ርዕደ መሬት እንዴት ይከሰታል፤ እንዴትስ የሚያስከትለውን አደጋ መከላከል ይቻላል

ልጅ እያለሁ ስለመሬት መንቀጥቀጥ ሲወራ መስማቴን አስታውሳለሁ። ነፍስ ካወቅሁ በኋላ ደግሞ ከጋዜጣ አንብቢያለሁ፣ ከሬዲዮ ሰምቻለሁ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን እየተመለከትሁ ነው። የመሬት መንቀጥቀጥ ነገር በተወሳ ቁጥር ቀድማ ወደ አእምሮዬ የምትመጣው ጃፓን ናት። ከዚያ ሄይቲ ናት። የስምጥ ሸለቆ ቀጣና ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ እንደሆነም ደጋግሜ ሰምቻለሁ።

በሕይወት ዘመን ሲከሰት አያለሁ ብዬ ግን በጭራሽ አስቤ አላውቅም። ላካ ይሄን ማሰቤ ስህተት ነበር። ባለፈው እሁድ በሕይወት ዘመኔ ለተወሰኑ ሰከንዶች በስሱ ተከስቶ አየሁት። የኮንዶሚኒየሙ ግንባታ እንደነገሩነት አካል ጉዳተኛ ከመሆኔ ጋር አሰብሁትና ፈራሁ። ራሴን ታዘብሁት። የመሬት መንቀጥቀጥ ለካ እንዲህ በአንድ ጊዜ ቅርብ ይሆናል። ይቺ የማንቂያ ድወል ናት። የሚነቃ ይንቃ። ግንባታዎቻችንንና የመሠረተ ልማቶቸን ይሄን ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል።

መስከረም 26 እሑድ ምሽት አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ በሬክተር ስኬል 4.9 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተ መሆኑን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም መገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ ይህን አረጋግጧል። እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት ኦፊሴላዊ የመሬት መንቀጥቀጥ ድረ-ገፅ አሁናዊ መረጃ በሚያደርስበት ገፁ መተሀራ አካባቢ መካከለኛ የሚባል የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አስታውቋል። ንዝረቱ መዲናችንንም አዲስ አበባ ተሰምቷታል።

ምሽት 2፡10 ገደማ በርካታ የአዲስ አበባ እና የናዝሬት ከተማ ነዋሪዎች የመሬት ንዝረቱ እንደተሰማቸው በማኅበራዊ ሚዲያዎች አጋርተዋል። እኔ በምኖርበት ኮንዶሚኒየም ለጥንቃቄ በተደረገ ልፈፋ ከየቤታችን ወጥተን ሜዳ ላይ ሆነን የሚሆነውን ለመጠባበቅ ተገደን ነበር። ሁሉ በዛች ቅጽበት የሆነውን አፍ ለአፍ ገጥሞ እያወራ ነበር። የተቀረው እጅ ስልኩ ላይ ተደፍቶ ስለመሬት መንቀጥቀጡ መረጃ እየጎለጎለ ነበር።

የአሜሪካው ድረ-ገፅ እንደገለፀው፤ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 2 ሰዓት ገደማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ 10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ነበረው። ድረ-ገፁ አክሎ ከመተሀራ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ የተከሰተው መንቀጥቀጥ ንዝረቱ ከ380 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ተሰምቷል፤ ፍጥነቱም 0.48 ሰከንድ ነው ብሏል። የመሬት ንዝሩ በተለይ በአዲስ አበባ በርካታ መንደሮች የተሰማ ሲሆን ሀያት፣ ሲኤምሲ፣ ቦሌ አራብሳ፣ የካ አባዶ እና ሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች የመሬት ንዝረት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፉ ፎቶዎች በርካታ ነዋሪዎች በድንጋጤ ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው መንገድ ላይ ሰብሰብ ብለው አስመልክተዋል። ክራይሲስ 24 የተባለው ድረ-ገፅ ደግሞ የመሬት መንቀጥቀጡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች መሰማቱን ፅፏል። ይህን ተፈጥራዊን ክስተት የሚከታተሉ ድረ-ገፆች ከአዋሽ 23 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.9 ነው፤ ይህም መካከለኛ የሚባል ነው ሲሉ ዘግበዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጂኦፊዚክስ እና ስፔስ ሳይንስ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ “የመሬት መንቀጥቀጡ ለነዋሪዎች አስጊ አይደለም”ሲሉ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መግለጻቸው ይታወሳል። ባለሙያው አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ አበባ የተሰማው ንዝረቱ መሆኑን፤ ከሰሞኑ በአፋር ክልል የመሬት መንቀጥቀጦች እንደነበሩም አረጋግጠው፤ እሑድ ምሽት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ እስካሁን ምንም አልተሰማም። ለመሆኑ ርዕደ መሬት ማለት ምን ማለት ነው? የሚከሰተውስ እንዴት ነው? የሚለውን እንመልከት።

የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ርዕደ መሬት በመሬት ውስጥ በታመቀ ኃይል ልቀት የተነሳ ሳይዝሚክ ሞገዶች ወይም seismic waves በሚባሉ ሞገዶች አማካኝነት የሚመጣ የተፈጥሮ አደጋ ነው። አደጋው በ ሬክታር የመለኪያ መሳሪያ የሚለካ ሲሆን ሲስሞግራፍ ወይም ሲስሞሜትርም ለመለኪያነት ያገለግላሉ። ከዚህ የተያያዙ ሳይንሳዊ እውነታዎችን እንመልከት።

የአሜሪካ የጅኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ እንደሚያሳየው ርዕደ መሬት የሚፈጠረው የምድር ንጣፎች ወይም «ቴክቶኒክ ፕሌትስ» በሚሰኙት ጠርዝ ላይ ነው። እነዚህ የምድር ቅርፊቶች የተደራረቡ እና ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን እርስ በእርስ የሚጋጩበት ጊዜ አለ። በነገራችን ላይ እንስሳት ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት እንግዳ ባህሪ ያሳያሉ። ለተረዳው እንደ ተፈጥሮአዊ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሊጠቀምበት ይችላል።

የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ እንደሚያሳየው ርዕደ መሬት የሚፈጠረው ከምድር በታች በሚገኙ አለታማ ቁሶች ግጭት ነው። ይህ ግጭት የሚፈጠረው የምድር ንጣፎች ወይም «ቴክቶኒክ ፕሌትስ» በሚሰኙት ጠርዝ ላይ ነው። እነዚህ የምድር ቅርፊቶች የተደራረቡ እና ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን እርስ በእርስ የሚተሻሹበት እና የሚጋጩበት ጊዜ አለ። ይህ ድንገተኛ ግጭት የሚፈጥረው ንዝረት እና ሞገድም ምድርን በመሰንጠቅ ርዕደ መሬት እንዲፈጠር ያደርጋል።

በዚህ ሁኔታ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ/ም በቱርክ እና በሶርያ የተከሰተው አስከፊ ርዕደ መሬት በርካቶች ጉዳት ሲደርስባቸው ከ36 ሺህ በላይ ሰዎችንም ሕይወት ነጥቋል። በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 የተለካው ይህ ክስተት ከተሞቹንም ወደ ፍርስራሽነት ቀይሯል። ይህንን መሰሉን ተፈጥሯዊ ክስተት መከላከል የሚያስችል ሳይንሳዊ መላ ይኖር ይሆን በሚል በዶቼቬለ የተጠየቁት የባህርዳር ዩንቨርሲቲ መምህር እና የስነ-ምድር ተመራማሪ የሆኑትን ዶክተር ምንያህል ተፈሪ፤ «ርዕደ መሬትን መከላከል አይቻልም። መከላከል ሳይሆን የሚቻለው የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ሕብረተሰቡን ከአካባቢው ማንሳት እና ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ነው »ብለዋል።

“ነገር ግን መቼ እንደሚከሰት ትክክለኛ ጊዜ መናገር ባይቻልም ርዕደ መሬት ከመድረሱ በፊት የመሬትን የላይኛውን የአካል ክፍል እንቅስቃሴ በመመልከት ቅድመ ትንበያ ማድረግ እንደሚቻል ተመራማሪው ያስረዳሉ። «መተንበይ ይቻላል። ለምሳሌ የጃፓኑ የ2011 ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት ተተንብዮ ነበረ። በ30 ዓመት ውስጥ ይከሰታል ብለው ሳይንቲስቶች የፊዚክስ ባለሙያዎች ተንብየው ነበር። ያንን ትንበያ ባደረጉ በዓመቱ ነው የተከሰተው። ምክንያቱም የሚተነበየው የመሬትን የላይኛውን አካል እንቅስቃሴ እንደሆነ አመልክተዋል።

ርዕደ መሬት ከተፈጥሯዊ በተጨማሪ በሰው ሰራሽ መንገድ በግንባታ፣ በማዕድን ቁፋሮ እና በአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ ሊከሰት ይችላል። በዓለም ላይ አነስተኛ ርዕደ መሬት በየትኛውም ቦታ የሚከሰት ሲሆን፤ ፍሎሪዳ እና ሰሜን ዳኮታ አነስተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ያለባቸው የአሜሪካ ግዛቶች ናቸው። አንታርክቲካ ከየትኛውም አህጉር ትንሹ ርዕደ መሬት የሚከሰትበት አህጉር ነው። አብዛኛው አውዳሚ ርዕደ መሬት የሚከሰተውበፓስፊክ አካባቢ ነው።

ይህ የሆነበት ምክንያትም የመሬት ንጣፍ /ፕሌቶች/ በአብዛኛው የሚንቀሳቀሱት በዚሁ አካባቢ በመሆኑ ነው። በቅርቡ ርዕደ መሬት የተከሰተባቸው ቱርክ እና ሶርያም በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ናቸው። ባለሙያዎቹ እንደሚሉትም እነዚህ ክስተቶች የአረቢያን የመሬት ንጣፍ /ፕሌት/ ወደ ሰሜን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከምስራቅ አናቶሊያ የመሬት ንጣፍ /ፕሌት/ ጋር በመጋጨቱ የተፈጠረ ነው። በኢትዮጵያም የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ለዚህ ክስተት የተጋለጠ መሆኑን ተመራማሪው ይገልፃሉ።

«ክረስት» የሚባለው የመሬት የላይኛው ክፍል «ማንትል»በሚባለው የታችኛው የመሬት ክፍል ላይ እንደሚንቀሳቀስ የሚገልፁት ባለሙያው ጠቁመው በእንቅስቃሴው በሚፈጠር ግጭት እና ንዝረትም በተለዬ ሁኔታ በርዕደ መሬት የሚጠቁ ሌሎች ሀገራት መኖራቸውንም ያስረዳሉ። ከፍ ብሎ ለመጠቆም እንደተሞከረው፤ ይህንን የመሬት ውስጣዊ እንቅስቃሴም ከሰዎች ይልቅ እንስሳት ቀድመው እንደሚረዱት፤ እንደ ውሻ ፣ አሳ፣ አዕዋፍ፣ ተሳቢ እንስሳት እና ነፍሳትን የመሳሰሉ እንስሳት አውዳሚ ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት እንግዳ ባህሪ እንደሚያሳዩ፤ ይህንንም እንደ ጃፓን እና አሜሪካ ያሉ ሀገራት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንደሚጠቀሙበት ተመራማሪው አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ዋናው ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት እና በኋላ ቅድመ እና ድህረ ርዕደ መሬቶች ይከሰታሉ። የመጀመሪያው ቅድመ ርዕደ መሬት ከዋናው ጋር በተመሳሳይ ቦታ የሚከሰት ቢሆንም አነስተኛ ስለሆነ ፤ ይህንን ክስተት ርዕደ መሬት መሆኑን ሊቃውንት እንኳ መናገር አይችሉም። ሌላው ድህረ ርዕደ መሬት ወይም / After shocks/ ሲሆን፤ ዋናው ርዕደ መሬት /Mainshocks/ በኋላ የሚከሰት እና በሬክተር ስኬል ሲለካ ከዋናው ያነሰ ነው። ነገር ግን ባለሙያው እንደሚሉት የበለጠ ጉዳት የሚያደርስ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ድህረ ርዕደ መሬት ለሳምንታት፣ ለወራት ወይም ለዓመታት ሊቀጥል ይችላል። በቱርክ-ሶሪያ አዋሳኝ አካባቢ ከተከሰተው ርዕደ መሬት በኋላም ከ 100 ጊዜ በላይ ተከስቷል። በተለምዶ የድህረ ርዕደ መሬት መጠን ከመጀመሪያው ክስተት በአንድ ዲግሪ ያነሰ ሲሆን፤ ይህ ግን መጀመሪያው 7.8 ከተመዘገበ በኋላ የተከሰተው 7.5 ማግኒቲዩድ ያለው በመሆኑ ከተለመደው ጠንከር ያለ ነበር።

የብሪታኒያ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተመራማሪ ሮጀር ሙሶን እንደገለፁት አንዳንድ ጊዜ ከዋናው የሚበልጥ የድህረ ርዕደ መሬትም ሊያጋጥም ይችላል። ስለዚህ እንደ ባለሙያ፣ ምድር በምትሰጠን አዳዲስ ነገር ለመደነቅ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን አለብን። በማለት ሳይንስ ያልደረሰባቸው እውነታዎች መኖራቸውን ገልፀው፤ ክስተቱ በምስራቅ አናቶሊያን የመሬት ንጣፍ/ፕሌት /እንደተከሰተ በተሻለ ሊገለጽ ይችላል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ዋናው ርዕደ መሬት አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ በመባል በሶስት ሊከፈል ይችላል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከፍተኛ የሚባለው ርዕደ መሬት በጎርጎሪያኑ 1960 ዓ.ም በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ችሊ የተከሰተው ሲሆን 9 ነጥብ 5 ሬክተር ስኬል ነበር። ሌላው በሬክተር ስኬል 9 የተመዘገበው በ2011 ዓ.ም በጃፓን የተከሰተው ርዕደ መሬት ሲሆን፤ ይህም መነሻው የባህር ዳርቻ በመሆኑ ተከታታይ ሱናሚዎችን በማስከተል በአካባቢው በሚገኝ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

በቅርቡ በቱርክ እና ሶርያ የተከሰተው ደግሞ 7 ነጥብ 8 ቢሆንም የከፋ ጉዳት የታየበት ነው። ለዚህም የሕንፃዎቹ ጥንካሬ እና ችግሩ የተከሰተው ንጋት ላይ ሰዎች በመኝታ ላይ እንዳሉ መሆኑ ለጉዳቱ በምክንያትነት እየተጠቀሰ ነው። ከዚህ አንፃር ዶክተር ምንያህል ጉዳቱ ከመከሰቱ በፊትም ሆነ፤ በኋላ መደረግ አለበት የሚሏቸው የጥንቃቄ ርምጃዎች አሉ።

«እንደዚህ አይነት አካባቢዎቸ ላይ የከተሞች መስፋፋት እንዳይኖር ጂኦሎጅስቶች ትልቅ አስተዋጾኦ አላቸው። ከተማ ምስረታ ወይም «ሴትልመንት» ሊሆን ይችላል። ስለዚህ «ሳይቲኒክ አክቲቭ» የሆነበት ቦታ ላይ አማራጭ ካልጠፋ ለምሳሌ እንደ ጃፓን ሌላ የሚሄዱበት አኀጉር ቢኖር ደስ ይላቸዋል። ስለሌለ ግን እየኖሩ ነው። እየኖሩ ግን ርዕደ መሬትን በቴክኖሎጂ እየተቋቋሙት ነው።

እንደኛ አይነት ሀገር ብዙ ቦታ ባለበት አዳዲስ ከተማዎች መስፋፋት «ሴተልመንት» የሕንጻ ኮንስትራክሽን ያሉበት ቦታ ከሆነ ጂኦሎጅስቶች ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል። ቢያንስ ከተሰራም ጠንካራ ሕንጻ ቢሆንና በዙ «ሴትልመንት» ባይኖር ይመከራል። ስለዚህ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ዞሮ ዞሮ በቦታው እየኖሩ ከሆነ፤ መረጃ ማግኘት እና ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት ቦታውን መልቀቅ አስፈላጊ መሆኑን”ይመክራሉ።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You