበያ ያለውን አጠቃላይ ሂደት የሚሸፍኑ ውጤታማ የግብርና ፖሊሲዎች ኖረው በውጤታማነት መተግበር ይኖርባቸዋል ብላለች። ካቱሲሜ ይህ የአመጋገብ ሚዛንን ለማረጋገጥ ወሳኝ ስለመሆኑ ትናገራለች።
በአፍሪካ በሀብት የበለፀጉ እና በድሃ አካባቢዎች መካከል ያሉ ክፍተቶችን በማስተካከል የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ችግርን በመቅረፍ ረገድ መሥራት ከሁሉም ባለድርሻ አካለት ይጠበቃል የምትለው ካቱሲሜ፤ የጋራ ችግርን ለመፈታት የጋራ ትብብር ወሳኝ ነው ብላለች።
ኒዮን ሽኩዛ ሌላኛው ከናሚቢያ የመጣ የጉባኤው ተሳታፊ ወጣት ነው። እርሱ እንደሚናገረው፤ ወጣቶች ከአፍሪካ የሕዝብ ቁጥር አብዛኛው ድርሻ ይይዛሉ። እነዚህ ወጣቶች በመጀመሪያ እራሳቸውንና አህጉሪቱን ለመጥቀም በትምህርት እራሳቸውን ማብቃት ይኖርባቸዋል ይላል።
በተለይ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የአህጉሪቱን ችግሮች የመቅረፍ ኃላፊነት የወጣቶችም መሆኑን የሚናገረው ሽኩዛ፤ በዚህ ጊዜ እንስሳትን ተጠቅሞ እያረሱ በምግብ እራስን ስለመቻል ማሰብ አዳጋች ነው። ከዚህ አኳያ ዘመናዊ የእርሻ ማሽነሪዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው፤ ይህንን ማሽነሪ ደግሞ ሌሎች አምርተው እንዲሰጡ ከመጠበቅ ይልቅ በራስ አቅም ማምረት የሚቻልበትን አቅም መፍጠር ይገባል ይላል።
አፍሪካውያን ከውሃ የአሳ ሀብታቸውን ከመሬት የተለያዩ ማዕድናትን አውጥተው ለመጠቀም የቴክኖሎጂ እገዛ ከምዕራባውያን የሚጠይቁበት ዘመን መብቃት እንዳለበት የሚናገረው ሽኩዛ፤ ሁሉንም ነገር በራስ አቅም የማድረግ ደረጃ ላይ መድረስ ከልታቸለ የሀገራት ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ይናገራል።
የአፍሪካ መንግሥታት በወጣቶች ላይ እምነት ሊኖራቸው ይገባል የሚለው ሽኩዛ፤ የብድርና የመስሪያ ቦታ አቅርቦት በማመቻቸት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ በተለይ በግብርናው ዘርፍ ከሰፋፊ ኢንቨስትመንት ባሻገር ወጣቶች በአነስተኛ መሬት የሚያከናውኑት የግብርና ሥራ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆን አለባቸው ይላል።
በአጠቃላይ ወጣቶቹ እንደተናገሩት፤ የአፍሪካ መፃዒ ተስፋ የተሻለ ለማድረግ የአህጉሪቱ ወጣቶች የላቀ ሚና መወጣት አለባቸው። አፍሪካ የበለፀገችና የኢኮኖሚ ነፃነቷን ያረጋገጠች እንድትሆን ከመሥራት ባለፈ ሰላሟ የተረጋገጠ አህጉር እንድትፈጠር መትጋት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም