ኢትዮጵያ የብዙ ባሕሎች እና ወጎች ስብጥር መሆኗን በብዙ አውታሮች ስንገነዘብ ኖረናል፤ አይተናልም:: አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ጠቅለል ያለ መረዳት ይሆኑና ዝርዝር እውነታዎች ሲቀርቡ ግር እንሰኛለን:: እኔን የገጠመኝ ይሄው ነው:: አዎ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔረሰቦች መገኛ፣ የእልፍ ወጎች ማህደር፣ የቱባ እሰቶች ማማ ብዬ ስረዳ ቆይቻለሁ:: ከሰሞኑ የጋሞ ብሔረሰብን ወግና ልማድ ከእነ ተፈጥሯዊ ክዋኔው ለመረዳት በብሔሩ በከፍተኛ ድምቀት በሚከበረው የመስቀል በዓል ላይ ተገኝቼ ነበር:: አንዳንዴ ሁኔታዎች ከጠበቅናቸው እና ካስቀመጥንላቸው መጠን ሲያልፉ እኛነታችንን ተቆጣጥረው ግኡዝ እስከ ማድረግ ይደርሳሉ::
ከአዲስ አበባ ተነስተን አርባ ምንጭ ከተማ የገባነው ከምሽቱ 12፡30 ገደማ ነበር:: በማግስቱ በዶርዜ የሚካሄደውን የእርድ ሥነ ሥርዓት ለመታደም በአስተባባሪያችን ዶ/ር ሰኢድ መሐመድ በዞኑ የባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙናዬ ሞሶሌ እንዲሁም በኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ወንድይፍራው ከተማ አማካኝነት በመስቀል ዋዜማ ጉዟችንን ከአርባ ምንጭ ጀመርን::
ዶርዜ አነስተኛ ቀበሌ ስትሆን በዚያን ቀን የእርድ ሥነ ሥርዓቱን እና እሱን ተከትለው የሚካሄዱ ኩነቶችን ለመቃኘት አቅሟን የሚፈትኑ እንግዶች፣ ቱሪስቶች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም የበዓሉ ከወኞች የገበያ ሜዳውን ሞልተውት ደረስን:: እንደ ጋዜጠኛ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ መቃኘት ጀመርኩ:: ወደ ገበያው መሀል እየቀረብኩ ስመጣ እልፍ ባሕላዊ ኩነቶችን ታዘብኩ::
ካሜራ ባለሙያውን እነዚህን ያዝልኝ ብዬ ሳልጨርስ ሌላ አስደማሚ ኩነት ከጎኔ ይፈፀማል:: ደግሞ ሌላ፣ ደግሞ ሌላ ልዩ፣ ሌላ በጣም ልዩ:: በመጨረሻ በሚገባኝ እና በምችለው ልክ ብቻ ዋና ዋና ብዬ የለየኋቸውን ባሕላዊ ክዋኔዎች መከተል ጀመርኩ:: በዚህ ቅጽበት ከ2000 በላይ ከብቶች ታረዱ:: ይበላል፣ ይጨፈራል፣ ባሕላዊ ፒፓ ይጨሳል፣ ቁርጥ እዚህም እዚያም ይሸጣል፣ ዘመድ ከዘመዱ ይተቃቀፋል፣ መስቃላ ዮ፣ ዮ…ዮ…ዮ… ከሚገርም ስልታዊ አዘላል ጋር ይታያል:: በዚህ መካከል አንድ ነገር ቀልቤን ሳበኝ::
በገበያው ዳር አካባቢ ሴቶች ብቻ በነፃነት ባሕላዊ መጠጥ ሲጠጡ ተመለከትኩ፤ ጎራ አልኩ:: በመካከላቸው ቁጭ አልኩ እና ጨዋታ ጀመርን:: ምነው ሴቶች ብቻ ሆናችሁ… ወንዶች አይቀላቀሉም እንዴ አልኩ:: ሁሉም ተያይተው ፈገግ አሉ:: “እዚህ ቦታ እኛ ሴቶች ተገናኝተን እንጠጣለን፣ እንጫወታለን:: በሸጥነው ገንዘብ እንዝናናለን አሉኝ::” ቀና ብዬ ዶ/ር ሰኢድን ጠየኩት:: በኋላ የምታይው ፕሮግራም አለ:: ያኔ የበለጠ ግልፅ ይሆንልሻል አለኝ:: እና ወጌን በዚሁ ገትቼ ጉዞ ወደ ጨንቻ አልፎም ወደ ኤዞ ዱቡሻ ቀጠልን::
ጨንቻ የእርጎ ሀገር ነው ተብለን ወደሚታወቅ ቤት አቀናን:: ለሁላችንም እጅግ ልዩ ጣዕም ያለው እርጎ ቀረበልን:: ምሳም ስላልበላን የቀረበልንን ብርጭቆ ጨልጠን ወደ መኪናችን አቀናን:: እጅግ በሚገርም ሁኔታ የእርድ ፕሮግራሙ እንደተጠናቀቀ፣ ተከታትለው የሚፈፀሙ ሥርዓቶችን ለመፈፀም ሽማግሌዎች እና ታዳሚዎች ቀድመውን ሥርዓቱን ጀምረውት ደረስን::
በጋሞ ዞን እጅግ ልዩ እና አስደማሚ ኩነቶችን የሚያመላክት ባሕላዊ አስተዳደር ወይም ደሬ አላቸው:: በአሁኑ ሰዓት ወደ 42 የሚሆኑ ደሬዎች እንደሚገኙ ከ ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራን እና ኃላፊዎች ገልጸውልናል:: ባሕላዊ ደሬ ማለት ከዘመናዊ አስተዳደር በፊት እና አሁንም ላይ ያለ የአመራር ሁኔታ ነው:: አንድ ደሬ ማለት አንድ አገዛዝ ሲሆን ይህን ደሬ ወይም ባሕላዊ ክልል የሚያስተዳድረው አለቃ ሲኖረው ጉዳዮች ከቤተሰብ ጀምረው የሚዳኙበት እና የሚወሰኑበት ስብሰባ ወይም መሰብሰቢያ ቦታ ዱቡሻ ይባላል::
ያ ማለት በጋሞ ባሕላዊ ዱቡሻ እያንዳንዱ ጉዳይ ሥርዓትና ሕግጋትን ተከትሎ ካለምንም አድሎ እና የፍርድ መዛባት ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ በተለያዩ የሥልጣን ደረጃ የተከለለውን ጎሳ ወይም ደሬ ለዘመናት ሲያስተዳድሩበት የቆዩበት እና አሁንም ያለ እጅግ አስደማሚ ባሕል ነው:: ዱቡሻ በእያንዳንዱ ደሬ ውስጥ የሚገኝ ከፍ ያለ ሰፊ ሜዳ ሲሆን ከምንም ዓይነት አገልግሎት የተገለለ እና ለመሰብሰቢያነት ብቻ የተገደበ ስፍራ ነው::
የባሕሉ ሽማግሌዎች እንደገለፁልኝ ዱቡሻ በጣም የተከበረ እና የተለየ ስፍራ በመሆኑ እያንዳንዱ ደሬ ስፍራውን የሚያስተዳድር እና የሚጠብቅ አለቃ አለው:: ይህ አለቃ በስፍራው ላይ ቀርበው ውሳኔ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመጨረሻ የማፅደቅ ሥልጣን አለው:: ዱቡሻ የጎሳዎች ሁለንተናዊ ኩነቶች መከወኛ ቦታም ነው:: በመሆኑም መስቀል ሊደርስ አካባቢ ቦታው ከምንም ዓይነት ንክኪ ይጠበቃል::
ከብቶች ወደ ቦታው መግባት ይከለከላሉ:: የደመራ እለት ሜዳው ብዙ ሁነቶችን ያስተናግዳል:: በመጀመሪያው የታደምነው እውነት እጅግ በፍጥነት እና በቅፅበት የተፈፀመው የታዳጊ ሕፃናት ሹመት ነበር:: 7 ዓመት ወይም 9 ዓመት የሆናቸው ያልተገረዙ ወንድ ሕፃናት በየዓመቱ ወይም በየ2 ዓመቱ ሥልጣን ይሰጣቸዋል ወይም ሽግግር ያደርጋሉ:: የኤዞ ሀለቃ እንደገለፁልን እነዚህ ሕፃናት የሥልጣን ኃላፊነታቸው ለምሳሌ መስቀል ሲደርስ የዱቡሻ ሜዳዎችን ሕዝቡ በከብት እንዳያስነካ መከልከል፣ ለሕዝቡ መስቀል መድረሱን ማብሰር፣ በመስቀል የሚጠበቁ ጉዳዮችን ማሳሰብ እና የመሳሰሉት ናቸው::
አዲስ የተሾሙት እነዚህ ሕፃናት በባዶ እግራቸው መንገድ በሌለው ማሳ ውስጥ ከሩጫ ባልተናነሰ ፍጥነት ሲተሙ ተመለከትኩ:: ለምን ብዬ ሀለቃውን ጠየኩ:: እነዚህ ብላቴናዎች ባላቸው ሥነ ሥርዓት እና በሕዝብ አመኔታ የተመረጡ ንፁሃን ናቸው:: ስለዚህ ተመርቀዋል እና በእህሉ ሲያልፉ በረከት ያመጣሉ ተብሎ ይታሰባል:: ስለአየሁት አለባበሳቸው እና በባዶ እግር የመሆናቸውን ተርጓሜ ለሚቀጥለው ሀተታ ላስቀምጥ እና በደቂቃዎች ልዩነት የተከናወነውን ሌላ አስደናቂ ኩነት ላጋራችሁ::
በዚሁ ኤዞ ዱቡሻ ትንሽ ከፍ ብሎ በሚታይ ስፍራ ላይ አንድ የተለየ ሥርዓት አየሁ:: ጥንዶች እጅግ ተውበው እና በተለይ ሴቶች በጌጣጌጥ ደምቀው ከባሎቻቸው ጎን ቆመዋል:: ግርምቴን እና ግራ መጋባቴን ያስተዋለው የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ በጉዳዩ ዙሪያ የሚያናግረኝ አዋቂ አገናኘኝ:: “ዛሬ እያያችሁ ያላችሁት ኩነት ሶፌ ይባላል:: ይህም ማለት ባለፈው ዓመት ጋብቻቸውን የፈፀሙ ጥንዶች በዛሬው እለት ወጥተው በዚህ በዱቡሻው በሕዝብ ፊት ቀረበው ባል እና ሚስት መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት ሥርዓት ነው::” በማለት አጠቃላይ መረጃ ሰጠኝ::
እልፍ ጥያቄዎችን እያጠነጠንኩ ወደ ጥንዶች ቀረብኩ:: ሴቶቹ በባሕል ልብስ አምረው፣ በጨሌ እና የተለያዩ ጌጣጌጦች ታጅበው ቆመዋል:: አንዳንዶቹ ቡሉኮ አድርገዋል:: ከቆዳ የተሰራ ካባም ደርበዋል:: ከምንም በላይ የደነቀኝ ከኪሎ በላይ የሚመዝን የፀጉር ቅቤ ጭንቅላታቸው ላይ ተደራርቦ ሲታይ ላስተዋለ የሆነ ነጭ ኮፍያ ይመስላል:: ግምባራቸው ላይ ቀጭን ሻሽ ጠምጥመዋል:: ሌላው ገራሚ ነገር ደግሞ በጭንቅላታቸው ዙሪያ የሰጎን ላቫ ሰክተዋል:: የእነዚህ ስብጥሮች ትርጓሜ እያጓጓኝ ወደ ቃለመጠይቄ ተመለስኩ:: በደፈናው እባክህ ተጨማሪ ነገር ንገረኝ አልኩት ቅድም ወሬዬን ያስጀመረኝን ጎልማሳ::
ያደረኩትን ቆይታ ከሌሎችም የባሕል አዋቂዎች ጋር በማቀናጀት እንደሚከተለው መረዳቴን አስቀምጫለሁ::በጋሞ ባሕል አንዲት ሴት ካገባች በኋላ የምትሄደው ወደ ባሏ ቤተሰቦች ጊቢ በተሰራላቸው ቤት ነው:: ሙሽሪቷ እስከ ዛሬዋ ቀን ማለትም ሶፌ ድረስ በዚህ ቤት ውስጥ በልዩ ሁኔታ እየተቀለበች እና ከፍተኛ እንክብካቤ እየተደረገላት ትቆያለች:: ሙሽሪት ምንም ዓይነት የቤት ሥራ የመሥራት ኃላፊነት የለባትም:: የባሏ እናት እና እህት በልዩ ሁኔታ ሙሽራዋን ይንከባከቧታል:: በተለይ አማቷ ሙሽራዋን ማየት አይፈቀድላትም:: የተለያዩ ምግቦችን እያቀረበች መመገብ እና መንከባከብ ዋናው ኃላፊነት የአማቷ ነው::
ቀኑ ደርሶ ሶፌ ሲወጣ የባልዬው ቤተሰቦች የልጃቸውን ሚስት አስውበው ብዙ ቅቤ ቀብተው ወደ ዱቡሻው ያወጣሉ:: በዚህም የተሰበሰበው ሕዝብ ከቀረቡት ጥንዶች ውስጥ በጥሩ ሁኔታ የተያዘችውን ሴት ውበቷን፣ ሰውነቷን፣ አለባበሷን እና የተቀባችውን የቅቤ መጠን በማየት ፍርድ ይሰጣል:: ይሄን መስፈርት ያለፈች ሴት የባሏን ቤተሰብ ታኮራለች:: በቁንጅናም ቀዳሚ የሆነችዋ ልዩ ምርቃት እና ምስጋና ታገኛለች::
ሶፌ የሚወጡ ጥንዶች ያልወለዱ ብቻ መሆናቸውን ለገለፁልን አባት ከመስከረም ጀምሮ ከተጋቡ ልጅ የመውለድ ዕድል አላቸው እና ይሄ እንዴት ነው የሚታየው ስል ጠየኩ:: ልጅ ከወለዱ ወደ ሶፌ ባይወጡም ባልና ሚስት መሆናቸው ይረጋገጣል:: ግን ሶፌ እጅግ ልዩ ባሕል ስለሆነ ጋብቻ ከሚያዝያ ወር በኋላ እንዲፈፀም ይመከራል:: ሶፌ ያልወጡ ጥንዶች ጋብቻቸው በማህበረሰቡ እውቅና አይሰጠውም:: ማለትም ሳይወልዱ ሶፌ ያልወጡትን ማለት ነው::
ይሄ ባሕል ከአብዛኛው የሀገራችን አባታዊ መዋቅር በተለየ ለሴት ልጅ ልዩ ጥበቃ እና እንክብካቤን የሚያሳይ የተለየ ልማድ ነው እና እንደ ኢትዮጵያዊ እና አፍሪካዊ ሴት ትልቅ ኩራት የሚያጎናፅፍ የኔነቴ ኩራት ነው ብዬ አምናለሁ:: በመስቀል ዋዜማ በዱቡሻ መሰብሰቢያ ቦታ ለቀናት ብሎም ለወራት ተከልክለው የቆዩ ከብቶች ወደ ቦታው ገብተው ለመንካት እንኳን የሚያሳሳውን ሳር ያለስስት እንዲመገቡ ይፈቀዳል:: ምክንያቱን ለሀገሬው አዋቂዎች ጠይቄ የተሰጠኝ ምላሽ አሁንም ድንቅ ነበር:: እኛ ሰዎች አርደን ስንበላ ስንጠግብ፣ ከብቶችም እንደኛ መጥገብ አለባቸው:: የሚል ግንዛቤ የያዙ መልሶች ጎረፉልኝ:: ከሰው አልፎ ለእንስሳት የሚጨነቅ የሚያቅድ ድንቅ ሕዝብ!
ምንም እንኳን ምሽቱ እየቀረበ የታዳሚው ቁጥር እየተመናመነ ቢሄድም በቀኑ የሚከወኑ ሥርዓቶች በተያዘላቸው ቅደም ተከተል ቀጥለዋል:: ምረቃዎች፣ የአለቃ ሹም ሽሮች እና አስፈላጊ ጉዳዮች ተከናወኑ:: በመጨረሻ ዳመራው በባሕሉ መሠረት የመጀመሪያው ዳመራ በኤዞ ተለኮሰ ወይም ተጀመረ:: ይሄ ማለት ሌሎች የዳመራ መለኮስ ኩነቶች በየተራ በሁሉም ደሬዎች በተለያዩ ቀናት ይቀጥላሉ እንደ ካዎዎች ማብራሪያ::
መስቀል ለጋሞ ዞን ከፍተኛ ቦታ እና ልዩ አክብሮት የሚሰጠው በዓል ነው:: ዶ/ር አዲሱ አዳሙ የጋሞ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የአካባቢው ተወላጅ እንደሚሉት ዳመራ ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በጋሞ ማህበረሰብ ዘንድ የዘመን መለወጫ ምልክት ሆኖ ይከበር እንደነበር ጠቁመው ክዋኔው ከክርስትና መምጣት በኋላ ከሚደረገው ሥርዓት ጋር ተመሳስሎ በዛው ቀጠለ የሚል እሳቤ እንዳለ ተናግረው በጉዳዩ ላይ ግን ሰፋ ያለ ጥናት ያስፈልጋል ብለዋል::
ለማናገር የሞከርኳቸው ካዎዎች ወይም ንጉሶች እንዳሉት መስቀል ለጋሞ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ከዝናብ ከችግር መውጫ ምልክት ነው:: ለዚህም ምልክት ለማሳየት በመስከረም የእንግጫ ሳር ይዘው ወደ ገበያ በመውጣት የፀሐይ ዘመን መምጣቱን የክረምቱ ወቅት መገባደድን ስለዚህም መስቀል እየደረሰ መሆኑን እንግጫውን እየሰጡ ያመላክታሉ:: በዚህም ዘመን መቀየሩን ወሩም አዲስ መሆኑን ይረዳሉ:: ከላይ ጠቅለል አድርጌ ለማሳየት የሞከርኩት እልፍ ሃሳብ ያነገበ ባሕላዊ ክዋኔ ባለቤት እምዬ ኢትዮጵያ እውነትም ምስጥራዊ ምድር አንዱ ጋሞ ነው ብዬ አምናለሁ:: የተጠቀሱትን እና ሌሎችንም ጉዳዮች በተናጠል በቀጣይ ሀተታዎቼ እዳስሳቸዋለሁ::
መቅደስ ታዬ (ፒ ኤች ዲ)
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም