አዲስ አበባ፡- “የተቋማት የበጀት ብክነት ተጠያቂነትን የሚያስከትል እንጂ እንዳለፉት ጊዜያት በሪፖርት ማቅረብ ብቻ ይታለፋሉ ብሎ የሚያስብ ካለ ተሳስቷል፤ በመሆኑም ሁሉም እራሱን ቤተሰቡንና ተቋሙን ቢጠብቅ እንደሚሻል እመክራለሁ “ ሲሉ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ገለጹ።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ መንግሥት ሙስናን የመንግሥት ሀብትን አለአግባብ መጠቀምንና ማባከንን እንደሚዋጋ አመልክተው፤ ተቋማቸው እስከ አሁን ይህን ሲያደርግ እንደነበረ በቀጣይም ስራቸውን የበለጠ ገፍተው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
እያንዳንዱ መስሪያ ቤት ከተወካዮች ም/ቤት ጋር ሲፈራረም አንዱ መለኪያው ኦዲት ነበር ያሉት ዋና ኦዲተሩ፤ ይህ ጥሩ እርምጃ ከመሆኑም በላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለው እርምጃ የመውሰድ ቁርጠኝነት የሚያበረታታ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ዋና ኦዲተሩ ገለጻ፤ አንደ ባለፉት ጊዜያት ሪፖርቶችን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እርምጃዎችም ስለሚኖሩ በተለይ የሥራ ኃላፊዎች ብክነትን እና ጉድለትን መከላከል ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በእነዚህ ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ እርምጃ ባይወሰድ እንኳን በተቋማት ኃላፊዎች ዘንድ ከፍተኛ የእጠየቃለሁ ስሜት ተፈጥሯል፤ በመሆኑም ምክር ቤቱ አሁን ያለውን መነሳሳት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 5/2011
እፀገነት አክሊሉ