- ስምንት ኮሪደሮች ይለማሉ
- አጠቃላይ 132 ኪሎ ሜትር ርዝመት አላቸው
- ለግል ባለይዞታ ተነሺዎች አምስት ቢሊዮን ብር ካሳ ተዘጋጅቷል
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ በሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ስምንት ኮሪደሮች እንደሚለሙ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። ልማቱ በአጠቃላይ 132 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው እና ለግል ባለይዞታ ተነሺዎች አምስት ቢሊዮን ብር ካሳ መዘጋጀቱም ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ በሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ስምንት ኮሪደሮች ይለማሉ።
የኮሪደር ልማት ዋና ዓላማ ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፣ ገጽታዋን ማሻሻልና ከልማቱ ማንም ወደ ኋላ ሳይቀር ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል
ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ የኮሪደርና መልሶ ማልማት በመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ መለወጥ እንደሚቻል የታየበት ጠንካራ ትብብርና የሥራ ባህል የተፈጠረበት ነው ብለዋል።
የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ቅድመ ዝግጅትን በተመለከተ ከነዋሪው ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ በአጠቃላይ ሁለት ሺህ 817 ሄክታር መሬት፣ 132 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው ቦታ ላይ እንደሚገነባ ገልጸዋል።
በልማቱ ከተካተቱ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ውስጥ የመንገድ ግንባታ፣ የአረንጓዴ ቦታዎች ግንባታ፣ የብስክሌት መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የሕፃናት መጫወቻዎችን ጨምሮ የታክሲና አውቶቡስ መጫኛና ማውረጃ ተርሚናሎች እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የመኪና ማቆሚያዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቦታዎች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች፣ የከተማ መብራትን ጨምሮ የቴሌኮም መሠረተ ልማትና የደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጂዎች ዝርጋታ እንደሚካሄድ አስረድተዋል።
በሁለተኛ ዙር ኮሪደር ልማት ከካዛንቺስ – እስጢፋኖስ – መስቀል አደባባይ – ሜክሲኮ – ቸርችል – አራት ኪሎ ኮሪደርና መልሶ ማልማት ሥራ 40 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚሸፍን ከንቲባዋ ገል ጸዋል። ከጫካ ፕሮጀክት (ሳውዝ ጌት)-መገናኛ – ሃያ ሁለት – መስቀል አደባባይ ኮሪደር ድግሞ 7 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው ብለዋል።
ከሲኤምሲ- ሰሚት- ጎሮ- ቦሌ ቪአይፒ ተርሚናል ኮሪደርና የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል ኮሪደር 10 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው ጠቅሰው፤ ከሳር ቤት- ካርል አደባባይ- ብስራተ ገብርኤል- አቦ ማዞሪያ- ላፍቶ አደባባይ- ፉሪ አደባባይ ኮሪደር 15 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ከአንበሳ ጋራዥ- ጃክሮስ- ጎሮ የሚለማው ኮሪደር 3 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው የገለጹት ከንቲባዋ፣ ከአራት ኪሎ- ሽሮ ሜዳ- እንጦጦ ማርያም- እጽዋት ማዕከል የሚገነባው ኮሪደር ደግሞ 13 ነጥብ 19 ኪሎ ሜት ርዝመት አለው ብለዋል።
በተጨማሪም የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ኮሪደር 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚሸፍን ጠቅሰው፤ የእንጦጦ-ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ ኮሪደር 21 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው ተናግረዋል።
ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን በመግለጽ፤ በመልሶ ማልማት ለተነሱ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤቶችን፣ በቂ የመስሪያ ሼዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ከ500 በላይ የሚሆኑ የንግድ ሱቆችን ለነዋሪዎች ዝግጁ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል።
በልማቱ ለሚነሱ የግል ባለይዞታዎች 5 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ካሳ በጀት መያዙን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ 100 ሄክታር ምትክ መሬትና የሁለት ዓመት የቤት ኪራይ ክፍያ፣ እንዲሁም ሁሉም የልማት ተነሺዎች የዕቃ ማጓጓዣና የስነ ልቦና ካሳ ክፍያም ጭምር እንደተዘጋጀላቸው ገልጸዋል።
የልማት ተነሺ ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሥራም እንዳይስተጓጎል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው፤ ተነሺዎች ያላቸው ማህበራዊ ትስስር እንዳይበተን በአንድ አካባቢ እንዲሰፍሩ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም