በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት 700 ሺህ ሰዎች ራሳቸውን እንዲሚያጠፉ ድብርት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ሀዘን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ቀዳሚ ምክንያቶች እንደሆኑ ይነገራል። በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 በመቶ የሚሆኑ በአዋቂ እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ደስተኛ እንዳልሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ። በርካታ ውጥረት እና ውጥንቅጥ በሞላባት ዓለም ውስጥ ሰዎች መሰረታዊ የኑሮ ጥያቄን ለመሙላት ከሚያደርጉት ግብግብ ባለፈ ደስተኛነትን ፍለጋ በርካታ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ።
ደስተኛ የመሆን ሚስጥር በተለያዩ ምሁራን እና ፈላስፎች የተለያየ ትርጓሜ ቢሰጠውም ሰዎች እንደሚገኙበት ኢኮኖሚያዊ፣ የጤና እና ማህበራዊ ሁኔታ ደስተኝነትን የሚለኩበት መንገድ ይለያያል። በድብርት፣ ተስፋ በመቁረጥ፣ የሕይወት ትርጉም በማጣት፣ በጭንቀት፣ ሀዘን እና በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሰበብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት 700 ሺህ ሰዎች እራሳቸውን እንደሚያጠፉም ነው የሚገለፀው። በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 በመቶ በአዋቂ እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች በሕይወታቸው ደስተኛ አለመሆናቸውን እንደተናገሩ ይጠቁማሉ።
በእርግጥም ደስታ ለጥቂቶች ብቻ የሚገለጥ ሚስጥር አይደለም። ደስተኛ መሆን እንፈልጋለን ግን አልቻልንም የሚሉ ሰዎች ገጥመውህ ያውቃል? ነገር ግን ለመደሰት ከየት ልጀምር? የሚለውን ጥያቄ በሚከተለው መልክ በጥቂቱ መቃኘቱ ግድ ይልሃል።
- ደስተኛ ለመሆን ቀጠሮ አትያዝ፡- ሕይወቴ ሲቀየር፣ ስኬታማ ስሆን፣ ያሰብኩትን ሳሳካ እደሰታለው እያልክ የምታስብ ከሆነ ደስታህ መቼ እንደሚመጣ አታውቀውም። መቼ እንደምትመጣ የማታቃትን ወዳጅህን እንደመጠበቅ ሰቀቀን ይሆንብሃል። ብዙዎቻችን ጤናማ፣ ደስተኛ እና ውጤታማ መሆንን እንመኛለን። ለዚህም የተዋበ መልክ እና ቁመና፣ የተትረፈረፈ ገንዘብ፣ ቆንጆ መኪና አልያም ቪላ ቤት እንዲኖረን እንሻለን። ይሁን እንጂ እነዚህም ሆኑ ሌሎች የተመኘናቸው ነገሮች ሁሉ ቢሟሉም የፈለግነውን ደስታ እና ጤና ላናገኝና ስኬታማ የሆንን መስሎ ላይሰማን ይችላል።
- ደስተኛ ሰው ከዛሬ ጋር በቅጡ የተግባባ ሰው ነው።
- ደስተኛ ለመሆን፤ የግድ ሃብታም፤ ስኬታማ እና ታዋቂ መሆን አይጠበቅብንም።
- እውነተኛና ደስተኛ ሰው በሌለው ነገር እየተጨነቀ ዛሬውን የሚያባክን ሳይሆን፤ ባለው ነገር እየተደሰተ የሌለውን በተስፋ የሚጠብቅ እጅግ ብልህ ነው።
- ለማመን ቢከብደም ሰው በምንም አይነት የኑሮ ሁኔታ ላይ ቢሆንም ደስተኛ መሆንን ምርጫው ካደረገ፤ በእርግጠኝነት ደስተኛ መሆን ይችላል።
- ኑሮዋችን እንደ እይታችን ይወሰናል፤ የጎደለንን እያየን ማማረር፤ ወይም ያለንን እያየን ማመስገን። ሁለቱም ምርጫዎች በኑሮ ገበታችን በየቀኑ የሚቀርቡ ናቸው፤ አስተሳሰባችን ምርጫችንን ይወስነዋል።
- እርግጥ ነው ደስተኛነት፤ በየቀኑ መፍለቅለቅ አይደለም፤ ምክንያቱም ሕይወት በውጣ ውረዶች የተሞላች ስለሆነች።
- ደስተኛ ለመሆን ሁሌም ምርጫችን ከሆነ ግን፦ ቢያንስ ወጣውረዱን ለመጋፋጥ አንሸበርም፣ ቀናችን በሃዘን እና በማማረር አይባክንም፣ ከሌሎችን ሰዎች ጋር ስንሆን ደስ የሚል መንፈስን እናንጸባርቃለን።
- ደስታ ተላላፊ ነው፣ ሳቅ ልክ እንደ ሰደድ እሳት ይቀጣጠላል፣ ደስተኛ ስትሆን በመንገድህ የምታገኛቸው ሰዎች ላይ ሁሉ ትልቅ ተጽዕኖ እደምታመጣ እመን።
- ደስታ የምኞት ውጤት፣ የማሳደድ ትርፍም አይደለም። ደስታን ተመኝቶ ያገኘ፣ አሳድዶ የያዘ የለም።
- ደስተኛ ለመሆን አትኩሮትህን በሌለህ ነገር ላይ ሳይሆን ባለህ ነገር ላይ አድርገው። ደስተኛ ለመሆን ሁሉም ነገር ሊኖርህ አይገባም። በደንብ ካስተዋልከው አሁን ያለህ ነገር ደስተኛ ለመሆን በቂ ነው። ምክንያቱም አንተ ያለህን የሚመኙ ምስኪኖች ብዙ ናቸውና።
መቼም ደስተኛ መሆን የማይመኝ ሰው ይኖራል? በፍፁም! ታዲያ ለምን አብዛኛዎቻችን ደስተኛ መሆን ያቅተናል? ለምንስ ደስተኛ አለመሆናችንን ከማመን ይልቅ ከራሳችን ለመሸሽ እንሞክራለን? በድብልቅልቁ ውስጥ እየተሹለከለክን፤ ሕሊናችን እንዳይጠይቀን አይምሮዋችንን በምኑም በምኑም ጠምደን እስከመቼ እንዘልቃለን? ደስተኛ መሆን ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር ይሉት አይነት ነገር ለምን ሆነብን? መፅሃፍቱ፤ ሃይማኖቱ፤ ሳይንሱ፤ ፍልስፍናው ሁሉ ደስተኛ የመሆንን ቀመር እጅግ አቅልለው እያሳዩን ስለምን በተግባር ስንሞክረው ከበደን?
ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጠስ የደስተኛነን ሚስጥር እንዲህ ይገልፀዋል “ደስተኛ ለመሆን ቁልፉ አትኩሮታችንን ከስጋችን ላይ አንስተን ወደ ነፍሳችን ማድረጉ ነው” ይላል። ደስታን ከአይምሮ ውጪ የሚፈልጋት ሰው በፍፁም ሊያገኛት አይችልም። ለዚህ ደግሞ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ሃብት ሳየኖራቸው፤ ጤንነት እየጎደላቸው ደስተኛ የሆኑ ሰዎች አይታቹህ አታውቁም?
ውጫዊ ገጽታቸው ሳያምር፤ አለማዊ ፍላጎታቸው ሳይሟላ ደስተኛ የሆኑ ሰዎች አይታቹህ አታውቁም? ቤታቸው ባዶ ሆኖ፤ ዘመድ ጓደኛ እንደልብ ሳይኖራቸው ደስተኛ የሆኑ ሰዎች አይታቹህ አታውቁም?
ይህን ስናይ ደስታ በፍፁም ከቁሳዊ እና አካላዊ ነገሮች ጋር ግንኙነት እንደሌላት እናያለን።
የሰው ልጅ ሁሉ ነገር ቢኖረው አይምሮው ግን ደስታን ከተራበ ምን ዋጋ አለው?
ለምን ተፈጥሮ ያደለችንን የደስተኛነት ፀጋ በገዛ ፈቃዳችን ሳንጠቀምበት ሕይወታችን ያልፋል?
ለማመን ትንሽ ቢከብድም እንኳን እውነቱ ግን ይህ ነው……..በማንኛውም አይነት የሕይወት አጋጣሚ ውስጥ ብንሆንም እንኳን ደስተኛ መሆን እንችላለን።
እስቲ አስቡት የጎደለን ነገር ቢኖር እንኳን ያለን
እንደሚበዛ ካሰብን፤ ለሌሎች ሰዎች መልካም ነገር ማድረግን ከለመድን፤
ተስፋ ከልባችን ካልጠፋ፤ ትላንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ መለየት ከቻልን፤
በጠዋት ከምትፈካው ጀንበር ጋር አብረን ከሳቅን፤ ማታ ከምትወጣው ጨረቃ ጋር አብረን ከደመቅን፤ ከተፈጥሮ ምት ጋር አብረን ከዘፈንን፤ ከሁሉም በላይ ደስታን ከሰው ምንጭ ሳይሆን ከራሳችን የሕይወት ምንጭ ለመቅዳት ከሞከርን …….እንዴት ደስተኛ አንሆንም?
ደስታ እርስዎ ዘንድ እስኪመጣ መጠበቁን ይተውትና ደስታን እርስዎ እራስዎ መፈለግ ይጀምሩ። ደስታ በምትሃት ወይም በአንዳች ነገር የሚመጣ አይደለም። እንዲያውም ድንገት እርስዎ ላይ የሚከሰት ክስተትም አይደለም። እርስዎ እራስዎ የሚያዳብሩት/የሚያሳድጉት ባህሪ ነው እንጂ። እንዴት ደስተኛ መሆን እንደሚችሉ /ምን ደስተኛ እንደሚያደርግዎ መፈለግ ይጀምሩ። ስለዚህ በተቻለ መጠን ደስተኛ ለመሆን እራስን በማለማመድ ደስታን ማግኘት ይቻላል ማለት ነው።
10 በመቶ ብቻ በሚሆኑ በሰዎች መካከል ያለው የደስተኝነት አገላለፅ ልዩነት በሁነቶች መለያየት ሊገለፅ ይችላል። በተረፈ በአብዛኛው ሰዎች ላይ ደስተኝነትን የሚወስኑት የሰዎች ስብዕና ሲሆኑ በተለይ ሊለወጡ የሚችሉ አስተሳሰብና ባህሪይ ናቸው። ምንም እንኳን እርስዎም ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት ደስተኛ መሆን የሚቻለው ሀብታም ሆነው ሲወለዱ፣ ቆንጆ ሲኮን አሊያም ጭንቀት የሌለበት ኑሮ/ሕይወት ሲኖሩ ነው የሚል አስተሳሰብ ከሆነ ያልዎት እውነቱ እንደሱ አይደለም። ይልቁንስ ሀብት ያላቸው ሰዎች፣ ቁንጅና ያላቸው ወይም ጭንቀት የሌለው ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች በአቬሬጅ ሲታይ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ካልታደሉ ሰዎች ጋር ሲዋዳደሩ ምንም የተለየ/የበለጠ ደስታ የሌላቸው መሆኑ ነው።
ስለሆነም ደስተኛ ለመሆን ሁሌም መለማመድ፣ መለማመድ አሁንም መለማመድ ያስፈልጋል። ደስተኛ ለመሆን እየፈለጉ ከሆነ የደስታዎ መጠን የሚወሰነው በምርጫዎ፣ ሀሳብዎና በተግባርዎ ላይ ነው። ግባችን ላይ ስንደርስ ወይም የተመኘነውን ነገር ስናገኝ ደስተኛ እንደምንሆን የተረጋገጠ ቢሆንም እንዲህ ዓይነቱ ደስታ ቀስ በቀስ እየከሰመ ሊሄድ ይችላል።
ዘላቂ ደስታ የሚኖረን ስኬት ወይም አንድ ዓይነት ንብረት ስላገኘን አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው ጤናማ መሆኑ በተለያዩ ነገሮች ላይ የተመካ እንደሆነ ሁሉ እውነተኛ ደስታም የተለያዩ ነገሮች ድምር ውጤት ነው።
ሁላችንም የተለያየን ሰዎች ነን። አንተን የሚያስደስትህ ነገር ሌላውን ሰው ላያስደስተው ይችላል። በተጨማሪም ዕድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ ፍላጎታችንም ይለወጣል። ምንም እንኳ ቀላል ባይሆንም የደስተኝነትዎን መጠን በተወሰነ መልኩ ከፍ ማድረግ ይችላሉ። ይህ ለማድረግ የሚከተሉት መንገዶች ሊከተሉ ይችላሉ።
ደስተኛ የመሆን ሚስጥር እንደ ሰው እና አካባቢው ቢለያይም የስነልቦና ሀኪሞች ማንኛውም ሰው በቀላሉ ተግብሯቸው ደስተኛ ሊሆንባቸው የሚችሉ በሚል የዘረዘሯቸውን አምስት ልማዶች ግን አሉ።
- ለሰዎች ደግ መሆን ወይም በጎ ማድረግ
ሰዎች ካላቸው ነገር ላይ ቀንሰው ለሰዎች በጎ ነገርን ማድረግ ደስታ ከሚፈጥሩ የመኖር ትርጉም ጥያቄን ከሚመልሱ ልማዶች መካከል አንዱ ነው ተብሏል። ከመልካምነት በመነጨ ስሜት ለሌሎች ሰዎች የሚደረግ መልካምነት ሰዎች ስለሚገኙበት ሁኔታ አመስጋኝ እንዲሆኑ፣ በራሳቸው እንዲተማመኑ እና ስለራሳቸው መልካም ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል።
በዚህ ምግባር ምክንያት በማህበረሰብ ውስጥ እና በሚገኙበት አካባቢ ሰዎች የሚሰጧቸው አክብሮት እና ተቀባይነት ስለሚጨምር በሰዎች ዘንድ መወደዳቸው ደስታን ይፈጥራል ተብሏል። ትንሽ የሚባል የደግነት ምግባር የለም የሚሉት የስነልቦና ተመራማሪዎቹ ሰዎች አካባቢያቸውን በደንብ ቢቃኙ መልካም ለመሆን ገንዘብ ማውጣት የማይጠይቁ ምግባሮችን ያገኛሉ ብለዋል።
2ኛ. አመስጋኝነት
ምስጋና በሀይማኖታዊው ትእዛዛትም በጎ ምግባር ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ስለተሰጣቸው ነገር የሚያመሰግኑ ሰዎች ስለጎደላቸው ስለማይጨነቁ እንዲሁም በቁሳቁሳዊ ጉዳዮች ራሳቸውን ለማነጻጸር ጊዜ ስለማይኖራቸው ደስተኞች መሆን እንደሚችሉ ተገልጿል። ሰዎች ወደ መኝታቸው ከማቅናታቸው በፊት አልያም ከቅርብ ሰዎቻቸው ጋር ሲወያዩ አመስጋኝ ስለሆኑባቸው፣ በሕይወታቸው ስለተሰጧቸው ነገሮች ማመስገንን ልማድ ማድረግ አለባቸው ተብሏል።
ለምሳሌ በነጻነት መንቀሳቀሳቸው፣ በሕመም አልጋ ላይ ባለመዋላቸው፣ ሙሉ አካል እና ሙሉ ጤና ስላለቸው እንዲሁም ለሌሎች ውድ የሆኑ እነርሱ ጋር ግን ያሉ ነገሮችን በመቁጠር አመስጋኝ እንዲሆኑ ይመከራል።
3ኛ. መልካም ግንኙነትን ከሰዎች ጋር መመስረት
ማህበራዊ እንስሳ እንደሆነ የሚነገርለት የሰው ልጅ በምድር ላይ ብቸኛ ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም። ከቤተሰብ፣ ከልጆች፣ ከጎረቤት፣ ከጓደኛ በአካባቢ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ግንኙነትን የተቃና ማድረግ የደስተኛነት ሚስጥር ከሆኑ ልማዶች መካከል አንዱ ተደርጎ ተጠቅሷል።
ሰዎች ከሌሎች ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር አካባቢያቸው ከጭንቀት እና ድብርት እንዲሁም ያለመፈለግ ስሜትን ስለሚያጠፋ ለመኖር ተጨማሪ ምክንያትን የሚያክል ነው ሲሉ የስነ ልቦና ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል። በችግር እና ደስታ ጊዜ በአቅራቢያ የሚገኝ ሰው መኖር እንዲሁም በወዳጆች መከበብ ሰዎች ደህንነት እና በራስ መተማመን እንዲሰማቸው ያደርጋል።
4ኛ. መልካም ዜናዎችን በተገቢው መጠን ማጣጣም
በርካታ የጭንቀት እና የሀዘን ዜናዎች በሞሏት ዓለም ውስጥ መልካም ዜናዎች ከብዙ ጊዜ አንድ ጊዜ የሚገኙ በመሆናቸው በልካቸው መከበር ይገባቸዋል። በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ መልካም አጋጣሚዎችን እና የስኬት ወሬዎችን ከቅርብ ሰዎች ጋር በመሰባሰብ ማክበር ሕይወት አንድ አይነት እና አሰልቺ እንዳትሆን ከማገዙም በላይ በተስፋ የተሞላ ነገ እንዲኖር ያደርጋል። በዚህም በስራ እና በሕይወት ስላጋጠሙን ስኬቶች ደስታን በተገቢው መንገድ መግለጽ ይመከራል።
5ኛ. ከሰዎች አለመጠበቅ
ለሰዎች ስኬት እና ውድቀት ቀዳሚ ኃላፊነቱን የሚወስዱት ራሳቸው ናቸው። መልካም ወዳጅነትን መመስረት ለደስተኛነት ወሳኝ ቢሆንም ደስተኛነት በሰዎች ላይ መንጠልጠል አይኖርበትም። ለሰዎች በሰጠናቸው መጠን ምላሽ የምንጠብቅ ከሆነ የታሰበው ሳይሆን ሲቀር ደስተኛ አለመሆንን እና ስለራስ መጥፎ ስሜት እንዲሰማ በማድረግ ከሰዎች መራቅን እና ብቸኝነትን ያስከትላል። በመሆኑም ደስተኛ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች የደስተኝነት ምክንያታቸው በሰዎች ላይ መመርኮዝ የለበትም ብለዋል የሰነ ልቦና ሀኪሞቹ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም