‹‹አዲስ አበባ ሁሉም ነገር ብዙ ነው›› አለ ሰለሞን ደሬሳ የሚል ጽሑፍ ከአንድ መጽሔት ላይ አንብቤ ነበር:: በሄድኩባቸው የማህበራዊ አገልግሎት ማግኛ ቦታዎች ሁሉ ይህ የሰለሞን ደሬሳ አገላለጽ ትዝ ይለኛል:: አዲስ አበባ ሁሉም ነገር ብዙ ነው!
በቻይና/ቤጂንግ ቆይታ የነበረው አንድ ጋዜጠኛ የጻፈውን ገጠመኝ አንብቤ ነበር:: ገጠመኙ በአጭሩ ሲጠቃለል፤ በኢትዮጵያ ዓውድ ከረፋዱ 4፡00 ሰአት ሊሆን በሚችል ሰዓት ካረፈበት ሆቴል ወደ መስመሩ ወጣ አለ:: አስፋልቱ ፀጥ፣ ረጭ ያለ ነው:: ‹‹አልፎ አልፎ እንኳን ሰው ውር ውር አይልም እንዴ?›› ብሎ የተገረመው ይህ ጋዜጠኛ ከሆቴሉ ሰራተኞች አንዱን ‹‹ዛሬ ምን ኖሮ ነው መንገድ የተዘጋው?›› ሲል ጠየቀው:: የተጠያቂው መልስ አጭር ነበር:: ‹‹በዚህ ሰዓት ሰው መንገድ ላይ ምን ይሰራል?›› የሚል ነበር::
ቻይና ለትምህርት ከአንድ ዓመት በላይ ቆይቶ የመጣ አንድ የተቋማችን ባልደረባ ይህንኑ ገጠመኝ ነገርኩት:: የሥራ መግቢያና መውጫ ላይ ካልሆነ በስተቀር፤ ሰው ዝር እንደማይልና ገጠመኙ ትክክል እንደሆነ አረጋገጠልኝ::
ብዙ የአውሮፓና አሜሪካ ከተሞችን የማየት ዕድል ያላቸው ሰዎችም የጻፉትንና የተናገሩትን አንብበናል፤ ሰምተናል:: እንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ ያልተመሰቃቀሉ ናቸው:: በእርግጥ በሚገባ የተዘረጋ ሥርዓት ስላላቸው የእነርሱ ከተሞች እንዲመሰቃቀሉም አይጠበቅም::
አሁን ደግሞ የሰለጠኑ ሀገራት ከተሞችን ትተን እልም ወዳለው ገጠር እንሂድ:: አርሶ አደር የሚኖርባቸው የሀገራችን ገጠራማ አካባቢዎች ልክ እንደ ቻይና ከተሞች ናቸው ማለት ይቻላል:: በሥራ ቀንና በሥራ ሰዓት የሚታይ ሰው ይሳቀቃል:: ምክንያቱም በጎዳናው የሚታየው እሱ ብቻ ነው:: ጉዳይ እንኳን ሲያጋጥመው ‹‹በነጩ ሥራ ሰውስ ምን ይለኛል?›› እያለ ከቤተሰብ ጋር ሊጨቃጨቅ ይችላል:: በመንገዱ ላይ የሚታይ እሱ ብቻ ስለሚሆን ሥራ ላይ ሆነው የሚያዩት ሰዎች ሁሉ ጠርተው ‹‹ምነው በሰላም ነው?›› ሊሉት ይችላሉ። ምክንያቱም አስገዳጅ ጉዳይ ካላጋጠመ በስተቀር በሥራ ቀንና በሥራ ሰዓት ሰው መንገድ ላይ አይታይም:: እረኛውም፣ ገበሬውም የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት አላቸው:: ጎዳናው የሚደምቀው ጠዋት የሥራ መውጫ ሰዓት ላይ እና ማታ ከሥራ መግቢያ ሰዓት ላይ ነው::
ምንም እንኳን የከተማ ባህሪ ቢሆንም የአዲስ አበባ ምስቅልቅሎሽ ግን ይለያል:: አሁን አሁን ጭራሽ እየባሰበት የመጣ ይመስላል:: ከዓመታት በፊት ለትራንስፖርት ምቹነት ሰዓት እንመርጥ ነበር:: ለምሳሌ፤ ከረፋዱ ሦስትና አራት ሰዓት በኋላ መንገድ ክፍት ስለሚሆን፣ ታክሲም ስለሚገኝ፣ የግል ጉዳይ ያለው ሰው ይህን ሰዓት ይመርጥ ነበር:: በዚህ ሰዓት ካፌዎችም ሆኑ ባርና ሬስቶራንቶች ባዶ ይሆኑ ነበር:: ሰው የሚበዛባቸውም ቅዳሜና እሁድ ነበር::
አሁን ግን በሰኞ እና በቅዳሜ መካከል ያለው ልዩነት ቀኑን በማወቅ ብቻ ካልሆነ በስተቀር በድባቡ መለየት አይቻልም:: ሁለቱም ትርምስ ነው:: በዋናው የሥራ መግቢያ ሁለት ሰዓት እና በአራት ሰዓት መካከል ያለው ልዩነት እዚህ ግባ አይባልም:: ሁለቱም የተዘጋጋ ነው:: በየትኛውም ሰዓት ካፌ ወይም ባርና ሬስቶራንት ቢገቡ ቦታ ሊጠፋ ሁሉ ይችላል:: ታክሲ ይጠፋል፣ መንገዱም ይዘጋጋል::
ፍትሕ መጽሔት ላይ ይጽፍ የነበረ አንድ ዓምደኛ፤ የአዲስ አበባን የትራፊክ ፍሰት ያስተዋለች አንዲት ፈረንጅ ‹‹Orderly disordered›› አለች የሚል ገጠመኙን አንብቤ ነበር:: በሚገባ የተበላሸ፣ በሥነ ሥርዓት የተመሰቃቀለ … በአጠቃላይ ሆን ተብሎ እንዲበላሽ የተደረገ የሚመስል ማለቷ ይመስላል:: የተሽከርካሪ መዓት ተቆላልፈው፣ ተቆላልፈው ሲታይ ለሆነ ትርዒት ተፈልጎ እንጂ መንገድ እየሄዱ አይመስልም:: ፈረንጇ የእንግሊዘኛ ባለቅኔ ሳትሆን አትቀርም!
ከዓመታት በፊት በትራፊክ ጉዳይ ላይ በተደረገ ውይይት አንድ ተሳታፊ የተናገሩትን የግርምት ጥያቄ ከዚህ በፊት አካፍለን ነበር:: የሰውየው አስተያየትና ጥያቄ በአጭሩ፤ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋም ውስጥ የሚሰራ ሰራተኛ ቢበዛ እስከ 3፡00 የሥራ ገበታው ላይ መገኘት አለበት:: በግል ንግድ ሥራ የተሰማራ ደግሞ ከዚህም ቀድሞ ይገባል:: ታዲያ ከ4፡00 እስከ 10፡00 መንገድ ዘግቶ የሚውለው ያ ሁሉ ባለ ውድ መኪና በምን ሥራ ላይ የተሰማራ ነው? የሚል ነበር::
የሰውየው አስተያየት የየዋህነት ቢመስልም ልብ ብለን ካሰብነው ግን የምርም የሚገርምና ጥናት ሊደረግበት የሚገባ ነው:: እውነት ሀገሪቱ ይሄ ሁሉ ሀብታም አላት ወይ እንዳይባል ሀብታም ሥራ ላይ እንጂ ሲንሸራሸር አይውልም:: የሆቴሎችንና የካፌዎችን በረንዳ ተመልከቱ ሰኞም ማክሰኞም… ቅዳሜም ውድ ውድ መኪኖች ታጭቀውባቸው ነው የሚውሉት::
ነገርየው ጥናት ቢፈልግም፤ ከነባራዊ ሁኔታዎች ተነስተን ግን ምክንያቶችን መገመት እንችላለን:: ኢትዮጵያ ውስጥ ጥረው፣ ግረው፣ ለፍተው የሚኖሩ ጥቂቶች ናቸው:: ሌላውና አብዛኛው የእነዚህ ጥገኛ ነው:: የተቀረውም በድህነቱ እየማቀቀ የሚኖር ነው:: ብዙ አየር በአየር የሚሰሩ የማጭበርበርና የማታለል ሥራዎች አሉ:: የሀገሪቱ ትልቁ የሥራ ዘርፍ ድለላ የሆነ ይመስላል:: ድለላ ሲባል የተለመደው አከራይና ተከራይ፣ ገዥ እና ሻጭ የማገናኘት ድለላ ብቻ አይደለም፤ ብዙ አይነት ህገ ወጥ ድለላ አለ:: እንዲህ አይነቶቹ ደላሎች ቋሚ ቢሮና አድራሻ የላቸውም:: በየካፌውና በየሆቴሉ ነው የሚገናኙት:: ሕግና መርህ፣ ህሊናውን ተከትሎ ጥሮ፣ ግሮ ከሚኖረው ዜጋ የተሻለ መኪና ይይዛሉ። ውድ ሆቴሎችን ያዘወትራሉ::
በሌላ በኩል ሳይሰራ የሚኖረውም ቀላል አይደለም:: ውጭ ካለ ዲያስፖራ ገንዘብ እየተላከለት የሚኖር ብቻ አለ:: የእንዲህ አይነቱ ሰው እንቅስቃሴ ከካፌ ካፌ፣ ከሆቴል ሆቴል ብቻ ይሆናል ማለት ነው:: ሕይወቱ መዝናናት ብቻ ነው ማለት ነው::
ምንም ሥራ ሳይሰሩ ከውጭ በሚላክላቸው ገንዘብ የሚዝናኑትን መብታቸው ነው ብሎ ማለፍ ይቻላል:: አየር በአየር የድለላና የማጭበርበር ሥራ የሚሰሩት ግን ህገወጥነትንና ወንጀልን እያስፋፉ ነው:: ሥርዓት አልበኝነትን እያሰፈኑ ነው:: ህጋዊ አሰራሮችና አካሄዶች ዋጋ እንዳይኖራቸው እያደረጉ ነው:: በሕጋዊ መንገድ የሚሰሩ ሥራዎች የማይፈለጉና የማያዋጡ ስለሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኛው ሳይቀር ወደ ድለላና የአየር በአየር ሥራ እንዲሄድ እያደረገ ነው::
ብዙዎች እንደሚሉት እንደ ቤት ያሉ ነገሮችን ያስወደዳቸው ደላላ ነው:: ሥራው ማጫረት ስለሆነ ለአንዱ ሊሸጥ ወይም ሊከራይ የነበረውን ነገር ዋጋ አስጨምሮ ለሌላ እንዲከራይ ወይም እንዲሸጥ ያደርጋል ማለት ነው::
እንደ ሥርዓት ካየነው ደግሞ አዲስ አበባ እንዲህ አይነት ምስቅልቅል እንድትሆን ያደርጋል:: መደበኛ የሚባል ነገር አይኖርም። ሥርዓት የሚባል ነገር አይኖርም:: በመሆኑም፣ ይህ ምስቅልቅሎሽ ሊታሰብበት፣ ሊፈተሽና በአግባቡ ሊጠና ይገባዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም