የቺካጎ ማራቶን በኀዘን የሚዘክረው ባለክብረወሰን

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ልክ በዚህ ሳምንት የቺካጎ ማራቶን እምብዛም ስሙ በርቀቱ የማይነሳ ወጣት አትሌት በቀዳሚነት ወደ መጨረሻዋ መስመር ሲገሰግስ ታየ፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ በይበልጥ የሳበው ግን የአትሌቱ ድል ሳይሆን ሩጫውን ሊያጠናቅቅ የሚችልበት ሰዓት ነበር፡፡ በርካቶች ባለማመን ስሜት ውስጥ ሆነው በአግራሞት እየተመለከቱት ነበር፡፡ ኬንያዊው አትሌት ኬልቪን ኪፕቱም የመጨረሻዋን መስመር አቋረጠ፤ ፊትለፊቱ ያገኘው የቺካጎ ማራቶን ዳይሬክተር ኬሪ ፒንኮውስኪ ላይም በደስታ ማዕበል ተውጦ ተጠመጠመበት፡፡ ውድድሩን ሲያስተላልፉ የቆዩ የዓለም መገናኛ ብዙሃንም ከዚህ ቀደም ማንም ያልፈጸመውን ይህንን ገድል በምን ሁኔታ ለአትሌቲክስ ወዳጆች እንደሚያደርሱት ግራ እስከመጋባት ደርሰው ነበር፡፡

የ23 ዓመቱ ወጣት አትሌት በእርግጥም ለዓመታት ሲጠበቅና በስፖርቱ ባለሙያዎች ክትትል ሲደረግበት የቆየውን የማራቶን የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል በሰው ልጅ ታሪክ አዲስ ታሪክ ከፍቷል፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ ያደረገው ደግሞ የርቀቱ የመጀመሪያ ግማሽ (21ኪሎ ሜትር) የተሸፈነው በ1:00:48 ሰዓት ሲሆን፤ ሁለተኛው ግማሽ (21ነጥብ195 ኪሎ ሜትር) ግን በ59 ደቂቃ ከ47 ሰከንድ መሆኑ ነበር፡፡ ማጠናቀቂያው በግራንት ፓርክ የሆነውና በነፋሳማው የአየር ሁኔታ የተካሄደው ሩጫ የዓለም የማራቶን ክብረወሰን በሆነ 2:00:35 ሰዓት ተጠቃለለ፡፡ በርካቶች የተቃረቡት ነገር ግን በሰከንዶች ልዩነት ሊያስመዘግቡ ያልቻሉትን አዲስ ሰዓት ማራቶንን በቅርብ የጀመረ ወጣት ሊነግስበት ቻለ፡፡

በሰው ልጅ የስፖርት ተሳትፎ ታሪክ እጅግ ከባድና ታላቅ ጽናትን ከሚጠይቁ ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው ማራቶን ክብረወሰን ማሻሻል የተለየ ትርጉም ይሰጠዋል። ርቀቱ ለዘመናት 2 ሰዓትና ከዚያ በላይ መሮጡን ተከትሎም እንደ ኪፕቱም ልዩነት ፈጣሪ ሰዓት ማስመዝገብ ደግሞ የተለየ ብቃትን ይጠይቃል፡፡ እአአ በ2011 ኢትዮጵያዊው ጀግና አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ 2:03:59 በሆነ ሰዓት ማራቶንን በመሮጥ የክብረወሰን ባለቤት መሆኑን ተከትሎ ርቀቱን ‹‹ከ2:00 ሰዓት በታች መግባት ይቻላል ይሆን?›› የሚለው ሃሳብ መነሳቱን ታሪክ ያወሳል። በርካታ የስፖርት ሳይንስ ምሁራንን ጨምሮ የስፖርቱ ወዳጆች ምክንያታዊ መላምቶችን በመደርደርም ይሆናል ያሉትን ሃሳብ ሰነዘሩ፡፡

እአአ በ2017 ዘ ኢኮኖሚስት በጥናት ላይ ተመስርቶ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በርቀቱ እየተሻሻለ ያለው ሰዓት በአማካይ ከ8 እስከ 9 ሰከንድ ብቻ በመሆኑ፤ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ሌሎች አስርት ዓመታትን እንደሚጠይቅ ዘግቦ ነበር፡፡ ጉዳዩ ትኩረት እየሳበ መሄዱን ተከትሎም ናይኪን የመሰሉ ዓለም አቀፍ የስፖርት አልባሳትና ቁሳቁስ አምራቾች ጭምር ፕሮጀክት ቀርጸው ምንም እንኳን ተቀባይነት ባይኖረውም ሃሳቡን እውን ማድረግ ችለዋል፡፡ በአንጻሩ ባለሙያዎች እንደተነበዩት ሳይሆን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ምስራቅ አፍሪካሳያኑ ኢሉድ ኪፕቾጌ እና ቀነኒሳ በቀለን የመሳሰሉ አቦሸማኔዎች ብዙዎች ሳይንሳዊ መፍትሄ ለሚሹለት ለዚህ ጥረት መቋጫ ለማበጀት እጅግ ተቃርበው ነበር፡፡ ሁለቱ አንጋፋ የማራቶን ኮከቦች ለተዓምር እየተጠበቁ ሳለ ግን ያልተገመተው ወጣት ስሙን በወርቅ ቀለም በደማቁ ማጻፍ ቻለ፡፡

ይህ ከሆነ አንድ ዓመት ቢያስቆጥርም የአትሌቲክስ ቤተሰቡ ልብ ግን ዛሬም አትሌቱን በኀዘን ያስታውሰዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የጣፋጩ ታሪክ ባለቤትና በቀጣይም ስፖርቱን አንድ ርምጃ ሊያራምደው ይችላል የተባለለትን ወጣት አስደንጋጭ ህልፈት መርዶ ከወራት በኋላ መስማቱ ነበር፡፡ ሀገሩ ኬንያ ላይ መኪና ሲያሽከረክር በደረሰበት ከባድ አደጋ በአትሌቶች ሕይወት የመጨረሻዋን ጣፋጭ ድል በቅጡ ሳያጣጥም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ጀግናውን ጋብዞ ዳግም ሩጫውን ማድመቅ ያልቻለው አንጋፋው የቺካጎ ማራቶንም ዛሬ ሲካሄድ የውድድሩን መታሰቢያነት ለኬልቪን ኪፕቱም አድርጓል፡፡

‹‹በዚህ ዓመት ለእሱ እንሮጣለን›› የሚል መልዕክት በማህበራዊ የመገናኛ ገጹ ላይ ያሰፈረው የቺካጎ ማራቶን፤ የአትሌቱን ምስል የሩጫው ተሳታፊዎች በመሮጫ ቁጥራቸው ላይ እንደሚለጥፉም አስታውቀዋል፡፡ በአጭሩ የተቀጨው አሳዛኙ ኪፕቱም ሩጫውን እንደፈጸመ አቅፎት ደስታውን ያጋራው የቺካጎ ማራቶን ዳይሬክተሩ ፒንኮውስኪ በበኩሉ ‹‹በቺካጎ ጎዳናዎች ላይ ድሉን በዓይናችን በመመልከታችን እድለኞች ነን›› በማለት ገልጾታል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You