የ14 ሀገራት ድርጅቶች የሚሳተፉበት የእንስሳት ሀብት ልማት አውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፦ በእንስሳት ሀብት ልማት ከ14 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ውጤታማ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ ከጥቅምት 21 ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገለፀ።

አውደ ርዕዩ በግብርና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት፣ በኢትዮጵያ ግብርና ባላሥልጣን፣ በኤስኤንቪ – የኔዘርላንድስ ልማት ድርጅት ፕሮግራም እንዲሁም በዓለም አቀፍ የነፍሳት ፈዚዮሎጂ እና ሥነ ምህዳር ማዕከል (ICIPE) የተዘጋጀ ሲሆን ይህም በእንስሳት ሀብት ልማትና የተዋጽኦ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የአውደ ርዕዩ አስተባባሪና የፕራና ኢቨንት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ አውደ ርዕዩ የእንሰሳት ሀብት የገበያ ሰንሰለቶች ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ይረዳል። በዚህም ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሀብት ዘርፍ ተዋናዮች ይሳተፋሉ።

ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ዓውደ ርዕይና ጉባዔ ከቻይና፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ኬንያ፣ ጆርዳን፣ ኔዘርላንድሰ፣ ስኮትላንድ፣ ቶጎ፡ ቱርክ፣ ዩጋንዳ እና አሜሪካ የሚመጡ ዓለም አቀፍ የዘርፉ መሪዎች እና ጠንካራ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ከንግድ ጎብኚዎች ጋር ጠንካራ የሥራ ግንኙነት ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

በዚህም 13ኛው የኢትዮ ፖልተሪ ኤክስፖ (ኢትዮፔክስ)፣ 9ኛው የአፍሪካ እንሰሳት ዓውደ ርዕይና ጉባዔ (አሌክ) እንዲሁም 4ኛው የአፒካልቸር እና አኳካልቸር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ዘንድሮ የሚጀመረው የባዮ ኢነርጂ የንግድ ትርዒት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በኹነቱ ከ5000 በላይ የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካ እና ዓለም አቀፍ ሀገራት ጎብኚዎች እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የኔዘርላንድ መንግሥት ኤምባሲ የግብርና አማካሪ ሚስተር ሚዩዌስ ብሩወር በበኩላቸው፤ በአውደ ርዕዩ ከዶሮ ርባታ ጋር የተያያዙ ምርቶችን እና አገልግሎቶቻቸውን እንደ መኖ፣ መሣሪያ፣ ክትባቶች እና የማርቢያ ቴክኖሎጂዎች ይቀርባል ብለዋል።

አውደ ርዕዩ ለተሳታፊዎች ግንኙነቶችን ለመገንባት እና የንግድ እድሎችን ለማሰስ ከኢንዱስትሪ ባለሙያዎች፣ ደንበኞች እና አቅራቢዎች ጋር የሚገናኙበትን ዕድል እንደሚፈጠርም ጠቁመዋል።

ባለሙያዎች ስለ የዶሮ ርባታ ኢንዱስትሪው የተለያዩ ገጽታዎች፣ የምርት ቴክኒኮችን፣ በሽታን መከላከል እና የገበያ አዝማሚያዎችን ጨምሮ ግንዛቤዎችን እና ዕውቀትን ያጋራሉ ብለዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ጽጌሬዳ ፍቃዱ በበኩላቸው፤ መንግሥት በዘርፉ ያለውን ምርታማነት ለማሳደግ በሌማት ትሩፋት ዕቅዱ ፕሮግራም ነድፎ የወተት፣ ዕንቁላልና የዶሮ ስጋ እንዲሁም የማር ምርት ለማሳደግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል ብለዋል።

በዚህም የላም ወተት ምርትን አሁን ካለበት 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሊትር ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሊትር፤ የዕንቁላል ምርትን ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ወደ 9 ነጥብ አንድ ቢሊዮን እና የዶሮ ስጋ ምርትን ከ90 ሜትሪክ ቶን ወደ 296 ሺህ ሜትሪክ ቶን እንዲሁም የማር ምርትን ከ147 ሺህ ወደ 296 ሺህ ሜትሪክ ቶን ለማሳደግ ግብ አስቀምጦ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

በአጠቃላይ አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስፈላጊውን አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You