ሩሲያ በማሊ የሊቲየም እና ነዳጅ ፍለጋ ልታደርግ መሆኗን ገለጸች

ሩሲያ በማሊ የሊቲየም እና ነዳጅ ፍለጋ ልታደርግ መሆኗን ገለጸች፡፡ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ማሊ ከምዕራባውያን በተለይም ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ማሊ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራት፡፡ በኮሎኔል አስሚ ጎይታ የሚመራው ወታደራዊ ክንፍ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ከፈረንሳይ ጋር ያለውን ግንኙነት በማቋረጥ ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መሥርቷል፡፡

ሩሲያ እና ማሊ በየጊዜው ትብብራቸው እያደገ የመጣ ሲሆን አሁን ደግሞ በዓለም ላይ ተፈላጊ ከሆነው ማዕድን ውስጥ ዋነኛው የሆነው ሊቲየም ለማውጣት ከሞስኮ ጋር ስምምነት ፈጽማለች፡፡ ማሊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለመሥራት ዋነኛ ግብዓት የሆነው ሊቲየም እንዳላት ቢታወቅም እስካሁን ይህን ሀብት በማውጣት ለገበያ ማቅረብ ሳትችል ቆይታለች፡፡

ሀገሪቱ ከሩሲያ ጋር በደረሰችው ስምምነት መሠረትም ከአንድ ወር በኋላ የሞስኮ ማዕድን ፍለጋ ባለሙያዎች ሥራቸውን እንደሚጀምሩ ተገልጿል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ከሊቲየም ባለፈ የነዳጅ ሀብት ፍለጋ ስምምነት መፈራረማቸውን የማሊ የኢኮኖሚ እና ገንዘብ ሚኒስትሩ አሉሴኒ ሳኑ ተናግረዋል፡፡

የማሊ ኢነርጂ እና ኢንቨስትመንት ሚኒስትሮች ወደ ሞስኮ አቅንተው የማዕድን ፍለጋ ስምምነት ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ተፈራርመዋል፡፡ ማሊን ጨምሮ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ከምዕራባውያን ሀገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጥ ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት የመሠረቱ ሀገራት ናቸው፡፡

ሦስቱ ሀገራት ከአፍሪካ ኅብረት አባልነት የታገዱ ሲሆን በራሳቸው ፈቃድ ደግሞ ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አባልነታቸው ለቀዋል ሲል የዘገበው አል ዐይን ነው፡፡

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You