ዘርፈ ብዙ ምላሽ ለአዕምሮ ጤና

ከዓለም ሕዝብ አንድ አምስተኛ ያህሉ እርዳታ የሚሻ የአእምሮ ጤና ችግር ያለበት መሆኑን ከዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ ውስጥ ከ76 አስከ 86 ከመቶ ያህሉ ደግሞ ሕክምና ያላገኙ የአእምሮ ጤና ችግሮች ያለባቸው መሆኑን አመላክቷል።

ይኸው መረጃ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአእምሮ ጤና ችግር የሚጀምረው በአስራ አራት ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ መሆኑንና እድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ዓመት ውስጥ ባሉ አምራች ወጣቶች ለሚከሰተው ሞት ራስን ማጥፋት ሁለተኛው ገዳይ ምክንያት መሆኑንም ያሳያሉ።

ከ 90 በላይ የሚሆኑ ራስ ማጥፋት መንስኤዎች የሚከሰቱት ደግሞ ባልታከመ የአእምሮ ጤና ችግር ምክንያት መሆኑንም እነዚሁ መረጃዎች ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ 78 ከመቶ ያህሉ ራስን ማጥፋት የሚታየው በታዳጊ ሀገሮች መሆኑንም አስታውቀዋል።

በጥቅሉ በድባቴ /depression/ እና ተያያዥ የአእምሮ ጤና ችግሮች ብቻ ዓለማችን በየዓመቱ ከ 2 ነጥብ 5 እስከ 8 ነጥብ 5 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደምታጣም ይኸው መረጃ ይጠቁማል።

በኢትዮጵያም ሁሉንም የአዕምሮ ጤና ሕመሞች ከግምት ውስጥ በማስገባት ከአምስት ሰዎች ውስጥ አንዱ የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለበት ከጤና ሚኒስቴር በተገኙ መረጃዎች አማካኝነት ለማረጋገጥ ተችሏል። ይህም የስነ-ባህሪይ ችግሮችን (personality disor­der)፣ እንቅልፍ ማጣትን፣ ድብርትን፣ ጭንቀት እና ሌሎችም ሕመሞችንም ሊያጠቃልል እንደሚችል መረጃው ይጠቅሳል። ከነዚህ መረጃዎች በመነሳት ለአእምሮ ጤና ትልቅ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ መገመት አያዳግትም።

ለዛም ነው የዓለም አእምሮ ጤና ቀን በየዓመቱ የሚከበረው። የዘንድሮው የዓለም አዕምሮ ቀንም “በስራ ቦታ ለአዕምሮ ጤና ቅድሚያ የሚሰጥበት ጊዜ ነው!” በሚል መሪ ቃል የጤና ሚኒስቴር በሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ፣ የክልል ጤና ቢሮዎችና የሆስፒታሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዚህ ሳምንት ተከብሯል።

የጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ሌሊሴ አማኑኤል በመድረኩ የመክፈቻ ንግግራቸው እንደገጹት፣ ይህንን ቀን የምናከብርበት ዋነኛ ዓላማ ስለ አእምሮ ጤና ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ በአእምሮ ጤና መታወክ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡና እና ዘርፈ ብዙ እየሆኑ በመምጣታቸው፤ ችግሮቹ የሚሹት ምላሽም እንዲሁ ዘርፈ ብዙ በመሆናቸው የአእምሮ ጤና ችግር እያደረሰው ካለው ጫና አንፃር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እየሰጡት ያለው ምላሽ አናሳ በመሆኑ ነው። ስለሆነም በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው፣ የዓለም በሽታዎች ጫና መረጃ እንደሚያሳየው በዓለማችን የአእምሮ ሕመም ስርጭት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ሰዎች ተጠቂ ሲሆኑ በአህጉራችን በአፍሪካ ወደ 116 ሚሊዮን ያክል ሰዎች ከአእምሮ ሕመም ጋር ይኖራሉ። ከዚህም ውስጥ የድባቴ ሕመም ትልቁን ድርሻ ይይዛል። በሀገራችን በኢትዮጵያ ከ5 ሰዎች አንዱ/ዷ በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ በአዕምሮ ሕመም የመያዝ እድል አላቸው። ችግሩን ስፉት ያህል መስራት ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም አሳስበዋል።

የአእምሮ ጤና ላይ ጤና ሚኒስትር በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፣ ከዚህ ውስጥ የ5 ዓመት የአእምሮ ጤና ስትራቴጂ እቅድ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ እንዲውል እየሰራ ይገኛል። ‹‹የዛሬው የአእምሮ ጤና ቀን ስናከብር በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአእምሮ ጤና ላይ የተሰሩ ስራዎችን ልምድና ተሞክሮ ለመውሰድ በማሰብ ነው›› ሲሉ በጤና ሚኒስቴር የሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሕይወት ሰለሞን ገልፀዋል።

የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ካሊድ ሽፉን በበኩላቸው፣ ሆስፒሉ ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር ከአማኑኤል ሆስፒታል ቀጥሎ ፎረንሲክ ሳይካትሪ፣ በስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ አገልግሎት በመስጠት በተመላላሽ እና ተኝቶ ሕክምና የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሁሉም ሰው የትም ቦታ ሁለንተናዊ ጤና እንክብካቤ ማግኘት እንዲችል የጤና ሚኒስቴር የአእምሮ ጤና አገልግሎት ከመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት እስከ ስፔሻሊቲ አገልግሎት ድረስ በሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት ተደራሽ እንዲሆን ትልቅ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል። ይሁን እንጂ አሁንም በአእምሮ ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ይነገራል።

ዶክተር ሙሉቀን ተስፋዬ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የአእምሮ ሀኪምና ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ የአእምሮ ጤና የባህሪ፣ የስሜትና የአስተሳሰብ ጤንነት ተብሎ ሊገለፅ ይችላል። ይህም አንድ ሰው በባህሪ፣ በስሜትና በአስተሳሰብ የተረጋጋ ሆኖ በሕይወት ለሚገጥሙት የተለያዩ ጫናዎች መፍትሄ ማበጀት የሚችልበት የአእምሮ ጤና ሁኔታ ላይ ሲሆን፤ በማህበረሰቡም ውስጥም አምራች ሆኖ ሲገኝ የአዕምሮ ጤናው የተሻላ ደረጃ ላይ ነው ብሎ መግለፅ ይቻላል።

እንደ ዶክተር ሙሉቀን ገለፃ፣ የአእምሮ ጤና መታወክ ስርጭቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይ ደግሞ ግጭቶች በሚበዙባቸው ቦታዎች ላይ የስርጭቱ መጠን በጣም ከፍ ያለና ከአራቱ ሰው አንዱ ላይ በሕይወት ዘመኑ እርዳታ የሚሻ የአእምሮ ጤና ችግር እንደሚገጥመው ያሳያል። የኢትዮጵያ ሁኔታም ሲታሰብ የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለ ያሳያል። በቅርቡ የተሰሩ ጥናቶችም ይህንኑ ያመለክታሉ።

የአእምሮ ጤና ችግር በብዙዎች ዘንድ ሲታሰብ ወደ አእምሮ የሚመጣው ራሳቸውን የጣሉና የጎዱ ሰዎች ቢሆንም በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከአንድ ከመቶ በላይ አይሆኑም። ነገር ግን እንደ አብዛኛው ሰው የሆኑና 99 ከመቶ የሚሆኑት ማሰብና መናገር የሚችሉ ግን ደግሞ በገጠማቸው የባህሪ፣ ስሜትና አስተሳሰብ ጫና የአእምሮ ሕመም ውስጥ የሚገቡ አሉ።

የተሻለ መስራትና ፍሬያማ መሆን ሲችሉም በሕመሙ ምክንያት ጫና ውስጥ የሚቆዩም ይኖራሉ። ይህም በየሁሉም ቤት ውስጥ ያለና ውጤቱም ኢኮኖሚውን፣ ፖለቲካውንና የተሻለ ለመኖር የሚያስፈልጉ እሴቶችንም ጫና ውስጥ የሚከት ነው። ከዚህ አኳያም ሁሉም ግንዛቤውን በማስፋት ለመፍትሄው መረባረብ ይጠበቅበታል።

ጥናቶቹ ከአራቱ ሰው አንዱ በዚህ የአእምሮ ችግር ውስጥ እንደሚያልፍ የሚያሳዩ በመሆናቸው ችግሩ ቅርብ መሆኑንና የጤና ሁኔታን አሳሳቢ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥም አንዱ ስርጭቱ በመሆኑ የአእምሮ ጤና ችግር በኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ መሆኑንና የእያንዳንዱን ሰው ርብርብ የሚፈልግ ነው። የአእምሮ ሕመም የትኛውንም የማህበረሰብ ክፍል የሚያጠቃ መሆኑ፣ በሌላ በኩል ሕመሙ ሕይወትንም ጭምር የሚቀጥፍ ከመሆኑ አኳያ በሁሉም አቅጣጫዎች ርብርብ ይፈልጋል።

ዶክተር ሙሉቀን እንደሚያስረዱት፣ ከሕክምና ተቋማት ተደራሽነት አኳያ በኢትዮጵያ 10 ከመቶ የሚሆኑ የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ባለሞያ ያገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ የሕክምና ክትትላቸውን አጠናቀውና አስፈላጊውን እንክብካቤ የሚያገኙት ግን ከአንድ በመቶ አይበልጡም። ይህም የሕክምና ተቋማት ተደራሽነትን ከማስፋትና አገልግሎቱን ከማዳረስ አንፃር ብዙ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ይጠቁማል።

የአእምሮ ጤና እንክብካቤ ከመስጠት አንፃርም ቀደም ሲል በተወሰኑ ሆስፒታሎች ብቻ ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት በሁሉም ሆስፒታሎች ውስጥ ከሌሎች ሕክምናዎች ጎን ለጎን እንዲሰጥ እየተደረገ ይገኛል። በዓለም ጤና ድርጅት አቅጣጫ መሰረትም ማህበረሰቡ ለአእምሮ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆንና ባሉት ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ሞያተኞችን ማብቃትና ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራዎች እየተሰሩ ነው። ማግለልና መድሎንም ለመቀነስ ሕብረተሰቡ በነዚህ ሆስፒታሎች ውስጥ ያሉ የአእምሮ ሕክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ይመከራል። ይሁንና ከችግሩ ስፋት አንፃር ይህ በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም።

ከአእምሮ ጤና ሕመም ጋር በተያያዘ እንደ ችግር ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ የግንዛቤ እጥረት መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሙሉቀን ታማሚው በራሱ የአእምሮ ጤና ችግር ሲገጥመው ሕመሙ አለብኝ ብሎ ላያምን ይችላል ይላሉ። አንዱ የሕመሙ መገለጫም ያለውን ሁኔታ መረዳትና እርዳታ የመሻት ባህሪውን ተፅእኖ ስለሚጨምር የሕመሙ ሌላኛው ችግር መሆኑን ይገልፃሉ።

በሌላ በኩል የአእምሮ ሕሙማንን በሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የማህበረሰቡ ንቃተ ሕሊና አለማደግ በራሱ ሌላ ችግር መሆኑንና በአእምሮ ጤና ላይ ያለው ግንዛቤ ማነስም ትልቅ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ዶክተር ሙሉቀን ይጠቁማሉ።

ይህንን ሁሉ መንገዶች አልፎ ታማሚው በራሱ ተነሳሽነት፣ በቤተሰብና በሕብረተሰብ እገዛ የሕክምና አገልግሎቱንና ርዳታውን ለማግኘት ፍላጎቱ ቢኖረው እንኳን ረጅም መንገድ ለመጓዝ እንደሚገደድ ያመለክታሉ። ታማሚው በበቂ ሁኔታና ሕክምናው በሚፈቅደው አግባብ ለምሳሌ ተኝቶ መታከም ቢፈልግም አገልግሎቱን በቀላሉ ማግኘት እንደማይችልም ይገልፃሉ። በዚህም ምክንያት ረጅም ጉዞ ላለመሄድ ታማሚዎች አገልግሎቱን ማግኘት እየፈለጉ በቤታቸው ለመቅረት እንደሚገደዱም ይጠቁማሉ።

ከዚህ ሁሉ ውጣውረድ በኋላም ታማሚዎች የሕክምና አገልግሎቱን ቢያገኙ እንኳን ከመድሃኒት እጥረት ጋር በተያያዘ ለከፋ እንግልት እንደሚዳረጉም ዶክተር ሙሉቀን ያስረዳሉ። አንዳንዶቹም ሕማማቸው እንደገና ሲያገረሽና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ ሲገቡ እደሚታዩም ይገልፃሉ።

የአእምሮ ጤና ደህንነትን ለማከም የሚያስፈልጉ ወሳኝ መድሃኒቶችም በአሁኑ ግዜ ገበያ ላይ እንደልብ እንደማይገኙ ጠቁመውም፤ ይህም በተለይ ለአእምሮ ታማሚዎች ረጅም ግዜ የሚሰጡ መድሃኒቶች እንዲቆራረጡ፤ ይህንንም ተከትሎ የጤና ባለሞያው ተነሳሽነት የሚቀንስና የመንፈስ ስብራትንም የሚፈጥር መሆኑንም ይጠቁማሉ። ይሁንና ችግሮቹ ብዙ ወጪ የሚጠይቁ ባለመሆናቸው ጠንካራ ስራዎች ከተሰራባቸው ሊስተካከሉ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

ዶክተር ሙሉቀን እንደሚሉት፣ ከአእምሮ ሕክምና ባለሞያዎች ጋር በተያያዘ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን በአእምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ደረጃ ሲታይ ቁጥሩ አሁንም አነስተኛ ነው። ይሁንና ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር አበረታች ሁኔታዎች እንዳሉ ያሳያሉ። በስልጠና ላይ የሚገኙና በቀጣይ ወደ አገልግሎት የሚገቡ ባለሞያዎችም አሉ። ይሁንና ከሚፈለገው መጠን ጋር ሲወዳደር የነዚህም ቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው።

በተመሳሳይ ሌሎችም በማስተርስ ደረጃ ያሉ የአእምሮ ጤና ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ባለሞያዎችም አሉ። በአእምሮ ጤና ላይ አተኩረው የሚሰሩ ሳይካትሪክ ነርሶችም ይገኛሉ። የነዚህ ሁሉ ሞያተኞች ርብርብ ነገሮችን ለማሻሻል የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ሆኖም አሁንም የአእምሮ ጤና ሞያተኞችን በስፋት አሰልጥኖ ማውጣት ያስፈልጋል።

የአዕምሮ ችግሩን ከመፍታት አኳያ ሁሌም የጤና ባለሞያዎች በቅድሚያ የሚመክሩት ቅድመ መከላከልን ነው። ከዚህ አንፃር በቅድሚያ የአእምሮ ጤና ምንነት ላይ በቂ ግንዛቤ መጨበጥ ያስፈልጋል። ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ የማህበረሰቡ ንቃተ ህሊና እንዲጎለብትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። የተለያዩ የሞያ ማሕበራትም በአእምሮ ጤና ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራትና ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

እያንዳንዱ ግለሰብም በእለት ተእለት ሕይወቱ ለአእምሮ ጤና የሚያግዙ ነገሮችን መተግበር ይጠበቅበታል። ለምሳሌ አመጋገብን፣ የእንቅልፍ ስርዓትን ማስተካከል ጭንቀትና ሃሳብን ለማስወገድ የጤና ባለሞያዎችን ማማከር ያስፈልጋል። ከሱስ አምጪ ነገሮች ራስን ማራቅ፣ ማህበራዊ ሕይወትን ማዳባር፣ መንፈሳዊ ሕይወትን ማጠናከር እንዲሁም የስሜት፣ የባህሪና የአስተሳሰብ ለውጦች ሲያጋጥሙ በቶሎ እርዳታ ማግኘት ችግሩን በአጭሩ ለመፍታት ያስችላል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም

Recommended For You