“በአዲስ አበባ የተሠሩ የልማት ሥራዎች የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን የሚመጥኑ ናቸው” – አፍሪካውያን ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎች መዲናዋን እና የአፍሪካ ህብረትና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መቀመጫነቷን የሚመጥኑ መሆናቸውን አፍሪካውያን ጎብኚዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና እና የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ የመሠረተ ልማት አውታሯን ለመለወጥ አቅዳ እየሠራች ያለው የልማት ሥራ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መቀመጫነቷን በትክክል የሚመጥኑ መሆናቸውን የሴኔጋልና ኬንያ ጎብኚዎች ገለጹ።የመንገድ ደረጃዎችና የመንገድ ዳር ልማቶች ለከተማዋ ውበት የሰጡ መሆናቸውንና ይህም ወጥና ደረጃውን የጠበቀ ከተማ እንዳደረጋት ተናግረዋል፡፡

6ኛውን የሚላን የከተማ የምግብ ፖሊሲ ስምምነት ፎረም ለመካፈል አዲስ አበባ የተገኘው ሴኔጋላዊው ጆሴፍ ሳምቡ፤ አዲስ አበባ ጉልህ የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ መሆኗን እንደታዘበ ተናግሯል።የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የበርካታ ዲፕሎማሲያዊ ተልእኮዎች ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ዘመናዊ የከተማ ገጽታ በመፍጠር የመንገድ እና የኮሪደር ልማቶች አስደናቂ ስኬቶች ጎልተው ማየታቸውን ጠቅሷል። ይህም ከተማዋ የአፍሪካ  ህብረት መቀመጫነቷን በትክክል የሚመጥን እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

የከተሞች መሻሻል ለአንድ ሀገር ወሳኝነት ያለው መሆኑንና ለዚህ ደግሞ የልማት ፕሮጀክቶች ቀዳሚ መሆናቸውን ገልጿል።በአዲስ አበባ የታየው ተግባርም ይህንን ያስመለከተ እንደሆነ ተዘዋውሮ ከተመለከተው ትዝብቱ ተናግሯል።

ኬንያዊው ኤሪክ ኦጋሎ በበኩሉ፤ ምንም እንኳን አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ ቢያያትም በተለያየ አጋጣሚ ከሚያገኘው መረጃ አንጻር ከተማዋ ታሪካዊ መሆኗን ይናገራል።አሁን ላይም ከተማዋ ፈጣን እድገት ላይ መሆኗን መገንዘቡን ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ የማስዋብ ሥራ አድናቆት የሚሰጠው ነው ያለው ኤሪክ፤ ጎዳናዎች እና መንገዶች በከፍተኛ ደረጃ መለወጣቸውን፤ ይህም ከተማዋን በከተማ ፕላን የአህጉሪቱ ተምሳሌት የመሆን ምኞቷን የሚያመለክት ወጥ የሆነ መልክ እንዲይዝ ማድረጉን ተናግሯል።

የመንገድ ሥራ ወጥነት እና መሻሻሉ የአዲስ አበባን ውበት እንዳሳደገው፤ ከተማዋ በፍጥነት እየተቀየረችና ዘመናዊነትን እያስቀጠለች መሆኗን፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የከተማ ከባቢ ለመፍጠር ከሚተገበረው ራዕይ ጋር የሚስማማ እንደሆነ አመላክቷል፡፡

በአጠቃላይ አዲስ አበባ እያከናወነች ያለው የልማት ሥራ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷን ብሎም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን የሚመጥን ነው ያለው ኤሪክ፤ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ከዚህ ልምድ በመነሳት በከተማ የልማት ሥራዎች ላይ ጥራትንና ወጥነትን ለማስጠበቅ ትምህርት የሚያገኙበት መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You