አግሮ ኢንዱስትሪንና የወጪ ገበያን ያማከለው የክልሉ ግብርና ልማት

ለእርሻ ሰፊ፣ ምቹ፣ ሥነ-ምህዳር እንዲሁም የአየር ንብረት ካላቸው ክልሎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዱ ነው፡፡ ክልሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ይሁን እንጂ ይህንን ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል የሕዝቡን ኑሮ ማሻሻል ላይ የተሠራው ሥራ እምብዛም እንደሆነ ይገለጻል፡፡በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት በግብርና ዘርፍ ለመሠማራት ፍቃድ ወስደው ሰፋፊ መሬቶችን የተረከቡ ባለሀብቶችም ቢሆኑ እንደታሰበው ዘርፉንም ሆነ ክልሉን አንድ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል ልማት ሲያከናወኑ አልታዩም፡፡

ይህንን የክልሉን እምቅ ሀብት በመጠቀም በተለይ የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግል ባለሀብቶችንም ሆነ አርሶአደሩን የሚያሳትፉ የተለያዩ የግብርና ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡በዋናነትም አርሶ አደሩን የማሳመን ሥራ በመሥራት ኩታ ገጠም እርሻዎችን በክላስተር አደረጃጀት በማጣመር የተቀናጀ የግብርና ልማት እንዲመጣ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡

የክልሉ መንግሥት ለምግብ ዋስትና መጠበቅ ወሳኝ ሚና አላቸው ከሚባሉ ዋና ዋና ሰብሎች በተጨማሪ ለኢንዱስትሪና ለወጪ ንግዱ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊ የሆኑ እንደ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ለውዝ የመሳሰሉትን ሰብሎች በስፋት በማምረት ሀገሪቱ ከዘርፉ የላቀ ተጠቃሚ እንድትሆን ጥረት እያደረገ ነው፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባብከር ሃሊፋ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የክልሉ መንግሥት በምርት ዘመኑ የክልሉን ግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡ ፡ የቴክኖሎጂና የግብዓት አጠቃቀምን በማሳደግ፤ አስፈላጊውን ሳይንሳዊ ድጋፍ በማድረግ የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም የማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦትን እንዲሁም እንደ ትራክተር ያሉ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ለአርሶአደሩ ተደራሽ ለማድረግ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የተናበበ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፡፡

‹‹በዘንድሮው የምርት ዘመን አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን 370 ሺ ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈንና 45 ሚሊዮን 184 ሺ 874 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ አቅደን እስካሁን ድረስ አንድ ሚሊዮን 154ሺ 375 ሄክታር በዘር ተሸፍኗል፡፡›› ይላሉ፡፡በቀሩት ጊዜያት እቅዱ ሙሉ ለሙሉ ይሳካል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ቦታዎች ላይ ካገጠመው በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ባሻገር የአብዛኛው የክልሉ አካባቢ የዝናብ መጠን ጥሩ የሚባልና ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነም አስታውቀዋል። በዘር ለመሸፈን ከታቀደው ውስጥም 30 በመቶ የሚሆነውን (370 ሺ229 ሄክታር) መሬት በኩታ ገጠም እርሻ (ክላስተር) ለማረስ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፣ እስከአሁን 191ሺ 124 ሄክታር ያህሉ በኩታ ገጠም እርሻ እየለማ ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በምርት ዘመኑ ወሳኝ የሚባሉ የአገዳ፣ የብርእና የጥራጥሬ ሰብሎች ላይ ትኩረት የተደረገ ሲሆን፣ በዋናነትም በክልሉ ሕዝብ በስፋት ለምግብነት የሚውሉት በቆሎና ማሽላ በስፋት እንዲለሙ ተደርጓል፡፡352 ሺ373 ሄክታር መሬት በማሽላ እንዲሁም 291 ሺ361 ሄክታር በበቆሎ ተሸፍኗል፡ ፡በተጨማሪም 60ሺ 240 ሄክታር መሬት አኩሪ አተር እንዲሁም ቦሎቄ 51 ሺ 577 ሄክታር መሬት እንዲለማ ተደርጓል፡፡

በክልሉ መንግሥት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተመረቱ ካሉ ሰብሎች መካከል ሰሊጥ ዋንኛው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ባብኬር ፤ በምርት ዘመኑ 194 ሺ ሄክታር መሬት በሰሊጥ ለመሸፈን ታቅዶ 115 ሺ 988 ሄክታር እስካሁን መሸፈን መቻሉን ያመለክታሉ፡፡‹‹ሰሊጥ ሀገራችን ወደ ውጭ ከምትልካቸውና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ሰብሎች ዋነኛው እንደመሆኑ የክልሉ መንግሥት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሰሊጥ በስፋትና በጥራት እንዲመረት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል›› ብለዋል፡፡

ለውዝም እንዲሁ ዘይት ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ተፈላጊ የሰብል ምርት መሆኑን ጠቅሰው፣ 70 ሺ ሄክታር መሬት በለውዝ ለመሸፈን ታቅዶ እስከአሁን 63 ሺ 176 ሄክታር የሚሆነውን መሬት ለመሸፈን መቻሉን አስታውቀዋል፡፡በተመሳሳይ ኑግ በ34 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፤ 25 ሺ79 ሄክታሩን ማልማት መቻሉን ይጠቁማሉ፡፡በክልሉ ዝናብ ዘግይቶ እንደሚመጣ ገልጸው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ አሁንም ድረስ አርሶ አደሩ ኑግ እየዘራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹የክልላችን መንግሥት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየሠራ ነው›› የሚሉት የግብርና ቢሮ ኃላፊው፤ በተለይም አሲዳማ አፈርን በማከም፤ ማደበሪያና ምርጥ ዘር በስፋት ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ ሰፊ ርብርብ መደረጉን ያመለክታሉ፡ ፡በዋናነትም ከዚህ ቀደም በአርሶ አደሩ የሚነሳውን የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ጥረት መደረጉን ጠቅሰው፣ በምርት ዘመኑ 203 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ 82 በመቶውን ማዳረስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል በወረዳ፣ በዩኒየን፣ በማህበርና በሌሎችም አካላት አማካኝነት ማዳበሪያ ሲከፋፈል መቆየቱን ጠቅሰው፣ ማዳበሪያው ግን በቀጥታ ለአርሶአደሩ ባለመድረሱ ዘወትር ቅሬታ ይቀርብ እንደ ነበር አስታውቀዋል፤ በዚህ የተነሳም ምርታማነትን በታሰበው ልክ ማምጣት የማይቻልበት ሁኔታ እንደነበር ያመለክታሉ፡፡

‹‹ዘንድሮ ግን አሠራራችንን በማሻሻል በመሃል ላይ ያሉ ሰንሰለቶችን በማስወጣት አርሶ አደሩ ማዳበሪያውን በቀጥታ የሚገዛበት ሁኔታ አመቻችተናል›› ሲሉም ይጠቅሳሉ፡፡በዚህም ቅሬታዎችን ማስቀረት መቻሉን ይናገራሉ፡፡ የአፈር ማዳበሪያ ተደራሽ መሆን ባልቻለባቸው አካባቢዎች ደግሞ አራት ሚሊዮን ኩንታል የእንስሳት ተረፈ ምርት፤ ኮምፖስት በመጠቀም ልማቱ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር ተያይዞም የበቆሎ ምርጥ ዘር እጥረት እንደ ሀገር አጋጥሞ እንደነበር ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም በማህበረሰቡ ዘንድ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን በቆሎ በታሰበው ልክ ማልማት እንዳልተቻለ አመልክተዋል፡፡‹‹የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ከአርሶ አደሩ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡በዘንድሮ የምርት ዘመን ብቻ የሚፈለገው 10 ሺ ኩንታል ነበር፤ የቀረበው ግን አራት ሺ ኩንታል ብቻ ነው›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹በክልላችን የተከሰተውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በዚህ ክልሉ ኮርቴፋ፤ በአማራ ምርጥ ዘር ድርጅት፣ በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽንና በሌሎች ድርጅቶች ትብብር እስከአሁን በ5 ሺ 64 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ በቆሎ ምርጥ ዘር እንዲለማ ተደርጓል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡በተጓዳኝም አርሶ አደሩ ማሽላ በስፋት እንዲያመርት መደረጉን ገልጸዋል፡፡የበቆሎ ዘር እጥረትን ለመፍታት በሚል በዚህ ዓመት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ዓመት የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ የክልሉን አርሶአደር ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ያስችል ዘንድ ለአርሶ አደሩ በተሻለ መልኩ እገዛ እየተደረገ ነው፡፡አርሶ አደሮች በዋናነት በባለሙያ የተደገፈ የአመራረት ሂደት እንዲከተሉ ሰፊ እንቀስቃሴ ተደርጓል፡፡ሥልጠና እና ምክር በመስጠት አርሶአደሩ አቅሙ እንዲጎለብትም ተሠርቷል፡፡ የአርሶ አደሩን የአመራረት ሂደት ከማዘመን አኳያም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በዚህም ካለፉት ሁለት ዓመት ወዲህ የክልሉ መንግሥት ትራክተር ገዝቶ አርሶአደሩ 30 በመቶ እየከፈለ የሚወስድበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡

ይህም በአርሶአደሩ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃት መፍጠሩን፤ ይህንን መሠረት በማድረግም በተያዘው የምርት ዘመን የክልሉ መንግሥት ትራክተር በማቅረብ 200 ሺ ሄክታር መሬት በትራክተር ለማረስ ታቅዶ እስከአሁን 196 ሺ 194 ሄክታር በትራክተር ማረስ ተችሏል፡፡በሌላ በኩል በገንዲ በሽታ ምክንያት በእንስሳት ማረስ ከባድ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለመፍታት አርሶአሶአደሩ ትራክተር ላይ ትኩረት መደረጉን ይጠቁማሉ፡፡በተጓዳኝም በምርት ዘመኑ ከስደት ተመላሽ የክልሉ ተወላጆች ወደ ግብርና ልማት እንዲገቡ መደረጉን ተናግረው፤ ወደእርሻ የገቡ ከስደት ተመላሾችን መደገፍ ያስችል ዘንድ 51 ትራክተሮች መሠራጨታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በዚህ ዓመት ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች የክላስተር አደረጃጀት ዋነኛው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ባቡክር፤ ‹‹ለግብርና ልማቱ ከተያዘው መሬት 30 በመቶው /ከ1ነጥብ 372 ሺ 229 ሄክታሩ/ በክላስተር እንዲለማ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው›› ብለዋል፡፡ በዚህም አንዳንድ ወረዳዎች በጣም ውጤታማና ለሌሎችም ተምሳሌት የሆኑ የልማት ሥራዎች መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡ለእዚህ አብነት አድርገውም የባምበሲ ወረዳን ጠቅሰው፤ በወረዳው ካለው 124 ሺ ሄክታር መሬት ውስጥ 61 ሺ ሄክታር የሚሆነው በክላስተር አደረጃት እንዲታረስ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡27 ሺ ሄክታር መሬት በበቆሎ፤ ቀሪው ደግሞ በማሽላ፣ አኩሪ አተርና፣ ሰሊጥ መሸፈኑን ያመለክታሉ፡፡

በተመሳሳይ በመተከል ዞን ዳንጉር፣ ቡለን በተባሉ አካባቢዎች ላይ ሰፋፊና ውጤታማ የክላስተር እርሻ እየለማ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፤ እስከአሁን ምንም ያልተንቀሳቀሱ አካባቢዎች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ ወር ከሌሎች ክልሎች ተሞክሮ ለመውሰድና አርሶ አደሩን በማሳመን በተሻለ መንገድ እንዲያመረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ በቴክኖሎጂ ምርት የመሰብሰብ አቅም ዝቅተኛ መሆኑን ሃላፊው ጠቅሰው፣ ‹‹በክልላችን ያለው ኮምባይነር አንድ ብቻ ነው፤ በዚህ የተነሳም በክላስተር ያሉ የበቆሎ አዝመራ በሰው ጉልበት እየተሰበሰበ መሆኑን አመልክተዋል፡፡በሰው ከተሰበሰበ በኋላ ግን በማሽን እንደሚፈለፈል ጠቅሰው፣ የምርት ብክነትን ለማስቀረት ኮምባይነር ከአማራ ክልል በኪራይ ለማስገባት ጥረት እንደሚደረግ አቶ ባቡኬር ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ምንም አይነት የምርት ብክነት እንዳያጋጥም ለማድረግ የሌሎች አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው፡፡በስፋትና በትጋት እያመረተ ያለው አርሶአደር ድካሙን የሚያቀሉለት ቴክሎጂዎች እንዲቀርቡለት ተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረበ ነው፡፡በተለይም ማሽኖቹ በብድርም ሊቀርቡለት፣ ተከራይቶ የሚገለገልበት ሁኔታም ሊመቻችለት ይገባል፡፡አሁን ባለው ሁኔታ ግን አብዛኛው የቦሎቄ ምርት በሰው ጉልበት መሰብሰቡን፤ እስከ ጥቅምት የመጀመሪያ ሳምንት ደግሞ የሰሊጥ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

እንደ አቶ ባቡኬር ገለፃ፤ የክልሉን ሕዝብ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ የጎላ ችግር የለበትም፡፡ በተለይም ለምግብነት በስፋት የሚጠቀምባቸው የበቆሎና ማሽላ ምርቶችን በስፋት የሚያመርትና በርካሽ የሚያገኝ በመሆኑ የምግብ ዋስትና ጉዳይ ስጋቱ አይደሉም፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግሥት በየምርት ዘመኑ ለውጪ ገበያ እና ለአግሮ ኢንዱሰትሪዎች ወሳኝ የተባሉ እንደ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ለውዝና ኑግ ያሉ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ትልቅ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡፡ይህ እቅዱ ከግብ እንዲደርስ ጥራት ያለው ምርጥ ዘር ማቅረብ እንዲሁም አርሶአደሩ ያለበትን የቴክኖሎጂ እጥረት አስቀድሞ መፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ሊሆን ይገባል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You