ኢትዮጵያ ሀገራችን ከተፈጥሮ ሀብቷ እኩል በባሕል ሀብቷም ምስጉን ሀገር ናት። ሰውነትን ባስቀደሙ፣ አብሮነትና ወንድማማችነትን ባጸኑ መካሪና ዘካሪ፣ አግባቢና አስታራቂ የአብሮነት ባሕሎች የበለፀገች መሆኗ እሙን ነው። በአንድ ግንድ ላይ እንዳቆጠቆጡ ቅርንጫፎች ኢትዮጵያዊነት የተደነቀባቸው ቱባ ባሕሎች ባለቤቶች ነን። ልዩነትና ቅያሜ በሌላቸው ቢኖራቸውም ከኢትዮጵያዊነት ባልበለጠባቸው የታሪክ ገድል ስር ፊተኞች ነበርን።
ኢትዮጵያዊነት በልጦብን ጥልና አለመግባባትን በይቅር ለግዜር ስንፈታ፣ ቅያሜና ቁጣን በይቅርታ ስናበርድ ታሪክ አለን። ወንድማማችነት ልቆብን ልዩነቶቻችንን በምክክር፣ ጥያቄዎቻችንን በምክክር ስናስታርቅ ገድል አለን። ለተገፋውና ፍትሕ ለራቀው መልከ ጥቁር ድምፅ ሆነን አፍሪካን ነፃ ስናወጣ ‹የፍትሕ ደሴት› የሚል ስም ተችሮን ነበር። በኮንጎ፣ በኮሪያና በኩባ ሠላም አስከባሪዎች ሆነን ስንሰለፍ ‹የሠላም ዘቦች› የሚል መጠሪያ ነበረን። አፍሪካን በጠቅላላና የዓለምን አንድ ሁለተኛ የሚሆን ሕዝብ ከባርነት አላቀን፣ ፍትሕና እኩልነት እንዲሰፍን በማድረግ ለተወጣንው ኃላፊነት ዛሬም ተመስጋኞች ነን።
እኚህ ሁሉ የድልና ገድል ታሪኮቻችን ደምቀው የተጻፉት በማኅበራዊ ሥርዓታችን በኩል ነው። ሀገርና ሕዝብ በቀደሙበት፣ ከምንም በላይ ደግሞ ለሠላምና ፍትሕ ቀናዒ መሆናችን ያመጣው ክስተት ነው። ተያይዘንና ተደጋግፈን የነበረንበት ዘመን ተለያይተው የነበሩን ጎረቤት ሀገራት አንድ አድርጓል። በእኛ እውነት፣ በእኛ ጽናት፣ በእኛ ፍትሕ፣ በእኛ ፍቅር ከባርነት ነፃ የወጡ ሀገራት ብዙ ናቸው።
ዛሬስ? አይደለም ለሌላው ለራሳችንም አልሆንም። ለምን ካልን የመጀመሪያው ሰውና ባለክብር ካደረጉን ባሕልና እሴቶቻችን ርቀናል። የሚበልጠውን ትተን የማይጠቅመንን መከተል ጀምረናል። ሠላም አጥተን በጦርነት የናወዝነው፣ ሀይ ባይ ጠፍቶ በእርስ በርስ መገዳደል ዋጋ እየከፈልን ነው።
ፖለቲካ የሰዎች አስተሳሰብ ቢሆንም እሳቤው ሀገርና ትውልድ ከሌለበትና ራስንና ጥቂት ቡድኖችን የሚጠቅም ከሆን ውሎ አድሮ ጦርነትን መፍጠሩ አይቀርም። ከዓፄው ወደአብዮታዊ መንግሥት ስንመጣ፣ በዘመነ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያዊነት እየደበዘዘ ዘረኝነት እየተስፉ ሲመጣ አላስተዋልንም። ዘረኝነት በአንድ ያቆመንን፣ አስተሳስሮና አጋምዶ ያጸናንን ወንድማማችነታችንን ሲናጠቀን አልነቃንም።
ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በዓለም ያስተዋወቀልንን ጨዋነትና ግብረገብነትን ሽሮ ሌላ የጥላቻ መንፈስ ሲወልድ ተኝተን ነበር ፤ እነሆ በዛ መንፈስ ዛሬም ድረስ በኃይል እና በይዋጣልን ዋጋ እንከፍላለን። ለሽምግልና ቁጭ ያልንባቸው ዋርካዎቻችን ተሲያት ውጧቸዋል። በአንተም ተው በአንተም ተው የአባቶች ግሳጼ ፍቅር ያበጁ ሸንጎዎቻችን በዝምታ ጸልመዋል።
ለምን ዝም አልን? በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አለመናገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ አውቀነዋል? እነዛ ዝምታዎች ግን ዛሬ ላይ ዋጋ እያስከፈሉን ነው፤ ሰው ተረት ፈጥሮ የብቻ ትርክት ሲተርክ አዋቂዎች ለምን ዝም አሉ? ማንም እየተነሳ ያልበላውን ሲያክ፣ አብሮነትን የሚሸረሽር የዘረኝነት ወግ ሲያወጋ መለኞች ለምን ዝም አሉ?
መናገር..መነጋገር አለብን። መወያየት እውነትን መግለጥ አለብን። በእርቅና በይቅርታ ጸቦቻችንን ንቀን ወደፊት መገስገስ ይኖርብናል። ሀገር የሠሩ ማኅበራዊ ትስስሮቻችን በዝምታ ደብነው ወደማይነሱበት እንጦሮጦስ የገቡ ቀን ብንናገር እንኳን ላንደመጥ እንችላለን። በእውነትና በብዙኃን ሀሳብ ሀገር የምናቀናበት ጊዜው አሁን ነው። ሠላሳ ዓመታትን ፖለቲካው እያወራ ሕዝብ እያዳመጠ መጣን። ሦስት አስርት ዓመታትን ፖለቲከኞች ያሻቸውን እየተናገሩ ሕዝብ የጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ ከዛሬ ደረስን። ይሄው ዛሬ የዝምታችንን ፍሬ እንበላለን።
ፖለቲከኞቻችን ዝም ብለው ሕዝብ እንዲናገር መድረክ ይበጅ። መንግሥት ሲናገርና ሕዝብ ሲናገር የተለያየ ነው። ድሃና ኋላ ቀር እንዲሁም በጦርነትና በዘር ሽኩቻ በደበነች ሀገር ላይ ሕዝብ ተናጋሪ መንግሥት አድማጭ ነው መሆን ያለበት። ያለፉትን ሠላሳ ዓመታት ሕዝብ ተናግሮባቸው ቢሆን ኖሮ ለዚህ ሁሉ ጣጣ ባልበቃን ነበር። እንደብሔራዊ ምክክር ያሉ የብዙኃን አፎች የሚሰሙበት መድረክ ዋጋው የላቀ ነው። ሳይቃጠል በቅጠል በሚል መርሕ ዝምታችንን ሰብረን፣ እልኸኝነታችንን ጥለን ለእርቅና ለምክክር እንቀመጥ።
ሲያስታርቁንና ሲያስተቃቅፉን የነበሩ ዋርካዎቻችን የሉም..። አዛውንቶቻችን ለመናገር ድፍረት አጥተዋል። ጥላዎቻችን ላይ ተሲያት ፈንጥቋል። እርቅ ሜዳችን ላይ ጠራራ ወድቋል። ለዘረኝነት መደራጀት የለብንም። ለጥላቻና ወንድማማችነትን ለመሽረፍ መቧደን አይኖርም። ዳግም በሥርዓቶቻችን በኩል እንብቀል።
እኛ ካልሄድንባቸው ሥርዓቶቻችን ምንም ናቸው። ባሕልና ወግ በሕዝብ በኩል የሚገለጹ እንጂ በራሳቸው የሚንጸባረቁ አይደሉም። በዘረኝነት የለወጥናቸውን፣ በትላቻ የሸሸናቸውን አስታራቂና አዋሓጅ እሴቶቻችንን ዳግም መቃኘት ያስፈልጋል።
አባቶቻችን ዛሬ ላይ ድሮን ሲያጡ ‹የዛሬን አያድርገውና› ብለውስ ወጋቸውን ይጀምራሉ በሁሉም ወጎቻቸው ውስጥ ይሄ አባባል አይጠፋም። ፊታቸውን አጠይመው፣ መልካቸውን አወይቦ ይሄን ያክል ያስከፋቸው ዘመን፤ በጥላቻና በዘረኝነት የጨቀየው የኛ ዘመን ነው። የድሮ ናፋቂ ያደረጋቸው ።
ስለቀደመው ዘመን ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ አንድ የመሆንን እውነታ ሲተርኩ ተረት ፈጥረው የሚያወሩት እንጂ እውነት አይመስልም ነበር። ‹ይብላኝ ለእናንተ በዚህ ጉድ ዘመን ለተፈጠራችሁ እኛስ ደግ ዘመን አሳልፈናል› ብለው ስለኛ ነገዎች ሲያስቡ እና ሲቆዝሙ ማየት የተለመደ ነው ።
በዓለም ላይ ካሉ ድንቅ የፍልስፍና አስተምሕሮች መሐል ‹እኛ ሁላችንም የምርጫዎቻችን ውጤቶች ነን እንጂ በእኛ ላይ የሚሆነው ነገር ውጤቶች አይደለንም› የሚለው አስተምሕሮ ብዙ ጊዜ ውስጤን ይይዘዋል። አስተምሕሮ ዘርዘር አድርገን ስናየው እንዲህ ነው። በሕይወት በኩል ካየንው በሕይወት ውስጥ የደረሰብን መከራ ሳይሆን ለመከራው የምንሰጠው ምላሽ ነው ወደነገ የሚያራምደን እንደ ማለት ነው።
እንደስኬት ካስተዋልነው ደግሞ ስኬት ማለት በተንገዳገዱ ቁጥር ወደኋላ ማፈግፈግ ሳይሆን ተግዳሮትን ለድል መወጣጫነት መጠቀም የሚለውን ይይዛል። አሁን ካለው የሀገራችን አሁናዊ ሁኔታ ጋር ሲተያይ ደግሞ ጦርነትን ምርጫችን በማድረጋችን ዋጋ በመክፈል ላይ እንገኛለን። በቃ ካልን፣ በመነጋገር ለመግባባት ከተቀመጥን ነገሮች የሚስተካከሉ እንደሆኑ የሚጠቁም አስተምሕሮ ነው።
እውነት ነው ብዙ ነገሮች እንዲጎዱን በይሁንታ ፈቅደንላቸው ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛሉ። ጦርነትን ስለመረጥን ሠላም አጥተናል። ዘረኝነትን ስላስቀደምን ኢትዮጵያዊነትን ተነጥቀናል። ባሕልና ሥርዓቶቻችን በነውር ተውጠው መገዳደል ተራ ነገር ሆኗል። በቃ ባለማለታችን ወይም ደግሞ ለመነጋገር ባለመፍቀዳችን ሞትና ጉስቁልና የእለት ተዕለት ዜናዎቻችን ሆነዋል።
እስኪ በቃ እንበል። ጦርነት በቃ እንበል። ጥላቻ፣ ዘረኝነት ይብቃን እንበል። ሠላምና ወንድማማችነትን እንዲጎመሩ የመገፋፋት ልማዶቻችንን እንተው። ያኔ ያለመጠራጠር ሠላም ይመጣል። እርቅ ይወርዳል። የእምነታችንን ፍሬ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በአንድ ፎሌ እንመገባለን።
ግብረገብነት የዘመናዊነት ራስ ነው። ሥልጣኔ ብዙ መነሻዎች ቢኖሩትም እንደጨዋነት ግን አይሆኑም። ሥልጡን ስንባል ታሪክ የጻፈን፣ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ፊተኞች ሆነን ስንጠራ ሰብዓዊነትን ከአብሮነት ጋር በቀየጠ ሥርዓት በኩል ነው። ሳይገባን ወደአውሮፓና ወደምዕራባውያን እንመለከታለን እንጂ እውነተኛ ሥልጣኔ ያለው በታሪኮቻችንና በባሕሎቻችን ውስጥ ነበር።
ይሄን ለማረጋገጥ የታሪክ መነሻችንን መቃኘት መልካም ነው። በባሕልና በሥርዓት እንደዳበረ ሀገር አስፈሪ የለም። ከጦር መሣሪያ በላይ ሥርዓትና ጨዋነት በአንድ ሀገር ላይ አስፈሪ ነው። ምንም ሳይኖረን አቻችለውና አፋቅረው ያኖሩን መልካም ባሕሎቻችን ናቸው። አሁንም ከእርስ በስር ግፊያ ወጥተን ሠላማዊቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ሥልጣኔያችንን አብሮነትን ማድረግ ይኖርብናል። በአባቶች አስታራቂነት፣ በባሕልና ሥርዓቶቻችን መሪነት ተጋፍተን ከመውደቃችን በፊት ልንያያዝ ይገባል።
ዘረኝነት መርዝ ነው። ጥላቻ እሳት ነው። ለጊዜው እንጂ ሁላችንንም መብላቱ አይቀርም። እነዛ ሰብዓዊነትን የተማርንባቸው፣ አብሮነትና ፍቅርን የተቋደስንባቸው፣ የፍትሕና የሚዛናዊነት ወኔዎቻችን ዛሬ ላይ በብሔር ካባ ባይወይቡ ኖሮ በልማትና በእድገት ፊተኞች በሆንን ነበር። በባሕል ታርቀን፣ በሥርዓት ተገርተን ስለሰው ልጆች ግድ የሚሰጠው ማንነታችን ዛሬም ነፍስ ይዝራ።
በተፈጥሮና በግብረገብነት ከበለፀጉ ጥቂት የዓለም ሀገራት አንዷ ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት። በዚህ ስምም ለዘመናት ተጠርተንበታል። የተፈጥሮ ሀብታችንን ወደእድገትና ሥልጣኔ በመቀየር ላይ የምንታማ ቢሆንም ሀገር የሠራንበት የባሕል ሃብታችን በብሔር ወይቦ ዘረኝነትን ማቀንቀን እስከጀመረበት ጥቂት ዓመታት ድረስ ኢትዮጵያዊነትን ገንብተንበታል። አሁንም የሚበጀን ከዘረኝነት ማጥ መውጣት ነው።
የነበረውን ሽሮ የሚመጣውን የሚቀበል የጋራ ትርክት እንፍጠር። ፍቅርን የሚቀበል፣ አብሮነትን የሚዋጅ ብዙኃነትን ያቀፈ የተግባቦት ታሪክ በእጅጉ ያስፈልገናል። የጥላቻ ስብከቶቻችን ትተን ስለሠላምና ስለእርቅ አንደበቶቻችንን እናስላ። ጥላቻ የመጣንበትን የጦርነት ታሪክ ከመድገም ባለፈ የሚሰጠን ሌላ ክብር የለም።
በጋራ ትርክት ውስጥ የበለፀገ ሥርዓት የላቀ ዋጋ አለው። ፖለቲካችን ከዚህ ቢጀምር፣ ፖለቲከኞቻችን ከዚህ ቢነሱ ለጦርነት የሚሆን ሞራል አይኖረንም ነበር። ትውልዱም በፊተኞቹ ፈር ላይ አንጋጦ የጥላቻ ሰንፈጥን ባላነፈነፈ ነበር።
የሥነምግባርና የግብረገብነት አስተምሕሮች በብዛትና በጥራት መኖራቸው ትውልዱን በፍቅርና በኢትዮጵያዊነት አርቀው ጭምት ከማድረግ ባለፈ ሀገርና ሕዝብን በተመለከተ ዋስትና የሚሰጡን ጉዳዮች ናቸው። ሁላችንንም የሚያግባባ እውነት ልጥቀስ ብል ልጠቅስ የምችለው በጨዋነትና በሥነሥርዓት የተገነባውን የኢትዮጵያዊነት ወግ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ሥርዓትና ጨዋነት ነው። አስተዳደጋችን፣ አስተሳሰባችን፣ ማኅበራዊ ልምምዳችን፣ አኗሯሯችን፣ ባሕል ወጋችን ከዚህ እሳቤ ውስጥ የተቀዳ ነው። ተቀድተን ግን አልባከንም በሥርዓትና በጨዋነት በሥነምግባርም የታረቀውን ወግ አጥባቂ ሀገርና ሕዝብ ፈጥረናል። ይሄ መሆኑ ያጎደለብን አንዳች እንደሌለ የሚያስማማን ሲሆን በምትኩ በእምነትና በፈሪሐ እግዚአብሄርም በልፅገን ክፉን እንድንጸየፍ አድርጎናል።
አሁን ላይ እነዛ ፀዓዳ መልኮቻችን ተገፈው ከመከባበር ወደመደፋፈር፣ ከመቻቻል ወደ ይዋጣልን ገብተናል። እነኚህም ከውርደት ባለፈ ምንም እንዳላበረከቱልን ያለፉት ዓመታቶች የዓይን እማኞቻችን ናቸው። በአንድ ጥላ ስር ለአንድ ጉዳይ የሚመክረው የጨዋነት ሥነምግባራችን ወይቦ ዋጋ እያስከፈለን ነው።
ልዩነታችንን ረስተን በአንድነትና በቤተሰባዊ መንፈስ ተቀላቅለንና ተዋሕደን የኖርንባቸው ጊዜያቶች ዛሬ ላይ ይናፍቁናል። ዘመን የሰው ልጅ የሀሳብ ባሪያ ነው። ድሮና ዘንድሮ በእኛው የአስተሳሰብ ሚዛን አምረውና ጎሸው ታዩ እንጂ እንደነበሩ ናቸው። በበጎ ሃሳብ በጎ ሀገር መፍጠር መጪውን አስተካክሎ ነገን የተሻለ ማድረጊያ ብቸኛ ዋስትናችን ነው። እንዳንበጠስ ሆነን የተገመድንው፣ እንዳንላላ ሆነን የጠበቅንው በአብሮነት ባሕሎቻችን በኩል ነው። እናም ሀገር ለሰጡን የጋራ ሥርዓቶቻችን እንገዛ።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም