አሮጌው ዘመን አብቅቶ የኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት በተበሰረበት ወርሐ መስከረም ላይ እንገኛለን። እንዲህ አሮጌው በአዲሱ እየተተካ እልፍ ዘመንና ትውልድ አልፎ፤ እዚህ ዘመን ላይ እኛ የዛሬው ትውልድ ደርሰናል። ስንቶች ይህንን ዘመን ወይም አዲስ ዓመት ሳያዩ አልፈዋል። እኛ ግን እንደሥራችን ወይም እንደበደላችን ሳይሆን እንደ አምላክ ቸርነት ዛሬን ለማየት ታድለናል። ከዘመን ወደ ዘመን ለመሸጋገር በቅተናል። አዲስ ሕይወት ተሰጥቶናል።
የተሰጠንን አዲስ ዘመን ደግሞ የደስታ፣ የፍቅር፣ የሠላም፣ የእድገት፣ የአንድነት … የምናደርገው እኛው ነን። በአንጻሩ ደግሞ የጦርነት፣ የመገዳደል፣ የጥላቻ፣ የመለያየት፣ የዘረኝነት … ዘመን የምናደርገው እኛው ነን። ምክንያቱም ዘመን ማለት እኛ ነን። ስንከፋ የሚከፋ ደግ ስንሆን ደግ የሚሆን የእኛው ነጸብራቅ ነው። ለዚህ ነው አበው በአነጋጋሪ ፈላስፋ “ዘመን ማለት አንተ ነህ” ያሉት። አንተ ሠላማዊ ስትሆን ሠላማዊ ትሆናለች፡፡ አንተ ጠንክረህ ታጥቀህ ስትሠራ በዘመንህ ጎተራው ሙሉ፤ ገበያው ጥጋብ ይሆናል።
በተቃራኒው ደግሞ አንተ የከፋህ እንደሆነ ትከፋለች፡፡ በተሰጠህ ዘመን አንተ ትብስ አንቺ ትብስ ተባብሎ ተከባብሮ መኖር ካቃተህ፤ ምድር ሠላም ርቋት የጦርነት አውድማ፤ የደም ዥረት የሚወርድባት መሆና አይቀሬ ነው። በዘመንህ ሠላምህን አጥብቀህ ካልጠበቅሃት፣ ለሠላም የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ካልከፈልህ ሠላምህ ይርቅሀል። እንዲሁም በዘመንህ መግፋት መገፋትን፣ መናቅ መናናቅን፣ ማዋረድ ውርደትን፣ መጥላት መጠላትን፣ … ያመጣል።
ከዚህ የምንረዳው ጊዜው የሚመስለው እኛን ነው። እኛ ነን ዘመኑን ደግ ወይም ክፉ የምናስብለው። “ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም” እንዲሉ አሮጌው ዘመን አልፎ የዘመን ቅብብሎሽ አዲሱ ዓመት ላይ አድርሶናል። አዲሱን ዓመት የደስታ፣ የመፈቃቀር፣ የመተሳሰብ፣ የተድላ፣ የሠላም… የምናደርገው እኛው ነን። በተገላቢጦሽ ደግሞ የኅዘን፣ የጦርነት፣ የኹከት፣ የብጥብጥ፣ … እንዲሁ የምናደርገው እኛው ነን።
እናም ዘመን እኛ፤ እኛም ዘመን ነን። ነገር ግን ሰዎች ብዙ ጊዜ ዘመኑ ተቀይሯል፣ ዘመኑ ተበላሽቷል፣ ዘመኑ ከፍቷል፣ … ሲሉ ይደመጣሉ። እውን ዘመኑ ተለውጧል፣ ከፍቷል፣ ተበላሽቷል፣ ተቀይሯል ….? እስኪ በሞቴ ንገሩኝ ትናንትም ሆነ ዛሬ አንድ ዓመት ከ365 ቀን ወይም ከአሥራ ሁለት ወራት ጳጉሜን ጨምሮ ተጓሎ ያውቃል? ወሩስ ከ30 ቀን ይጎላል? ሳምንቱስ ከሰባት ቀን ተቀንሶ ያውቃል? አንድ ቀን ከ24 ሰዓት ጎሎ ያውቃል? ጎሎ ከሆነ አዎ! ዘመኑ ተለውጧል፣ ተቀይሯል፣ ተበላሽቷል።
እውነታው ግን ዛሬም ሆነ ትናንት ዓመቱ ካለው ወራትና ቀናት አልተቀነሰበትም። ወሩም፣ ሳምንቱም እንዲሁም ቀኑም እንደዚያው ነው። ዛሬም ፀሐይ በምሥራቅ ወጥታ፣ በምዕራብ ትጠልቃለች፤ ጨረቃ ብርሃኗን ያለስስት ለዓለም ትለግሳለች፣ ቀንና ሌሊቱ እንዲሁ በየተራቸው ይፈራረቃሉ። ስለዚህ ብዙዎቻችን እንደምንለው ዘመኑ ተቀይሮ ወይም ከፍቶ አይደለም። እውነታው እኛ ሰዎች ከሰውነት ተራ ስንወርድ ዘመኑ ይቀየራል፣ ይቆሽሻል፣ ይበላሻል፣ ይከፋል … እንጂ።
ትናንት አባቶቻችን ከሰውነት ውሃ ልክ ዝንፍ ሳይሉ በአንድነት፣ በፍቅር አንተ ትብስ አንቺ ተባብለው ተፈቃቅረው በይቅር ባይነት፣ በመተሳሰብ፣ በመተጋገዝ፣ ሀገርን በጋራ በመጠበቅ፣ ከልዩነቶች ይልቅ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ቅድሚያ በመስጠት፣ በታማኝነት፣ በአርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት፣… ወዘተ ልክ እንደ አንበሳ ተከባብረው በመኖራቸው ዘመናቸው ያማረ፣ የሰመረ ነበር። ዛሬም ያ ደጉ፣ የሠላሙ፣ የተድላው፣ የአንድነቱ፣ የተባረከው … ዘመን እየተባለ ይታወሳል፤ ይናፈቃል፣ ይወደሳል። አባቶቻችን ሀገራችን ኢትዮጵያንም ከዜጎቿ አልፏ የጥቁር ሕዝቦች መመኪያ እንድትሆን አድርገው አልፈዋል።
“እሳት አመድ ይወልዳል” እንዲሉ የነዛ የጀግኖች፣ የታማኞች፣ የሃይማኖተኞች፣ የደጎች ልጆች ዛሬ ላይ ከሰውነት ተራ ወርደን በዘር፣ በቋንቋ ተከፋፍለን በርስ በርስ ጦርነት ምድሪቱን አኬልዳማ አደረግናት። ሕዝቡ ሠላም ወጥቶ ሠላም መግባት ልክ እንደ እንጀራ ራበው፣ እንደውሃ ጠማው። “በዓለም አደባባይ እንግዳ ተቀባይ” በመባል የሚታወቀው ሕዝብ ዛሬ ላይ ተወልዶ በአደገበት፣ ወልዶ ከብዶ ኩሎ በዳረበት ከቀዬው ባይተዋር ሆኖ ተሰደደ። በቀዬው ደመከልብ ሆኖ ቀረ። እልፍ ዜጎች በስደት የባሕር አሣ ነባሪ ሲሳይ፤ የበረሃ አውሬ እራት ሆነው ቀሩ። ኩሩው ሕዝብ በስደት ተዋረደ።
ከገዛ አብራኩ የወጡ ልጆቹ መንገድ እየዘጉ ቋንጃ ይቆርጣሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ይገድላሉ፣ ያፈናቅላሉ። አግተው በሚሊዮን ገንዘብ ይቀበላሉ። እስኪ ንገሩኝ ዕጣ ፈንታው ደርሶ የታገተ መቼም አንዴ ታግቷል እንበል። ነገር ግን የታገተ ዘመዱን ለማስለቀቅ ገንዘብ ከጁ ቢያጣ በእድር፣ በሃይማኖት ሥፍራ፣ በጎዳና ነጠላ አንጥፎ የሰው ፊት እንደ እሳት እየገረፈው ለምኖ የተጠየቀውን ገንዘብ አሟልቶ ይዞ የሄደ ጭምር የሚታገተው ጊዜው በመክፋቱ ወይስ በመቀየሩ ነው? ይልቁንም እኛ ሰዎች ሳጥናኤል እራሱ የሚቀናብን ክፋተኞች፣ ግብዞች፣ ነፍሰ በላዎች በመሆናችን ነው። ይህንን መራራ ሐቅ እየመረረንም ቢሆን መቀበል አለብን።
እስኪ ንገሩኝ በዓይን እንኳን ሞልቶ ለማየት የምታሳሳ የሰባት ዓመት እምቦቃቅላ ሕፃን ልጅን፤ አፍና አፍንጫዋን አሸዋ ጠቅጥቆ አይሆኑ አድርጎ ደፍሮ ለመግደል ያስቻለው እውን ጊዜው ወይም ዘመኑ በመቀየሩ ነው? አይደለም ወዳጄ አትሸወድ። እውነታው እኛ ሰዎች ከሰውነት ውሃ ልክ በመውረዳችን ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ በየዘመናቱ የተነሱባት ጠላቶቿ ቅጥሯን ጥሰው፣ ድንበሯን አልፈው ካደረሱባት/ብን ሁለንተናዊ ኪሳራ በላይ በርስ በርስ ጦርነት ያወደምነው ንብረት፤ ያጣነው የእልፍ የዜጎች ሕይወት ይበልጣል። ለዚህ ደግሞ እርቀን ሳንሄድ ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት የወደመው ንብረት፣ የጠፋው የሰው ልጅ ሕይወት ሕያው ምስክር ነው።
ስለዚህ ሰው በዚህ ልክ ከሰውነት ተራ ወርዶ ወንድም ወንድሙን እየገደለ፣ እያፈናቀለ፣ እያሰደደ፣ አግቶ ገንዘብ እየተቀበለ፣ ሕፃናትን በጭካኔ ደፍሮ እየገደለ፣ እህት ወንድሙን በቁም ለመቅበር ሴራ እየጎነጎነ … ቀኑ ተቀይሯል፣ ጊዜው ከፍቷል፣ ዘመኑ ተለውጧል ሊባል አይገባም። ይልቁንም ዘመኑን ዘመነ ፍዳ፣ የደም ዘመን፣ የደም ምድር፣ የግፍ መሬት … ያደረግነው እኛው እራሳችን ነን። ምክንያቱም ዘመኑ የሚመስለው እኛን ነው።
ዘመኑ ሳይሆን እኛ እንደተቀየርን፣ ከሰውነት ተራ እንደወረድን አውቀን እራሳችን ልንፈትሽ ይገባል። የራቀን ሠላም እንዲመለስ፣ የከበበን ችግር ሁሉ ከላያችን እንደጉም ተኖ እንዲጠፋ፣ ሠላም በሀገራችን እንዲፀና፣ እድገት ልማት እንዲመጣ፣ እንደጥንት አባቶቻችን ፍቅርና አንድነት በመሐላችን እንዲጎለብት ሁሉም ጣቱን ወደሌላው ከመቀሰር ይልቅ እራሱን ሊያይ ይገባል። ሁሉም ከእኩይ ምግባሩ መታረም አለበት።
“ቀናት እየሮጡ ነው፣ ዓመታቱም እየነጐዱ ነው። ከዚህ ምድር የማልፍበት ቀን እየቀረበ ነው” ብለን እስኪ ሁላችንም እናስብና በአቅማችን የሠላም፣ የተድላ፣ የፍቅር፣ … ዘመን በሀገራችን እንዲመጣና የተሻለች ሀገር ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ “እንደ አቅሜ ምን እያደረግሁ ነው?” ብለን እራሳችንን ቆም ብለን መጠየቅ አለብን። ዘመናችንን እንደ ቀድሞው ደጉ ጊዜ እናድስ። ከክፉ ሥራ ተቆጥቦ ደግ ደጉን በመሥራት ዘመኑን እንዋጀው!
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም