በተፈጥሮ ፀጋ ከታደሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ የሆነው የምዕራብ ኦሞ ዞን የማጂ ወረዳ፤ መሬቱ የዘሩበትንና የተከሉበትን የሚያበቅል ለም መሆኑን ለመቃኘት ዕድሉን አግኝተናል። አካባቢው ላይ የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኙ እንደ ቡና፣ ሰሊጥ የመሳሰሉ ልማቶችን በስፋት ማከናወን የሚያስችሉ እድሎች መኖራቸውን አረጋግጠናል። መሬቱ አልሚ ካገኘ ሳይሰስት እንደሚሰጥ ያስታውቃል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ልማት የናፈቃቸው ከመሆናቸው ባሻገር፤ የእናልማ ጥሪም አቅርበዋል።
እንዲህ ያለውን እድል ቀድመው ከተጠቀሙ ኢንቨስተሮች መካከል በላይነህ ክንዴ ይርት ሸለቆ እርሻ ልማት ድርጅት አንዱ ነው። የድርጅቱ ባለቤት ባለሃብቱ በላይነህ ክንዴ ናቸው። ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ በሰፋፊ የእርሻ መሬት ላይ የልማት ሥራዎችን በማከናወን፣ የዘይት ፋብሪካ ከፍተው የምግብ ዘይት ለገበያ በማቅረብና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራቸው ይታወቃሉ። በዚህ ሰፊ የኢንቨስትመንት ሥራቸውም ለዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል። ለሀገርም የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሀገር ባለውለታነታቸውን እያሳዩ ናቸው።
እኛም በኦሞ ዞን ተገኝተን በአካባቢው ከሚካሄዱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ የሆነውን የበላይነህ ክንዴ ይርት ሸለቆ እርሻ ልማት ድርጅትን ቃኝተናል። የባለሀብቱ አንዱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የሆነው ይህ ድርጅት የኢንቨሰትመንት ፈቃድ ወስዶ የልማት ሥራውን የጀመረው በ2006 ዓ .ም ሲሆን፤ በወቅቱ ወደ ልማት የገባው ወደ 250 ሺህ ሄክታር መሬት ተረክቦ ነበር። ድርጅቱ በተረከበው መሬት ላይ ቡናን ጨምሮ የሰብልና የሰሊጥ ልማቶችን በማከናወን ውጤታማነቱን ማረጋገጥ ችሏል።
በየጊዜውም የማስፋፊያ ፈቃድ በመጠየቅ የሚያለማውን የእርሻ መሬት ማሳደግ ችሏል። ልማቱንም ለማሳደግ በየጊዜው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ወደ ተቀናጀ የግብርና ኢንቨስትመንት ለመሸጋገር በሚያስችለው ደረጃ ላይ እንዲገኝ አስችሎታል። ድርጅቱ አሁን እያከናወነ ካለው የሰብልና የቡና ልማት በተጨማሪ፤ የእንስሳት እርባታንም ለማካተት ማቀዱን ለማወቅ ችለናል። ለእቅዱ ማስፈጸሚያም ተጨማሪ 10ሺህ ሄክታር መሬት ለማስፋፊያ ሥራ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ ይገኛል። እቅዱን ከግብ ለማድረስ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቅቋል። በተወሰነ ደረጃም ከእቅዱ የጀመራቸው ሥራዎች ይገኛሉ።
በልማት ስፍራ ተገኝተን የቡና እና የበቆሎ ልማትን ቃኝተናል። እንዲህ ያለው ልማት ከመከናወኑ በፊት አካባቢው ዘመናትን የተሻገረው ጫካ ሆኖ እንደነበር ወደኋላ መለስ ተብሎ ሲታወስ፤ ልማቱ መዘግየቱ ቁጭትን ይፈጥራል። የማልማት አቅም ያለው ሲያገኝ ግን ከፈጠረው ሀብት በተጨማሪ የአካባቢውንም ገጽታ ቀይሮታል። ማልማት ይቻላል የሚለውንም አስተሳሰብ በአካባቢው ነዋሪ ላይ ፈጥሯል። የልማትን ጥቅም ለማጣጣም ዕድል ሰጥቷል። አሁንም ብዙ ለልማት ሊውል የሚችል በጫካ የተከበበ መሬት በመኖሩ እንደ ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ የፈርቀዳጆቹን አርአያ ተከትሎ በልማቱ መሳተፍ የሚቻልበት እድል አለ።
እኛ በተገኘንበት ማጂ ወረዳ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ወደ 85ሺህ ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ምቹ ተደርጓል። ለቡና፣ ለሰሊጥ፣ ለሩዝ፣ ለበቆሎና ለተለያዩ ኢንቨስትመንት ዝግጁ የተደረገው መሬት ላይ ለማልማት ፍላጎት ያሳዩ ባለሀብቶች እንዳሉም ሰምተናል። አካባቢው ላይ ቀድመው ወደ ሥራ የገቡት ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ ብቻ ሳይሆኑ፤ የድርጅቱ ሠራተኞችንም የልማቱ አጋር አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
በድርጅቱ ውስጥ በቋሚነትና በጊዜያዊነት ተቀጥረው እየሰሩ የሚገኙት በተለያየ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ናቸው። በተለይም ወጣቶች የከተማ አኗኗር ሳያማልላቸው ከከተማ በብዙ ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ስፍራ የግብርና ሥራ ላይ መገኘታቸው ለሥራ ያላቸውን ዝግጁነት ያሳያል። ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በሙያቸው በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞችም ለሥራው ከፍተኛ ጉጉት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሠራተኞቹ መብታቸውን ለማስከበር፣ ግዴታቸውንም ለመወጣት በማህበር ተደራጅተው ለመንቀሳቀስም ጅማሬ ላይ እንደሆኑ ማስረጃዎችን አግኝተናል። የሠራተኞች በማህበር የመደራጀት መብት ጥያቄ ብዙ እንቅፋት በሚገጥመው በዚህ ጊዜ ለዚያውም ገና ልማቱ ባልተስፋፋበትና ባላደገበት አካባቢ እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ መኖሩ ለሌሎችም በአርአያነት የሚጠቀስ በመሆኑ ይበል የሚያስብል ነው። በድርጅቱ የነበረንን ምልከታ በዚህ መልኩ ከቃኘን በኋላ ከምሥረታው ጀምሮ ስላለው እንቅስቃሴና የድርጅቱን የወደፊት እቅድ እንዲሁም ድርጅቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለያየ መንገድ እያደረገ ስላለው አበርክቶ፣ የፈጠረው የሥራ እድልን በተመለከተ የበላይነህ ክንዴ ይርት ሸለቆ እርሻ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ከአቶ አብረሃም አያሌው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ፡-
አዲስዘመን፡- በቅድሚያ በላይነህ ክንዴ ይርት ሸለቆ እርሻ ልማት ድርጅት በአካባቢው ኢንቨስትመንት የጀመረበትን ሁኔታ እና በአጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴውን ይግለጹልን?
አቶ አብረሃም፡- በቅድሚያ ድርጅቱ ለልማቱ የተረከበው አካባቢ ላይ ምንም አይነት የልማት ሥራ አልነበረም። ጫካ ነበር። መሬቱን ከተረከብን በኋላ ግን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል በማሰማራት ጫካውን መንጥረን ለልማት ዝግጁ እንዲሆን አድርገናል። ድርጅቱ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስዶ ወደ ሥራ የገባው ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ወደ ሥራ የገባው 250 ሄክታር መሬት ተረክቦ ነው። በተረከበው ማሳ ላይ ልማቱን በማጠናከር ከዓመት ዓመትም ለውጦችን በማስመዝገብ በየጊዜውም ለኢንቨስትመንት ማስፋፊያ መሬት በመጠየቅ ደረጃ በደረጃ ሥራውን እያሳደገ ይገኛል። አሁን ላይ በአጠቃላይ የመሬት ይዞታውን ወደ 2 ሺህ 750 ሄክታር በማድረስ ሰፊ የልማት ሥራ በማከናወን ላይ ነው።
ድርጅቱ በዋናነት የተሰማራው በቡና እና ዓመታዊ የሰብል ልማት ላይ ሲሆን፤ ሰሊጥ፣ አኩሪአተር፣ ማሾ ያመርታል። ምርቶቹም በጥራት ተመርተው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ናቸው። ከዘር አባዢ ድርጅቶች ጋር ውል በመግባት የዘር ብዜት ላይ በቆሎና ማሽላ ላይ ይሰራል። በተጨማሪ ለሀገር ውስጥ ገበያም ሩዝና በቆሎ ያመርታል። በቀጣይ ድርጅቱ ኢንቨስትመንቱን ወደ ተቀናጀ የእርሻ ሥራ ከፍ በማድረግ በሀገር ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የረጅም ጊዜ እቅድ ነድፏል። በዚህ የተቀናጀ የእርሻ ሥራ እንስሳት ማድለብና ንብ ማነብን ያካተተ ሲሆን፣ ለእቅዱ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግም የበግና ከብት እርባታ በመጠኑ ጀምሯል። እቅዱን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር የሚያስችል ሥራ እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ ኢንቨሰትመንቱን ወደ ተቀናጀ የእርሻ ሥራ ከፍ ለማድረግ እየተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸውልኛል። እቅዱ የምርቱን መጠን መጨመር ብቻ ነው ወይስ እሴት የተጨመረበትን ምርት ለገበያ ለማቅረብ ነው?
አቶ አብረሃም፡- እቅዱ ሰፊ ነው። ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ፣ ልማቱን በሚያከናውንበት ቦታ ላይ እሴት የተጨመረበት ምርት በማምረት ለውጭና ለሀገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ እቅድ አለው። አጠቃላይ እቅዱ ቡናን አጥቦና አበጥሮ ሁሉንም ሥራ በልማቱ ስፍራ አጠናቅቆ ለገበያ ለማቅረብ ነው። ለዚህም ቡናን ከማጠብ ጀምሮ ያለውን ሂደት የሚያከናውን ማሽን ይተክላል። ድርጅቱ እያከናወነ ያለው የዘር ብዜት ሥራ ላይም ለውጥ ለማድረግ አቅዷል።
ቀደም ሲል ከዘር አባዥ ድርጅቶች ጋር ውል በመግባት ዘር አባዝቶ ለማቅረብ ሲሰራ ነበር። በቀጣይ ግን በእቅዱ ያካተተው የዘር ብዜት ፈቃድ ወስዶ በራሱ ድርጅት ውስጥ ዘር እያባዛ እስከ ስርጭት ያለውን ለመስራት ነው። እስካሁን እያከናወነ ባለው የዘር ብዜት ሥራ የአካባቢውን አርሶ አደር እያሳተፈ ይገኛል። በራሱ ድርጅት ውስጥ ማከናወን ሲጀምር ደግሞ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የበለጠ ያጠናክራል።
ድርጅቱ ላቀደው የተቀናጀ የእርሻ ኢንቨስትመንት ሥራው፤ 10ሺ ሄክታር መሬት ኢንዲፈቀድለት ለክልሉ ጥያቄ አቅርቧል። ድርጅቱ ላቀደው ሥራ ምቹ የሆነ ቦታም ስለሚያስፈልገው ይሄም ግምት ውስጥ እንዲገባ ጭምር ነው ክልሉን የጠየቀው። ጥያቄው ምላሽ እንዳገኘም እቅዱን ለማሳካት ፈጥኖ ወደ ሥራ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ በአካባቢው ላይ እያከናወነ ባለው የእርሻ ልማት ለአካባቢው ነዋሪዎች የፈጠረው የሥራ ዕድል እና ተጠቃሚነታቸው እንዴት ይገለጻል?
አቶ አብረሃም፡- ድርጅቱ የሥራ ዕድል ቅድሚያ የሚሰጠው ለአካባቢው ነዋሪዎች ነው። ቀጥሮ እያሰራ የሚገኘውም በቋሚ የሥራ መደብና በጊዜያዊነት ነው። አንዳንዴ የሰው ኃይል እጥረት ያጋጥማል። በዚህ ጊዜ ከሌሎች አካባቢዎች የሰው ኃይል አምጥቶ በጊዜያዊነት ያሰራል። ከተጠቃሚነት አንጻር ቀደም ሲል አካባቢው ላይ ምንም አይነት የልማት ሥራ ባለመኖሩ ወጣቶች እንዲህ ያለውን እድል አያገኙም ነበር። ይህ ድርጅት መኖሩ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የቴክኖሎጂ ሽግግር መኖሩ የተለያየ እውቀት እንዲያገኙ አግዟቸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ለኢንቨስትመንት እጅግ ምቹ ነው። አካባቢው ላይ ለተለያየ ልማት የሚውል ሰፊ የእርሻ መሬት አለ። ይህም ለወጣቶችም ሆነ ለሌላው ሕብረተሰቡ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል። የጠየቅነው የማስፊፊያ መሬት ተፈቅዶ በሰፊው ወዳቀድነው ሥራ ስንገባ አሁን በቋሚነት ከያዝናቸው ሠራተኞችና በጊዜያዊነትም በመቅጠር ከምናሰራቸው በተጨማሪ ለሌሎችም የሥራ እድሎችን እንፈጥራለን። በተለይም በእርሻ ሥራ ዝግጅት፣ በአረም ጊዜ፣ በሰብል ስብሰባ፣ ቡና ለቀማና ለሌሎችም ወቅታዊ ሥራዎች በሚበዙበት ወቅት በጊዜያዊነት የሚፈጠረው ሥራ ሰፊ በመሆኑ ከአካባቢውም አልፎ ከሌሎች አካባቢዎች ሰራተኞችን የማስመጣት ሁኔታ ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡- አንድ ድርጅት በአንድ አካባቢ ኢንቨስት ሲያደርግ አካባቢው ላይ የመጠጥ ውሃ፣ የመንገድ ሥራና ሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶች የማቅረብ ኃላፊነት እንዲወጣ ይጠበቃል። ከዚህ አንጻር በላይነህ ክንዴ ይርት ሸለቆ እርሻ ልማት ድርጅት የተወጣቸው ኃላፊነት ካለ ይግለጹልን
አቶ አብረሃም፡- የአካባቢ ድጋፍ በተለያየ መልኩ ይገለጻል። በተለይ አርሶደሩን በማገዝ በኩል እየሰራን ነው። የቡና ችግኝ ሲፈልግ በነፃ እንሰጣለን። የትራክተር ሜካናይዜሽን ለአርሶ አደሩ እንዲቀርብ ከዞንና ከወረዳ ደግሞ ጥያቄዎች ሲቀርቡም በመቀበል እንደግፋለን። ሌላው ከፀጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ ድርጅቱ የሚያደርገው ድጋፍ ነው። በዚህ በኩል እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ አርሶ አደሮች የተለያዩ ተሞክሮዎችን እያገኙ በመሆኑ የአመራረት ዘዴያቸውን እያሻሻሉ ነው። አንዳንዶችም ድርጅቱ ከሚያመርተው ምርት ባልተናነሰ ማምረት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ያላቸው ፍላጎትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው። በድርጅቱ አማካኝነት በአርሶ አደሩ በኩል መነቃቃት መፈጠሩና ለውጥ መምጣት መጀመሩ ለድርጅቱም ቢሆን ኃላፊነቱን መወጣቱን ከማሳየት ባለፈ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ተቋም ደስታ ይሰማዋል። ወደፊትም ቢሆን ለአርሶ አደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል። ድርጅቱ ማህበረሰቡ ለሚያስፈልገው ድጋፍ ሁሉ በሩ ክፍት ነው።
በላይነህ ክንዴ ይርት ሸለቆ እርሻ ልማት ድርጅት አካባቢው ላይ በልማት ሥራ ከመሰማራቱ በፊት አካባቢው ላይ ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት ነበር። በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች መኖሪያቸውን እየለቀቁ ወደ ሌላ አካባቢ ይሄዱ እንደነበር ከአካባቢው መረጃዎችን አግኝተናል። ድርጅቱ አካባቢው ላይ የእርሻ ልማት ሥራ ከጀመረ ወዲህ ግን ሰዎች ተረጋግተው በቀያቸው መኖር ጀምረዋል። የግብርና ሥራቸውንም ሆነ የእንስሳት እርባታ በሰላም እያከናወኑ ይገኛሉ። የፀጥታ ስጋቱም እየቀነሰ ነው። እንዲህ ያለ ለውጥ የመጣው ድርጅቱ የሠራዊት አባላት ቀጥሮ የአካባቢው ደህንነት እንዲጠበቅ በማድረጉ ነው። በተጨማሪም ከመንግሥት አካላትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት በጋራ በመሥራት የበለጠ ሰላም እንዲረጋገጥ እያደረገ ይገኛል። ድርጅቱ በዚህና በተለያየ መንገድ ለአካባቢው ማህበረሰብ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎችም ከነበረባቸው ፀጥታ ሥጋት እፎይታ ማግኘታቸውን ለድርጅቱ በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተሰራው ሥራ አንፃራዊ በሚባል ደረጃ የፀጥታ ችግርን ማሻሻል ተችሏል። ሆኖም ግን አሁንም በፀጥታ ዙሪያ ሥራዎች ይሠራሉ። በላይነህ ክንዴ ይርት ሸለቆ እርሻ ልማት ድርጅት የሚገኘው ሱሩማ፣ ማጂና ኬሻ ወረዳዎች መካከል ነው። በሶስቱም አዋሳኝ ወረዳዎች በኩል በተለያየ ጊዜ ግጭቶች ይነሳሉ። ችግሩ በቀጥታ ድርጅቱን ባይነካም አለመረጋጋቱ ግን የድርጅቱን ሥራ እየረበሸው ነው። ድርጅቱ የሚገኘው መተላለፊያ ላይ ስለሆነ በሚፈጠረው ችግር ሠራተኞች ተረጋግተው እንዲሰሩ እያደረጋቸው አይደለም፤ ይሰጋሉ። ስጋቱ የሰው ኃይላችን ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ነው።
ወረዳዎቹ አብዛኞቹ አርብቶ አደሮች የሚገኙባቸው ናቸው። ከአካባቢው ባገኘነው መረጃ መሠረት የቁም እንስሳት እና የትጥቅ መሣሪያ ይፈልጋሉ። ይሄን አብዝተው የሚፈልጉት በአካባቢው ባህል መሠረት ለጋብቻ ጥሎሽ የሚሰጠው እንስሳና መሣሪያ በመሆኑ ነው። እነዚህ ለጥሎሽ የሚያስፈልጉ ነገሮች ደግሞ በቀላሉ አይገኝም። የሚወስዱት አማራጭ ከብቶችን በኃይል ቀምቶ መውሰድ ነው። በዚህ ግጭት ይፈጠራል። ለዚህ መፍትሄ ለመስጠትም በጣም አስቸጋሪ ነው። በርግጥ ከወረዳና ከቀበሌ አመራሮች ጋር አብረን እየሰራን ነው። አካባቢው እንዲለማና እንዲያድግ ፍላጎቱ ስላላቸው በተቻለ መጠን ድርጅቱ ላይ ምንም አይነት ተጽእኖና እንቅፋት እንዳይኖር በሚችሉት ሁሉ እያገዙን ናቸው። የፀጥታው ሁኔታ ሲያይልም የፀጥታ አካላትን በመመደብ ጭምር ድርጅቱን የመታደግ ሥራ ይሰራሉ። ያላቸውን የልማት ፍላጎት የሚያሳዩት በተግባር ነው።
አዲስዘመን፡- ድርጅቱ በሥራ እንቅስቃሴው የተለያዩ ውጣ ውረዶችን እንደሚያሳልፍ ይታወቃል። በሥራው የገጠመው ተግዳሮት ምን ነበር? እንዴትስ ተሻገራቸው?
አቶ አብረሃም፡– ድርጅቱ አካባቢው ላይ መኖሩ የአካባቢውን ማህበረሰብ በሥራ እድልና በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ አድርጓል። ጥቅሙንም በተግባር እየታየ በመሆኑ ለድርጅቱ ሕልውና ተቋሙ ብቻ ሳይሆን፤ የአካባቢው ማህበረሰብና አስተዳደር ጭምር ዘብ መቆም አለበት ብዬ አምናለሁ። ሕብረተሰቡ ከድርጅቱ ጎን ሲሆን፣ ድርጅቱም ሥራውን ያስፋፋል፤ ያሳድጋል። ድርጅቱ ሲያድግ ደግሞ የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት በዚያው ልክ ይጨምራል። ስለዚህ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታትና መፍትሄ በመስጠት በጋራ መሥራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።
ችግሩ በከፍተኛ ደረጃ በድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል ብሎ ለመግለጽ ሳይሆን ግንዛቤ በመፍጠር በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉ ጉዳዮችን ግን ማንሳት እፈልጋለሁ። አንዳንዴ ውስን በሆኑ ግለሰቦች አላስፈላጊ ጣልቃገብነት ይስተዋላል። ነገሩም ለመተባበር ፈቃደኛ ካለመሆን ጋር ይያያዛል። ለምሳሌ በድርጅቱ ክልል ውስጥ አንዳንድ አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ይስተዋላሉ። ለአብነት በድርጅቱ ክልል ውስጥ በግለሰቦች የሚከናወን የንብ ማነብ ሥራ ነበር።
ድርጅቱ ለሥራ የሚጠቀምባቸው ትራክተርና የተለያዩ ማሽኖች በሚነሱበት ወቅት ንቦች ከቀፎአቸው በመውጣት የሚያስቸግሩበት ሁኔታ ይፈጠራል። ለሥራው እንቅፋት በመሆኑ ይሄ ከድርጅቱ ክልል ውስጥ እንዲወጣ ጥያቄ በሚቀርብበት ወቅት ጥሩ ምላሽ አልነበረም። ነገሩን ቀለል አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ግን ደግሞ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ስለሚኖሩ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
ሌላው ሊስተካከል ይገባል ብዬ የማነሳው እገዛ ወይም ድጋፍ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን የተመለከተ ነው። አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ድርጅቱ ከተሰማራበት የልማት ሥራ ጋር የሚያያዝ ወይም የሚገናኝ አይደለም። ከፍ ባለ ወይም በክልል ደረጃ መቅረብ ያለባቸው ጥያቄዎች ታች ባለ መዋቅር ወይም በአካባቢና በግለሰብ ደረጃ ጥያቄው ይቀርባል። እንዲህ ያለ ጥያቄ የሚያቀርቡም በመንግሥት ድጋፍ አግኝተው ባለመሆኑ ጥያቄያቸው ከድርጅቱ አሰራር ጋር ይቃረናል። ድርጅቱ የተለያዩ ወጪዎችን ለማድረግም ሆነ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ወደ ሥራ የሚገባው ዓመታዊ እቅድ አውጥቶ ነው። በዓመታዊ እቅድ ውስጥ ያልተካተቱና ያልተጠበቁ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ምላሽ ለመስጠት ያስቸግራል። ጥያቄዎቹ ቀድመው ከታወቁና ድርጅቱ አምኖበት የሚፈጽመው ከሆነ የእቅዱ ኣካል ሊያደርገው ይችላል።
አርሶአደር ወይም በማህበር ተደራጅተው ወደ ልማት የሚገቡ ወጣቶችን በቡና ችግኝ፣ በሰብል ዘር፣ በግብርና ሜካናይዜሽን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው። ይሄም ጥያቄ ሲቀርብ ከእርሻ ሥራችን ጋር የተናበበ ቢሆን የተሻለ ነው። ለምሳሌ የቡና ችግኝ ቢፈልጉ መጠየቅ ያለባቸው ከተከላ ወቅት በፊት ነው። ምክንያቱም የድጋፍ ሥራውን የሚያከናውነው ችግኙን ከድርጅቱ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ከወረዳና ቀበሌ የግብርና የልማት ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት ነው። በዚህ የድጋፍ ሥራ የመሬት ዝግጅትን ጨምሮ በተከላው ወቅት መደረግ ሥላለባቸው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችና ተከላው ከተከናወነ በኋላ ደግሞ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያደርጉ በሥልጠናና በተግባር ይታገዛሉ። በዚህ የተደራጅ አሰራር በእቅድ መንቀሳቀስ ከተቻለ ድጋፍ የተደረገላቸው አርሶአደሮችም ሆኑ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ውጤታማ ይሆናሉ። ከዚህ ቀደም ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ተሞክሮ ውጤታማ ያልሆኑ አጋጥመዋል። የተደራጀ አሰራር ግን ብክነትን ያስቀራል። ስኬትም ለማስመዝገብ ያግዛል።
አዲስዘመን፡- በላይነህ ክንዴ ይርት ሸለቆ እርሻ ልማት ድርጅት በአካባቢው ላይ ግንባር ቀደም የግል አልሚ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ አብረሃም፡- እርግጠኛ ሆኜ በአካባቢው ላይ ብቸኛ ድርጅት ነው ለማለት አልደፍርም። ነገር ግን ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅቱ በሚገኝበት ወረዳ ውስጥ ከእርሱ በፊት በልማት የተሰማራ ድርጅት የለም። ወደ ልማት ሥራ የገባው ጫካ መንጥሮ ነው ። ለነበረው የፀጥታ ችግር የመፍትሄ አካል በመሆንና ችግሩንም በመቋቋም ሲሠራ ቆይቷል። ልማቱ ከከተማ በጣም የወጣ አካባቢና መሠረተ ልማትም ያልተሟላበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሰው ኃይልም ለማግኘት ከባድ የሆኑ ፈተናዎችን በመጋፈጥ፣ ለነበረው የፀጥታ ችግርም የመፍትሄ አካል በመሆንና ችግሩንም በመቋቋም አሁንም እየሰራ ይገኛል።
የተለያዩ ተግዳሮቶችን በመቋቋም የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኘው እንዲህ ተቋቁሞ ነው ። በሀገር ደረጃ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ላይ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለልማት ሥራ በተሰማራበት አካባቢ ላይ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የአርሶአደሩ የግብርና ሥራ እንዲሻሻል በማስቻል፣ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ በቴክኖሎጂ ሽግግር በሚችለው ሁሉ እያደረገ ባለው እገዛ ለውጥ ማምጣት ችሏል። በሌሎችም ድጋፎች እያደረገ ያለው እገዛ ባለሀብቱ ለልማት ያለውን ቁርጠኝነትና የዜግነት ድርሻውን ለመወጣት ያለውን ጥረት ማሳያዎች ናቸው። ድርጅታንም ከዚህ የበለጠ ለመስራትም ዝግጁ ነው።
አዲስዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።
አቶ አብረሃም፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም