በ″አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ″ ሥርዓት ስብራትና ውልቃት ከደረሰባቸው የትምህርት አንጓዎች አንዱ የቋንቋ ትምህርት ነው።
″አዲስ″ (ከሱ በፊት የነበረውን ያረጀ፣ ያፈጀ፣ ለትምህርት ጥራት ብዙም አስተዋፅዖ የማያደርግ ወዘተ ለማለት ነው) በዚህ ሥርዓት ወደ ዳር ተገፍተው ከነበሩት የትምህርት አይነቶች አንዱ ቋንቋና ከሱው ጋር ተያይዘው የነበሩት የሥርዓተ ትምህርቱ አካላት እንደነበሩ አይዘነጋም። ይህ ደግሞ፣ በተለይ በድረ 1983 ዓ·ም ጎልቶ ይታይ የነበረ፤ እስከ ዛሬም የዘለቀ፣ ለመግባባትም ጭምር እያስቸገረ ያለ ርዕሰ-ነገር ነው።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የትምህርት ተቋማትን መልሕቅ አልባ አድርጎ በማንሳፈፍ ግራ ሲያጋባ የነበረው ይኸው የቋንቋ ትምህርት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። የግል ትምህርት ቤቶች እንግሊዘኛን ″ተደብቀው″ እስከ ማስተማር ከመንግሥት ደንብና መመሪያ እንዲሸፍቱ ሲያደርግ የነበረው ይሄው ምክንያቱ በግልፅ ባልሰፈረው ″እንግሊዝኛ እንዳታስተምሩ″ ቀጭን ትእዛዝ እንደ ነበር የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት ሁሉ በሀዘኔታ የሚናገሩት ጉዳይ ነበር። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ፣ በአሁኑ ዘመን የዓለም እውቀት ታጭቆ የሚገኘው በዋናነት እንግሊዘኛ ቋንቋ ውስጥ ሆኖ ሳለ እሱን አለማስተማር ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ ግራ ቢያጋባም።
ባለፈው በተባለው የትምህርት ሥርዓት መምህራንን ሲያተራምስና ወዲህና ወዲያ ሲያንከራትት የነበረው፤ የክልሎችን የትምህርት ቢሮዎችን እጅጉን ሲያስጨንቅ፣ የዘርፉ እምብርትና አስኳል የሆኑትን ተማሪዎችን ተረጋግተው በመቆም ትምህርታቸውን ይከታተሉ ዘንድ የሚያስችላቸውን የስበት ኃይል ሲያሳጣ የነበረው ከሁሉም በላይ ይኸው የቋንቋ ትምህርትና የ”ቋንቋ ፖለቲካ” ነበር ።
በዚህ በ“ሰነድ ፍተሻ″ ዘዴ በተደራጀና በተዘጋጀ ጽሑፍ አማካኝነት ለመፈተሽ እንደምንሞክረው፣ ጉዳዩ ከሀገራትም አልፎ ዓለም አቀፋዊ ገፅታ ያለው ዐቢይ ርዕስ ነው።
″ካለፉት ጊዜያት በመማር ደካማ የሆነ የትምህርት ዝግጁነት እና አሰጣጥን ለማሻሻል″ እየሠራ ከሚገኘው ትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከትምህርት ዓበይት የሪፎርም ትኩረቶች አንዱ የሥርዓተ ትምህርት ሪፎርም ነው።
አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አንድ ተማሪ ሦስት (3) ቋንቋዎችን እንዲናገር የሚያስችል መሆኑን በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሳይንስ ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ኃላፊ ዛፏ አብርሃ በቅርቡ ለብዙኃን መገናኛ ገልፀዋል።
በሥርዓተ ትምህርቱ ችግሮች ዙሪያ ከመምህራን፣ ከወላጆች እና ከተማሪዎች የሚነሱ ሀሳቦችንም እንመለከታለን ያሉት የዝግጅት ክፍሉ ኃላፊ፣ ተማሪዎች በቅድመ አንደኛ ደረጃ በአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ በአንደኛ ደረጃ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ማለትም እንግሊዝኛ ከዚያም ከሦስተኛ ክፍል በኋላ ሌላ የአጎራባች ክልል ቋንቋ እንደሚማሩም ተናግረዋል።
ሥርዓተ ትምህርቱ በምሑራን ጥናት ላይ ተመሥርቶ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ መዘጋጀቱ በተነገረለት በዚህ ሰነድ ላይ እንደተብራራው፤ የአጎራባች ክልል ቋንቋዎችም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሳይሆን በክልሎች የሚመረ(ጡ)ጥ ነው የሚሆነው።
እዚህ ላይ “ትምህርትንና የቋንቋዎች ብዛትን አያይዞ ማቅረብ ለምን አስፈለገ?″ የሚል አስተያየት አዘል ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል። ከተነሳ መልሱ በጣም አጭርና ግልፅ ነው። እሱም ሁሉንም የዘርፉን ምሑራን ያግባባውና “ከአንድ ቋንቋ (Monolingualism)፣ ወይም ሁለት ቋንቋ (Bilingualism) ይልቅ ብዙ ቋንቋዎችን ማወቅ (Multilingualism) ጠቀሜታው እጅግ የላቀ″፤ በተለይም በሥርዓተ ትምህርቱ ተካትተው በትምህርት አይነትነት ሊሰጡ የሚገባቸው የመሆኑ ጉዳይ ነው።
ይህ ሁሉ መንደርደሪያ ተማሪዎች የተለያዩ ቋንቋዎችን መማርና ማወቅ ያለባቸው መሆኑን፤ የትምህርት ፖሊሲውም ሆነ እየተከናወነ የሚገኘው ሪፎርም፤ እንዲሁም ሥርዓተ ትምህርቱ የቋንቋ ትምህርትን በተመለከተ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡ የሚገባቸው ስለ መሆኑ፤ ዘመኑ፣ በተለይም መጪው ዘመን (የወጣቶቹ ነውና) በአንድ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን ሊስተናገድ የሚችለው በተለያዩ ቋንቋዎች እውቀትና ክሂል ነውና ይህንን መሠረታዊ ጉዳይ ተማሪዎችም ሆኑ ማንኛውም የትምህርት ባለ ድርሻ አካል ሊያውቅ የሚገባ መሆኑን ለማስረፅ ነው።
የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ዛሬ ዓለም ላይ የተለያዩ ቋንቋዎችን ማወቅ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው። ልክ የእኛኑ አማርኛ ሀገራት እየተሻሙና ባለሙያዎችንና የወደፊት ዲፕሎማቶቻቸውን ከወዲሁ እያፈሩበት እንዳሉት ሁሉ፤ እኛም የተለያዩ ቋንቋዎችን ለማወቅ መጣር፤ መጪው ትውልድም ከፊቱ እየመጡ ያሉ ዕድሎች ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ እንዲያውቅ ማድረግ፤ ማስተማር ግዴታ ይሆናል።
ይህንን ስንል ዛሬ፣ የተለያዩ ዕድሎችን ይዞ እየመጣ መሆኑ እየተነገረለት ያለውን ቻይኒኛ (ማንድሪን) ለመማር ዓለም እየተሰለፈ ይገኛል። ዓለምን እንግሊዝኛ ቋንቋ ሲመራ እንዳልነበረ ሁሉ ቻይኒኛን አስቀድሞ ተከታይ ለመሆን ያለው ጊዜ ሩቅ አይመስልም። ዛሬ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ቻይኒኛን በማወቅ ከሥራ ጀምሮ የተለያዩ ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን አጫጭር ኮርሶችን በመማር ላይ ናቸው።
ፖለቲካን ከቋንቋ ነጥለው ማየት የቻሉ ሀገራት፣ በተለይም የአውሮፓ ሀገራት ከአንድ በላይ ቋንቋዎችን በሥርዓተ ትምህርታቸው ውስጥ በማካተት ዜጎቻቸውን የብዙ ቋንቋዎች ተናጋሪ (መልቲሊንጉዋል) የማድረግ ሥራዎችን መሥራት ከጀመሩ ቆይተዋል። የሀገር ውስጦችንም ሆነ የሌላ ሀገራት ቋንቋዎችን በማስተማር ብቁ ዜጋ ማፍራት ለነገ የሚባል ሥራ አለመሆኑን በመገንዘብ ትምህርት ቤቶች የቋንቋዎች መገኛ ብቻ ሳይሆን መፍለቂያ እስኪመስሉ ድረስ ከሌሎች የትምህርት አይነቶች ጋር አጣጥመው እያስኬዱት ይገኛሉ።
የተለያዩ (የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ) ቋንቋዎችን ማወቅ ጥቅሙ የትየለሌ መሆኑ የገባቸው ሀገራት የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታና ይዞታ፤ እንዲሁም የወደ ፊት አቅጣጫ ከወዲሁ በመረዳት (ወይም፣ ስትራቴጂካሊ በማሰብ) በርካታ ዜጎቻቸውን እያበለፀጉና እያበቁ ይገኛሉ።
ጉዳዩን ያላደጉት ችላ ይበሉት እንጂ ያደጉቱ ግን ሥራዬ ብለው እየሠሩበት የሚገኙ ሲሆን፤ ለዚህም የአውሮፓ ኅብረት ሀገራት ተገቢ ማሳያዎች ከመሆንም በላይ ምሳሌዎች ናቸው።
መረጃዎች (ለምሳሌ “ዩሮኒውስ″) እንደሚያሳዩት፣ የበለፀጉት የአውሮፓ ሀገራት ሁለትና ከዛ በላይ የውጪ ቋንቋዎችን (ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ጣሊያንኛ፣ እንግሊዝኛ ወዘተ) በማስተማር ረገድ “ግሩም″ የሚባል ሪከርድ እያስመዘገቡ ሲሆን፣ ይህም ከዓመት ዓመት እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል።
ከላይ የጠቀስነው የመረጃ ምንጭ እንደሚያስረዳው፤ ሀገራቱ በሁሉም (ከቅድመ-መደበኛ ትምህርት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት) የትምህርት እርከኖች የቋንቋ ትምህርቶችን አብዝተው የሚሰጡ ሲሆን፣ ከ2013 ጀምሮ እስከ 2022 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ እመርታን እያሳዩ፤ ከልሳነ ብዝኃነት አኳያ የኋልዮሽ ሄደው የነበሩትም እያገገሙና ወደ ተሻለ ውጤት እየመጡ ናቸው ። ከመካከለኛ ደረጃው እንጀምር።
በመካከለኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ የውጪ ቋንቋዎችን የማስተማር እድገት በ2013 ከነበረበት 58·4 በመቶ በ2022 ወደ 60·7 በመቶ ደርሷል።
ከ2013 ጀምሮ እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ በእነዚሁ የአውሮፓ ሀገራት ሁለትና በላይ የውጪ ቋንቋዎችን በማስተማር ሽፋናቸውን ከ4 ነጥብ 6 ወደ 6 ነጥብ 5 ከመቶ ማሳደጋቸው ተመዝግቧል።
በ2022 በእነዚሁ የአውሮፓ ኅብረት ሀገራት የቋንቋ ማስተማር ሽፋናቸው በሁለት ተከፍሎ የተመዘነ ሲሆን፣ እንግሊዝ 98፣ ጣሊያን 96፣ ግሪክ 96 በመቶ ሽፋን ላይ በመድረስ በ“ከፍተኛ″ ስር የተመደቡ ሲሆን፤ አየርላንድ (6 ነጥብ 1 )፣ ሀንጋሪ (6 ነጥብ 6)፣ አውስትራሊያ (7 ነጥብ 7 ከመቶ ) ደግሞ በዝቅተኛ ውጤት አስመዝጋቢነታቸው ተለይተዋል።
በ2022፣ በአውሮፓ ኅብረት ሀገራት ውስጥ ካሉ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል 6 ነጥብ 5 ከመቶ የሚሆኑት ሁለትና ከዛ በላይ የውጭ ቋንቋዎችን ይማራሉ።
በሉዘንበርግ 79 ነጥብ 6 በመቶ የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች የውጪ ቋንቋዎችን በመማር እየመሩ ሲሆን፣ ላቲቪያ 37 ነጥብ 2 በመቶ፤ ግሪክ 34 ነጥብ 9 በመቶ፤ ኢስቶኒያ 33 ነጥብ 6 በመቶ ሽፋን በመስጠት እንደየቅደም ተከተላቸው ተቀምጠዋል።
እነዚህን ስኬቶች እናንሳ እንጂ፣ ልሳነ ክለኤነትንም ሆነ ልሳነ ብዙነትን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ከማካተት አኳያ የወደቁና ከወደቁበትም የተነሱ ሀገራት እንዳሉ መዘንጋት አይቻልም። ፖላንድ ነጌቲቭ 6·8 በመቶ፣ ሉግዘንበርግ ነጌቲቭ 42 በመቶ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል።
እነዚህን ማሳያዎች እዚህ ማስቀመጥ ያስፈለገበት ዐቢይ ምክንያት አንድም የዓለም ሕዝብ ከግማሽ በላይ ልሣነ ክለኤ መሆኑ፤ እንደ ሀገርም ሲታይ አብዛኞቹ ሀገራት ልሣን ብዙ በመሆናቸው ነው። ችግሩ “አንዱ የአንዱን ምን ያህል ያውቃል?″ ነው እንጂ ኢትዮጵያም እንደ አገር ልሣነ-ብዙ ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
ላለፉት ዓመታት፣ እዚህ በመዲናችን አዲስ አበባ ለበርካታ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ እንግሊዝኛ እንደ አንድ የቋንቋ ትምህርት አይነት እንዳይሰጥ መደረጉ (ከዘንድሮ ጀምሮ የመማሪያ መጻሕፍት ሁሉ ተዘጋጅቶለት እንዲሰጥ ተወስኗል) አግባብ አለመሆኑን፤ እንዲሁም፣ ትምህርት ሚኒስቴር እያካሄደ ያለውን ሪፎርም ተከትሎ ″ተማሪዎች በቅድመ አንደኛ ደረጃ በአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ በአንደኛ ደረጃ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ማለትም እንግሊዝኛ፤ ከዚያም ከ3ኛ ክፍል በኋላ ሌላ የአጎራባች ክልል ቋንቋ እንደሚማሩ″ መወሰኑን ለማፅደቅ ነው።
″ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የተለያዩ የቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩባት ትልቅና ብዝኃነት ያላት ሀገር ነች፡፡″ የሚለውን የራሱ የትምህርት ሚኒስቴር ሰነድ (“አምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሐ-ግብር″) መግቢያ ዓረፍተ ነገርንም ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባትና ″አንድ ኢትዮጵያዊ ስንት የሀገሩን ቋንቋ(ዎች) ይችላል?″ የሚለውን ጥያቄም ለማንሳትና ተማሪዎቻችን ከአንድ በላይ የብሔረሰብ ቋንቋ(ዎች)ን መማር ያለባቸው መሆኑን ማሳሰብ ነው።
በአሁኑ በማኅበረሰባችን፣ በተለይም በፖለቲካው ማኅበረሰብ ዘንድ ሁሉም የራሱን ቋንቋ እንዲማር እንጂ የሌላውን እንዲያውቅ ያለማበረታታት ሁኔታዎች ናቸው የሚታዩት። ይህ ጽሑፍ እንደዚህ አይነቶቹ አስተያየትና አስተሳሰቦች ታርቀው በዘመነ ግሎባላይዜሽን ሁሉም ብዙ ቋንቋዎችን ከሀገር ውስጥና ከውጪ እንዲያውቅና የመጪ ሕይወት ዕድሉን ከወዲሁ እንዲያሰፋ ያበረታታል።
ኢትዮጵያ ይህንን ካደረገች በ1972 ″የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ በማካሄድ ከዩኔስኮ″ International Reading Association literary prize″ የተባለ ″ሽልማት″ እንዳገኘችው ሁሉ አሁንም ባለብዙ ልሳን ትውልድ በመፍጠርም ከእነ ዩኔስኮ ሽልማት ማግኘቷ የማይቀር ይሆናል።
በመጨረሻም፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን ማወቅ በረከት እንጂ መርገምት ሆኖ አያውቅም። በተለያዩ ቋንቋዎች መጻፍም ሆነ ማንበብ፤ የተለያዩ ቋንቋዎችን መስማትም ሆነ መናገር በብዙ እርምጃዎች ከሌሎች ቀድሞ መሄድ እንጂ የኋልዮሽ ጉዞ አይደለም። የተለያዩ ቋንቋዎችን ማወቅ ስመ-ጥር ያደርጋል እንጂ ከሰው በታች አያደርግም፤ ያስመሰግናል እንጂ አያስወቅስም።
ከዚህ አኳያ ነው እንግዲህ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንግሊዝኛ ቋንቋ እንዳይሰጥ ተደርጎ መቆየቱን የምናወግዘው። እውቋ የግብፅ ንግሥት ኪሊዮፓትራ ውበቷ፣ የአመራር ችሎታዋ ብቻ አልነበረም ለዝናዋ መነሻና ለተራዘመ እውቅናዋ መሠረት የሆናት፤ ከዘጠኝ ቋንቋዎች በላይ አቀላጥፋ መናገርና መስማት ብቻ ሳይሆን በቋንቋዎቹ መጻፍና ማንበብ መቻሏም እንጂ። ወደ እኛም ሀገር ስንመጣ በርካታ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች ጥለውልን ያለፉት እውቅ ሰዎች ቢያንስ ከአንድ በላይ ቋንቋዎችን የሚችሉ መሆናቸውን መገንዘብ ጠቃሚ ነው።
ከላይ የጠቀስነው የትምህርት ሚኒስቴር ሰነድ ″በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃዎች መሠረታዊ ክሂሎቶች ካላዳበሩ፣ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ አቀላጥፈው እንዳይማሩ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ በተከታታይ ደረጃዎች ባሉት ክፍሎች በሚማሩዋቸው የትምህርት አይነቶች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ የዝቅተኛ ክፍል ደረጃ የንባብ ዳሰሳ /EGRA/ ውጤትን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሰባት የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች አዲስ ሥርዓተ ትምህርት የተነደፈ ሲሆን፤ በዚሁ ሥርዓተ ትምህርት መምህራን እንዲሠለጥኑና የመማሪያ ቁሳቁሶች ተመርተው እንዲከፋፈሉ ተደርጓል።″ የሚል አንቀፅ አለው። ይህ አንቀፅ ይኑረው እንጂ ያ ሰነድ ለአደባባይ ከበቃ ከስንት ዓመት በኋላ እንኳን እንግሊዝኛ ቋንቋ ከሥርዓተ ትምህርቱ እንዲነቀል ተደርጎ እንደ ገና (በዚህ ዓመት) ተመልሶ ተተከለ። ይህ አይነቱ ስህተት ሊደገም አይገባም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም