በአውቶቡሱ ጉዞ …

አንዳንዴ አንዳንድ ቀን ያስገርማል። ዕለቱን መለስ ብለው በቃኙት ጊዜ በአስገራሚ ገጠመኞች የተሞላ ነው። እንዲህ ሲሆን ደግሞ ማስደነቁን የምናስበው ቀኑ ካለፈ አልያም ሁኔታዎች ከተረሱ በኋላ ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ ታዲያ በ‹‹ነበር›› እናወሳቸዋለን። ጥቂቶቹ እያስገረሙን፣ ገሚሶቹ እያሳቁን ወይም እያሳዘኑን።

በቅርቡ ካጋጠመኝ እውነት ልጀምር። ጉዞዬን ለማቅናት ከአንድ የመንገደኞች አውቶቡስ ወንበር ተደላድዬ ተቀምጫለሁ። የምሄድበት አካባቢ ትንሽ ርቀት አለው። ይህ ብቻ አይደለም። መንገዱ በእጅጉ ይዘጋጋሉ ከሚባልላቸው የከተማችን መስመሮች አንዱ ነው። ይህን አሳምሬ አውቃለሁና አስቀድሜ ቦታ በማግኘቴ ደስ ብሎኛል።

አጋጣሚ ሆኖ አውቶቡሱ እምብዛም አልሞላም። መጠነኛ መንገደኞችን በልኩ አሳፍሮ መንቀሳቀስ ጀምሯል። ‹‹ተመስገን›› ማለቴ አልቀረም። ጢም ብሎ ቢሞላ ኖሮ የሚፈጠረውን መገመቱ ቀላል ነው። ሁሌም ቢሆን ይህን መንገድ ስጀምረው ሀገር አቋርጩ የመጓዝ ያህል ይሰማኛል። ምክንያቴ ደግሞ ያው እንዳልኳችሁ ነው። በመኪኖች ጫና የመዘጋጋቱ አጋጣሚ ጉዞውን የኤሊ ጎዳና ያደርገዋል።

በዕለቱ የጀመርኩትን መንገድ በወጉ ከመያያዜ በፊት ዙሪያ ገባዬን መለስ ቀለስ ብዬ ቃኘሁት። ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች ከስልካቸው የተገናኘ ማዳመጫን በጆሯቸው ሰክተዋል። አይፈረድባቸውም። ይህን ጎታታ መንገድ ከመሸወጃው አንዱና ቀላሉ ዘዴ እንዲህ ማድረግ ነው።

አሁንም ዓይኖቼን ጣል አድርጌ አንዳንድ ወንበሮችን ቃኘሁ። በተወሰኑት ላይ እጆቻቸውን ደገፍ አድርገው ለማሸለብ የተዘጋጁ ጥቂት ሰዎችን ቆጠርኩ። እነዚህኞቹ ጥሩ ዕንቅልፋሞች ከሆኑ መንገዱን ሳያውቁት ይጨርሱና በቅስቀሳ ይነሳሉ። የጸሀይዋ ግለት የመኪናውን አናት እያጋየችው ነው። መንገዱ ሳብ ሲል ደግሞ ከዚህም ይብሳል። አጋጣሚው ለእነሱ እንደሚያመች አሰብኩና መልካም እረፍትን ተመኘሁ።

አሁንም ዓይኖቼ መቃበዛቸውን አልተዉም። መጽሀፍ፣ መጽሄትና ጋዜጣ በእጆቻቸው የያዙ ሰዎችን እያየሁ ነው። እነዚህኞቹ ጥሩ አንባቢዎች ከሆኑ መንገዱ ምቹ ይሆንላቸዋል። ከእነሱ የተረፉት ደግሞ ጎን ለጎን ተቀምጠው እርስ በርስ የሚያወጉ ናቸው። የእነዚህም ዕጣ ፋንታ ከሌሎቹ አይለይም። ጨዋታቸው ሸጋ ከሆነ መንገዱን ሳያውቁት ካሰቡት ይደርሳሉ። መኪናው ጉዞውን ቀጥሏል።

እኔ ወዳለሁበት ወንበር አካባቢ በቅርብ ርቀት እያየሁ ነው። ትርጉም በማይሰጥ ሁኔታ ከፊት፣ ከኋላዬ እንዲሁም ከጎኔ የተቀመጡ ሰዎች ታዩኝ። እነዚህ ያለምንም አማራጭ መንገዳቸውን ለመቀጠል የተዘጋጁ ናቸው። በእጆቻቸው ስልክና መጽሀፍ የለም። ምንአልባት መንገዱ ሲሰለቻቸው እርስ በርስ ያወጉ ይሆናል።

በዙሪያዬ ያሉትን አንዳቸውንም አላውቃቸውም። በበኩሌ መንገዱን በወጉ ለማሳለጥ ልማደኛውን ዕንቅልፌን እየተማመንኩ ነው። ጥሎብኝ በጉዞ ላይ ጥቂት ደከም ካለኝ ለጥ ማለት እወዳለሁ። ደግሞ መተኛት ቢባል የውሸት ሸለብታ አይምሰላችሁ። ትክክለኛውን ዕንቅልፍ ከጫፉ አድርሼ መነሳቱ አይከብደኝም።

የአውቶቡሱ ሬዲዮ ወቅታዊ መረጃዎችን ከሙዚቃዎች እያዋዛ መንገዱን ተያይዞታል። በየፌርማታው የሚገቡት መንገደኞች የመሀል ብረቱን ምሰሶ በእጃቸው ጨብጠው ቆመዋል። ውስጤ ከአሁኑ እያዘነላቸው ነው። ይህ አሰልቺ መንገድ ተዘጋግቶ እስኪከፈት መቆማቸው ጉዞውን ከድካም በላይ ያደርገዋል።

ከቆሙት ሰዎች መሀል በዕድሜ ጠና ያሉ ይገኙበታል። ጥቂቶቹ ዓይኖቻቸውን ወደተቀመጡት ልጅ እግሮች ጣል አድርገው ‹‹ቁልጭ ቁልጭ›› ማለት ይዘዋል። ወንበር ከያዙት መሃል አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። ሁሉም በሚባል ሁኔታ ግን ካሉበት ተነስተው የቆሙትን አንጋፋዎች ለማስቀመጥ የወደዱ አይመስልም።

እንደውም አንዳንዶቹ በትኩረት በመታየታቸው መናደድ፣ መበሳጨታቸው ከፊታቸው ያስታውቃል። አይተው እንዳላዩ አንገታቸውን እያዞሩ ነው። አጋጣሚ ሆኖ ከነዚህ መሀል ልበ ቀናዎች አልታጡም። ከእኔ አጠገብ የነበረው ወጣት የአባት ያህል ለሚበልጡት ሰው ደንገጥ ብሎ ወንበሩን ለቀቀላቸው።

ሰውየው ጥቂት እንደመግደርደር ብለው ፈጥነው ከአጠገቤ ቁጭ አሉ። ምስጋና ይሁን አልያም ሌላ የሚሉት አልተሰማኝም። የሆነ ነገር እያልጎመጎሙ ነው። የወጣቱን በጎነት ያየች ሌላዋ ልጅ ደግሞ ለአንዲት ወይዘሮ የፊተኛውን ወንበር አስረክባ በእሳቸው ቦታ ላይ ቆመች። እኚህ እናት የምርቃት ነዶ አዘነቡላት።

ቀርፋፋው ጉዞ በሙቀትና ጸሀይ እንደተዋዛ ቀጥሏል። ጥቂት አለፍ እያለ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆመው አውቶቡስ ጫን እየተነፈሰ ነው። አሁን የመንገዱ አሰልቺነቱ እንደተጀመረ አውቄያለሁ። ልማደኛው ዕንቅልፌ ደግሞ ‹‹መጥቻለሁ፣ ደርሻለሁ›› ለማለት ምልክቱን እየሰጠኝ ነው። ደጋግሜ ማዛጋት ፣ ማፋሸክ  ጀምሬያለሁ። ይህኔ ማንም ባያወራኝ፣ ስልክ ባይደውልልኝ እወዳለሁ።

የአውቶቡሱ መስኮቶች በወጉ አልተከፈቱምና ንጹህ አየር ወደ ውስጥ እየገባ አይደለም። እንዲህ መሆኑ የተሳፋሪውን ትንፋሽ እርስ በርስ እያቀባበለ ጭንቀትን ፈጥሯል። ለመፍትሔው ግን ማንም ነገሬ ያለው የለም። በሙቀት፣ በላብና ትንፋሽ የተጨነቀው ተጓዥ እንደተዳከመ መንገዱን ቀጥሏል። ዓይኖቼን ክፉኛ ከብዷቸዋል። ዕንቅልፌ እየዞረኝ ነው። ሳላስበው እጄን ሰጠሁ። ደስ የሚል ዕንቅልፍ ይዞኝ እብስ አለ።

ጥቂት ቆየት እንዳልኩ ከጎኔ የተቀመጡት ትልቅ ሰው በእጃቸው ትከሻዬን ወዝወዝ አድርገው ከጣመ ዕንቅልፌ ቀሰቀሱኝ። ከምቹ አልጋዬ የገፈተሩኝ ያህል በድንጋጤ ብንን ብዬ ተነሳሁ። እሳቸው የኔን ያህል አልጨነቃቸውም። በቀላሉ አየት አድርገውኝ ‹‹ሰአቱ ስንት ይላል ? ሲሉ ጠየቁኝ። አንጀቴ እርር፣ ድብን እያለ ከእጅ ስልኬ ላይ ትክክለኛውን ጊዜ ነገርኳቸውና ወደነበርኩበት ተመለስኩ። ዳግም ዕንቅልፌ ከወጣበት እስኪመለስ ብዙ አሰብኩ። የአንዳንድ ሰው ሥርዓት ማጣት፣ ቅጥ የለሽ መሆኑ፣ አናደደኝ። ድርጊታቸው ራስ ወዳድነትን በግልጽ ቢያሳየኝ ደግሜ፣ ደጋግሜ ወረፍኳቸው።

ደግነቱ የዋሁ ዕንቅልፌ አልጨከነብኝም፤ ጅምር ሃሳብና ወቀሳዬን በወጉ ሳያስጨርሰኝ ዳግም ይዞኝ እብስ አለ። የአሁኑ እረፍት ደግሞ ከቀደመው ይለያል። ያለሁበትን እስክረሳ በዕንቅልፍ ስካር ናወዝኩ። ከአፍታ በኋላ ህልም አይሉት ቅዥት አንድ ቀስቃሽ ሃይል ከነበርኩበት ጣፋጭ ዓለም ሲነጥለኝ ተሰማኝ። ‹‹እግዜር ይይላቸው›› አሁንም ከጎኔ ያሉት አመለኛ ሰው ናቸው።

ፊቴን እንዳጨፈገኩ በንዴት ጦፌ አፈጠጥኩባቸው። እሳቸው እቴ አይሞቅ አይበርዳቸው። ኮራ፣ጀነን እንዳሉ ‹‹ይህ ሰፈር ምን ይባላል?›› ሲሉ በጥያቄ አዋከቡኝ። ሁኔታቸው አሁንም በእጅጉ እያናደደኝ ነው። ይሉኝታ ይሉትን የማያውቁ፣ ሥርዓት በሚባለው መንገድ ያላለፉ ሰው መሆናቸውን ተረዳሁ። የሚገርመው ለጥያቄያቸው በቂ መልስና ማብራራያን መፈለጋቸው ነው።

ከእሳቸው ብሶ ጥያቄያቸው በፍጥነትና በተገቢው መንገድ እንዲመለስላቸው ይሻሉ። ፍላጎታቸው ይሙላ እንጂ ማንም ምቾቱ ቢጓደል ፣ ሃሳቡ ቢፋለስ ደንታ ይሰጣቸው አይመስሉም። የሌላውን ውሰጠት ሳይረዱ የራሳቸውን ሃሳብ ብቻ ያራምዳሉ። ከዚህ በኋላ ተመልሼ ማሸለቡ ዋጋ እንደሌለው ገብቶኛል። በልቤ እሳቸውን ተክቶብኝ የተነሳውን ወጣት ጭምር መራገም ጀምሪያለሁ። የአንዳንድ ሰው ያልተገባ ባህርይና አጉል ልማድ እያስገረመኝ ነው። ዓይኖቼን አብሼ ቁልጭ ካልኩ ደቂቃዎች ተቆጥረዋል።

ከጎኔ ያሉት ሰው ሙሉ ለሙሉ መንቃቴን እንዳዩ ወሬያቸውን ጀመሩ። ከጨዋታቸው መሀል አንዱም አልጣመኝም። ሃሳባቸው እርስ በርስ ይጋጫል፣ ያነሱት ርዕሰ ጉዳይ የእሳቸውን ፈጽሞ ዕድሜያቸውን የሚመጥንና ለጆሮ የሚጥም አይደለም። መድረሻ እስኪጠፋኝ፣ ስልችት እስኪለኝ ብዙ አወሩ። ሳልወድ በግድ አዳመጥኳቸው።

አንዳንዴ ሰውዬው ራሳቸው፣ በጀመሩት ወሬ፣ ራሳቸው፣ አስተያየትና ምላሽ ሰጥተው ይደመድማሉ። ሁኔታቸው ቢያናድደኝም ችሎታቸውን አደነቅኩት። ሰው እንዴት የራሱን ሃሳብ ብቻውን ገንብቶ ብቻውን ያፈርሳል? እንዴትስ በረጅም ውጣ ውረድ ተጉዞ አይደክመውም ? ይህ እንግዲህ ተፈጥሮና ልምድ ለሰውዬው የቸሯቸው ስጦታዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

የተጨናነቀው መንገድ አሁን ጥቂት ሳብ እያለ ነው። በየፌርማታው መሀል የሚሳፈሩ ሰዎች ቁጥር ተበራክቷል። የቆሙት መንገደኞች ድካም ከፊታቸው እየተነበበ ነው። እኔን ጨምሮ ‹‹ጥቂት አረፍ በሉ›› ሲል ወንበር የለቀቀላቸው ባለመኖሩ ባሉበት ቀጥለዋል። ያዝ ለቀቅ በሚያደርገው መንገድ ተሳፋሪዎቹን በሆዱ ያጨቀው አውቶቡስ ካሰበው ለመድረስ ጥቂት ቀርቶታል። የማይደክማቸው ሰውዬ አሁንም ከጎኔ ተቀምጠው መለፍለፋቸውን ቀጥለዋል።

ለመውረድ ጥቂት አፍታዎች እንደቀሩን አውቶቡሱ ቆም ብሎ ጥቂት ሰዎችን አሳፈረ። ትኬታቸውን የያዙት መንገደኞች እንደተለመደው ‹‹ወደውስጥ አለፍ፣ አለፍ በሉ›› እየተባሉ ወደ መሀል ዘለቁ። የአውቶቡሶቹ በሮች ጥርቅም ከማለታቸው ጉዞው ቀጠለ። ጥቂት ቆይቶ ግን ከባድና ሃይለኛ የሚባል ሽታ አካባቢውን ያናውጠው ያዘ ሽታው የጫማ፣ የላብ፣ የሽቶና የቅቤ ሃይል እንዳይመስላችሁ።

ወዳጆቼ! ሥፍራውን በአንዴ አናውጦ መድረሻ ያሳጣን ጉዳይ ‹‹ነጭ ሽንኩርት›› ይሉት ሃይለኛ ‹‹ኒውክለር›› ነበር። ከገቡት ተሳፋሪዎች መሃል የትኞቹ እንዳላመጡት ባይታወቅም ሽንኩርቱ የእያንዳንዱን ተሳፋሪ ጭንቅላት በጭንቀት ወጥሮ ይቀውረን ይዟል። እኔ ግን ከዚህ በላይ አቅሜ አልቻለም አዎ! በፍጥነት ወሰኛለሁ። ‹‹ወራጅ! ወራጅ!ወራጅ!

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You