ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ ለስኬታማነቱ በሙያቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል:: ለብዙ ዓመታትም በውሃና መስኖ ላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰርተዋል:: የኢትዮጵያ ሸለቆዎች ልማት ጥናት ባለሥልጣን፤ መጀመሪያ ሥራ የተቀጠሩበት ተቋም ነው:: በሂደት ደግሞ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ከባለሙያነት እስከ ቡድን መሪነት፣ ከዚያም ከፍ ሲል በፕሮጀክት አስተባባሪነት እና በመምሪያ ኃላፊነት አገልግለዋል:: የዛሬው የዘመን እንግዳችን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀድሞው ተደራዳሪና የውሃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው አቶ ፈቂአሕመድ ነጋሽ::
እንግዳችን አቶ ፈቂአሕመድ፣ በቀድሞው አጠራሩ የኢፌዴሪ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ (በአሁኑ አጠራር የውሃና ኢነርጂ) ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ ያሉ ሁለት የተለያዩ ዳይሬክተሮችንም በተለያየ ጊዜ በምክትል ዳይሬክተርነት መርተዋል:: በናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ስር ካሉ ሶስት ተቋማት አንዱ የሆነውን የምሥራቅ ናይል የቴክኒክ ቀጣናዊ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ በመሆን ለሰባት ዓመት አገልግለዋል:: በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ በተደራዳሪነት ለተወሰነ ዓመት ሰርተዋል:: በብዙ የትብብር መድረኮች ላይ ደግሞ ኢትዮጵያን ወክለው በቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴነት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት ችለዋል::
እኚህ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ሰበታ አካባቢ ዳለቲ ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ ተወልደው ያደጉት የዛሬው የዘመን እንግዳችን፣ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በዚያው በዳለቲ ቀበሌ ነው:: ሁለተኛ ደረጃን የተማሩት ደግሞ ሰበታ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዓለማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በእንግሊዝ ሀገር በክራንፊልድ ዩኒቨርሲቲ (Cranfield University) በውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ ሰርተዋል:: አሁን እየሰሩ ያሉት በግል ሲሆን፣ የሚያማክሩትም በውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ ነው:: አዲስ ዘመንም ከሰሞኑን ሕጋዊ ሰነድ በመሆን ይፋ የተደረገውን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነትን አስመልክቶ ስለሂደቱና ተፈጻሚነቱ ከካበተ ልምዳቸው እንዲያጋሩን እንግዳ አድርጎ ተከታዩን አቅርቦላችኋል:: መልካም ንባብ::
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ሕጋዊ ሰነድ የሆነው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ዋና ዓላማው ምንድን ነው?
አቶ ፈቂአሕመድ፡- የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት በተፋሰሱ ስድስት ሀገራት በተለይ የላይኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 14/2010 ከተፈረመ በኋላ ስድስቱ ሀገራት አጽድቀው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 13 ቀን 2024 ወደ አፈጻጸም የገባ ነው:: ይህ ስምምነት ከዚህ በኋላ የሚሆነው ዓለም አቀፍ ሕግ ነው::
የዚህ ስምምነት ዋና ዓላማ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ትብብር ማስፈን፤ የውሃ አጠቃቀምን፣ የውሃ ጥበቃን፣ የውሃ ቁጥጥርን እና አስተዳደርን ዘላቂ በሆነ መልኩ ሀገራቱ እንዲፈጽሙ ግዴታ ውስጥ ማስገባት ነው::
አዲስ ዘመን፡- የስምምነት ማሕቀፉ ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ፈቂአሕመድ፡- የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል:: ዋናው ነገር በናይል ተፋሰስ ውስጥ እንደሚታወቀው እስካሁን ድረስ የውሃ አመንጭ የሆኑት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የበይ ተመልካች ሆነው ቆይተዋል:: በውሃ ሀብቱ ላይ ደግሞ ምንም አስተዋጽኦ የሌላቸው የታቻኛው ተፋሰስ ሀገራት ውሃውን ሙሉ በሙሉ ሲጠቀሙበት ኖረዋል:: መጠቀሙ ባልከፋ ነበር:: ነገር ግን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ራሳቸውን ችለው እንዳይቆሙ እና ውሃውንም እንዳይጠቀሙ ሁሌም ደካማ እና ተጋላጭ እንዲሆኑ ሲያደቡ ቆይተዋል::
በተለይ ደግሞ ከአሁን በፊት የነበሩት ነባር የቅኝ ግዛት ሕጎች ከአሁን በፊት በቅኝ ግዛቶች መካከል እንዲሁም በቅኝ ግዛት እና በሉዓላዊ ሀገር፣ መጨረሻ ላይም የድኅረ ቅኝ ግዛት ስምምነቶች ሳቢያ የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮችን ጠፍንጎ ለመያዝ ይሞክሩ የነበረበት ሁኔታ መኖሩ ግልጽ ነበር::
አሁን የሚመጣው አዲስ ነገር የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የራሳቸው የሚገዙበት፣ አምነው የገቡበት ሕግ ይኖራቸዋል ማለት ነው:: ይህ ሕግ ደግሞ በተፋሰሱ ውስጥ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ማንኛውም የውሃ ተጠቃሚ ሀገር በሌላኛው ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳያደርስ ሀገራት መረጃ እንዲለዋወጡ እና እንዲተባበሩ እንዲሁም ተፋሰሱን አንድ ላይ እንዲንከባከቡ አስገዳጅ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ነው:: እንዲሁም ሕጉ ሀገራት በየሀገራቸው የሚያካሔዱት የውሃ አስተዳደር ዘመናዊ እና ዘላቂ እንዲሆን ስለሚያደርግ የተለየ የውሃ አስተዳደር መፍጠሩ ላይ ትልቅ ጠቀሜታ የሚኖረው ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት፣ ሂደቱ ዋጋ የተከፈለበት መሆኑ የሚታወቅ ነው፤ ሂደቱ ስኬታማ እንዳይሆን ተግዳሮት የነበረው ነገር ምን ነበር?
አቶ ፈቂአሕመድ፡– ስምምነቱ የፈጀው ወደ 13 ዓመት አካባቢ ነው:: የ13 ዓመት ድርድር ሲካሔድ የነበረው በዘጠኝ ሀገራት ነው:: ኤርትራ በፈቃደኝነቷ አልተደራደረችም:: በወቅቱ ደግሞ ደቡብ ሱዳን ሉዓላዊ ሀገር ስላልሆነች አልተሳተፈችም:: እነዚያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኝ ሀገራት ሲደራደሩ በጣም እልህ አስጨራሽ፣ አሰልቺ፣ አድካሚ፣ አንዳንዴም ደግሞ እልህ ውስጥ የሚያስገባ ሂደትን የተከተለ ነበር ማለት ይቻላል::
በተለይም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከዚህ ውስጥም ዋናዋ ግብጽ ነች፤ በመጀመሪያ ጊዜ ሲጀመር የግብጾች ሃሳብ የነበረው በድርድሩ አማካይነት እነኚህ አቅም የሌላቸው የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የቅኝ ግዛት ስምምነቱ እውቅና እንዲሰጡ አደርጋለሁ የሚል አካሔድ ነበር:: በርግጥም አጀማመሩ ላይ በተወሰነ መልኩ የሚሳካላት ዓይነት ሆኖ ተስምቷት እንደነበርም የሚታወስ ነው:: የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትም የግብጽን አቋም ወደ መደገፍ አዘንብለው ነበር::
በኋላ ላይ ግን መሠረታዊ ጉዳዩ ሲጤን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው አንድ ነው:: ስለዚህ በዚያ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው ዙሪያ አንድነትን እና አጋርነትን በመፍጠር ያንን አንድነት እና አጋርነትን ወደ ጉልበት ለወጡት:: በመሆኑም ድርድሩ አቅጣጫ እየቀየረና ፍትሃዊ እየሆነ ሲመጣ ግብጾች በተቃራኒው ደግሞ ለማደናቀፍ በጣም በርካታ ጋሬጣዎችን በየቦታው ሲያስቀምጡ ነበር:: በተደጋጋሚም ድርድሩ የተቋረጠበት ሁኔታ ነበር፤ ቢያንስ ሁለት ጊዜ መቋረጡ የማይታበል ነው:: ይሁንና ሁለቴ ተቋርጦ የተወሰነ ጊዜ ያህል ከቆየ በኋላ እንደገና በተደረገ ጥረት ደግሞ ሊካሔድ ችሏል::
በመጨረሻ አካባቢም ቢሆን ሁሉም ሀገር ከተስማማ በኋላ በተለይ ግብጾች ላለመፈረም ብዙ ምክንያት ይፈልጉ ነበር:: የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ደግሞ ምክንያቱን ለማሳጣት በጣም በርካታ ጥረት አደረጉ:: በተለይ እነ ግብጽን ያላስማማው ንዑስ አንቀፅ የሚገኝበት አንቀፅ 14 ሲሆን፣ ይህም የውሃ ዋስትናን የሚመለከት ነው።
ይህ ንዑስ አንቀጽ ለጊዜው ከስምምነቱ ውጭ የሆነው ስምምነቱ ከጸደቀ በኋላ ኮሚሽኑ እንደተቋቋመ በስድስት ወር ተደራድረው ሊጨርሱ በመስማማት ነው:: ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ግን መጨረሻ ላይ ግብጾች፤ ቀጥሎ ሱዳኖች ጥለውት ወጥተዋል:: መውጣት ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሀገራት ስምምነቱን ለማደናቀፍ ያላደረጉት ጥረት የለም:: በኢትዮጵያ በኩል ግን ጉዳዩን በከፍተኛ ትዕግስትና ብልጠት እንዲሁም ብቃት ስምምነቱ በስኬት ሊጠናቀቅ የቻለው ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡- ታችኛው ሀገራት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል፤ ይሁንና ስምምነቱ ሕጋዊ ሰነድ ሆኗል፤ ከዚህስ በኋላ በተለይ የግብጽ ጉዞ የት ድረስ ሊሆን ይችላል ይላሉ?
አቶ ፈቂአሕመድ፡– አሁን ሁሉም ነገር እየጠበበ መጥቷል:: በፊት የነበረው እንደሚታወቀው ያልፈረሙ ሀገራት እንዳይፈርሙ፤ የፈረሙ ሀገራት እንዳያጸድቁ፤ ያጸደቁትም ሀገራት መልሰው እንዲወጡ ጥረት ሲያደርጉ ነበር:: የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ዓለም አቀፍ ሕግ ሆኗል:: ይህ ማለት ደግሞ ተፈጻሚነቱ እውን ሆኗል ማለት ነው:: ይህ የሆነው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ካለፈው ጥቅምት 13 ቀን 2024 ጀምሮ ማለት ነው::
አሁን ደግሞ እያደረጉ ያሉት ነገር ኮሚሽኑ እንዳይቋቋም ጥረት ማድረግ ነው:: ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንዳይገባ ግብጾች በመጣር ላይ ይገኛሉ:: ስምምነቱ የሚለው፤ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት እንደጸደቀ የናይል ወንዝ ኮሚሽን አሁን ያለውን የናይል የትብብር መድረክ ወይም ናይል ቢዚን ኢንሼቲቭ መብት የእሱን መብት ግዴታዎችን እና ሀብቶች ይወርሳል ይላል:: ስለዚህ ኮሚሽኑ የሚቋቋመው በናይል የትብብር መድረክ ላይ ስለሆነ ያ እንዳይሆን የትብብር መድረኩ የእኛም ስለሆነ በዚያ ላይ መቋቋም አይችልም:: ይህ የጋራችን ስለሆነ ይቀጥላል የሚል አንድ አቋም ይዟል:: ሌላኛው ደግሞ ስምምነቱ ራሱ ሙሉ አይደለም፤ ሁሉንም ሀገር አላካተተም፤ አልተጠናቀቀም፤ ጎዶሎ ነው:: የሁሉም ሀገር ስምምነት የሌለበት ስለሆነ ውድቅ መደረግ አለበት የሚል አመለካከት በተደጋጋሚ ያነሳሉ:: ስለዚህ በዚህኛው የሚቀጥሉ ይመስለኛል::
ይህ ሁኔታ እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው ለተባለው የሚወሰነው ይህንን ስምምነት ያጸደቁ ሀገራት የሚያቋቁሙት ኮሚሽን ብቃቱ ለዚህ ኮሚሽን የሚሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት እንዲሁም ለኮሚሽኑ የሚሰጠው አቅም በተለይ ደግሞ የፋይናንስ አቅም የመወሰን አቅም በጣም ወሳኝ ይሆናል:: ሀገራቱ ራሳቸው በኮሚሽኑ እየተረዱ ወደ ልማት ከገቡ ኮሚሽኑ ሀገራቱን ወደ ትብብር፣ ወደ ውሃ አጠቃቀም እና ውሃ አጠባበቅ እንዲሁም ክትትል በአግባቡ ካስገባቸው፣ የኮሚሽኑ መኖር ደግሞ ግዙፍ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት መድረክ ከሆነ ግብጽና ሱዳን እንዲህ ዓይነት ግዙፍ ውሳኔ ከሚወሰንበት መድረክ ላይ ይጠፋሉ የሚል እምነት የለኝም:: ስለዚህ በወቅቱ ይመጣሉ ብዬ አስባለሁ::
አለበለዚያ ሀገራቱ ልክ ከአሁን በፊት የናይል የትብብር መድረክ ላይ እንደነበረው ደካማ የሆነ ሥልጣን እና ኃላፊነት ሰጥተውት ዓመታዊ መዋጮ እንኳ መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ካሉ ኮሚሽኑ ለፋይናንስ ፍላጎቱ የልማት አጋር የሆኑ ተቋማት እጅ ይገባና እነሱ የሚዘውሩት ከሆነ ደካማ ይሆናል፤ ደካማ ከሆነ ደግሞ ግብጽ እና ሱዳን ወደኮሚሽኑ ይመጣሉ የሚል እምነት የለኝም:: እንዲያውም እንዲያፈርሱት እድል የሚሰጣቸው ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- የትብብር ማሕቀፉን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ጨምሮ ያላጸደቁ አሉ፤ ኬንያ ብትፈርምም አለማጸደቋ ይታወቃል፤ እነዚህ ሀገራት ስምምነቱን ፈርመው እንዲያጸድቁ በኢትዮጵያ በኩል ከዚህ በኋላ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ፈቂአሕመድ፡– አሁን እነዚህን ሀገራት በሶስት መክፈል የምንችል ይመስለኛል:: ከእነዚህ ሀገራት ውስጥ ግን ኤርትራን እዚህ ውስጥ አንከትም፤ ምክንያቱም የኤርትራ ፍላጎት አይታወቀም:: አንደኛዋ ኬንያ ነች:: እንደሚታወቀውም ኬንያ ስምምነቱን ፈርማለች:: እንዲያውም የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት በመፈረም ደረጃ አራተኛዋ ሀገር ኬንያ ነች:: መፈረም ብቻ ሳይሆን ከዚያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አጸድቃለች::
ሌሎች ሀገራት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነቱን ከፈረሙ በኋላ ያጸደቁት በፓርላማዎቻቸው ሲሆን፣ በኬንያውያን አሰራር መሠረት ግን ጉዳዩ ወደ ፓርላማ አይሔድም ይባላል:: በኬንያውያን አሰራር ፕሬዚዳንቱ የሚያወጡት ድንጋጌ አለ:: እርሳቸው ያንን አውጥተው ከፈረሙ ጸድቆ ወደ አፍሪካ ሕብረት ይሔዳል ይባላል::
ኬንያ በተለይ በኢትዮጵያ በኩል የራሷ የምታነሳቸው ጥያቄዎች አሏት:: የኬንያ የማጽደቅና የማዘግየት ጉዳይ በኢትዮጵያ እና በምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ የሚባሉ አሉ:: በእነርሱ እጅ ነው ያለው፤ የእነ ዑጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡርንዲ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያ ያሉበት አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ አለ:: እነሱ መወሰን ይችላሉ:: ኢትዮጵያም ኬንያን ወደእዛ ማስገባት ትችላለች፤ ያለው በእጇ ነው:: ስለዚህ የኬንያ የተለየ ነው:: የእርሷ ቀላልም ነው ማለት ይቻላል::
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አልፈረመችም፤ ስምምነቱን ግን ተቀብለዋለች:: እንዲያውም ስምምነቱ እንዲፈረም በወቅቱ ኮንጎ የተጫወተችው ሚና ትልቅ ነው:: የናይል ተፋሰስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ስለነበረች ተቋርጦ የነበረው ድርድር እንደገና እንዲቀጥል አድርጋ ተሯሩጣ ወደ ፊርማ እንዲቀርብ አድርጋለች:: ያልፈረመችበትን ምክንያት በግልጽ አስቀምጣለች፤ ዋና ምክንያቷም ግብጽ እና ሱዳን እስካልፈረሙ ድረስ አልፈርምም የሚል ነው::
ይሁን እንጂ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ናይል/ዓባይ ላይ ብዙም መሠረታዊ ፍላጎት የላትም:: ወደ ናይል የምትገባው አንዲት ትንሽ ወንዝ (sibiliti) ናት:: የኮንጎ ግዛት በናይል ወንዝ ላይ ያለው ተፋሰስም ቢሆን ከአንድ በመቶ በታች ነው::
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የኮንጎ ወንዝ ባለቤት ነች:: የኮንጎ ወንዝ ደግሞ በዓለማችን ሁለተኛው ትልቁ ወንዝ ሲሆን፣ ናይልን 18 ጊዜ የሚገዝፍ ወንዝ ነው:: ከዚህ የተነሳ እኛ ብዙም ለማይረባ ነገር ስለምን ብለን ከሱዳን ጋር እንጣላለን የሚል አቋም ያላቸው ይመስለኛል:: ይህ የእኔ አስተያየት ነው::
ኮንጎዎች በናይል ወንዝ ላይ እምብዛም ፍላጎት የላቸውም፤ ቢመጡም ደግሞ በማንኛውም ሰዓት መምጣት ይችላሉ:: በመጡበት ጊዜ ፈርመው ኮሚሽኑን መቀላቀል ይችላሉ:: ደግሞም የሚያግዳቸው ምንም ነገር የለም::
በሶስተኛው ቡድን ውስጥ የሚወድቁት ደግሞ ግብጽ እና ሱዳን ናቸው:: እንደሚታወቀው ሁለቱም ሀገራት ስምምነቱን ውድቅ አድርገውታል:: የወጡት ከናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ብቻ ሳይሆን ከናይል ቤዚን ኢንሼቲቭም ጭምር ነው:: በርግጥ ሱዳን ከሶስት ዓመት በኋላ ተመልሳለች:: ሱዳን ትብብር ላይ ትኑር እንጂ ስምምነቱን እንደ ግብጽ ሁሉ አልተቀበለችም::
ሱዳኖች የተለሳለሰ አቋም አላቸው:: ወደ እዚህ ስምምነት የማይመጡት ደግሞ ግብጽን ፍራቻ ነው:: የ1959 ስምምነት ላይ ሁለቱም ሀገራት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚያነሱትን የውሃ አጠቃቀም ጥያቄ በጋራ ምላሽ እንሰጣለን የሚል ስምምነት ስላላቸው ያው ከግብጽ ተለይተው ወደእዚህ መምጣት የሚቸገሩ ይመስለኛል::
ስለዚህ እነርሱን ለማምጣት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት አንደኛ የእነርሱን ፍላጎት እና የእነርሱን ፍርሃትና ስጋት መረዳት መቻል አለባቸው:: የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ደግሞ ጠንክሮ መሥራት መቻል አለባቸው:: ግልጽ አሰራሮችን ማስፈን፤ ቁልፍ ቁልፍ ስልታዊ የሆኑ ውሳኔዎች ላይ ግን በራሳቸው የመወሰን አሰራር ካሰፈኑ ግብጽ እና ሱዳንም ይመጣሉ የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- በኤርትራስ በኩል?
አቶ ፈቂአሕመድ፡- ኤርትራ በፊትም ታዛቢ ነበረች፤ በድርድሩም ሆነ በትብብሩ ላይ በገዟ ፈቃዷ ታዛቢ መሆን ፈልጋለች:: የኤርትራ አቋም ወዴት እንደሆነ አይታወቅም:: በዚህም ላይ ኤርትራም ብትሆን ምናልባት ከኤርትራ የሚነሳ ሳቶ ወንዝ (Saato River) የሚባል አንድ ወንዝ አለ፤ እሱም ቢሆን ናይል አይደርስም:: ወንዙ ወደ ሱዳን አቅንቶ ረግረግ ውስጥ የሚሰርግ ነው::
ኢትዮጵያ ድንበር ላይ ሁመራ አካባቢ የተከዜ ወንዝ ድንበር ላይ ስለሚፈስ እዚያ ላይም የጋራ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል:: ከዚህ ውጭ በኤርትራም በኩል ይህ ነው የሚባል ወደ ናይል የሚሔድ ወይም የምታበረክተው የውሃ ሀብት የላትም::
አዲስ ዘመን፡- የዓባይ/ናይል ወንዝ ኮሚሽን በዓለም ላይ ካሉ ኮሚሽኖች በተሞክሮነት መውሰድ ያለበት ምንድን ነው?
አቶ ፈቂአሕመድ፡- በዓለማችን ላይ በጣም በርካታ የተፋሰስ ተቋማት አሉ፤ እነዚህ የተፋሰስ ተቋማት ሀገራቱ የሚሰጧቸው ሥልጣን እና ኃላፊነት፤ ሀገራቱ የሚሰጧቸው የዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካ እና የፋይናንስ ድጋፍ በጣም ወሳኝ ነው የሚሆነው:: በቂ ሥልጣን እና ኃላፊነት ከተሰጣቸው በተለይ ደግሞ ኮሚሽኑን የሚያስተዳድር የበላይ ውሳኔ ሰጪ አካል፣ የሀገራት መሪዎች፣ የመሪዎች ጉባኤ ከሆነ በጣም ጠንካራ ኮሚሽን ሊሆኑ ይችላል:: የናይልም የተቀረጸው በዚያ መልክ ነው::
ስለዚህ የናይል ተፋሰስ ዋና ውሳኔ ሰጪ አካል የመሪዎች ጉባኤ ከሆነ በቂ ፋይናንስ፣ በቂ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ሀገራት ከሰጡት፣ የተፋሰሱን የውሃ ሀብት በፍትሃዊነት እንዲጠቀሙ፣ እንዲለሙ፣ እንዲንከባከቡ፣ ዘላቂ ልማት እንዲያስፍኑ፣ ግጭት እንዳይፈጠር፣ ትብብር እንዲኖር ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፤ እናም ብዙዎቹ ስኬታማ የሆኑ ኮሚሽኖች የጠቀስኳቸው ጉዳዮች የተሟላላቸው ስለሆነ ከዚያ ትምህርት ተወስዶ የዓባይ/ናይል ተፋሰስም ጠንካራ የሆነ ኮሚሽን ይቋቋማል የሚል እምነት አለኝ፤ ሀገራቱንም ወደ ልማት የሚያስገባ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- የደቡብ ሱዳንን፣ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነትን ማጽደቅ ተከትላ ‘ሰነዱ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነውና አይመለከተኝም!’ በሚል ግብጽ መግለጫ ማውጣቷ ይታወቃል፤ ይህ ማሕቀፍ ግብጽ የተጣበቀችበትን የቅኝ ግዛት ውሎች በመሻር ደረጃ ሚናው የት ድረስ ነው?
አቶ ፈቂአሕመድ፡- አንድ ዓለም አቀፍ ስምምነት አስገዳጅ የሚሆነው በፈረሙትና ባጸደቁት ሀገራት ላይ ነው:: ያልፈረመው እና ያላጸደቀውን ሀገር ስምምነቱ አይመለከተውም:: ልክ እኛ የቅኝ ግዛት ስምምነት የሆኑትን የ1929ኙን እና የ1959ኙን ስምምነቶች የቅኝ ግዛት ስምምነት ናቸውና አናውቃቸውም ብለን እውቅና እንደነሳናቸው ሁሉ፤ እነሱም ይህን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት አንቀበልም ማለት መብታቸው ነው:: ስለዚህ ስምምነቱ በእነሱ ላይ አስገዳጅነት አይኖረውም:: አስገዳጅነቱ እና ተፈጻሚነቱ ፈራሚዎቹና አጽዳቂዎቹ በሆኑት የላይኛው ስድስት ሀገራት ላይ ነው::
እነሱ ማለትም ግብጽ እና ሱዳን የቅኝ ግዛት ስምምነታቸውን ከፈለጉ ይዘው መቆየት ይችላሉ:: ይህ የግብጽና ሱዳን የቅኝ ግዛት ስምምነት ከዚህ በኋላ የሚገዛው ድንበራቸው ውስጥ የገባውን ውሃ ብቻ ነው:: ይህ ነው በጣም ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ:: እስካሁን ድረስ የዓለም ማኅበረሰብ ብዥታ ውስጥ ነበረ:: የዓለም ማሕበረሰብ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትም ብዥታ ውስጥ ነበሩ:: ለምሳሌ ኬንያን፣ ዑጋንዳን መውሰድ እንችላለን:: አንዳንድ ባለሥልጣኖቻቸው የ1929 ስምምነት በእኛ ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል ብለው መግለጫ ሲሰጡ እንደነበር እናውቃለን:: ለዚህም ነው ወደ ልማት ላለመግባት ፈራ ተባ ሲሉ የነበረው:: አሁን ግን የዚህ ስምምነት መውጣት አንደኛ እነዚያ ብዥታ ውስጥ የነበሩ ሀገራት በግልጽ ያ ስምምነት በእነሱ ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ያውቁታል:: ምክንያቱም ይህን ስምምነት ካጸደቁ ከዚህ ስምምነት ጋር የሚያጋጭ ማንኛውንም ዓይነት ስምምነት እንዳይተገብሩ ወይም እንዳይቀበሉ ያስገድዳቸዋል::
ስለዚህ አንደኛ እነዚህ ሀገራት ሙሉ በሙሉ ያኛው ውድቅና ጠፊ መሆኑን አምነውበት ወደዚህ ይገባሉ:: ስለዚህ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ውስጥ ያለው ውሃ ሙሉ በሙሉ ተገዥ የሚሆነው በዚህ መሠረት ነው:: ግብጽ እና ሱዳን ውስጥ ዘልቆ የገባው ውሃ ደግሞ በቅኝ ግዛት ስምምነት መሠረት ሊተዳደር ይችላል:: ስለሆነም የውሃው ምንጭ ያለው ይህን ስምምነት ያጸደቁ ሀገራት ዘንድ ስለሆነ የናይልን ውሃ ሙሉ በሙሉ በተዘዋዋሪ መልኩ የሚያስተዳድሩት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ነው ብለን መውሰድ እንችላለን::
ሌላው የሚታየው የዓለም ማኅበረሰብ በምን መልኩ ያያቸዋል የሚለው ነው:: በተፋሰሱ ውስጥ ሁለት ስምምነቶች አሉ:: እነዚህን ሁለት ስምምነቶች የሚያያቸው በምን መልኩ ነው? የሚለውን ነው:: ዓለማችን ፍትሃዊ ከሆነች ሁለቱንም ስምምነቶች ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ነው:: ያኛው ስምምነት ዓለም አቀፍ መርህን፣ ዓለም አቀፍ መልካም ተሞክሮን ማለትም የሁለቱ ሀገራት የቅኝ ግዛት ስምምነት ዓለም አቀፍ መርህን ተሞክሮውንና ዓለም አቀፍ ሕግን ያልተከተለ ሁለት ሀገራትን ብቻ አሳትፎ ሌሎቹን የተፋሰስ ሀገራት ያገለለ፣ ውሃውን ሙሉ በሙሉ ለሁለቱ ሀገራት ብቻ የደለደለ፣ ውሃ ክፍፍል ላይ የውሃ ጥበቃ፣ እንክብካቤ፣ አስተዳደር ላይ ያላተኮረ፣ ምናልባትም ብዙ የዘርፉ ምሁራን ዋጋ የሌለው እና በመስኮት ወደ ውጭ መወርወር ያለበት ነው ብለው የፈረጁት ስምምነት ነው::
በዚህ መልኩ ስናይ ደግሞ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን ጠብቀው፣ ሀገራዊ አንድነታቸው ተረጋግጦ፣ በፍላጎታቸው የተደራደሩት፣ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያካተተ፤ እስከ መጨረሻው ድረስ የተቀበሉትም ያልተቀበሉትም ሀገራት በእኩልነት የተደራደሩበት ስለሆነ ትልቅ ተቀባይነት ይኖረዋል:: የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነትን ይዞ መገኘት ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ትልቅ የሞራል ልዕልና የሚሰጥ ነው፤ ስለሆነ ዓለም ፍትሃዊ ከሆነች ያንን የቅኝ ግዛት ስምምነት ውድቅ አድርጋ ይኸኛውን ስምምነት ትቀበለዋለች የሚል እምነት ነው ያለኝ:: የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ከዚህ በኋላ የሚኖራቸው የውሃ አጠቃቀም ፍትሃዊ የሆነ ይሆናል:: ከአሁን በፊት በቅኝ ግዛት እንደነበረው ዓይነት ስምምነቱ የውሃ ድርሻን ለግብጽ እና ሱዳን የሚሰጥ አይሆንም:: በመሆኑም በቀጣይ በናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት መሠረት የሚሰራ ይሆናል ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፡- ለሁልጊዜ ትብብርዎ ከልብ አመሰግናለሁ::
አቶ ፈቂአሕመድ፡– እኔም አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም