ለአንድ ሀገር ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የሠላም ጉዳይ መሆኑ ለማንም አጠያያቂ አይደለም። ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ለማሳካት ያለ ሠላም የሚታሰብ አይሆንም። እንደ ሀገርም ሀገር ሆኖ ለመቀጠል ሠላም የግድ ይላል። ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት ነውና። ይሁን እንጂ የሠላም አስፈላጊነትን በቅጡ ያልተገነዘበ “ሠላም”ን እንደ ቃላቱ ፊደላት ቁጥር አሳንሶ ያያል።
የሰው ልጅ ወልዶ ለመሳም፣ አስተምሮ ለማስመረቅ፣ ድሮ ለመኳል፤ ሀብት ንብረት ለማፍራት፣ ወጥቶ ለመግባት፣ ነግዶ ለማትረፍ ሠላም ያስፈልገዋል። ሠላም ከሌለ እንኳንስ ፍላጎትን ማሳካት ቀርቶ ሊጎርሰው በእጁ የጠቀለለውን ምግብ ወደ አፉ ማድረግ ይሳነዋል። ለዚህም ነው በሀገር ላይ የተሟላ ሠላም መኖር የግድ የሚሆነው።
በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገራችን የተሟላ ሠላም አለ ብለ ደፍሮ ለመናገር አይቻልም። በተለያየ አካባቢ የሚታይ የሠላም መደፍረስ ሀገሪቷንም ሆነ ዜጎቿን መስዋዕትነት እያስከፈለ ይገኛል። የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደል፣ የንብረት መውደም የመሳሰሉት ችግሮች በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ሲሰሙና ሲታዩ ቆይተዋል።
በዚህም ምክንያት ዜጎች ሕይወታቸውን እያጡ ነው፣ ሀብት ንብረታቸው እየወደመ እና ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ይገኛሉ። አርሶ አደሩ የዕለት ተግባሩን ማከናወን ተስኖታል፤ ደብተር ይዞ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄደው ተማሪ ቁጥር ቀደም ሲል በሚታወቀው ልክ አይደለም። በተለይ በአማራ ክልል የሚታየው የሠላም መደፍረስ የዜጎችን ተስፋ እያጨለመ እንጂ እያለመለመ አይደለም።
የአማራ ክልላዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ ለ2017 በጀት ዓመት በክልሉ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተማሪ ለመመዝገብ አቅዶ ነበር። ነገር ግን ለመማር ምዝገባውን ያደረጉት አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብቻ ናቸው። ይሄ የሚያሳየው ተማሪዎች እያሉ ፤ የትምህርት ፍላጎትም እያላቸው በክልሉ ባለው የሠላም እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው መራቃቸውን ነው።
በየትኛው ዓለም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነት ይኖራል። በልዩነቱ ዙሪያ አለመግባባት ይፈጠራል። ይሄን አለመግባባት በሠላማዊ ትግል ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ወደ ጦርነት ማምረት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ከአዋጪነቱ ይልቅ አክሳሪነቱ ያይላል። ጦርነት ምን ያህል በሀገር ላይ የከፋ ጉዳት እንደሚያስከትል ከትናንቱ የሀገራችን የሰሜኑ ጦርነት አይተነዋል።
ምን ያህል ዜጎቻችን በሞት እንደተለዩን ምን ያህሉ አካል ጉዳተኛ እንደሆኑ የሠላም ማጣት ምን ያክል ከባድ መሆኑን በተጨባጭ አጣጥመነዋል። የክልሉ ኢኮኖሚ ወደ ዕድገት ሳይሆን ወደ ቁልቁለት መውረዱን፣ መሠረተ ልማቱ ውድመት ምን ያህል ኢኮኖሚውን እንዳጎበጠው አስተውለነዋል። ከዚህ መማር ይገባል።
አሁንም በየትኛው አካባቢ የሚታየውና የሚሰማው ደም አፋሳሽ ግጭት ሊቆሙ ይገባል። ችግሮች በድርድር እና በውይይት መፈታት አለባቸው። የሠለጠነ ዲሞክራሲ መኖር የሚገለጠው ስለዲሞክራሲ በማውራት ብቻ ሳይሆን የተገኘውን ዲሞክራሲ በአግባቡ በመጠቀም ነው።
በመሆኑም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞች እየተገበሩት ያለው የትጥቅ ትግል ሀገር ከማፍረስ የዘለለ ጥቅም እንደሌለው ተገንዝበው ለሠላም እጁን ከዘረጋው መንግሥት ጋር በሠላማዊ መንገድ መነጋገር ይገባቸዋል። ስለ ሀገርና ሕዝብ ሲባል ችግሮችን በውይይት መፍታት ያስፈልጋል። ዛሬ በየትኛውም አቅጣጫ እየረገፈ ያለው የራሳችን ዜጋ ነው።
በየትኛም አቅጣጫ እየወደመ ያለው የራሳችን ሀብት ነው። ለጦርነቱ የሚውለው መሣሪያ ግዢ የሚፈጸመው በሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ሀብት ነው። በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ችግሩ የአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ከሚሰሙና ከሚታዩ የሠላም መደፍረሶች ወጥቶ ወደ ሠላም መንገድ መግባት ይገባል።
የጦርነትን አዋጭነት ሳይሆን አውዳሚነትን ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከነበረው ጦርነት አይተነዋል። ከጦርነቱ ሀገርን ማውደም፣ ዜጎችን ማሰቃየት ካልሆነ በስተቀር አንድም ያተረፍነው ነገር የለም። ስለዚህ አሁንም ሀገር ከወደመ በኋላ ሳይሆን ዛሬውኑ ወደ ሠላም መንገድ መምጣት ያስፈልጋል።
የሠላም አማራጭን አማራጭ ማድረግ አንድም የሥልጣኔ መገለጫ ነው፤ ሌላው የተነሱበትን ዓላማ ማሳካት ጭምር በመሆኑ ጽንፈኞች የሠላምን መንገድ ዋና አማራጭ ሊያደርጉ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ከኃይል አማራጭ ይልቅ ለሠላማዊ መንገዶች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም