ከጅማ አናት ላይ በኩራት ተቀምጧል። የጅማን ጓዳና ጎድጓዳዋን፤ ወጭና ወራጁን ቁልቁል በትዝብት ይመለከታል። የጅማን እድገትና ውድቀት ለ141 ዓመታት ታዝቧል። ጅማን ከአፈጣጠሯ ጀምሮ ያውቃታል። ስለጅማ ቃል አውጥቶ ቢናገር ከሱ በላይ የሚመሰክር አይኖርም። የጅማ ከተማና የስልጣኔዋም መገለጫ ነው። የጅማ አባጅፋር ቤተ መንግሥት።
ይህ ቤተ መንግሥት 29 ክፍሎች፣ 65 በሮችና 54 መስኮቶች አሉት። የቀደመው ዘመን ስልጣኔ ፈስሶበታል። ድንቅ የእጅ ጥበብና የአዕምሮ እሳቤም አርፎበታል። የእንጨት ጣውላ ጥበቡ ህሊናን ይገዛል። በድንጋይ የተሰራውም ድንቅ የኪነ ህንጻ ሥራን የሚናገር ጥበብ ይታይበታል። የቤቱ ጣሪያ ቅርጽና ኪነ ህንጻ ሥራ ያስደምማል።
ግድግዳው የተለሰነበት ጭቃና ቀለም፣ ልስላሴና ውበቱ ለሚያየው ዓይንና ለሚዳስሰው እጅ ልዩ ስሜት ይፈጥራል። በአጠቃላይ ቤተ መንግሥቱ “ልዩ የኢትዮጵያ የኪነ ህንፃ ውጤት ነው” ለማለት የሚያስደፍር ነው።
ነገር ግን “ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል” እንደሚባለው ቤቱ ቢቆምም ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦበታል። ቤተ መንግሥቱ በተንከባካቢ እጦት ምክንያት ለጉስቁልና ተጋልጧል። ከውጭ ያለው ግርማ ሞገስ ወደ ውስጥ ሲገባ የለም። በቤቱ ውስጥ የንጉስ አባጅፋር እቃዎች የሉም። ውስጡ ኦና ኦና መሽተት ጀምሯል።
ግድግዳውም አልፎ አልፎ ተሰንጥቋል። የእንጨት ጥበቦቹም በተንከባካቢ እጦት ምክንያት መበስበስ ጀምረዋል። ግድግዳው ላይ ስሜት የሚሰጠው ልስን ተፋፍቋል። በአጠቃላይ የጅማው መለያ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ምሳሌ የአባጅፋር ቤተ መንግሥት በጠና ታሟል። በቶሎ መድሃኒት ካላገኘ ህመሙ ወደ መፍረስ እንደሚያደርሰው ያስታውቃል።
ቤተ መንግሥቱን ለመጎብኘት ከአዲስ አበባ መጥተው ያገኘናቸው አቶ ብሩ ኪሮስ፤ የአገራችን ኪነ ህንፃ ልዩ ጥበብ እንደሆነ ይናገራሉ። “የዛን ዘመን ጥበብ እያሳደግነው ብንመጣ ዛሬ ላይ የትበደረስን? ” ሲሉ ይቆጫሉ። ይህን የኪነ ህንፃ ጥበብ ዛሬ ላይ ተግባራዊ ማድረግ ባንችል እንኳ አለመንከባከብ ግን አሳፋሪ መሆኑን ይጠቁማሉ። በቁጭት ተነስተን ቅርሶቻችንን መጠገንና መንከባከብ አለብንም ሲሉ ይናገራሉ።
ከደቡብ ክልል ጋሞጎፋ መጥቶ ሲጎበኝ ያገኘው አቶ ማርቆስ ማኖቴ፤ የአቶ ብሩን ሀሳብ ይጋራል። ቅርሶቻችንንና ታሪካችን ለዛሬ ማንነታችን መሰረት ናቸው። በዝርዝር አውቀን እየተጠቀምንባቸው ግን አይደለም። መንከባከብ አልቻልንም። የአባጅፋር ቤተ መንግሥትም ህንፃው ብቻ ነው በቦታው ላይ የሚገኘው። በውስጡ ያሉ ቁሳቁሶች የሉም። ህንፃውም ቢሆን አደጋ ላይ ነው። ስለዚህ መጠገን፤ መንከባከብና መጠቀም ይገባናል ሲልም ያሳስባል።
ሌላው የአዲስ አበባ ጎብኝ ወይዘሪት ሉባ መሀመድም ቤተ መንግሥቱን አዲስ አበባ ሆና ያሰበችውና በአካል ያገኘችው የተለያየ እንደሆነ ትናገራለች። በመሆኑም በተጎሳቆለው ቤተ መንግሥት ማዘኗንና መከፋቷንም ትናገራለች። መንግሥት ለዚህ ትልቅ ቅርስ ትኩረት አለመስጠቱ ሚዛን የማይደፋ ነው። አሁን በቶሎ ካልተጠገነ ለልጆቻችን ማውረስ አንችልምና አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋል ትላለች።
የቤተ መንግሥቱ አስጎብኝና ጊዜያዊ ተጠሪ አቶ ክብሩ ተስፋዬ፤ ለቤተ መንግሥቱ ችግር ላይ መውድቅ ጥናት ላይ ሳይመሰረት በየጊዜው የተደረገው ጥገና እንደሆነ ያመላክታሉ። እሳቸው እንደሚሉት ቤተ መንግሥቱ በ1984 ዓ.ም ያለጥናት በጣራው ላይ በተደረገው እድሳት ረጅም የነበረውን የህንፃው ጣሪያ ጌጡ እየታየ አይደለም።
ይህ ደግሞ በግድግዳው ላይ ጸሐይና ዝናብ እንዲፈራረቅበት አደረገ። በተለይም ዝናቡ ግድግዳውን ሲያረጥበው ምስጥ በመፍጠሩ የተሰራበት እንጨት በምስጥ እንዲበላ ምክንያት ሆነ። በ1994 እና በ2002 ዓ.ም የተደረገው ጥገናም ጎርፍ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲገባ በማድረጉ መሰረቱና ህንጻው እንዲሰነጠቅ ምክንያት ሆኗል።
የአሜሪካ ኤምባሲ ቤተ መንግሥቱ አደጋ ላይ መሆኑን ተገንዝቦ፣ የክልሉ መንግሥትና የፌዴራል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በወርልድ ሞንመንት ከተባለ ድርጅት ጋር ስምምነት ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቶ ነበር። የውጭ አገር ባለሙያዎችም መጥተው ጥናት አድርገዋል። እስከ ሰኔ 2011 ዓ.ም ሥራው እንደሚጀመርም ለህዝብ ይፋ ተደርጎ ነበር።
እስካሁን ግን ሥራው አልተጀመረም። ቅርሱ ግን እየፈረሰ ነው። ከሁለትና ሶስት ወራት በፊት ጎብኚዎች ፎቅ ላይ ወጥተው ይጎበኙ ነበር አሁን ላይ ግን አይቻልም። በዚህ ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ከቆየ መፍረሱ አይቀርም ሲሉ ያላቸውን ፍራቻ ይገልፃሉ።
ቤተ መንግሥቱ ቀደም ሲል ያረፈው 40 ሄክታር መሬት ላይ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን 1ነጥብ5 ሄክታር ብቻ ነው ያለው። ይህም ሌላው ቤተ መንግሥቱን ለጎብኚዎች ምቹ ያላደረገ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በመንግሥት ለውጥ ወቅት ግርግር ስለነበረ ቤተ መንግሥቱን የመዝረፍ ሙከራ ሲደረግበት የአባጅፋር የመጨረሻ ልጅ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ያለውን እቃ ለመንግሥት አስረክበዋል። ቅርሶቹ ወደዚህ ሳይመለሱ በጅማ ሙዚየም ይገኛሉ። ቤተ መንግሥቱ ከተጠገነ ቅርሶቹን ወደዚህ የመመለስ እቅድ ቢኖርም ጥገናው ባለመከናወኑ ቤቱ ባዶ ነው።
የቅርስና ጥናት ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብ እና ዓለም አቅፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፋንታ በየነ፤ በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንና ከወርልድ ሞንመንት ጋር በመተባበር ጥገና ለማድረግ ስምምነት ተደርጎ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ሥራው በይፋ መጀመሩን ይናገራሉ።
ሆኖም ወርልድ ሞንመንት ወደ ጥገና ከመገባቱ በፊት ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል በማለቱ ጥናት ተደርጓል። በዚህም መሰረት አሁን ላይ ጥገና ለማድረግ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እየተገዙ ነው።
በቅርብ ጊዜ ጥገናው ይጀመራል። በተገባው ውልና ቃል መሰረት ወደ ጥገና ያልተገባው ጥገናውን የሚያካሂደውን ድርጅት እኛም ማስገደድ ስላልቻልን ነው። በውሉ ላይ ጥገናውን ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ከ6 ወራት የሚፈጅ በመሆኑ ድርጅቱ በውሉ መሰረት እንደሚያጠናቅቅ እምነት አለን ይላሉ።
አሁን ላይ የሚደረገው ጥገና ከዚህ ቀደም እንደተ ደረገው ችግር አያመጣም ወይ ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄም “ችግር አለማምጣቱን መቶ በመቶ ማወቅ አይቻልም። ጥገናውን የሚያከናውነው ዓለም አቀፍና ልምድ ያለው ድርጅት በመሆኑ በጥሩ ሁኔታ እንደሚጠግነው እምነት አለን” ብለዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃም ከሱ የተሻለ ድርጅት አለ ለማለት እንደሚቸገሩም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ