ጥቅምት ሲመጣ፣ ጥቅምት ሲታሰብ ፊት ድቅን ከሚሉት የትውስታ ምስሎች አንዱ የጥቅምት አደይ አበባ ነው።የወርሃ ጥቅምት መልክ በጎበዝ ሰዓሊ ቢሳል ፊቷ እንደ ጸሐይ የሚያበራና ዓይነ ኩሉ የውበት ገንቦ ነው።ሀምራዊው የቀሚሷ ዘርፍ ከንፋሱ ጋር የሚምነሸነሽ ጸአዳ ነው።ዞማው ሀር ጸጉሯ በጀርባዋ ተነስንሶ ሲዘናፈል እንኳንስ ፊቷ የቆመውንና ከኋላዋ ያለውንም ታስከትላለች።መዓዛዋ የአደይ አበባ፣ ውበቷም ከአደይ አበባ ነው።አደይ አበባ ማራኪ የተፈጥሮ ውበትን ተጎናጽፎ የሚያጎናጽፍ ዘለዓለማዊ የጥቅምት ሽልማት ናት።ከውበት ውበቷን፣ ከሽልማት ሽልማቷን ስትቸር ደግሞ ሁሉም የተለየ ይሆናል።በዚህች የውበት ቁና የጥበብ ጎተራ ከሙላት አይጎድልም።ማድጋዋ በጥበብ በረከት፣ አቁማዳዋ በጠቢባን አንገት ላይ ነው።የኪነ ጥበብ ቤተሰቦችም ውበቷን የሚመጥን አንዳች ነገር ከጥቅምት ይጠብቃሉ።
ዛጎላማይቱ አንች የጥቅምት አበባ፤
የአደይ መዓዛ የሳሮን የሳባ፤
ምንኑ ታመጪልኝ ይዤሽ እንድገባ!
ቶሎ ቶሎ ነይ ቶሎ በጥቅምቱ፤
ጉማ ብትዪማ ቆመሽ ከዳገቱ፤
እጠብቅሻለሁ ይዤልሽ ካጥንቱ።
ያሏት እንደሆን በጥቅምት አበባ አምራና ተሞሽራ የወጣች ገራገር ጥበብ አትጨክንም።ከላይ እግዜር በጥበቡ የሸለማት ጥቅምትም አክብራ “ኑ! በእግዜር” ብላ የጥበብን እንግዳ ለመቀበል ወገቧ ጎንበስ፣ ቀና፣ እልል ብሎ የሚታክታት አይመስለኝም።በውበት ትሞሸራለችና አሁን ደግሞ እሷ ራሷ ጠቢባኑን ሞሽራ ልትሸልም ነው።
በጥበብ ሠረገላ በጠቢባን ፈረስ ሲጓዝ ዘንድሮ ከአሥረኛው የቁጥር ኮቴ ላይ ደርሷል።አሥረኛውም የጉማ ሽልማት አበባውን እንደታቀፈ ሠረገላው ከወርሃ ጥቅምት ላይ ቆም ለማለት ፈቅዷል።በኪነ ጥበብ ቤት በጥበብ ሥራዎቻቸው ድንቅ ድንቁን ያሳዩን፤ እንዲሁም ያስደመጡን ቀርበው ከአበባው ልዩ ስጦታ ይቀበላሉ።ጥበብ ስስትን አታውቅምና ለሰጡ ይሰጣቸዋል።በጉማ 2017 ታላቅ ገጸ በረከቶች ከአዳዲስ ነገሮች ጋር ስለመድረሱ አዘጋጆቹ ከወዲሁ እወቁት ሲሉ ሀሳብና እቅዳቸውንም አጋርተዋል።ማመን ከማየት ነውና አይተን፣ ተመልክተን፤ እሰይ! ደግ አደረጋችሁ እንድንል ወርሃ ጥቅምት ደርሳ ትዳኘን በማለት በጉዳዩ ዙሪያ ጥቂት በሀሳብ እንድንሸራሸር በዘመን ጥበብ ግብዣ ይሁን።
መነሻችን ከወደ ጉማ አዘጋጆች የሰማነው ነገረ ዓለም ነው።ጥበብ መቼ መቼ ይሆን በደስታ ሀሴት የምታደርገው … ከተባለ አንድም በዚህ ነገረ ዓለም ውስጥ ነው።ልጆቿ ከእርሷ የሚቀበሉትን ያለስስት ሲሰጡ በደስታ እንደምትፍነከነከው ሁሉ በምላሹ ለሥራቸው ዋጋ ሲሰጣቸውም በሀሴት ትሞላለች።እኚህን ልጆቿን ለአበርክቶዋቸው ትልቅ ቦታ በመስጠት በየዓመቱ ከፍ ሲያደርጋቸው አሥር ዓመታትን የዘለቀው ደግሞ የጉማ ሽልማት ነው።አንድ ብለው በመጀመር ዘጠኝን ፉት! አድርገው አሁን ለአሥረኛው ስንድትድት ማለት ጀመርዋል።ቤቱ የስንዱ እመቤት ሳሎን መስሏል።ከአንደበታቸው የሰማነው ነገርም፤ ሁሉንም ቅድመ ዝግጅቶች አጠናቀው “ጥቅምት 8″ን እንደሚጠብቁ ነው።በጥቅምት 8 ባለ ሥራዎች በሥራዎቻቸው ከፍ ይላሉ።ላደረጉት ጥበብ ውላታቸውን ትመልሳለች።“እነማን ናቸው?″ ለሚለው ጥያቄም፤ የዘንድሮዎቹ የጉማ አደይ አበባዎች ተመርጠው ተለይተዋል።
ምርጫው ግን እንዴትስ ይሆን? እውን ከስር መሠረቱ አስሰው በትክክል የሚገባውን ሰው መርጠው ይሆን? የምትለው መሠረታዊ ጥያቄ ናት።ብዙ ጊዜ እንዲህ እንደ ጉማ ለሽልማት በተሰናዱ ተቋማት ውዝግቦች፤ አለፍ ሲልም ዱላ ቀረሽ አታካራዎች ሲከሰቱ እዚሁ በሀገራችንም፣ በውጪዎችም ዘንድ አስተውለናል።ታጭተው ለሽልማቱ እመድረክ ላይ የሚቆሙ አካላት በውድድር ሳይሆን በመራጮች የሕሊና ሚዛን ላይ ተመርኩዞ ነው።
የመራጩ ሕሊና ሚዛኑን ባይስት እንኳን የሚመዝነውን ግለሰብ ማግኘቱ ላይ ሊፈተን ይችላል።እንደ ሦስተኛ ደግሞ የችሎቱ ዙፋን ላይ የተፈናጠጠው ዳኛ እይታና የኛ እይታ፣ የእርሱ ጀግናና የእኛ ጀግና በመሀከል ሊተላለፉ ይችላሉ።“ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት…” በማለት ሁሉንም ጉዳዮች ከጥያቄ በራቀ ገመድ ላይ ባናሰጣውም እኚህን ውል አልባ መስፈርቶችን ግን በቅንነት ልንገነዘባቸው ይገባል።ከዚሁ ጋር ያለፈውን ለማስታወስ ያህል አምና ጉማ 2016 መዘለሉንና አለመኖሩን ልብ ይለዋል።
9ኛው የጉማ ሽልማት የተካሄደው ሰኔ 2015 ዓ.ም ነበር።በስካይላይት በተደረገው በዚሁ ሽልማትም የ9ኛው የጉማ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የነበረው አንጋፋው አርቲስት ኪሮስ ኃይለሥላሴ፤ በሄርሜላ ደግሞ የአቢሲኒያ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት መስራች ወይዘሮ ገነት ከበደ፤ እንዲሁም በአርአያ ሰብ ከያኒ (በበጎ አድራጎት በሚሰሩ የጥበብ ሰዎች) አርቲስት መሠረት መብራቴ ነበረች።ዘንድሮስ እነማን ይሆኑ …?
በጉማ 2017 ወሳኙና መሠረታዊው ነገርም ይኼው ነው።እነ ማን ምን ሠርተው ተመረጡ? ማለት ደግ ነው።በጉማ ለሚሠሩ ማበረታቻ ብቻ ሳይሆን ሠርተው ላለፉትም ለቀሪ እድሜ የተስፋ ስንቅ የሆነው “የሕይወት ዘመን” ሽልማት መኖሩ ገሀድ ነው።እድሜ ዘመናቸውን በጥበብ ስኬት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጥበብ ሀሩርና ብርድ፣ በኮረኮንቹና ድቅድቅ ጭለማው ሁሉ አልፈው ዛሬ ላይ “አንቱ” ለተባሉት የክብር ጋቢን ይደርባል።
በዚህ መንገድ ላይ እናቶችም አባቶችም ቢኖሩም ሽልማቱ ግን አንድ ነው።ታዲያ የጾታውስ ጉዳይ ከምን መስፈርት ላይ ገብቶ? ቢሉም ጾታው ከመስፈርት መግቢያ የለውም።እንደጊዜውና ሁኔታው ለሚገባው ቅድሚያ ይሰጥበታል።ተራቸውን ጠብቀው ለየዓመቱ የሚጠባበቁ ገና እልፍ አደይ ጉማዎችና አበይ ጉማዎች አሉ።የዘንድሮው የ10ኛው ጉማ የሕይወት ዘመን ተሸላሚዋ አደይ ጉማ ደግሞ ድምጻዊትና ተዋናይት ፍቅርተ ደሳለኝ መሆኗ ተነግሯል።
ቀደም ሲል በጅምር ድምጻዊት ቀጥሎና አሁን ደግሞ ተዋናይት በመሆን ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትያትር ቤት እስከ ብሔራዊ ትያትር ድረስ ላደረገችው የጥበብ ተጋድሎ ጥበብ ውለታዋን ለመክፈል ተሰናድታለች።እስከ 90 ዎቹ አጋማሽ ድረስ ትወናው እንዳለም በድምጽዋ ብዙ መድረኮች ላይ ስታዜም ስታቀነቅን ትደመጥ ነበር።ከዚያ 90ዎቹ ወዲህ ደግሞ የፊልም ኢንዱስትሪው በሀገራችን መስፋፋቱን ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ ፊቷን ወደ ፊልሞች አዞረች።ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በአጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር ዓይኖቿን ከፊልም ኢንዱስትሪው ነቅላቸው አታውቅም።በበርካታ ፊልሞች ውስጥ በረዳት ተዋናይነቷ ያሳያቸው ድንቅ ብቃት ከሕይወት ዘመን አገልጋይነቷ ጋር ተደምሮ ለዚህ ክብር አብቅቷታል።ፍቅርተ በሥራዎቿ ብቻም ሳይሆን በምግባርና ስብዕናዋም የብዙዎችን ልብ ያሸነፈች ወለላዋ አደይ ጉማ ናት።
ከጉማ ተጠባቂ ሽልማቶች መካከል ሌላኛው “የሔርሜላ” ኒሻን ነው።“ሔርሜላ” የሚለውን ስም በአንድ የቀድሞ ፊልም ውስጥ የተመለከትንና የምናውቀው ብዙዎች እንደሆንን ተስፋ አደርጋለሁ።የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ተተክሎ ፍሬ መስጠት ሲጀምር “ሔርሜላ” የተሰኘውን ፊልም ያኔ ገና በጥቁርና ነጭ ምስል የተመለከትን በእርግጥም ስሙን ለመዘንጋት አይቻለንም።ለሽልማቱ የተሰጠው ስያሜም ከዚሁ የተወለደ ስለመሆኑ ለማስታወስ ነው።የዘንድሮዋ የሔርሜላ እናትም የፊልም ጥበብ አበርክቶዋ የሚጀምረውም ከዚያው የሩቅ ሰሞን ላይ ነው።
በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው የፊልም ትምህርት ቤት የተከፈተው በ1994 ዓ.ም ነበር።ታዲያ ትምህርት ቤቱ በዩኒቨርሲቲ፣ አሊያም በኮሌጅ አይደለም።ለዚህ መከፈት ትልቁን ትከሻ ሰጥታ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ በቃኝ አውርዱልኝ ሳትል እውን ያደረገችው ደግሞ ይህቺው የዘንድሮዋ ባለክብር እንስት ናት።እሷም የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ቀዳማዊት መጋቢ የሆነችው አዜብ ከበደ ናት።ነገራችንን ነገር ያንሳውና፣ አዜብ ከበደ በ9ኛው የጉማ ሄርሜላ ተሸላሚ የነበረችው የገነት ከበደ እህት ናት።በስጋ ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ተጋምደው፣ በጋራ ሠርተው በጋራ ሲሸለሙ መዓዛው የተለየ ነው።ሔርሜላም ከአባት ከበደ ቤት ንቅንቅ አልል ብላ ከሁለቱ እንቁ እህትማማቾች መካከል ተጣብቃለች።
አዜብ ከበደ ፋና ወጊ በመሆን በ1994 ዓ.ም በከፈተችው የፊልም ትምህርት ቤት ገና በጅምሩ 1ሺህ 57 ወንድና ሴት ተማሪዎችን ተቀብላ፤ ከወጭና ከሀገር ውስጥ በተውጣጡ መምህራን በ12 ወራት ቆይታ ጥበብን እንዲቀስሙ አድርጋለች።ትምህርት ቤቶቹንም በአዲስ አበባ ሁለት፣ አንድ ደግሞ በአዳማ ናዝሬት ከተማ ውስጥ በመክፈት ለጥበብ መጠለያን ሠርታለች።በትወና፣ በፊልም ኤዲቲንግ፣ በፎቶ ግራፍና በሌሎች ተያያዥ ዘርፎች በመሠልጠን የወጡት ተማሪዎቿም የፊልም ኢንዱስትሪውን ምሰሶ በደቦ አቁመውታል።የትምህርት ቤቱ መልካም ተሞክሮ፤ ተማሪዎቹን ማሠልጠን ብቻ ሳይሆን በማገባደጃው ላይ ለአራትና አምስት በመጣመር እያንዳንዱ ተማሪ ፊልሙን ሠርቶ ማቅረቡ ነው።ከሚሠሯቸው የ40 ደቂቃ ርዝመት ካላቸው ፊልሞች መካከል ቆንጆ የተባሉት ተመርጠው ለእይታ ይበቃሉ።ከዚያ ከ1994 ዓ.ም ጅማሮ አንስቶ በፊልም ጥበብ ዕውቀት የዳበሩና በሙያው የበሰሉ ባለሙያዎችን በማፍራት ለትልቁ ገደል ትልቁን ጠጠር ጥላለችና ሔርሜላ 2017 የእርሷ ነው።
ሌላው ጉማ አርአያ ሰብ ነው።በሙያቸው በኪነ ጥበቡ ዘርፍ እያገለገሉ መሳ ለመሳ ደግሞ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ውስጥ ትልቅ አሻራቸውን እያሳረፉ ያሉ የጥበብ ልጆች በርከት ብለው ይገኛሉ።ያላቸውን ዕውቅናና ተደማጭነት ለሀገራዊ ኃላፊነት በመጠቀም ሕይወትና ጥበብ እንዳይባክኑ አድርገዋል።በበጎ ሥራቸው አንቱ ተብለው እጃቸውን ለመሳም በቅተዋል።ለ15 ዓመታት የበጎነት ቆይታው፤ የዘንድሮው ጉማ ስሞና መርቆ አበባውን የሚያስታቅፈው የጥበብ ሰው ደግሞ አርቲስት ይገረም ደጀኔ (አስቴር) ሆኗል።በበጎ አድራጎት ሥራዎቹ በአምባሰደርነት ከሠራባቸውና ከሠራቸው ጥቂቱን በማንኪያ ለማንሳት ያህል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ባንክ፣ ሜሪ ጆይና ሜቄዶንያ ይገኙበታል።በደም ባንክ ውስጥ ከዚያ ቀደምም ሆነ በኋላ ያልተደገመውን 14 ሺህ ዩኒት ደም በአንድ ቀን ብቻ እንዲሰበሰብ በማድረግ በተቋማት ውስጥ ክብረ ወሰኑን እየመራ ያለ ባለታሪክ ነው።ከማገልገሉም በአንድ ወቅት የሠራውን የመዝሙር አልበም ሙሉ ለሙሉ ገቢውን ለሜቄዶንያ አበርክቶታል።ሜሪ ጆይ በሐዋሳ ከተማ ውስጥ ሕንጻ ለማስገንባት በማሰብ ሲያሰባስብ ከነበረው 1መቶ ሚሊየን 20 ሚሊየን የሚጠጋው የተሰበሰበው በእርሱ የዕለት ተዕለት ድካምና ብርታት ነበር።በሌሎች የበጎ አድራጎት ተቋማት ውስጥም ብዙ የሚያስጨበጭቡ ተግባራትን አከናውኗልና ለመልካምነቱ ጥበብ መልካሙን ሽልማት ልትሸልመው ተሰናድታለች።
በጉማ ሽልማት አደይ አበባዎች መካከል ስንሸራሸር ከሠሪው ወደ ሥራው የምታሳልጥ መንገድም አለች።በተዋበ የጥበብ መንደር ውስጥ በውበት ልቀው ለመታየት የበቁት አደይ ጥበባት በዋናነት ከበስተ ፊልም አቅጣጫ ላይ ያመለክተናል።ለሽልማቱ ለመታጨት የተመዘገቡ ፊልሞች ቁጥር በድምሩ 42 ደርሰዋል።ቁጥሩ በክልል የሚገኙትንም አካቶ ይዟል።ከዚህ ቀደም በነበረው ዙር ውስጥ በትግርኛ፣ በኦሮሚኛ እና በሀላቢኛ የተሠሩ ፊልሞችን ለሽልማት አድርሷል።አሁን ደግሞ በአፋርኛ (የአጭር ጊዜ ፊልም) እና በሶማሊኛ (ዶክመንተሪ) በማከል ዘንድሮን በጉማ ይመለከታሉ።በአጠቃላይም 20 የአጭር ጊዜ ፊልሞችና 22 ፊውቸር ፊልሞች በማህደሩ የሠፈሩት ናቸው።
ወገን! ከጥበብ ሁሉ ትልቁ ጥበብ፣ ከማወቅ ሁሉ ትልቁ ማወቅ ከአምናው ለዘንድሮ፣ ከዘንድሮና አምና ለከርሞው ተምሮ የያዙትን መንገድ በረዥሙ ማጽናት ነው።ይህን ስል አምና ጉማ ያስመለከተን አንዳንድ አግባብ ያልሆኑ ጉዳዮችም እንደነበሩ ልብ ይለው ዘንድ ነው።ልብ ያሉ እንደሆነም ዘንድሮን ማስተዋል አያዳግትም።ከ9ኛው አስቀድሞ የነበሩት የጉማ ሽልማቶች በአለባበስ ሥርዓትና በባህል ጥበቃው የሚታማ አልነበረም።እንዲያውም በባህል አልባሳት አሸብርቆ ከመጣው ታዳሚ መሀል በመምረጥ በድንገቴ ፈንጠዚያ አስፈንጥዘው ሲሸልሙ ሁሉ ነበር።በባለፈው 9ኛ ግን ጥቂት የማይባሉ እንስቶች ፈንገጥ ባለ አለባበስ ላይ ከፊት አንስቶ ሰውነታቸውን በቀለማት ቀልመው በመግባት የእድምተኛውን ቆሌ በመግፈፍ ውዝግብና ያልተገባ ንትርክ መነሳቱ አይረሳም።
በመሀል የዝግጅቱ ዓላማ ተዘንግቶም ወደ ሌላ አብዮታዊ ተቃውሞ ተለውጦም ነበር።እንስቶቹ “እሾህን በእሾህ” በማለት ከማንነታችን ጋር የማይሄደውን ድርጊት ፈጽመው የመግባታቸው ሀሳብ፤ ለውበት ሳይሆን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በአደባባይ ለመቃወም ነበር።ያም ሆነ ይህ ግን፣ ያለቦታና ጊዜው የተገኘ ወርቅም ቢሆን ድንጋይ ነው።የቱ ጋር ምን ማድረግ እንዳለብን ካላወቅን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ከመባል ሌላ የምናተርፈው አይኖርም።በእንደዚህ ዓይነት ዝግጅቶች መሀል ይህን መሰሉን ዱብ’ዳ የምናወርድ ከሆነ የሥነ ሥርዓቱ ዓላማ ከመሪው ተጠማዞ ታዳሚውንም ሳይቀር መፍጀቱ የማይቀር ነው።ሌላውን እንዳይጎረብጥ አድርጎ ወግና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በራሱ ቦታና ጊዜ ማድረግ ሲቻል፤ በታወቁ ዝግጅቶች ውስጥ ሌላ ያልታወቁ ዝግጅቶችን መፍጠር ለየትኛውም የሚበጅ አይደለም።የዝግጅቱን ድባብ ከመግመጣቸውም ባህል፣ ወግና ሥርዓትን ያጠለሻል።እንግዲህ “የቄሳርን ለቄሳር፤ የእግዜርንም ለእግዜር” ማለት መልካም ነው።ከአምናው ለዘንድሮ ስንማርም፤ ለሀገራዊው ዝግጅት በሀገርኛ የባህል አልባሳቶቻችን አሸብርቀን መሄዱን እንዳንዘነጋው ለማስታወስ ነው።
ጉማ ከአንድ አሀዝ ወደ ሁለት ከፍ በማለት ከ9ኝ ወደ 10 ተሸጋግሯል።ለተከታታይ ስድስት ዓመታት በብሔራዊ ትያትር አዳራሽ፣ አንድ በስካይላይት፣ አሁን ደግሞ በሸራተን አዲስ ሆቴል ውስጥ ለመድመቅ የሚጠብቀው አደይ አበባዋን፣ ጥቅምት 8ን ነው።እኛም የጥበብ ቤተሰቦች የጥቅምት 8 ሰው ይበለን!!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም