በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ-ጥርና ዝነኛ አትሌቶች መገኛ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ‹‹የሯጮች ምድር›› የሚል ስያሜ ተሰጥቷታል::
በተለያዩ ዓለማት የሚካሄዱ ታላላቅ የአትሌቲክስ ውድድሮች አድማቂ የሆኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የብቃታቸው ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ለማወቅም የማይጓጓ የለም:: በዚህም እንደ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያሉ ዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች ላይ በርካቶች ባህር አቋርጠው ተሳታፊ ይሆናሉ::
ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአፍሪካ ደረጃ እንደነገሰ መዝለቅ የቻለው ግዙፉ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅና አዝናኝ ከሆኑ ቀዳሚ አስር ሩጫዎች መካከል የሚመደብ ነው:: በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ከተለያዩ ዓለማት የሚሰባሰቡ ቱሪስቶችን የሚያሳትፈው ሩጫው ስመጥር የሀገር ውስጥ እና የጎረቤት ሀገራት አትሌቶችን በማሳተፍም ይታወቃል:: በዚህም የዓለም የማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር (AIMS) ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሰጠው ሲሆን፤ በመድረኩ የሚመዘገብ ሰዓት ተቀባይነት ያለው መሆኑ ይታወቃል:: የኢትዮጵያ በጎ ገጽታ ማሳያ የሆነው ተወዳጁ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሁን ደግሞ በዓለም አትሌቲክስ የሌብል ደረጃ የተሰጠው መሆኑን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል::
ስፖርቱን የሚመራው የዓለም አትሌቲክስ በተለያዩ ዓለማት የሚካሄዱና መስፈርቱን ለሚያሟሉ ሩጫዎች ደረጃዎችን የሚሰጥ ሲሆን፤ በአትሌቶች ዘንድ ውድድሮቹ ይበልጥ ዕውቅና እንዲያገኙና ተመራጭም እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው መሆኑ ይታወቃል::
ማህበሩ በየዓመቱ ደረጃ ሲሰጥ በዚህ ዓመት ለጎዳና ሩጫዎች የሰጣቸው አራት ደረጃዎች ናቸው:: በዚህም ቀዳሚውና ከፍተኛው ደረጃ የፕላቲኒየም፣ ቀጣዮቹ የጎልድ እና የኤሊት፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ ያገኘችው የሌብል ደረጃ ናቸው:: ያለፈው ዓመት ደረጃ የተሰጣቸውን 20 ውድድሮች ጨምሮ በዚህ ወቅት 262 ሩጫዎች ደረጃ ተሰጥቷቸዋል:: ከእነዚህም መካከል 148 የሚሆኑት ሩጫዎች ሌብል ሬስ ላይ የሚገኙ ናቸው:: በአፍሪካ እዚህ ደረጃ ውስጥ መግባት የቻሉት ጥቂት ሀገራት ብቻ ሲሆኑ፤ ዳይመንድ ሊግን ጭምር በብቸኝት የምታስተናግደው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ፤ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ ሁለት ሁለት ውድድሮቻቸው የሌብል ደረጃ ማግኘት ችለዋል:: የተቀሩት ሀገራት ደግሞ ኢትዮጵያ እና ጋና ናቸው::
የአትሌቶች መፍለቂያ ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያ የውድድሩ በዚህ ደረጃ መካተት ትልቅ እርምጃ ሲሆን፤ ሩጫውም ከዚህ ቀደም ከነበረው ተጨማሪ ዕውቅና ሊያሰጠው የሚችል ነው:: ዘንድሮ ለ24ኛ ጊዜ የሚካሄደው የሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር በመጪው ህዳር 8/2017 ዓ•ም ሲካሄድ 50ሺህ ሯጮች ይሳተፉበታል:: ይህም ቁጥር እንደ ለንደን፣ ፓሪስ እና ኒውዮርክ ማራቶን ካሉ የዓለም ታላላቅ የጎዳና ሩጫዎች ጋር ያስተካክለዋል:: የዓለም አትሌቲክስ “የሌብል ደረጃ” ሲል የሰየማቸው ውድድሮች በጥራት ዝግጅቶችን ከማድረግ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ ከመሆን እና የተሳታፊዎች ውድድሩ ላይ የነበራቸው ቆይታ፣ የከተማ አስተዳደሮች ለዝግጅቱ ያላቸውን ድጋፍ፤ እንዲሁም ዝግጅቱ በአትሌቲክስ ውድድር ዘርፍ አበረታች ቅመሞች ላይ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑንም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያብራራል።
እጅግ በርካታ የሩጫ ውድድሮች ባሉበት ዓለም ይህንን የሌብል ደረጃ ማግኘት ዝግጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያሳየውን ዕድገት እና በዓለም ካሉ ቀዳሚ እና ተመራጭ የጎዳና ላይ ውድድሮች መካከል መሆኑን ያሳያል። የዓለም አትሌቲክስ አስተዳዳሪ አካል (World Athletics) ውድድሮችን በመመዘን በየዓመቱ ደረጃዎችን ይሰጣል። የመሮጫ ርቀት ልኬት፣ የውድድር ሰዓት ምዝገባ እና የኤሊት አትሌቶች ተሳትፎም ከግምት ውስጥ የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም