በሆሳዕና ከተማ ዙሪያ የምትገኘው ለምቡዳ ዱምበንቾ ቀበሌ የትውልድ ስፍራቸው ናት። ትምህርት ቤት ገብተው መማር የጀመሩት እንደሌሎቹ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን አጸደ ሕጻናት ወይም አንደኛ ክፍል በመግባት አይደለም። ከአንድ እስከ ሶስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርት አባታቸው በቤት ውስጥ ጥሩ አድርገው ስላስተማሯቸው ቀጥታ የገቡት አራተኛ ክፍል ነው። እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን የተማሩት በዚያው በሆዕሳና ከተማ “ራስ አባተ” በሚባል ትምህርት ቤት ሲሆን፣ የዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍልን ደግሞ የተማሩት ጬንቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ከ11ኛ ክፍል ጀምሮ ያለውን ትምህርታቸውን ደግሞ በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው በፖሊ-ቴክኒክ የቀጠሉ ሲሆን፣ ለአራት ዓመትም ተከታትለው በአድቫንስ ዲፕሎማ ለመመረቅ በቅተዋል – የዛሬው የዘመን እንግዳችን ተሻለ ሰብሮ (ዶ/ር)።
እንግዳችን፣ ባገኙት ዲፕሎማ ተቀጥረው ጥቂት ከሰሩ በኋላ እድል አግኝተው በዘመኑ አጠራሩ ወደ ሶቬየት ኅብረት አቅንተዋል። በዚያም በአዘርባጃን ስቴት በባኩ ከተማ በራሻይኛ ቋንቋ በኪቭ ዩኒቨርሲቲ ለስድስት ዓመታት ያህል በዓለም አቀፍ ሕግ ተምረው በከፍተኛ ውጤት በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል። በወቅቱም የኢትዮጵያ ተማሪያዎች ማኅበር መስራችና ለተከታታይ አምስት ዓመት ያህል መሪም ሆነው ሰርተዋል።
በወቅቱ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ውጤት ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ የእርሳቸውና አንደኛ የወጡት ተማሪዎች ፎቶግራፍ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በሚገኙ አዳራሾች ጭምር ይሰቀል ነበር። የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዳጠናቀቁም በዚያው የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት የጀመሩ ሲሆን፣ የመማር እድል የተሰጣቸውም ካመጡት ከፍተኛ ነጥብ በመነሳት ነበር።
ይሁንና የዛሬው የዘመን እንግዳችን ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ጀምረው ገና ሶስት ያህል ወራት እንዳስቆጠሩ በደርግ ዘመን በነበረው በ”እናት አገር ጥሪ” መሰረት አገር ትበልጣልች ብለው የጀመሩትን ትምህርት ለጊዜው ቆም አድርገው ወደ እናት አገራቸው ኢትዮጵያ በመምጣት በቀጥታ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተቀጠሩ። በዚያም ዲፕሎማት በመሆን አገለገሉ።
የፒ.ኤች.ዲ ዲግሪያቸውን በወቅቱ በጅምር ይተውት እንጂ ቁጭት ስለነበረባቸው ከበርካታ ዓመታት በኋላ በማኔጅመንት እና ሊደርሺፕ (Management and leadership) በኢትዮጵያና በአሜሪካ አገር ቨርጂንያ ተመላልሰው ተምረው ከሁለት ዓመት በፊት መመረቅ ችለዋል። የዛሬው የዘመን እንግዳችን የቀድሞው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) መስራችና ፕሬዚዳንት ሆነው ፓርቲውን የመሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ፓርቲያቸው ኢራፓ ወደ ኢዜማ መቀላቀሉን አውግተውናል። ከእኝህ አንጋፋ ፖለቲከኛና የቀድሞ ዲፕሎማት ጋር ያደረግነውን ቆይታ አጠናቅረን አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ከሚዲያው አካባቢ ርቀዋል፤ በፓርቲ ውስጥ የነበረዎ እንቅስቃሴም ደብዝዟል፤ ምክንያቱ ይሆን? ከሶስተኛ ዲግሪ ምረቃ በኋላ ምን እየሰሩ ነው?
ተሻለ (ዶ/ር)፡– ሁለትና ሶስት ያህል ዓመት የፒ.ኤች.ዲ ትምህርቴን ለመከታተል ስል ጠፋ ብዬ ነበር። ይሁንና ስለአገር ጉዳይ በተፈለኩበት ጊዜ ሁሉ በ“ያገባኛል” መንፈስ ሐሳቤን ከመስጠት ተቆጥቤ አላውቅም። የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ መስራችና ፕሬዚዳንት ሆኜ ለ11 ዓመታት ያህል ሰርቻለሁ። ከዚያ በኋላ ወደ ኢዜማ መቀላቀል ነበረብን።
እርግጥ ነው፤ በወቅቱ ብልጽግናም መግባት ምርጫችን ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ ከሁሉም ኃላፊዎች ጋር እንነጋገር ነበር። ብልጽግና ለጊዜው ፕሪንሲፕሉ ቢኖርም ገና ጉዳዩ እምብዛም ጎልቶ አልወጣም ነበር። በወቅቱ የመደመርን ፍልስፍና ሙሉ ለሙሉ እያካሔደ ይሁን እንጂ ቴክኒካል ስራዎች ላይ አልተዘጋጀም ነበር። ስለዚህም በወቅቱ ቶሎ ተዘጋጅቶ የተሻማን ኢዜማ ነበር።
በኢዜማ ውስጥ እንቀላቀል እንጂ እኔ በወቅቱ በአመራርነት ልቀጥል አልፈለግኩም። ምክንያቱም በግልጽ አሳውቄ ወደ ትምህርት ቤት በመግባቴ ነው። እየተማርኩ እያለ ምንም እንኳ የወትሮውን ያህል በተደጋጋሚ ባልገኝም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በሚዲያ እንደ አንድ የሕግ ምሁርም ሆነ ዲፕሎማት ስሳተፍ ቆይቻለሁ። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይም በተጠራሁበት መድረክ ላይ ሁሉ አለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ያልዎ ተሳትፎ ከፍ ያለ ነው፤ እንደሚታወቀውም ግድቡ ሊጠናቀቅ የወራት ያህል ጊዜ ቀርቶታልና እዚህ በመድረሱ ምን ተሰማዎ?
ተሻለ (ዶ/ር)፡– ከግድቡ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ድርድሮች ሲካሔዱ ቆይተዋል። ብዙዎች ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚሞክሩ ነበሩና እሱ ሁሉ ተግዳሮት አልፎ ዛሬ ላይ መድረስ በመቻሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። እጅግም ደስተኛ ነኝ።
በተለያየ ጊዜ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ጋር በሚደረገው መስተጋብር የበኩሌን ለመወጣት ጥረት አድርጌያለሁ። ወደ ሕዳሴ ግድቡ አምስት ስድስት ያህል ጊዜ ከልዑካን ቡድን ጋር ሔጄ ጎብኝቻለሁ። በዚህ ግድብ ላይ ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነት የመሳተፋቸውን ያህል ከአጼ ኃይለስላሴ ጀምሮ ያሉ የኢትዮጵያ መሪዎች ጥናት በማስጠናት ብርቱ ትግል ከማድረግ እስከ ግድቡን መጀመርና መፈጸም የደረሱ በመሆናቸው ታላቅ ስኬት ነው።
እኔን በጣም ያስደሰተኝ ኢኮኖሚያዊ ድሉ አይደለም። ፖለቲካዊ ስኬቱ ነው። በጣም ያስገረመኝ ነገር ቢኖር ጦርነትን ማክሸፍ መቻላችን ነው። ምክንያቱም ከሕዳሴው ግድብ በተቃራኒው የቆሙ አካላት ሁሌም አማራጫቸው ጦርነት ነው። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ኢኮኖሚያዊም ፖለቲካዊም ውጤት አሳየ ማለት ነው። ስለዚህ ይህ በግድቡ የተገኘው ውጤት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው። እንዲሁም ሞራላዊ ድል ነው። በዚህ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የቀድሞ ዲፕሎማት እንደመሆንዎ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለይ ደግሞ ባለፈው ዓመት የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ አካሔድና ውጤቱን የተመለከቱት እንዴት ነው?
ተሻለ (ዶ/ር)፡- እኔ ቀደም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባልደረባ ሆኜ ለ11 ዓመታት ያህል ሰርቻለሁ። በሰራሁበትም ዘመን በተወሰነ መልኩ በአገር ደረጃ በደርግ ዘመነ መንግስት ከሱማሊያ ጋር ጦርነት የነበረበት ጊዜ ነው። በተጨማሪም የውስጥ ጦርነት ነበር። የውስጥ ጦርነቱ ልክ አሁን እንደምናየው አይነት ነው ማለት ይቻላል።
በእኔ እምነት ለውጪያዊም ሆነ ለውስጥ ጦርነቶች ባለቤቱ አንድ ነው። በዚያን ወቅት ግጭቶች ሁሉ የሚዘወሩት ከአንድ ጣቢያ ነው የሚል አተያይ አለኝ። እሱም ካይሮ ላይ ነው ባይ ነኝ። ከእርሷ ኋላ ያለች ደግሞ ዋሽንግተን ናት፤ እዚህ ላይ ምንም አይነት ብዥታ ሊኖር አይገባም። ስለዚህ አሁንም እየተደገመ ያለው የዚያ አይነት አካሄድ ነው።
በእርግጥ ዲፕሎማሲ በየዘመኑ የሚፈተንበት ወቅት ይኖራል። በእርግጥ ሁሉም ዘርፎች ይፈተናሉ። ነገር ግን ያንን ፈተና ለመቋቋም አንደኛ አንጻራዊ ሰላምን እየጠበቅን መሆን አለበት። በወቅቱ የደርግ መንግስት ሲያደርግ የነበረው ሰላምን ለማስፈን ደፋ ቀና ከማለት ጎን ለጎን ልማትንም በማሳለጥ ነበር። እንዲሁም መሰረት ልማትንም በማስፋፋት መታገልን ምርጫው አድርጎ ነበር።
በአሁን ወቅት ደግሞ እየተካሔደ ያለው ነገር ሲጤን የመሰረተ ልማቱ ስራ በስኬታማነት እየተሰራ በመሆኑ በአገር ውስጥ ፈታኝ የሆኑ ነገሮች ያሉ አያስመስለውም። በገጠርም ሆነ በከተማ አካባቢ እየተካሔደ ያለው ልማትና እድገት የሚያስገርም ነው። በተለይም ደግሞ ዲፕሎማሲያዊ አካሔዱ ሲታይ ባለፈው ዓመት ብቻ በርካታ ውጤታማ ስራዎች በመሰራታቸው በዘርፉ ብዙ ድል መመዝገቡ ሲታይ አስደናቂ ነው። ኢትዮጵያ ከባድ ውጥረት ውስጥ ሆና እና ጉሮሮዋ ታንቆ ባለበት በዚህ ጊዜ ውስጥ ጉልህ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በተለይ የዲፕሎማሲያዊ ስራ ላይ በእኔ በኩል ከሚጠበቀበው በላይ ድልን መቀዳጀት የተቻለበት ዓመት ነው ብዬ መናገር እችላለሁ። በጣም ብዙ ነገርም እየተሰራ መሆኑን ማስተዋል ችያለሁ። ዲፕሎማቶቻችንም ሆኑ አምባሳደሮቻችን በአሁኑ ወቅት የእረፍት ጊዜ የሌላቸው መሆኑን ማጤን ይቻላል። በመንግስት በኩል በየአቅጣጫው ያለው እንቅስቃሴና ውጤቱ ሲታይ ያለዕረፍት እየተሰራ መሆኑን አመላካች ነው። እየተሰራ ያለው ስራ እንደ ዲፕሎማትም እንደ ወታደርም፤ እንደ ዲፕሎማት ጭምር እየተነጋገሩ የሚሰሩበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
የውስጥና የውጭ አፋኝ ኃይሎችን ሁሉ መቋቋም የሚያስችለው መሳሪያ እግዚአብሔር ራሱ እርዳታ ካላደረገ በስተቀር አንዳንዴ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቆቅልሽ ሆኖ የሚታይ ጊዜ እንዳለ ግን መሸሸግ አልችልም። የኢትዮጵያን ጉዳይ ዝም ብዬ ሳጤነው እጅን በአፍ የሚያስጭን ሆኖም የሚታየኝ ጊዜ ይበዛልና ነው።
በተለይ ከዲፕሎማሲው አኳያ የብሪክስ አባል አገር የሆንበት ምከንያት በተሰራው ያላሰለሰ ስራ ምከንያት ነው። ይህም ታላቅ ድል ሆኖ የተመዘገበ ነው። ይህ የብሪክስ አባልነታችን ጉዳይ ለእኔ እጹብ ድንቅ የሆነ ድል ነው። ምክንያቱም ይህ የብሪክስ አባልነት ቅቡልነታችን የሚያስገርመኝ ጉዳይ ነው። ግብጽ ልክ እንደ እኛው አዲስ ገቢ ባትሆንና ቀድማ ገብታ ቢሆን ኖሮ እንዳንገባ ትገዳደረን ነበር ስልም ሐሳቤን መግለጽ እሻለሁ።
ሌላው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ የነበረው ግጭት በሕይወትም በንብረትም ጉዳት ያስተናገድንበት ቢሆንም በመጨረሻ በሰላም መቋጨት መቻሉ የዲፕሎማሲ ውጤት ነው። በእርግጥ በዚህ ላይ ውጣ ውረድና ከፍታና ዝቅታ እንዳለ የሚታወቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ ፖለቲከኛና የሕግ ሰው የቀጣናዊ ትስስራችን ምን መምሰል አለበት ይላሉ?
ተሻለ (ዶ/ር)፡- እኔ መሆን አለበት የምለው፤ ቀጣናዊ ትስስሩ በኢትዮጵያ ሐሳብ አመንጪነትና የበላይነት መሳለጥ አለበት ነው፤ ይህን የምለው ስሜታዊ ሆኜ አይደለም፤ አገሬ አቅም ስላላትም ጭምር ነው። በተለይ ደግሞ እኔ በዚህ መንግስት እምነት አለኝ፤ ይህንን አልክድም። በኢትዮጵያ መንግስት መሪነትና የበላይነት ቢመራ እድለኞች ነን ባይ ነኝ፤ ይህ መሆኑ ጠቀሜታው ደግሞ ለእኛ ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን ላሉ ለቀጣናው አገራት ጭምር ነው።
ይህ ሲሆን ሰላም ይሰፍናል፤ መከባበርና የጋራ እድገት ይመጣል። በአሁኑ ወቅት በቀጣናው ያለው ድባብ ደሰ የማይል ነው። ነገር ግን ያንን ደስ የማይለውን አየር መቀየር የሚችል ባለራዕይ ከኢትዮጵያ ውጭ ያለ አይመስለኝም። ኢትዮጵያ እና መሪዎቻችን ይህን መጥፎ ድባብ ለመቀየር እቅዳቸውን ቢገፉበት ውጤታማነቱ ለአገርም በዙሪያው ላሉትም አገራት ነው።
ዲፕሎማሲውም ሆነ ፖለቲካው በእኛ አሸናፊነት ቢሄድ እና የመሪነቱን ቦታ ኢትዮጵያ ከጨበጠች ሌሎች ከእኛ ጋር ስለሚተባበሩ የተሻለ ቀጣናን ትስስርን ለመፍጠር ያስችላል ብዬ አስባለሁ። የቱንም ያህል ጋሬጣ ቢበዛብንም በመሪነታችን ስፍራ ላይ ሆነን መቀጠል አለብን። የመሪነታችንን ሚና ለጎረቤት አገር ሳይሆን ያውም ከሩቅ ለመጣ አካል አሳልፈን መስጠት የለብንም። ምክንያቱም ቀጣናውን መምራት የሚያበቃን ብዙ አሳማኝ ነገሮች ጭምር ስላሉን ነው። ስለዚህም የመሪነቱ ሚና በእዚህ ትውልድና መንግስት እጅ ላይ ያለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎች ኢትዮጵያውያን፤ ኢትዮጵያ ቋሚ ጠላት እንዳላት አድርገው ይቆጥራሉ፤ እንደ አንድ የቀድሞ ዲፕሎማትም ሆነ ፖለቲከኛ ቋሚ ጠላትም ሆነ ቋሚ ወዳጅ አለ ብለው ያምናሉ?
ተሻለ (ዶ/ር)፡– ቋሚ ወዳጅ፣ አልፎ አልፎ ጠላት ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። ከዚህ የተነሳ ቋሚ ወዳጅም ሆነ ቋሚ ጠላት አለም፤ የለምም እላለሁ። ይህ የእኔ እምነት ነው። ቋሚ ጠላት አለን ያልኩበት ዋና እና በቂ ምክንያት ስላለኝ ነው፤ ይህን የምለው ዛሬም ብቻ አይደለም፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እየሰራሁ ባለሁበት በ1970ዎቹ ዓ.ም የጎረቤት አገራት ኤክስፐርት ነበርኩ። ሁልጊዜ የሚያነጫንጨኝ በርካታ ምስጢራዊ መረጃዎች በእጄም ገብተው ነበር። በወቅቱም ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ አለቃዬ ስለነበሩም በአጎራባች አገራት አብሬያቸው እንቀሳቀስ ነበር። በእነዚያ ጊዜያት የማይናቁ መረጃዎችንም አውቅ ስለነበር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁንም ባጤንኩት ሁኔታ ግብጽን ቋሚ ጠላታችን ናት እላለሁ።
ለዚህ ምክንያቴ ከመጀመሪያ ጀምሮ እስከወዲያኛውም የትኛውንም መሪዋን ብትቀያይርና የትኛውም ፓርቲ ቢመራት በኢትዮጵያ ላይ ያላትን የጠላትነት አቋሟን የማትቀይር አገር ናት። ወታደራዊም መንግስት ይምጣ ሲቪል፤ በተለይ የዓባይን ውሃ በተመለከተ ያላቸው አቋም አንድ አይነት ነው። የአባይ ወንዝ ቋሚ ውሃ እንደሆነው ሁሉ ግብጽም የኢትዮጵያ ቋሚ ጠላት ሆና ዘልቃለች፤ ትቀጥላለችም።
የተፈጥሮ ሀብቱን በመተባበርና በጋራ ማልማት ይቻላል። ኢትዮጵያ ደግሞ በፊትም ሆነ አሁን እያራመደች ያለችው መርህ ይህንኑ ነው። እርሷ ግን በጣም ራስ ወዳድ የሆነች አገር ስትሆን፣ ምሁራኗም ጭምር እንደዚያው ናቸው። 24 ሰዓት ምርምር የሚካሔደው በኢትዮጵያ ዙሪያ ነውና ነው።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ሆኜ በተለያየ ጊዜ ወደግብጽ አቅንቻለሁ። በፐብሊክ ዲፕሎማሲ በኩልም እንዲሁ ተጉዥያለሁ። ሕዝቡንም ሆነ የተለያዩ ተቋማትንና ተማሩ የተባሉትን ባነጋገርናቸው ጊዜ ብዙዎቹ የዓባይን ውሃ መነሻ እንኳ ጨርሶ የማያውቁ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ብዙዎቹ የሚቆጥሩት የናይል ውሃ መነሻው ከምስራቃዊ ግብጽ በኩል እንደሆነ ነው። ለቀሪዎቹም ቢሆን እውነተኛ መነሻውን የሚያስተምራቸው የለም።
ስለዚህ ግብጽ ቋሚ ጠላታችን ስለመሆኗ ከመናገር የሚያሽኮረምመን ነገር አይገባኝም ባይ ነኝ። ኬንያን ወይም ሌላውን አገር በምናይበት መነጽር ግብጽን ለማየት መገደድ የለብንም። ከሌሎቹ ጋር በተለያየ ነገር ላንስማማ እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን በመነጋገርና በመወያየት የሚፈታ እና ስናደርገውም የመጣነው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በአንድ ቤተሰብ መካከል እንኳ መጋጨት አለ፤ መስማማትም አለ። ስለዚህ ግብጽና ሱማሊያን በተመለከተ ግን አካሔዳችን የተጠና መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር መፈራረሟ ይታወሳል፤ ይህን ጥያቄ በማንሳቷ ብቻ ብዙ ተግዳሮት እየደረሰባት ነው፤ ኢትዮጵያ ጥያቄውን ማንሳቷ ክፋቱ ምኑ ላይ ነው ይላሉ?
ተሻለ (ዶ/ር)፡– አለመታደላችን ሆኖ ነው እንጂ ይሻለን የነበረውማ የራሳችንም አሻራ ያረፈበት አሰብ ነበር። አሰብም ሆነ ምጽዋ የቀድሞ መንግስቶቻችን አሻራ ያለበት ነበር። የኢሕአዴግ መንግስት ትቶልን ከሔደው ነቀርሳ መካከል አንዱ የጎሳ ፖለቲካ ሲሆን፣ ሌላው ወደብ ማሳጣትን ነው። ኤርትራ ነጻ አገር ልሁን በማለቷ እዛ ላይ ብዙ ማለት አልፈልግም። ነገር ግን ታላቅ ሕዝብንና አገርን መውጫ እና መግቢያ በር እንዳይኖረው አድርጎ የከረቸመበት የኢሕአዴግ መንግስት የሁልጊዜ ተወቃሽ እንደሆነ ይዘልቃል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እጅግ እየጨመረና እያደገ ነው። ከተጠበቀው በላይ እየሆነ በመምጣቱ የግድ ወደብ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፤ ለዚህ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን ደግሞ የዓለም አቀፉም ሕግ ቢሆን የሚፈቅድ ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በርን በሰላማዊ መንገድ ማግኘት እንደምትችል አያጠራጥርም። ደግሞም የኢትዮጵያ መንግስትም ወደዚህ ጥያቄ ሲገባና ሲፈራረም ዝም ብሎ ዘው ያለበት ነገር እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው። ወደ ፊርማውም የገባው የተለያዩ አማራጮችንም አይቶና ገምግሞ እንደሆነ የሚታመን ነው።
በጅቡቲ ብቻ የሚደረገው ቅብብሎሽ ኢትዮጵያን በፈለገችው ልክ ሊያስተነፍሳት አላስቻላትም፤ ኢትዮጵያ በጣም እያደገች ነው። ከዚህ የተነሳ በብዙ አቅጣጫ ብዙ አማራጮችን ያየች ስትሆን፣ ምንም እንኳ እነዚያ ላይ ተስፋዋ ባይሟጠጥም አማራጯን ማስፋት ግድ ይላታልና ያንን ማድረጓ አግባብ ነው።
ይሁንና ይህ የኢትዮጵያ ጥያቄ እንዳይሳካ በውስን ኃይላት ብዙ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፤ እንዲያውም ግብጽ ወደ ጎረቤት አገር ሱማሊያ የመምጣቷም አንዱ ገፊ ምክንያት ይህን ለማሰናከል በማሰብ እንጂ ለሱማሊያ ወይም ለሱማሊላንድ አስባ እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ ጤናማ በሆነ መንገድ ጥያቄዋን አቅርባ መስመር ውስጥ እየገባች በመሆኑ ከዚህ በኋላ ወደኋላ ማለት አይቻልም። በዚህ በኩል ከሕዝቡም ዘንድ ለመንግስታችን ድጋፍ ያለ በመሆኑ የሚጠበቅብን ከግብ ለማድረስ መስራት ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቅርበት ያሉ ጎረቤት አገራትም ሆኑ በርቀት ያሉ አገራት ኢትዮጵያን ተረድተዋታል ብለው ያስባሉ?
ተሻለ (ዶ/ር)፡– እኛ ብዙ ወዳጆች አሉን፤ እኔ በራሴ የግል ምክንያትም ሆነ በሌላ ሌላ ምክንያት ወደውጭ አገር ወጣ ገባ የምልበት ምክንያት ብዙ ነው። ከብዙ የውጭ ዜጎች ጋር የምገናኝበትም ጉዳይ በርካታ ነው። እናም የታዘብኩት ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ በብዙዎቹ ዘንድ ቀድሞውኑም ቢሆን ታዋቂ መሆኗን ነው። ኢትዮጵያ፣ ከአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ታዋቂ ናት። ምክንያቱ ምንድን ነው ያልሽኝ እንደሆን አንዳንዴ ለጥፋት የመጣብን ነገር ኢትዮጵያን የበለጠ እንድትታወቅ አግዟታል። አጼ ቴዎድሮስ ያደረጉት ውጊያ እርሳቸውንና ኢትዮጵያ ይበልጥ እንዲታወቁ ያበቃ ነው። ወደ አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ምኒልክም ሆኑ አጼ ኃይለስላሴ ዘንድ ሲመጣም የሆነው ነገር ተመሳሳይ ነው።
የተደረጉብን የግፍ ጦርነቶችና ጥቃቶች እና በቅኝ አንገዛም ባይነታችን አገራችን ኢትዮጵያን በብዙዎቹ ዘንድ እንድትታወቅ ያደረጋት ነው። በደርግም እንዲሁ ነው፤ በተለይ በ1969 እና 1970 ዓ.ም አካባቢ፤ ሶማሊያ ልትሸከመው የማትችለውን የጦር መሳሪያ በአሜሪካ አስታጣቂነትና በዛይድባሬ ግንባር ቀደምትነት ዓለም ሁሉ በወቅቱ ሲተባበርብን የሚታወስ ሲሆን፣ ምንም እንኳ ልጆቻችን መስዋዕት ቢሆኑና ኢኮኖሚያችንም ቢጎዳ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መደምደሙ ሁሉም የሚያውቀው ሐቅ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም ልከ እንደ አድዋ ድል የበላይነታችንን ያስተወዋቅንበት ድላችን ነው። በወቅቱ እኔ የኢሰፓ የፓርቲው አንደኛ ጸሐፊ እንዲሁም ከፍተኛ ዲፕሎማትም ስለነበርኩ ጉዳዩን በቅርበት የማውቀው ጉዳይ ነበር።
ስለዚህ በቅርበትም ሆነ በርቀት ያሉ አገራት ኢትዮጵያን መረዳት ብቻ ሳይሆን በአሸናፊነቷም ጠንቅቀው ያውቋታል። በተመሳሳይ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ የማትበገር አገር ስለመሆኗ አሳምረው ያውቃሉ ባይ ነኝ። መሪያችንም በአሁኑ ወቅት እያደረጉ ያለው ስራ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስገረም ላይ ያለ ከመሆኑም በተጨማሪ በዓለም ሚዲያዎችም ሆነ ፖለቲከኞች ዘንድ እውቅናውን አግኝተዋል። እንዲህ ስል የሚጠሉን እንዳሉ ከግምት ውስጥ መግባቱ ሳይዘነጋ ነው።
በጥቅሉ በውጭ በኩል ጥሩ የሆነ የአገር ገጽታ ግንባታ እንዳለን የማይካድ ሐቅ ነው እላለሁ። በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው በኩል አስገራሚ የሆኑ ስራዎች ከመሰራታቸው አልፎ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበም ይገኛል። ከፖለቲካውና ከኢኮኖሚው ወጣ ስንል ደግሞ ኢትዮጵያን በተለያዩ መድረኮች የሚያስጠሯት አትሌቶቻችን ሌላው ኩራታችን ናቸው። ዳያስፖራውም ቢሆን ለአገራችን ስኬትም ሆነ እውቅና የተጫወተው ሚና የሚዘነጋ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በአገር ውስጥ የተፈጠረውን የሰላም መታጣት ማስተካከል የሚቻለው እንዴት ነው? ኢትዮጵያውያንስ እርስ በእርስ መገፋፋታቸውን ትተው ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ድርሻቸው ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ተሻለ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያውያን በተለይ ከለውጡ በኋላ የምንገፋፋውና ግጭት ውስጥ የገባነው ለአገር ሳይሆን ለጥቅማችን ስንል ነው። የሚያገፋፋን የግል ጥቅም ነው። ግጭት ውስጥ የሚያስገባቸው ለአገር ሳይሆን ለወገን፣ ለሰፈር ምናልባት አልፎ ለጎሳ እና ለዘር በሚል የሚደረግ ጥቅም ፍለጋ ነው። የዚህ ጥቅም ምንጩ አሁንም ቢሆን ከውጭ ነው።
በግል ጥቅም ተሳክረው ግር ግር የሚፈጥሩትን የሚያባብሰው እና ቤንዚን የሚያርከፈክፈው ደግሞ ውጭ አገር ያለው አካል ነው። የእርሱ ልጅ ሳይሞትና ንብረቱ ሳይወድም በተደላደለ ሁኔታ ከአገር ውጭ ተቀምጦ እዚህ ያለውን የሚያባላው የውጪው ኃይል ነው።
እንዲያውም በግልጽ እንዳሉትም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ተቃዋሚዎችንና አመጽ የሚያስነሱትን እንደግፋለን ሲሉ የውጭ ኃይሎች ተናግረዋል። እንደ እሱ ማለት ደግሞ መበጥበጣችንን እንቀጥላለን እንደማለት ነው። ብጥበጣውን በዘር፣ በጎሳ፣ በክልልና በሌሎች ነገሮች በመከፋፈል ቀጥለዋል። ይህ ደግሞ የግብጽ አጀንዳ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። ይህን የሚያጠናክሩትና እንደ ቤታቸው ወደ ግብጽ መለስ ቀለስ የሚሉ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ናቸው። ምክንያቱም በምስራቅ የአፍሪካ ክፍል መግባት የሚችለው የግብጽ ጦር ነው በሚል እየፈቀደ ያለው ይኸው የኋይት ሃይውስ መንግስት ነው።
የአገር ውስጥ ሰላምን በተመለከተ ገና በእንጭጭነቱ መቅጨት ተገቢ ነበር፤ እንዲህ ስል የሰው ሕይወት ሳይጠፋና ንብረትም ሳይወድም ለማለት ነው። ይሁንና አሁንም ቢሆን ለሰላም ሲባል መሰለቸትና እልህ መግባት አያስፈልግም። መናናቅም ሳይኖር ለሕልውና ሲባል ሰላም ማምጣት ተገቢ ነው። ከውጭ የሚመጣውን ጫና ለማጥፋት በአገር ውስጥ ያለነው አካላት ለሰላማዊ ድርድር ራስን ማዘጋጀት መልካም ነው። ለዚህ ለሰላማዊ ድርድር መንግስትም ሆነ ሕዝብ ጫና መፍጠር አለባቸው።
በተለይ በቦታውና በስፍራው ያሉና ችግር የተፈጠረባቸው ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ሰላምን ፍለጋ ሊነቃቁና ሰላም እንዲታወክ የሚያደርጉትን አካላት “በቃችሁ” ሊሏቸው ይገባል። “ማረስ፣ መነገድ፣ ማምረት እንሻለን” በሚል መነሳሳት ይጠበቅባቸዋል እንጂ ሁሉን ነገር መንግስት ይጋፈጥልኝ በሚል ለመንግስት ብቻ መጣል ተገቢ አይደለም።
በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገው የአሸናፊነት ጥያቄ ሳይሆን የጋራ ቤታችንን በጋራ መስራት ነው። የጋራ ቤትን በጋራ መስራትን የማይፈልግ አካል ካለ ግን ማፍረስ እንደማይችል ሊገነዘብ ይገባዋል። የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀስ አካል ካለ አፈርሳለሁ የሚለው የሌላውን ቤት ብቻ ሳይሆን የእርሱንም ጭምር መሆኑን መረዳት አለበት።
ኢትዮጵያ ይህንን ፈተና ታልፋለች። ታሪክ እንደሚያሳየን ትናንትም የነበረብንን ፈተና በድል ተሻግረናል። ጊዜው ተቀያየረ እንጂ ጠላት ያው ጠላት ነው። ስለዚህ ተስፋ የሚያስቆርጥ አንዳች ነገር የለም። መንፈሰ ጠንካራ ባለራዕይ ሆነን እንሻገራለን። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሰላምን ለማምጣት ከመንግስት ጋር ሆኖ መስራት አለበት እላለሁ። ሁሉንም ጥፋት ወደመንግስት መወርወርና መቀመጥ ስህተት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቢሯችን ተገኝተው ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ተሻለ (ዶ/ር)፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም