ባለፉት አስራ አንድ ወራት የአገር ውስጥ ገበያን ሳይጨምር ከቆዳና ሌጦ ወጪ ንግድ 110 ሚሊየን ዶላር ማግኘት ተችሏል። ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ሁለተኛ እንደመሆኗ ከቆዳና ከሌጦ የምታገኘው ጥቅም አመርቂ አለመሆኑን ይነገራል።
ተገቢውን ጥራትና ብዛት ያሟላ ምርት አቅርቦት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ አለመገኘት፤ የውጪ ባለሀብቶች ተጽእኖ አንዳንድ ህጎችና መመሪያዎች ጥብቅ መሆን እንዲሁም የቴክኖሎጂና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት መኖሩ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳይገኝ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ደግሞ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ከተቋቋመው የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲ ትዩት ብዙ እንደሚጠብቁ አምራቾቹ ይናገ ራሉ።
ድሬ ኢንዱስትሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ቆዳ በማልፋት፤ ጫማና ጓንት በማምረት ለሀምሳ ዓመት ሰርቷል። በአሁኑ ወቅትም በዚሁ ዘርፍ በመሰራት ላይ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ የወጪ ንግዱን ለመቀላቀል ችግሮች ተጋርጠውበታል። የማህበሩ የንግድ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሃ አስራት እንደሚናገሩት፤ የቆዳው አንዱስትሪ ከቀን ወደ ቀን መሻሻሎች ቢኖሩትም የሚጠበቀውን ያህል የውጪ ምንዛሬ እንዳያስገኝ ተግዳሮቶች ተጋርጠውበታል። በአንድ በኩል የውጪ ባለሀብቶች እሴት ጨምሮ ማምረቱ ላይ መሰማራት የሚገባቸው ቢሆንም የሀገር ውስጥ ባለሀብት የሚሰራውን እንዲሰሩ በመፈቀዱ የሀገር ውስጥ ባለሀብት ላይ ጫና እየፈጠረ ይገኛል። በካፒታል ረገድም የሀገር ወስጥ ባለሀብት ከፍተኛ እጥረት አለበት። ከባንክ ለመበደርና ለመስራት እድሉን ቢያገኝ እንኳ ከውጪ ባለሀብቶች ጋር ለመወዳደር የሚያስችል አቅም አይኖረውም።
‹‹በሌላ በኩል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጫና እየተፈጠረብን ይገኛል። የፍሳሽ ማስወገጃ ሙሉ ለሙሉ ንጹህ እንዲሆን ቢፈለግም፤ አንዳንዴ በምክርና በማስጠንቀቂያ ሊታለፍ የሚገባውን ሳይቀር ወደ ቅጣት በመግባት በርካታ ሠራተኞች የሚያንቀሳቅሰውን ኢንዱስትሪ እስከ መዝጋት ይደርሳሉ። በዚህ በኩል ዘርፉን ለመደገፍና ለማብቃት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት›› ይላሉ አቶ ፍስሃ።
ከዚህ ቀደም ለኢንስቲትዩቱ ጥያቄ ስናቀርብ አስፈላጊውን የምክር አገልግሎትና የቴክኒክ ድጋፍ ሲሰጠን ቆይቷል የሚሉት አቶ ፍስሃ፤ ይህም ሆኖ ግን የስራውን ውስብስብነትና አስ ቸጋሪነት ኢንስቲትዩቱ በተሻለ ስለሚረዳውና ለመንግሥትም ምክረ ሀሳብ ማቅረብ ስለሚ ችል ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ እንደተለመደው ለችግሮች መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባው ጠቁመዋል።
በኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ሰርጄቦ በበኩላቸው የውጪ ባለሀብቶች በዘርፉ ሲሳተፉ በከፊል ከተጠናቀቀ ቆዳ መጀመር እንዳለባቸውና ብዙ ቴክኖሎጂ ካፒታልና የሰለጠነ የሰው ሀይል በማይፈልገው ላይ መስራት እንደሌለባቸው የሚቀርብ ቅሬታ መኑሩን ጠቅሰዋል። ‹‹በትክክልም የውጪዎቹ ጠንካራ በመሆናቸው የሀገር ወስጥ ባለሀብቱ ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል። የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች በቂ ግብዓት ማቅረብ ባለመቻላቸው መመሪያው ላይ ማሻሻያ ተደርጎ ከማልፋት ጀምሮ የውጪዎቹ እንዲሳተፉ ተፈቅዷል።
ይህም ሆኖ ፈቃድ ከሚሰጠው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የሀገር ውስጥ አምራቾች ብቁ ሲሆኑ በእነሱ ለማሰራት እያከወንን ያለነው ሥራ አለ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ እስከ 2004 ዓ.ም መላክ የሚቻለው ሙሉ ለሙሉ ያለቀለት ቆዳ ብቻ ነበር። የሀገር ወስጥ ባለሀብቶች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ጥናት ተደርጎ በአሁኑ ወቅት በከፊል ያለቀለት በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ እንዲላክ ተወስኖ እየሰሩ ይገኛሉ›› ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ የፍሳሽ ማስወገጃን በተመለከተ ባህርዳርና ደብረብርሃን ላይ ሁለት ፋብሪካዎች ተዘግተዋል። ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች ዘመናዊ ፍሳሽ ማስወገጃ ባለመገንባታቸው ለተወሰነ ጊዜ አንዲዘጉ ተደርጎ ነበር። ግንባታው ደግሞ እስከ 30 ሚሊየን ብር ወጪ የሚጠይቅ ነው። ለዚህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አቅም ስለማይፈቅድ ሁሉንም ፋብሪካዎች በአንድ አካባቢ በማስፈር በአንድ ማጣሪያ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ሞጆ አካባቢ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለመገንባት የተጀመረ ሥራ አለ።
ይሄ ሲጠናቀቅ ችግሩን በዘላቂነት ከመቅረፍ ባሻገር የጋራ መሰረተ ልማት ተጠቃሚም ያደርጋቸዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ፋብሪካዎች እስከ ሁለተኛ ደረጃ ማጣሪያውን መገንባት እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሶ በአዲስ አበባ ያሉት ይሄንን አድርገዋል። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ አካባቢ ብክለትን በሚመለከት በህዝብ ላይ ችግር የሚያደርስ ከሆነ መታገሱ አዳጋች መሆኑ መታወቅ አለበት። በኢንስቲትዩቱ በኩል ግን እስካሁን ሲደረግ የነበረው አስፈላጊው ድጋፍ የሚቀጥል ይሆናል።
በተመሳሳይ የባህር ዳር ቆዳ ፋብሪካ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይግዛው አሰፋ ዘርፉ የውጪውን ዓለም ገበያ ለመቀላቀል ብዙ ክትትልና ድጋፍ የሚፈልግ መሆኑን በማንሳት ኢንስቲትዩቱ የጀመረውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳስባሉ። የቆዳ ኢንዱስትሪ በየግዜው እየተሻሻለና እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ግዜውን የሚመጥን ቴክኖሎጂ የሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ እንዲሁም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል ማቅረብ ከኢንስቲትዩቱ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
አቶ ይግዛው እንደሚሉት፤ በሀገር ውስጥ ኬሚካል ኢንዱስትሪ የለም። አብዛኛው ግብዓት ከአውሮፓና ከእስያ የሚመጣ ነው። በዚህ ላይ የኬሚካል ዋጋ ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት ከነበረው በጣም ጨምሯል። በአሁኑ ወቅት ይሄንን ለመቅረፍና ዋጋ ለመቀነስ ፋብሪካዎችን በአንድነት በማደራጀት ኬሚካሎችን ለማስገባት እየተሰራ ነው። ይህ በቂ ባለመሆኑ ኢንስቲትዩቱ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ መስራት ይጠበቅበታል።
ዳይሬክተሩ ከላይ የሚነሱት አስተያየቶች በተደጋጋሚ የቀረቡ መሆናቸውን በማስታወስ፤ በዚህ ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ሲገልጹ፤ ‹‹ኢንስቲትዩቱ በሦስተኛ ዲግሪ ሰባት እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ አንድ መቶ ባለሙያዎች አሉት። በአሁኑ ወቅትም ህንድ ከሚገኙ ሁለት ተቋማት ጋር በቁርኝት እየሰራን ነው። በዚህም በሀገር ውስጥ ካሉ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎችና ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኤጀንሲ ስር ባሉ 42 ኮሌጆች፤ እንዲሁም በኢንስቲትዩቱ በቆዳ ቴክኖሎጂ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ስልጠና እየተሠጠ ይገኛል። የተግባር ላይ ድጋፍ በማድረጉም በኩል ጥያቄ ሲቀርብለት በየፋብሪካው በአካል በመሄድና ሠራተኞችንም በማስመጣት የማማከር የድጋፍና የምርምር ሥራ ይሰራል›› በማለት አብራርተዋል።
በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በቅርቡም በህንድ ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ ውሃ አልባ ቆዳ ማልፋት ቴክኖሎጂ ወደዘርፉ ለማሸጋገር ድርድር መጠናቀቁን፤ በተጨማሪም እስካሁን ስድስት ምርምሮችን በዓለም አቀፍ ጆርናል ለማሳተም መቻሉን፤ በቅርቡም በሀገር ውስጥ ያሉ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረገ የምርምር ሥራ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የኬሚካል አቅርቦትን በተመለከተ ከኬሚካል ኢንስቲትዩትና ከኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢዎች ድርጅት ጋር እንዲሁም ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ኮሚቴ ተቋቁሞ ከውጭ ስለሚገቡት ኬሚካሎች በወቅቱ እንዲቀርቡ የማድረግ፤ ይሄ ግን በዘላቂነት ችግሩን ለማስቀረት መፍትሄ ስለማይሆን የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ባለሀብቶች ኬሚካል ወደማምረት እንዲገቡ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 5/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ