የስደት አስከፊነት መነገር ከጀመረ ረዥም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም ዛሬም ድረስ ባለማወቅም ይሁን የመጣውን ለመቀበል በመወሰን ሀገራቸውን ጥለው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው። ከየቤቱ ለስደት የሚነሱ ዜጎች በተለይም ወጣቶች መንገድ ሲጀምሩ በይፋ ሳይሆን በድብቅ ነው። ምክንያቱም በርካቶች ለጉዞ የሚመርጡት ሕጋዊውን መንገድ ባለመሆኑ ከተጠያቂነትና ከአከላካይ ለመጠበቅ ሲሉ የሚያደርጉት ነው።
በአንጻሩ ወደ መዳረሻቸው በማቅናት በመንገድ ላይ እያሉ አልያም በየደረሱበት ሀገራት ችግር ሲገጥማቸው በሚደረግ የትብብር ጥሪ ቤተሰብ ማኅበረሰብና ሕዝብ የጉዳዩ ተካፋይ ሲሆን ይስተዋላል። ዛሬ ዛሬ በመንግሥት ከፍተኛ ርብርብ ከነበሩበት የስቃይ ሕይወት ወደ ሀገራቸው ከሚመለሱት ባለፈ በየመንገዱና ማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰሙትም ነገሮች አሳዛኝና አስፈሪም ናቸው። እኛም ለዛሬው ዝግጅታችን በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ተግይበሉ አነጋግረን የሚከተለውን አካፍለውናል።
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ የሰዎች ዝውውርን ሕገ ወጥና ሕጋዊ የሚያሰኘው ምንድን ነው?
አቶ ደረጀ፤ የሰዎች ዝውውር የሚባለው በዋናነት አንድ ሀገር ያወጣውን ሕግ ወይንም ደግሞ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሕጎች በመጣስ የዛን ሀገር ድንበር ጥሶ መግባት ማለት ነው። ሕገ ወጥ ስደት የሚባለው መደበኛ የሆነ ፍልሰት እና መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ተብሎም ይለያል፡፡ ይህ የሚባለው ከስደተኞቹ መካከል ተገደውም የሚሄዱ በመኖራቸው ነው። መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት የሚባለው መዳረሻ ወይንም መተላለፊያ የሆነው ሀገር ያወጣውን ሕግ ጥሰው፤ አልያም ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ያስቀመጠውን ሕግና መስፈርት እንዲሁም መረጃ ሳያሟሉ መግባት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሕገ ወጥ ስደት እንዲፈጸም የሚያደርጉት እነማን ናቸው? ድርሻቸውስ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ደረጀ፤ ይሄ ሲፈጸም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ይኖራሉ። ከእነዚህም መካከል ሰዎቹን የሚያቀባብሉ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች/ደላሎች እና በሕገወጥ መንገድ ሰዎቹን ድንበር የሚያሻግሩ አካላትንም ያካትታል ።
እነዚህ አካላት ዓላማቸው የተለያየ ነው። ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች/ደላሎች ዓላማቸው ብዝበዛን መሠረት ያደረገ ነው። በዚህም የገንዘብ ዝርፊያን እና ስደተኞቹን እንደ ባርያ የጉልበት ብዝበዛ ማድረግን፤ የግዳጅ ጋብቻ መፈጸምን፤ እንዲሁም ወጣትና ሕጻናት ሴቶችን ለሴተኛ አዳሪነት በማድረግ የገቢ ምንጭ ማግኛ ማድረግን ያካትታል። በተጨማሪም በአንዳንድ ቦታዎች ከስደተኞቹ ላይ የተለያዩ የሰውነት ክፍላቸውን አካል እስከመውሰድ የሚደርሱ ናቸው። በዚህ መካከል የሚፈጸሙ ጥቃቶች ስደተኞቹን እስከሞት የሚያደርሱም ናቸው። በሌላ በኩል በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የሚያሻግሩ አካላት የሚባሉት የተለያዩ ወንጀልና ጥፋቶችን የሚፈጽሙ ቢሆንም ዓላማቸው ገንዘብ ማግኘትን ብቻ መሠረት ያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን ፡- በሕገወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎች የሚደርስባቸው ችግር እንዴት ይታያል ?
አቶ ደረጀ፡– በሕገወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎች ድንበር ከተሻገሩበት ጊዜ አንስቶ ለተለያዩ ችግሮች መዳረግ ይጀምራሉ። ከእነዚህም ውስጥ በስፋት የሚታወቁት ለአካላዊ መጎሳቆል ከውሃ ጥም ጀምሮ የምግብና መጠጥ እጦት ይህንን ተከትሎና በሌሎች ምክንያቶች ለበሽታና ለሞት የሚጋለጡበት አጋጣሚም ይፈጠራል። በዚህ ሁኔታ በምድር የሚያደርጉትን ጉዞ ካጠናቀቁ ሌላውና ዋናው ፈተና የሚገጥማቸው ባሕር ሲያቋርጡ ነው። በዚህ ወቅትም ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የሚሳፈሩባቸው ጀልባዎች ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም። ከዚህም ባለፈ ከአቅም በላይ ስደተኞችን ስለሚያሳፍሩ በተደጋገሚ የምንሰማው የጀልባ መገልበጥና መስጠም ይከሰታል።
በተጨማሪ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹ ወደ ዳር ከተጠጉ ልንያዝና ችግር ሊገጥመን ይችላል በሚል ስጋት ወደ ድንበር ሳይጠጉ ስደተኞቹን ያወርዷቸውና ዋና የማይችሉት ሕይወታቸውን ለማጣት ይጋለጣሉ። በዚህ ረገድ በቅርቡ በጅቡቲ የተፈጠረውን ተመሳሳይ አሳዛኝ አጋጣሚ ማስታወስ ይቻላል። እነዚህ ስደተኞች ለአደጋ የተጋለጡት ወደ ሌላ ሀገር እየሄዱ አልነበረም። በነበሩበት ቦታ ምቹ ሁኔታ ስላልገጠማቸው ችግሩ አስመርሯቸው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ወስነው ባደረጉት ጉዞ ነው። ሕገወጦቹ አዘዋዋሪዎች ባሕሩን በሠላም ቢሻገሩም ድንበር እንደተጠጉ መሬት ሳይደርሱ ስላወረዷቸው ዋና የማይችሉት ሕይወታቸውን ለማጣት በቅተዋል። በባሕር የሚሄዱት ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች አልፈው ባሕር አቋርጠው መሬት ለመርገጥ ዕድሉን ቢያገኙም ለመተላለፊያ በሚያቋርጧቸው ሀገራትም የሚደርስ በርካታ ሰቃይ ይጠብቃቸዋል።
ለምሳሌ በጅቡቲ የሚንቀሳቀሱ ስደተኞች ባሕር አቋርጠው የሚያርፉት የመን ነው። የመኖች ደግሞ በአሁኑ ወቅት በርስ በርስ ግጭት ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ናቸው። በተጨማሪ እንደ ሀገርም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጦርነት አለባቸው። በዚህም የተነሳ አብዛኛዎቹ ስደተኞች ልጆችና ወጣቶች በመሆናቸው ለሽብር፤ ለውትድርና እና ሌሎች እኩይ ተግባራት የሚመለመሉበት አጋጣሚም ሰፊ ነው። አንዳንዶቹ ቡድኖችም ልጆቹን የየራሳቸው አገልጋይ አድርገው የሚያስቀሯቸው ሲሆን በመርከብ ላይ ለሚሠሩ ወንጀሎችና የሽብር ተግባራት የሚያሳትፏቸውም አሉ።
ይህንንም አልፈው በዛ አካባቢ መዳረሻ ተደርጋ ወደምትታሰበው ሳዑዲ ሲደርሱ የድንበር ጠባቂ ወታደሮች በጥይት እስከ መምታት የሚደርስ እርምጃ ይወስዱባቸዋል። በዚህ አይነት ለስደት ከተንቀሳቀሱት ዜጎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከላይ በተዘረዘሩትና ተመሳሳይ ችግሮች የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራትንም ሆነ አውሮፓን ሳይረግጡ ከመንገድ የሚቀሩ ይሆናል። በተመሳሳይ ችግር ወስጥ በመተማ በሱዳን በኩል እንዲሁም በደቡብ ክልል በኬንያ በኩል የሚሰደዱት በርካቶች ናቸው።
ይህ እውነት የየእለት ዜና መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል። በአሁኑ ወቅት እንደአዲስ እየተስፋፋ የመጣው ደግሞ ስደተኞቹ ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት እንግልትና ገደላ ባለፈ አስገድደው ከቤተሰብ ገንዘብ የሚያስልኩም መበርከታቸው ነው። ብዙ ልጆች በግለሰቦች እየታገቱ ሲሆን ቤተሰብ ለማስመለስ ገንዘብ ይጠየቃል። ደላሎቹ የሚጠይቁትን ገንዘብ አግኝተውም አንዳንዶቹን የላኩበትን መስመር ተከተለው የሚመልሷቸው ሲሆን አንዳንዶቹ ግን ብሩም ተበልቶ የውሃ ሽታ ሆነው ይቀራሉ። ይህ የስደተኞቹን ቤተሰቦች ለተደጋጋሚ የኢኮኖሚ ጉዳትና ለከፍተኛ ጭንቀት የሚዳርግ ነው።
ከዚህ ሁሉ እንግልት ባለፈም በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ በመያዛቸው ለረዥም ዓመታት በእስር የሚያሳልፉትም ብዙዎች ናቸው። በዚህ ረገድ በታንዛንያ ዛሬም ድረስ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን አይደለም ወደ ፈለጉበት ሀገር ሊደርሱ ወደ ሀገራቸውም መመለስ ሳይችሉ አዛው ይገኛሉ። በተመሳሳይ ዛምቢያ ሞዛምቢክና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ውስጥም አሉ ።
አዲስ ዘመን፡- ዜጎች ከሀገር ወጥተው ለመሥራት በሕገወጥ መንገድ በደላሎች ለመንቀሳቀስ የሚወስኑት ለምንድን ነው ?
አቶ ደረጀ፤ ዜጎች ሕገወጡን መንገድ መርጠው ለእነዚህ አስከፊ ችግሮች ሊዳረጉ የሚችሉት ደላሎቹ ለጥቅማቸው ሲሉ ቀድመው በሚያደርሷቸው የተሳሳተ መረጃ በመታለል ነው። የሚያታልሏቸውም የሚስብ አማላይ ነገሮችን በመንገርና ሊፈጸም የማይችል ተስፋ በመስጠት ነው። በሕገ ወጥ መንገድ የሄዱ ዜጎች ሁሌም ለጉዳት ተጋላጭ ናቸው። በለስ ቀንቷቸው የፈለጉበት ቦታ ቢደርሱ እንኳን በሕጋዊ መንገድ እንደሚሄዱት ሌሎቹ ተጓዦች መብታቸውን ማስከበር የሚችሉበት ዕድል አይኖርም። አንዳች ጉዳትና ችግር ቢገጥማቸው እንኳን በመንግሥትም ሆነ በሌሎች አካላት እርዳታ ለማድረግ ቢፈለግ ያሉበት ቦታ ስለማይታወቅ ሁሉም ነገር አስቸጋሪ ይሆናል። ያሉበት ቦታ ከታወቀ አዘዋዋሪዎቹም ሆኑ ደላሎቹ ተጠያቂ ስለሚሆኑ የሚያቆዩዋቸው በድብቅ ቦታ ነው። በዚህ ሁኔታ ቆይተው ሲመለሱ ብዙዎቹ ከሥነ ልቦና መቃወስ ጀምሮ በርካታ ችግሮች ይዘው ነው። በተለይም ሴቶቹ በተደጋጋሚ በሚደርስባቸው ፆታዊ ጥቃት አርግዘው የሚመጡ ሲሆን አብዛኛዎቹ ከማን እንደፀነሱ እንኳን ማወቅ አይችሉም። ስደተኞቹ ከሀገር ሲወጡ መሬትን ጨምሮ ንብረት አስይዘው ከአበዳሪ ተቋማት ተበድረው ወይንም የቤተሰብ ጥሪት የሚሆኑ ከብቶችን አሽጠው ነው። ተይዘው ሲመለሱ ግን ነጠላ ጫማ እንኳን ሳይዙ ነው። እነዚህ ችግሮች ዘላቂ ጉዳትና ጸጸት የሚያስከትሉ ናቸው።
ወጣቶቹ ተታለው የሚሄዱት በመንግሥት ከሚደርሳቸው መረጃ በላይ አጠገባቸው ያሉ ደላሎችን ስለሚያምኑ ነው። በተለይም ደላሎቹ ከዚህ በፊት ሰው ልከው የሚያውቁ ከሆነ የመታመን ዕድላቸው ሰፊ ነው። ከዚህም ባለፈ እኛ ቶሎ እንጨርስላችኋለን የመንግሥት ይቆያል የሚል የተሳሳተ መረጃ የሚሰጧቸው ሲሆን ሊገጥማቸው ስለሚችለው ችግር ግን የሚነግሯቸው ነገር አይኖርም። አብዛኞቹ ደላሎች ደግሞ በሚኖሩበት አካባቢ የተሻለ ተደማጭነትና ያቃሉ ተብለው የሚታሰቡ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ በዚህ ተግባር ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ወደ ውጪ የሚልኩ ኤጀንሲዎችም ሲሳተፉበት ይታያል። በዚህ ላይ ለስደት የሚነሱ ወጣቶች በገጠር አካባቢ የሚኖሩ በመሆናቸው ስለ ሕገወጥና ሕጋዊ ስደት ትክክለኛ ግንዛቤ ያላቸውን ሰዎች የማግኘትና በመደበኛውም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ መረጃ የማግኘት እድላቸው ጠባብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መደበኛ ስደተኞች የሚባሉት እነማን ናቸው? በመደበኛነት የሚደረግ ጉዞስ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ምንድን ነው ?
አቶ ደረጀ፤ መደበኛ ስደተኞች የሚባሉት በሕጋዊ መንገድ መንግሥት አውቋቸው በታወቁና ለዚህ ተብለው በተዘጋጁ ቦታዎች ሥልጠና ወስደው ወደሌሎች ሀገራት ለሥራ የሚሄዱትን ነው። በሕጋዊ መንገድ መሄድ በጉዞ ወቅት ከሚደርስ እንግልትና ስቃይ ከመዳን ባለፈ መብትና ጥቅሞቻቸው ቀደመው የታወቁ በመሆናቸው ተረጋግተው እንዲቆዩ ይረዳል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ቀጣሪዎቻቸው የሚታወቁ በመሆኑም ጉዳት ከደረሰ በወቅቱ ለመከላከል እንዲሁም ገንዘባቸውን ከተከለከሉ እና የጉልበት ብዝበዛ ከተካሄደባቸው በቀላሉ መጠየቅ ይቻላል። በዚህ ረገድ ለሚከሰቱ ችግሮች ሀገር ቤት የላካቸው ኤጀንሲ በመኖሩ ጉዳዩንም ለመከታተል በጣም ቀላል ይሆናል።
ለምሳሌ ሠራተኞቹ የሠሩበትን ክፍያ ቢከለከሉ ኤጀንሲዎች እዚህ ሆነው የሚከፍሉት ገንዘብ እንደዋስትና ያስይዛሉ። ነገር ግን በዚህ ረገድ እንደሚባለው የከፋ ችግሮች የሉም፡፡ ይህም ሆኖ ለኤምባሲ ያሳወቁና ችግሩ የተፈታላቸው በርካቶች አሉ። በቀጣይ አሠራሮችን ለማስተካከል የሚሠሩ ሥራዎችም ይኖራሉ። ከዚህም ውስጥ በሕጉ ላይ «ሌበር አታሼ» በየሀገራቱ እንደሚቀመጥ የተወሰነ በመሆኑ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሠራ ይሆናል። እነዚህም ለሀገሪቷ ወኪል ሆነው የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነቱን የሚከታተሉ በኤምባሲዎች የሚመደቡ ይሆናል። እነዚህ ባለሙያዎች የሠራተኞች መብት ከተጣሰ ስምምነቱን መሠረት በማድረግ ለማስከበር ይሠራሉ።
ዜጎች ይህንን በመረዳት በምንም መልኩ ወደ ደላሎች መሄድ አይኖርባቸውም። በአሁኑ ወቅት በመንግሥት በኩል ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እታች ደረስ ወርደው በሴቶች አደረጃጀት በኩል እየሠሩ ይገኛል። ይህም ሆኖ ከችግሩ ስፋት እና ካለው ድህነት አንጻር አሁንም ድረስ በሕገወጥ መንገድ የሚሄዱ ወጣቶች አሉ። ለዚህ በዘላቂነት መፍትሔ የሚሆነው የሥራ ዕድል በመፍጠር ዜጎች በሀገራቸው ሠርተው የሚለወጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሕጋዊ መንገድ የሚደረጉ የጉዞ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በቂ ናቸው ሊባል ይችላል ?
አቶ ደረጀ፤ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው በተለያዩ አካላት በስፋት እየተሠራበት ይገኛል። በተለይም የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይን የሚመለከቱ ቢሮዎች ተቀዳሚ ሥራቸው ይሄ ነው። በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ አደረጃጀታቸው የሥራና ክህሎትን የሚመለከት ሲሆን የአንድ ማዕከል የሚል አገልግሎት ተከፍቶ እየተሠራ ይገኛል። በእነዚህ ቢሮዎችም መረጃዎች ሥልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ ወረዳ ድረስ እየተሄደ ይሠራል። እነዚህ አካላት ከመንግሥት ተቋማትና የሰው ኃይል ባለፈ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ አደረጃጀቶችንም ይጠቀማል።
ነገር ግን ተቀባይነት በማግኘት ረገድ ወጣቶቹ ቅድሚያና ትኩረት ሰጥተው መረጃውን አምነው የሚቀበሉትና ለተሳሳተ ውሳኔ የሚዳረጉት በቅርባቸው ካሉ ደላሎች ነው። አንዳንዶቹ ካሉበት መንደር ከመንቀሳቀሳቸው በፊት ጀምሮ ክፍያ ሲሰጡ ስለሚቆዩ መጨረሻ ፌዴራል ደረጃ ሲደርሱ ሰማኒያ ሺህ ሰባ ሺህ አውጥተናል ይላሉ። በርካቶች ደግሞ የከፈሏቸውን ሰዎች በቅጡ ስለማያውቋቸውና አድራሻም ስለማይዙ ገንዘባቸው አየር ላይ ተበልቶ ይቀራል። አንዳንዶቹ ገንዘቡን የሚከፍሉት የራሴ የሚሏቸው ሰዎች እጅ ስለሚኖርበትም ዕድሉን አግኝተው ክስ ሲመሠረትም በቂ መረጃ የማይሰጡ አሉ። ይህም ወንጀል ተፈጽሞ ጉዳዩ ወደሕግ ቢቀርብ እንኳን ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን፡- ሕገ ወጥ ስደት ከግለሰብና ከቤተሰብ ባለፈ እንደ ሀገር የሚያስከትለው ተፅዕኖ እንዴት ይታያል?
አቶ ደረጀ፤ ሕገ ወጥ ስደት በሀገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ቀላል አይደለም። አብዛኛዎቹ የሚሰደዱት ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ከፍተኛ የሀገር ሀብት ፈሶባቸው የተማሩ ናቸው። እነሱም ለስደት የሚዳረጉት ያላቸውን አቅም በመጠቀም ራሳቸውን፤ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን ለመጥቀም በማሰብ ነው። በእርግጥም አካሄዳቸው በሕጋዊ መንገድ ቢሆን እንደ ሀሳባቸው እነሱም ቤተሰብም ማኅበረሰብና ሀገርም መጥቀም ይችላሉ። በአሁኑ ወቅት በርካታ ሀገራት ከውጪ ወደሀገር ውስጥ በሚላክ ገንዘብ ከውጪ ምንዛሪ ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሲሆኑ ይታያል።
ከዚህ በተጨማሪም ዜጎች በተለያዩ መንገዶች ከሀገራቸው ውጪ ወጥተው በሌሎች ሀገራት ሲቆዩ የሚያገኟቸው ጠቃሚ የሆኑ ልምዶች፤ እውቀቶች፤ ቴክኖሎጂና ጠንካራ የሥራ ልምዶችም ይኖራሉ። በአሁኑ ወቅት ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ይዘው በመምጣት በሀገራቸው ኢንቨስት በማድረግ ብዙዎችን ተጠቃሚ ሲያደርጉ እያየን ነው። ነገር ግን ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችለው በሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ሲቻል ነው። በአሁኑ ወቅት ግን አብዛኛዎቹ ከሀገራቸው እየወጡ ያሉት ሕጋዊ መንገድን ተከትለው ባለመሆኑ እነዚህን ዕድሎች ማግኘት አይችሉም። ይልቁን እዛው እያሉም በሚገባቸው ደረጃ ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ ይብስ ብሎ አንዳንዶቹ ለራሳቸውም ብሎም ለሀገርና ለቤተሰብ የሚተርፍ ዕዳ እና ስቃይ ይዘው ይመለሳሉ።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ሕገ ወጥ ፍልሰትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የሕገ ማዕቀፍና አሠራር አለ ለማለት ይቻላል?
አቶ ደረጀ፡- በኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የተዘጋጁትና እየተተገበሩ ያሉት ሕጎች ችግር የለባቸውም። አንዳንድ ክፍተቶች ሲኖሩም በየወቅቱ የእርምት ማስተካከያ እየተደረገላቸው የሚሠሩ ናቸው። በዚህ ረገድ መንግሥት መሥራት ያለበትን ሥራ በአግባቡ እየሠራ ይገኛል። ይህም ሆኖ ዘርፉ ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበትና ጥቅም የሚያስገኝም በመሆኑ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች እንደሚኖሩ ይገመታል። ይህ አይነት ችግር በሌሎች መስኮችም ሊከሰት የሚችል ነው። በአሁኑ ወቅት አብዛኛውን አሠራር በቴክኖሎጂ ለመምራት የተጀመሩት ሥራዎችም እንደ ደላሎችና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠርና በወቅቱ እርምጃ ለመውሰድ በማሰብ ነው። ይህም በሕገወጥ መንገድ የሚከናወኑ ተግባራትን በመግታት የዜጎችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ይሆናል። በተጨማሪ መንግሥት ይህንን የጀመረው በስሩ በአስፈጻሚው አካል በኩል ያለ የአገልግሎት አሰጣጥንም ሆነ ኤጀንሲዎችን ለመቆጣጠር ሁኔታዎችን የሚያመቻች በመሆኑ ነው።
ይህም ሆኖ ዛሬም ድረስ በሞባይል ስልክ መልእክት በመላክና በሌሎች መንገዶችም በሕጋዊ መንገድ ወደውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት አገልግሎት ለማግኘት ምንም ክፍያ እንደሌለ ቢነገርም እያታለሉ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ግን አሉ። ለምሳሌ በኦን ላይን የሲ ኦ ሲና ሌሎች መረጃዎችን ለመጫን በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ የሚጠይቁ አሉ። ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሲያጭበረብሩ የተያዙና ሕጋዊ እርምጃ የተወሰደባቸው ያሉ ሲሆን ለቀጣይም ኅብረተሰቡ ይህን የሚያደርጉ አካላትን ሲመለከት ያገባኛል በሚል መጠቆም ይጠበቅበታል ።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኞቹ ሕገወጥ ስደተኞች ከሀገር የሚወጡት በደንበር በኩል የጎረቤት ሀገራትን አቋርጠው መሆኑ ይታወቃል። መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ከእነዚህ ሀገራት ጋር የሚሠራቸው ሥራዎች አሉ ?
አቶ ደረጀ፤ በመንግሥት በኩል ችግሩን በመቅረፍ የዜጎችን መብትና ጥቅም ያስከብራሉ የሚላቸውን ሥራዎች በሙሉ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በዚህ ረገድ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በተያየዘ ያለውን ግንኙነት ውጤታማ ለማድረግ የድንበር አስተዳደርን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያቶች የተደረጉና ወደፊትም የሚደረጉ ውይይቶች አሉ። በተጨማሪ በዚህ ጉዳይ ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ አሳልፎ በመስጠት ረገድም የሚደረጉ ስምምነቶችም አሉ። በቅርቡ ከጅቡቲ መንግሥት ጋር ውይይት ተካሂዷል። በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም በተለያዩ ጊዜያት ይካሄዳሉ። የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ደግሞ በተለየ ከፍተኛ ፍልሰት የሚታይበት በመሆኑ ለፍልሰተኞች ጉዳይ ምላሽ የሚሰጥ የአምስት አመት እቅድ በመያዝ እየተሠራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ዛሬ ላይ ምን ያህል ስደተኞች በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ይወጣሉ ተብሎ ይገመታል ?
አቶ ደረጀ፤ በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገራት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል በጅቡቲ በር ብቻ በየዓመቱ ከአንድ መቶ ሀምሳ ሺ እስከ ሁለት መቶ ሺ የሚደርሱ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ከሀገር ይሰደዳሉ። በመተማ በኩል ወደሱዳንና በደቡብ በኬንያ ደግሞ ቁጥራቸው በዚህ ደረጃ ባይሆንም የሚሰደዱም አሉ። በሕገወጥ መንገድ ከሀገር የሚሰደዱ ዜጎች መዳረሻም እየጨመረ ነው። ለምሳሌ እስከ ቅርብ ጊዜ ስደት ሲታሰብ ማይናማር የምትባልን ሀገር የሚያስብ አልነበረም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ታይላንድ ትሄዳላችሁ ተብለው ደላሎች አታለው መዳረሻቸውን ማይናማር ያደረጉባቸው አሉ። ወደነዚህ ሀገራት የሚወስዷቸው ደግሞ በተለየ መልኩ የተማሩ የሠለጠኑ የሚባሉትን ነው። የሕገወጥ ስደተኞች ቁጥር የተጋነነ ስለመሆኑ የጀልባ መገልበጥን ጨምሮ በተለያዩ አደጋዎች በመንገድ ከሚቀሩትና በለስ ቀንቷቸው ያሰቡበት ደርሰው ሥራ ከጀመሩት ባለፈ በየወቅቱ ወደሀገረ ቤት የሚመለሱት አመላካች ነው ።
በዚህ ረገድ ባለው ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ማለትም ከጥቅምት አራት ሁለት ሺህ አስራ ስድስት እስከ ሁለት ሺህ አስራ ሰባት መስከረም ማጠናቀቂያ አንድ መቶ አርባ አምስት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ዜጎች ወደሀገራቸው ተመልሰዋል። እነዚህ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከሳዑዲ የመጡ ናቸው፡፡ ከሳዑዲ የመጡት ብቻ ዘጠና አንድ ሺ ስድስት መቶ አርባ ሁለት ናቸው። ከየመን ሦስት ሺ ስድስት መቶ አስራ ስድስት፤ ከኦማን ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ሃያ ስድስት ከሱዳንም የተከሰተውን የርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ አርባ ሰባት ሺ ሰባት መቶ አርባ ስድስት ናቸው። ይህን መነሻ አድርጎ በርካታ የተያዙ እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል። በየሀገራቱ ያልተያዙ በየእስር ቤቱ ያሉትንም ማሰብ ይቻላል።
አብዛኞቹ ከአስራ አምስት እስከ ሠላሳ አምስት ዓመት እድሜ ያላቸውና አምራች ወጣቶች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ የተማሩና በተለያየ ዘርፍ የሠለጠኑም ይገኙበታል። ይህም ሆኖ ከመጡ በኋላ በቀጥታ ሥራ እንዳይጀምሩና ራሳቸውንን ሀገራቸውን እንዳይጠቅሙም ተመላሾቹ አንዳንዶቹ የአካል አብዛኞቹ ደግሞ የአእምሮ መታወክን ጨምሮ የሥነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። ይህም በመሆኑ በቤተሰብ በመንግሥትና በሌሎች ተቋማት በኩል ቀዳሚ ሥራ የሚደረገው የእነሱን ጤና መመለስ ላይ ነው።
በመሆኑም ይህንን ሕገ ወጥ ተግባር ለመከላከልም ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል። በቀጣይም ችግሩን ለመከላከል ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ሌሎች ድርጅቶች ጋር የተጀመሩት ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል። ይህም ሆኖ ሕገወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ ጉዳዩ ይመለከተኛል በሚል በንቃት ሊሳተፍበት ይገባል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ወጣቶችም በተሳሳተ መረጃ ባለመታለል እራሳቸውን ከሕገወጥ ስደትና ያንን ተከትሎ ከሚከሰቱ ተደራራቢ ችግሮች ሊጠብቁ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ጊዜ እናመሰግናለን ፤
አቶ ደረጀ፤ እኔም አመሰግናለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም