በትምህርት ዓለም ያለፈ ሁሉ ስለ “ሳይንስ” ትምህርት ሲነሳ ሁሉም የየራሱ የሆኑ ትዝታዎች አሉት። ትዝታዎቹ ምንም ይሁኑ ምን ግን ምንጫቸውም ሆነ ምክንያታቸው ሳይንስን ከመጥላት የመነጨ እንደማይሆን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በተለይ በአሁኑ፣ በዚህ ሳይንስ ገላጮችን ጨምሮ “ኧርዝ ሳይንስ”፣ “ማቴሪያል ሳይንስ”፣ “ኮምፒውተር ሳይንስ” ወዘተ የመሳሰሉት ለአደባባይ ከበቁና የትምህርት አምባን ከተቀላቀሉ በኋላ የተማሪዎች ፍላጎት በዚያው ልክ ሰፍቶ ወደ ተወዳዳሪነቱ ዓለም እስኪመጡ ድረስ ገፋፍቷቸው እንመለከታለን።
በተለይ በትምህርት ተቋማት ውስጥ የተጓዳኝ ትምህርት ተገቢውን የክብር ቦታ አግኝቶ በነበረባቸው ዓመታት ክበባትና የተማሪዎች የክበባት ተሳትፎ ምን ያህል ብቁ ዜጎችን አፍርቶ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። አሁንም፣ የተቀዛቀዘው ተጓዳኝ ትምህርት ዳግም ነፍስ ይዘራ ዘንድ የሚመለከታቸው ሁሉ አምርረው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
ከላይ እንደዘረዘርናቸው ሁሉ፣ “ስፔስ ሳይንስ”ንም ከተመለከትን ከስምና ሥያሜው ጀምሮ ደስ ይላል፤ ቀልብን ይስባል። በተለይ በወጣትነትና ተማሪነት እድሜ ወደፊት የሳይንስ፣ በተለይም የስፔስ ሳይንስ ሰው “ለመሆን የማይመኝ የለም” ማለት እስኪቻል ድረስ የጥናት መስኩ ያጓጓል። ጉጉት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ከተሰራ ደግሞ መሆን የማይቻልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለምና መሆን የፈለጉ ሆነው እያየናቸው ነው።
በዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአስትሮኖሚ ኦሎምፒያድ ውድድር ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፉትና ሀገራቸውን ያስጠሩት የዛሬው እንግዳችን ተማሪ ፍትሕ ግርማ (የብር ሜዳሊያ)፣ ተማሪ ሚካኤል አሸናፊ እና ተማሪ አላዛር አዳነ (እያንዳንዳቸው የነሐስ ሜዳሊያ)፣ ተማሪ ሙሳ ከድር (የብርቱ ተወዳዳሪ የክብር ሽልማት) እና ሌሎችም የዚሁ እያየንለት ያለው ውጤቶች ናቸው።
የሰው ልጅ ከሚኖርባት ምድር ባሻገር በዩኒቨርሲቲ ወይም በሕዋ ውስጥ ስላሉ ነገሮች በየጊዜው የሚያደርጋቸው ምርምሮችና ጥናቶች፣ የሚደርስባቸው ውጤቶች የአዕምሮውን ምጥቀት የሚያሳዩ አስገራሚ ክስተቶች ናቸውና ወጣት ተማሪዎች ስፔስ ሳይንቲስት ለመሆን ቢጓጉ ከቶም ስህተት ሊሆን አይችልም። ወይም፣ ወደ ሌላ የጥናት መስክ ይሄዱ ዘንድ ጫና ሊደረግባቸው አይገባም። ይህንን ስንል ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረገውና በውድድሩ ለሀገሩ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው ተማሪ ፍትሕ ግርማ እና ጓደኞቹ ያለ ምንም መሰናክል ያሰቡበት ይደርሱ ዘንድ ከወዲሁ በመመኘት ነው።
የስፔስ ሳይንስ ጥናት ለዓለም ሥልጣኔና እድገት፣ ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፈጠርና ለሰው ልጆች አኗኗር ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አንጻር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፤ በመሆኑም እነዚህን የስፔስ ሳይንስ አበርክቶዎች ለይቶ ለማወቅ ካለ ጥልቅ ፍላጎት፣ ልክ እንደነ ፍትህ ግርማ ሁሉ፣ ወጣቶች ዝንባሌያቸው ወደዚህ የጥናትና ምርምር መስክ ቢሆን ትክክል ናቸውና ወደ ሌላ ሊጠመዘዙ አይገባም።
በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ስፔስ ሳይንስ ለሀገራችን አዲስ ጉዳይ አይደለም። ማለትም፣ ከዘመናዊ የትምህርት ተቋሞቻችን መፈጠር በፊት በጥንት ሊቃውንቶቻችን ዘንድ (ለምሳሌ የአስትሮኖሚ እውቀት) “ህያው” የነበረ ሲሆን፤ ስሙን እያዘመነ ከመምጣቱ በስተቀር የሀገር በቀል እውቀት ባለቤትና ሊቃውንት የነበሩት ቀደምት ልሂቃን ዘንድ (“አቡሻክር”ን ያስቧል፤ “መጽሐፈ ሄኖክ”ን ያነባል) ጉዳዩ መሬት ይዞ ተግባራዊ ሲደረግ ኖሯል።
ስፔስ ሳይንስ እንደ አንድ ዘመናዊ ተቋም በሀገራችን ከተቋቋመና ወደ ሥራ ከገባ እድሜው ሩቅ አይደለም። ይሁን እንጂ ወደ ሰፋፊ ሥራዎችና ዜጎች ልብ ውስጥ በመግባት ቀልብ መሳብ ሲጀምር ጊዜ አልፈጀበትም። ተቋሙም አዳዲስ አሰራሮችን፤ ተሞክሮዎችንና ውጤቶችን ይዞ ወደ ሕዝብ መውረድ በመቻሉ ቅቡልነቱ ባልተጠበቀ ፍጥነት እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።
መግቢያችን ወደ እራሳችን፣ ወደ ስፔስ ሳይንስን የሚመለከተው ተቋም (በፊት የነበረውን “ስፔስ ሳይንስ” ስያሜ ከ”ካርታ ሥራዎች ባለሥልጣን” ጋር ከተዋሀደ ጀምሮ “የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት” አድርጓል) ለመሄድ እንደ መንደርደሪያ የተጠቀምንበት መሆኑን እየገለፅን ተቋሙ ከሚያከናውናቸው በርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግባራት መካከል አንዱ ወደ ሆነው፣ ለወጣት ተማሪዎች ስለሚሰጠው ልዩ የክረምት ትምህርትና ስልጠና እንሂድ።
እንደ ሌሎች፣ በተለይም በዘርፉ አስቀድመው እንደ በለፀጉትና በዘርፉ ዝንባሌና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው አዳዲስ ትውልዶችን ለማብቃትም አበክረው እየሠሩ እንዳሉት ሀገራት ሁሉ ኢትዮጵያም በዚህ ዘርፍ እየሰራች ነውና ብትዘገይም እየፈጠነች ለመሆኗ ጥሩ ማሳያ ሲሆን፤ በተለያዩ የጥናት መስኩ ዘርፎች (በስፔስ፣ በአስትሮኖሚ፣ በፊዚክስ፣ በጂኦዴሲና ተዛማጅ መስኮች) ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ሕፃናት ለማብቃት የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች (ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወዳደረችበት ዓለም አቀፍ አስትሮኖሚ ኦሎምፒያድ (OWAO2024)) ላይ በመሳተፍ ከልምድና እውቀት በዘላለም አሸናፊነትን እየተላመደች በመምጣት ላይ መሆኗ የሚያበረታታ ነው። ከእንግዳችን ፍትህ ግርማ ማብራሪያም የተረዳነው ይህንን ነው።
“በቅርቡም ‘Open World Astronomy Olympiad′ በሚል ፕሮግራም ላይ ውድድር አድርገው ሜዳሊያ ይዘው እስከ መምጣት የደረሱ” ሰልጣኞች መኖራቸውን (አንድ የብር ሜዳሊያ፣ ሶስት የነሃስ ሜዳሊያ እና የእውቅና ሰርተፊኬት ይዘው የተመለሱ ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ዝግጅት ይህንን ውጤት ማምጣታቸው አስመስግኗቸዋል)። ወደ እለቱ ዝግጅታችን ስናመራ ጉዳያችን “ኢትዮ ስፔስ ኪድስ ክለብ” ሆኖ እናገኘዋለን።
በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ተመራማሪ እና ቡድኑን ወደ ሩሲያ (እ.አ.አ. ከሴፕቴምበር 15 እስከ 22 ቀን 2024፣ በሩሲያ የትምህርት ማዕከል በሆነችው፣ ተማሪዎች ሳይንሳዊ ምርምሮችን የሚያደርጉባትና ለጉብኝት ክፍት የሆኑ ታላላቅ የምርምር ማዕከሎችም የሚገኙባት ሶቺ ክፍለ ግዛት – ሳይረስ ከተማ) ለውድድር ይዘው የተጓዙት ኢንጂነር ግዮን አሸናፊ (አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም) “ከነበረው አጭር የዝግጅት ጊዜ፣ ከፈተናው ክብደት እና ከተወዳዳሪዎቹ ጥንካሬ አንጻር ታዳጊዎቻችን ያሳዩት የውድድር ብቃት የሚደነቅ” እና ብሩህ ተስፋን አመላካች ነው።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርነውና የብር ሜዳሊያን ያገኘው፤ ወደፊት ኮምፒውቴሽናል አስትሮፊዚክስ በማጥናት ሀገሩን የበለጠ ማገልገልና ማስተዋወቅ የሚፈልገው ፍትህ ግርማም የሚለው ይሄንኑ ነው። እንደ ፍትህ አስተያየት የሌሎች ሀገራት ተወዳዳሪዎች ለአንድ ዓመት ያህል ዝግጅት አድርገው ለውድድሩ የቀረቡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቡድን ግን በጣም አጭር ለሆነ ጊዜ በመዘጋጀት ነው ወደ ውድድሩ የገባው። ይህ ወደ ፊት እንደሚሻሻል ተስፋ አለ።
ይህ ክለብ፣ በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አማካኝነት በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦና ዝንባሌ ያላቸውን ታዳጊ ሕፃናት የበለጠ ለማብቃት በሚል የተቋቋመ የሥልጠና ማዕከል በተለያዩ ፕሮግራሞቹ አማካኝነት ፍላጎትና ብቃት ያላቸውን ታዳጊዎች እያበቃ እንደሚገኝ በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የኢትዮ ስፔስ ኪድስ ክለብ አስተባባሪ አቶ አልዓዛር ስዩም ይናገራሉ። በእስከዛሬዎቹ የአራት ዙር ስልጠናዎችም 411 (325ቱ ከክልሎች የመጡ) ተማሪዎችን ማስመረቁንም ይጠቅሳሉ።
ክለቡ ከተቋቋመ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል። የመጀመሪያውን ሥልጠና መስጠት የጀመረው በዘርፉ ልዩ ተሰጥኦና ዝንባሌ ያላቸውን ሰባት ታዳጊዎች በመያዝ እንደሆነ የሚያስረዱት የክበቡ አስተባባሪ ክበቡ፤ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች በመገናኛ ብዙኃን እየተጋበዙ ስለስፔስ ሳይንስ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ተቋሙ እነዚህን ታዳጊዎች በአንድ የሥልጠና ማዕከል አድርጎ እገዛ ቢያደርግላቸው ነገ በዘርፉ የሀገራችንን ስም የሚያስጠሩ ተመራማሪዎችን ማፍራት ይቻላል በሚል እምነት ተቋቁሟል። ለአራት ዓመት የሚሆን የትምህርት ፕሮግራም ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን ነው የሚናገሩት።
የስልጠናው ቅደም ተከተላዊ ሂደቱም በመጀመሪያው ክረምት በጂ.አይ.ኤስ፣ በሳተላይት ሳይንስ፣ በሮኬት፣ በአስትሮኖሚ እና በአስትሮ ፊዚክስ፣ በፕላኒታሪ ሳይንስ እና በጂኦዴሲ ጽንሰ ሃሳቦች (ቲዮሪዎች) ላይ በክረምት መርሃ-ግብር መሠረታዊ እውቀት እንዲጨብጡ ይደረጋል። በሁለተኛው የክረምት መርሃ-ግብር ደግሞ እነዚህን ከተግባር ጋር አያይዘው ይማራሉ። በሶስተኛው የክረምት መርሃ-ግብር ትምህርታቸውን በግሩፕ ሆነው ፕሮግራሞችን ቀርጸው እንዲሠሩ እና በአራተኛው ዓመት በግል ወይም በተናጠል ጥሩ ፕሮጀክት ይዘው እንዲሠሩ ይደረጋል። በአጭሩ፣ አቶ አልዓዛር እንደነገሩን ከሆነ በኮርሱ ከቲዮሪ ጀምሮ የተግባር ሥልጠና ሳይቀር ይሰጣል።
ከተግባራቶቹ መካከል በተቋሙ ኢንኩቤሽን ሴንተር አማካኝነት ስታርትአፖችን መደገፍ፤ እንዲሁም ባለ ተሰጥኦ ተማሪዎችን መደገፍ እና ማብቃት የሆነው የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በሰባት ተማሪዎች የጀመረውን ስልጠና በማሳደግ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ ከቲዮሪ ጀምሮ (በቡራዩ ማሰልጠኛ ማዕከል) የተግባር ሥልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አስተባባሪውን ጠይቀን ተረድተናል።
በሁለተኛው ዙር የገቡ ሠልጣኞች በዚህ ዓመት 16 ፕሮጀክቶችን ቀርጸው የተለያዩ ተግባራትን በመሥራት ወደ ሶስተኛው ዙር ያለፉ መሆናቸውን፤ እንዲሁም አራተኛ ዓመት የክረምት መርሃ-ግብር ትምህርት ላይ ያሉት የመጀመሪያዎቹ ሰባት ተማሪዎች በአሁኑ ሰዓት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበት የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን በመፍጠር ልጆቹ ከመክሊታቸው ጋር እንዲያገናኙ ሥልጠና ማዕከሉ ጉልህ እገዛ እያደረገ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አልአዛር በአሁኑ ሰዓት አንድ ተማሪ ዓለም አቀፍ ግንኙነት በመፍጠር ወደ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሄዶ የነፃ ትምህርት በመማር ላይ እንደሚገኝ፤ ሌሎችም ተመሳሳይ እድል የማግኘት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ያስረዳሉ።
በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የኢትዮ ስፔስ ኪድስ ክለብ አስተባባሪ አቶ አልዓዛር ስዩም እንደሚሉት፤ ወደ ተቋሙ እንዲሁ ዘው ተብሎ አይገባም። በማዕከሉ ሥልጠና የሚሰጣቸው ተማሪዎች በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ዝንባሌና ተሰጥኦ ያላቸው ሆነው የሚሰጠውን የመግቢያ ፈተና ማለፍ የሚችሉ ናቸው። በተጨማሪም በዚህ ዘርፍ የተለየ ተሰጥኦ ያላቸው ስለመሆኑ የሚያሳይ ሥራ ካላቸውም ያንን ይዘው በመቅረብ ስለጉዳዩ ያብራራሉ። ልጆቹ ተቀባይነት ካገኙ መደበኛ ትምህርታቸውን በማይነካ መልኩ፣ በክረምት መርሃ-ግብር ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ሥልጠናው ይሰጣቸዋል።
ሰልጣኝ ተማሪዎቹ የራሳቸውን ዲዛይን ቀርጸው ከ95ሺህ የጫማ ከፍታ በላይ ባሎን ልከው ሙከራዎችን እስከ ማድረግ መድረሳቸውን የሚናገሩት አቶ አልዓዛር አንዳንድ ጊዜ በበጋ ወቅት ውጭ ሀገር ካሉ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር በቨርቿል ተጨማሪ ሥልጠና የሚሰጥበት ሁኔታም አለ። ለምሳሌ አምና ሰኔ ወር አካባቢ የተመረቁ ልጆች ፋሴሳ የሚባል ድርጅት ከቦይንግ ጋር በመተባባር ባዘጋጀው የቨርቿል ሥልጠና ኤሮ ስፔስን በተመለከተ ለአምስት ወር የቆየ ሥልጠና ወስደዋል።
“እንደ ተቋም የተያዘው ግብ ከማሰልጠኛ ማዕከሉ የተመረቁ ልጆች ከስታርትአፕ ኩባንያ ጋር በመሆን የራሳቸውን ኩባንያ አቋቁመው በስፔስ ዘርፍ እንዲሰሩ ማስቻል ነው። በአሁኑ ሰዓት እንደ ሀገር ሁለት ኩባንያዎች ተቋቁመዋል። አንዱ ኩባንያ ስፔስ ኪድ ክለብ የነበሩ አራት ልጆች ያቋቋሙት ነው። በዚህ ኩባንያ ውስጥ ለተለያየ ዓላማ የሚውል ድሮን ያለማሉ። ያንን ድሮን በፋብሪካ በብዛት አምርተው ወደ ገበያ ማውጣት የሚል እቅድ ይዘው እየሠሩ ነው”። እንደ አቶ አልዓዛር ገለጻ፤ እንደ ሀገር እንደዚህ ዓይነት ክለብ መቋቋሙ ከፍተኛ ጥቅም አለው። በተለይም በዘርፉ ዝንባሌ ያላቸውና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ችሎታና ፍላጎት እያላቸው ተደብቀው የቀሩ ልጆችን ወደ ሜዳው ለማምጣት ጥሩ እድል ይፈጥራል። በያዝነው ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ እየገባ ያለው የዛሬው እንግዳችንም የረጅም ጊዜ እቅዱ ይሄው ነው። የራሱ የሆነ ኩባንያ አቋቁሞ የሰውን ልጅ መርዳትና ሀገሩንም ማስጠራት። በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል
ኢንስቲትዩት ተመራማሪ እና ቡድኑን ወደ ሩሲያ ለውድድር ይዘው የተጓዙት ኢንጂነር ግዮን አሸናፊ እንደ ተናገሩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተደረገው ውድድርና ውጤት አስፈላጊውን ልምድ በመውሰድ “የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ኪድስ ክለብ አዋርድ” ተቋቁሟል። በመሆኑም ሁሉም፣ አቅም፣ ፍላጎትና መሻት ያላቸው ወጣት ተማሪዎች ሁሉ ወደዚሁ ክለብ እንዲመጡ ተጋብዘዋል። ሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍም ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ራሳቸውን ከወዲሁ እንዲያበቁ ተጠይቀዋል።
በመጨረሻም፣ የመጪውን ዘመን የስፔስ ሳይንስ ባለሟሎች ከወዲሁ ማፍራት እንዲቻል፣ መምህራንና “ወላጆች በስፔስ ሳይንስ እና በፈጠራ ዘርፍ የተለየ ተሰጥኦና ዝንባሌ ያላቸውን ልጆች ከህልማቸው ጋር እንዲገናኙ ከተቋሙ ጋር የማስተዋወቅና የተሻለ እውቀት እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ” አቶ አልዓዛር ጥሪ ያቀርባሉ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም