ሕገ ወጥ ስደትን ለመከላከል የሚሰሩ ሥራዎች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው ?

ሰሞኑን ሁለተኛው አህጉራዊ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነት ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ጉባኤው በተጀመረበት ወቅትም የፍትህ ሚኒስቴሩ ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዮስ ኢትዮጵያ የፍልሰተኞችን ጉዳይ በልማት ፖሊሲዎቿና እቅዶቿ ውስጥ አካታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግርም ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2018 የጸደቀውን ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነትን በመተግበር ላይ ትገኛለች። በስምምነቱም ከተካተቱ ሃያ አጀንዳዎች ውስጥ ኢትዮጵያ አስሩን በተለያዩ የልማት ፖሊሲዎቿና እቅዶቿ ውስጥ ተካታው እንዲፈጸሙ በመሥራት ላይ ናት።

በዚህም መደበኛ ያልሆነውን ፍልሰት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም መደበኛ የሆነውን ፍልሰት በማስፋፋት ከሕጋዊ ፍልሰት የሚገኘውን ጥቅም በማሳደግ በኩል ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል። ‹‹ኢትዮጵያ የፍልሰት መነሻ፣ መተላለፊያ እና መዳረሻ ሀገር ናት።›› ያሉት ሚንስትሩ በዚህም መነሻነት መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሀገር አቀፍ የትብብር ጥምረት ካውንስል በማቋቋም እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል::

እኛም እነዚህ በመንግሥት በኩል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ከችግሩ አሳሳቢነትና ስፋት አንጻር ምን ያህል ውጤታማ ናቸው ሰንል ባለሙያዎችን አነጋግረናል።

በቀዳሚነት ምላሻቸውን እንዲያጋሩን ያነጋገርናቸው አቶ ደረጀ ተግይበሉን ነው። አቶ ደረጀ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። አቶ ደረጀ እንደሚያብራሩት ወደ ውጭ ሀገራት በመሄድ ሥራ መሥራት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራት ዜጎችም የሚፈጸምና ጠቃሚም ነገር ነው። በአሁኑ ወቅት በርካታ ሀገራት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚላክ ገንዘብ ከውጪ ምንዛሬ ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሲሆኑ ይታያል። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ዜጎች በመደበኛ መንገድ መንቀሳቀስ ሲችሉ ብቻ ነው። መደበኛ ስደተኞች የሚባሉት በሕጋዊ መንገድ መንግሥት አውቋቸው በታወቁና ለዚህ ተብለው በተዘጋጁ ቦታዎች ስልጠና ወስደው ወደ ሌሎች ሀገራት ለሥራ የሚሄዱትን ነው። ኢትዮጵያም ይህንን አገልግሎት እንደ ሀገር ለዜጎቿ በነፃ ተደራሽ በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ለሚጓዙት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ደመወዛቸውን፤ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችና መብታቸውን በተመለከተ ስለሚዋዋሉት ውል ጭምር ድርድር ማድረግ ጀምሯል። ይህ አሰራር እጅግ እየተሻሻለ መጥቶ በዲጂታላይዝድ መንገድ ምዝገባ መካሄድ ጀምሯል። ይህ በየመንደሩ በተደጋጋሚ በደላሎች ይጠየቁ የነበረውን ከፍተኛ ክፍያ የሚያስቀርም ሲሆን ዜጎቹም የትም ሀገር ቢሆኑ በመንግሥት በኩል መብታቸውን ለማስጠበቅ የሚሰሩ ሥራዎችንም ቀላል የሚያደርግ ይሆናል።

በሕጋዊ መንገድ መሄድ በጉዞ ወቅት ከሚደርስ እንግልትና ስቃይ ከመዳን ባለፈ መብትና ጥቅሞቻቸው ቀድመው የታወቁ በመሆናቸው ተረጋግተው እንዲቆዩ ይረዳል። ቀጣሪዎቻቸው ይታወቃሉ:: በመሆኑም ጉዳት ከደረሰ፤ ገንዘባቸው ከተከለከሉ፤ የጉልበት ብዝበዛ ከተካሄደባቸው በቀላሉ መጠየቅ ይቻላል። ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት መንግሥት ጉዳዩን በቅርበት ስለሚከታተለው ችግሩን ለመቅረፍ በቀላሉ ይቻላል::

ለምሳሌ ኤጀንሲዎች ሠራተኞቹ የሰሩበትን ቢከለከሉ እዚህ ሆነው የሚከፍሉት ገንዘብ እንደ ዋስትና ያስይዛሉ። ‹‹ነገር ግን በሕጋዊ መንገድ በተጓዙት በኩል እስካሁን የከፉ ችግሮች አልተከሰቱም›› ያሉት አቶ ደረጀ ይህም ሆኖ ለኤምባሲ ያሳወቁና ችግሩ የተፈታላቸው መኖራቸውን አስታውቀዋል።

‹‹በቀጣይ አሰራሮችን ለማስተካከል የሚሰሩ ሥራዎችም ይኖራሉ።›› ያሉት አቶ ደረጀ ከዚህም ውስጥ አዲስ በወጣው ሕግ ላይ «ሌበር አታሼ» በየሀገራቱ እንደሚቀመጥ የተወሰነ በመሆኑ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሰራ ይሆናል። እነዚህም ለሀገሪቷ ወኪል ሆነው የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነቱን የሚከታተሉ በየኤምባሲዎች የሚመደቡ ይሆናል።

እነዚህ ባለሙያዎች የሠራተኞች መብት ከተጣሰ ስምምነቱን መሰረት በማድረግ ለማስከበር ይሰራሉ። ይህም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ መንግሥት ለችግር የተዳረጉ ዜጎች መኖራቸውን ካወቀ ሊሰራ የሚችለው ከሀገራቱ ጋር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመደራደር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ነው። ይህ ግን ሁሌም ሊሳካ ስለማይችል በአሁኑ ወቅት በርካቶች በተለያዩ ሀገራት በስቃይ ውስጥ ይገኛሉ። ለዚህም በመንግሥት በኩል ችግሩን በመቅረፍ የዜጎችን መብትና ጥቅም ያስከብራሉ የሚላቸውን ሥራዎች በሙሉ ሲሰራ ቆይቷል በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ይላሉ አቶ ደረጀ።

በተጨማሪ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በተያየዘ ያለውን ግንኙነት ውጤታማ ለማድረግ የድንበር አስተደዳርን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያቶች የተደረጉና ወደፊትም የሚደረጉ ውይይቶች አሉ። ይህም ድንበሩን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል ? የጸጥታ ኃይሉን፤ መከላከያ፤ ኢምግሬሽን ሌሎች በሚመለከታቸው ተቋማት በኩል ምክክር ይደረጋል። የዜጎችን መብት ከማስከበርና ጥቅሞቻቸውንም በማስጠበቅ ረገድ እንዲሁም የሕፃናትና ሴቶች ልዩ ፍላጎት ከማሟላት አኳያም የሚሰሩ ሥራዎች አሉ። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተለየ መልኩ ከፍተኛ ፍልሰት የሚታይበት በመሆኑ ለፍልሰተኞች ጉዳይ ምላሽ የሚሰጥ የአምስት ዓመት እቅድ በመያዝ እየተሰራ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት አብዛኛውን አሰራር ዲጂታላይዝድ እየተደረገ ነው:: ይህ ደግሞ ደላሎችና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠርና በወቅቱ ርምጃ ለመውሰድ በእጅጉ ጠቃሚ ነው። ይህም በሕገ ወጥ መንገድ የሚከናወኑ ተግባራትን በመግታት የዜጎችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ይሆናል። በተጨማሪም አሰራሮችን በዘመናዊ መንገድ በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ ማከናወን ያስፈለገው በአስፈጻሚው አካል በኩል ያለ የአገልግሎት አሰጣጡንም ሆነ ኤጀንሲዎችን ለመቆጣጠር ሁኔታዎችን የሚያመቻች በመሆኑ ነው።

ይህም ሆኖ ዛሬም ድረስ በሞባይል ስልክ መልእክት በመላክና በሌሎች መንገዶችም በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አገልግሎት ለማግኘት ምንም ክፍያ እንደሌለ ቢገለጽም ከመረጃ እጥረትና በቅርብ ላለ ሰው እምነት በመኖር ብዙዎች በሕገ ወጥ መንገድ በመጓዝ ለችግር እየተጋለጡ ይገኛል።

በሌላ በኩል ችግር ከመደረሱ በፊት ለመከላከልም እንደ መንግሥት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው በተለያዩ አካላት በስፋት እየተሰራበት ነው ያሉት አቶ ደረጀ በተለይም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይን የሚመለከቱ ቢሮዎች ተቀዳሚ ሥራቸው አድርገው እያከናወኑት ይገኛል። በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ አደረጃጀታቸው የሥራና ክህሎትን የሚመለከት ሲሆን የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተከፍቶ በመሥራት ላይ ነው። በእነዚህ ቢሮዎችም መረጃዎችን ተደራሽ የማድረግና ስልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች ወረዳ ደረስ በመካሄድ ላይ ናቸው። በተጨማሪ ከመንግሥት ተቋማትና የሰው ኃይል ባለፈ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ አደረጃጀቶችንም በመጠቀም እየተሰራ በመሆኑ በየወቅቱ አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛል ብለዋል።

ሌላው ሃሳባቸውን ያካፈሉን በፍትህ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም አያሌው ናቸው። እንደ አጠቃላይ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ለማለት የሚያስደፍሩ ሥራዎች ተከናውነዋል ይላሉ አቶ አብርሃም ባለፉት ዓመታትም እንደ ሀገር ሲከናወኑ የቆዩ ሥራዎችን እንደሚከተለው ገልጸዋቸዋል። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በሕጋዊ መንገድ የተላኩት ሶስት መቶ አርባ አምስት ሺህ ዜጎች አደረጃጀት ተፈጥሮ ሕጎች ወጥተው በተቋማት ደረጃ ቅንጅት በመሰራቱ የተገኘ ውጤት ነው። እነዚህን ዜጎች በሕጋዊ መንገድ መላክ ባይቻል ኖሮ ኢመደበኛውን መንገድ በመጠቀም ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸው የማይቀር ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ የውጪ ምንዛሬ ገቢም «ረሚታንስ» በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል። በዚህም ዘንድሮ ብቻ ከአራት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል።

ወንጀል በመከላከልም ረገድ በጣም አበረታችና ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ማለት ይቻላል። እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊያዝ የሚገባው በኢመደበኛ የሰዎች ዝውውር ውስጥ የሚሳተፉ አካላት የሚሰሯቸው ወንጀሎች እጅግ የተወሳሰቡና ረዥም ሰንሰለት ያላቸው መሆናቸው ነው። የወንጀለኞቹ ግንኙነት ኢትዮጵያ ውስጥ በርቀት ከምትገኝ አንዲት የገጠር ቀበሌ ወይንም መንደር እስከ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎችም መዳረሻዎች የተዘረጋ ነው። መስኩ እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይም ከጦር መሳሪያና ከአደንዛዥ እጽ ቀጥሎ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር ያለበትም ነው። አጠቃላይ በሰዎች መነገድ በዓመት ከአንድ መቶ ሃምሳ ቢሊየን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት ነው። ይህን ጠንካራ እና ብዙ ቦታዎችን የሚያካትት ሰንሰለት ለመበጣጠስ የተጠናከረና የተቀናጀ ኃይልም ሥራም የሚያስፈልግ ይሆናል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች በተወሰነ ደረጃ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል።

በዚህ ረገድ ከተሰሩ ሥራዎች መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ይህንን ወንጀል ለመከላከል ብቻ ራሱን የቻለ ክፍል አቋቁሟል። በተመሳሳይ ዓቃቤ ሕግም ይህንን ወንጀል ለመመርመር፤ ለመከታተልና ወንጀለኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂ ለማድረግ ራሱን የቻለ አደረጃጀት መስርቷል። በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ለዚህ አገልግሎት የሚውል ራሱን የቻለ ችሎት ተቋቁሟል። በዚህም እስከ ናይሮቢና ታንዛንያ ድረስ መስመራቸውን የዘረጉ ከደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በሰዎች የሚነግዱ፤ ሰዎችን የሚበዘብዙና ኩላሊት እያወጡ የሚሸጡ ትልልቅ ወንጀለኞች ባለፈው ዓመት በቁጥጥር ስር ውለው ቅጣት ተላልፎባቸዋል። ይህም ሆኖ ወንጀለኞቹ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ በመሆኑ ከሌሎች ሀገራት ጋር በጥምረት መሥራትም የግድ የሚል ይሆናል።

በዚህም ረገድ ባለፈው ዓመት ከጅቡቲ ጋር የጋራ የወንጀል ምርመራ ቡድን ለማቋቋም የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ተችሏል። በዚህም በኢትዮጵያ በኩል ከየክልሉ ጀምሮ ያሉ ወንጀለኞችን ድሬዳዋና ጋላፊ ደረስ የመለየት ሥራ የሚሰራ ይሆናል። በጅቡቲ በኩልም በእነሱ በኩል ያሉትን በመለየት የጋራ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ የመረጃና የማስረጃ ልውውጥ በጋራ እየተደረገ ነው:: ከኬንያ ጋርም ሁለት ጊዜ ንግግሮች ተደርገዋል። በዚህም ረገድ ዋናውን ወንጀል የሚሰሩ የሚመለምሉ፤ የሚቀበሉና የሚያሻግሩ ከሞያሌ ጀምሮ እስከ ናይሮቢ ድረስ ያሉት መሆናቸው ይታወቃል። ይህንንም ለመፍታት ከኬንያ የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ውይይት ተጀምሯል።

በሌላ በኩል እኤአ በ2022 ሃያ ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን በማላዊ ጫካ ውስጥ ተገለው ተገኝተው ነበር። እነሱን በተመለከተ የሀገሪቱ መንግሥት ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች ለሕግ ለማቅረብ እየሰራ ይገኛል። ነገር ግን አሁንም ድረስ በርካታ ዜጎች በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ አሉ:: ለዚህም ከማላዊ ጋር የሁለትዮሽ ንግግር ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። ይህ አጋጣሚ በማላዊ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገራት እየተከሰተ ያለ በመሆኑ ዜጎች ባሉባቸው የመተላለፊያና የመዳረሻ ሀገራት ጋር የሚደረገው ውይይት የሚቀጥል ይሆናል።

በቅርቡም ከጅቡቲ ጀምሮ እስከ ሳውድ አረቢያ ያሉ ሀገራትን የሚያካትት በሚንስትሮች ደረጃ የሚደረግ ውይይት ይኖራል። የዚህ ዓላማም ዜጎች ከሀገራችን ወጥተው የሚሄዱት ሌላ ሀገር ለመውረር ወይንም ስጋት ለመሆን አይደለም። አሁን ላሉበት ነገርም የሚዳረጉት በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ነው።

ይህንን በተመለከተ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት የፈረሙት ስምምነት አለ። ስምምነቱ ሀገራት ወደነሱ የገቡ ፍልሰተኞችን እንደ ወንጀለኛ ሳይሆን እንደ ተጎጂ አይተው ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ ባለፈም እዛ ባሉበት ወቅትም እንደ እስር ሳይሆን በተለየ ማቆያ አቆይተው ከሀገራቸው መንግሥት ጋር በመነጋጋር እንዲመልሷቸው የሚል ነው። በተጨማሪ እንደ ፍትህ ሚኒስቴር ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት በሕግ ጉዳዮች በትብብር ለመሥራት ከኬንያና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስምምነት ተጀምሯል። እነዚህ ሁሉ ተግባራት በአጭር ጊዜ የተሰሩ መሆናቸው እንደ ሀገር በጉዳዩ ላይ የተሰጠውን ትኩረትና አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አመላካች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You