አዲስ አበባ፡- የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ወደፊት ለማስቀጠል የለውጥ ሀይሉ ከትክክለኛ ለውጥ ፈላጊ ሀይሎች ጋር ሊናበብ እንደሚገባ የሲዳማ ኣርነት ንቅናቄ (ሲኣን) ሊቀመንበር አስታወቁ።
የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ዱካሌ ላሚሶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ ለውጥ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቷል። ባለፉት ዓመታት ብዙ ዋጋ ያስከፈሉት አመጾች ህዝቡ የለውጥ ፍላጎት እንደነበረው ግልጽ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
ይህን የህዝብ ፍላጎት የተረዳ የለውጥ ሀይል ከኢህአዴግ ውስጥ ወጥቶ ለውጡን መምራት ጀምሯል ያሉት ሊቀመንበሩ ለውጡ ስኬታማ እንዲሆን የማይፈልጉ ሀይሎች ከለውጥ ሀይሉ ጋር ተቀላቅለው ለውጡን እየመከቱት ይገኛሉ።
‹‹ለውጡን በማይፈልጉ ሀይሎች ምክንያት ለውጡ ምኞትና ተስፋ ብቻ እየሆነ ነው። ወደሚፈለገው መንገድ መግባት አልተቻለም›› የሚሉት አቶ ዱካሌ፤ ለውጡን በሚፈለገው አቅጣጫ ለማስኬድ የለውጥ አመራሩ ውስጡን ሊፈትሽ ይገባል ብለዋል። ለውጥ ፈላጊዎች ከተፎካካሪም ሆነ ከገዥው ፓርቲ ውስጥ ከላይ እስከ ታች ነጥሮ ሊወጣ ይገባልም ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የፓርቲዎች አባል ያልሆኑና በስነምግባር የታነጹ ሰዎች ለውጡን እንዲያግዙ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ዱካሌ ማብራሪያ፤ የለውጥ ሀይሉ የህዝብን የልብ ትርታ በትክክል የሚያውቁ፤ ስለ ሀገሪቷ መሰረታዊ ችግሮች ጥናት ያካሄዱና በአግባቡ የሚገነዘቡ፤ የፖለቲካ አጀንዳና ፍላጎት የሌላቸው ምሁራን ለለውጥ ሀይሉ ሀሳብ በማቅረብና በማማከር ሊያግዙ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2011
መላኩ ኤሮሴ