አዲስ አበባ፡- በማዕድን ዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች ሥራቸውን በተለያየ ምክንያት አቋርጠው ወጥተዋል እየተባለ ያለው ሀሰት መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ። ከሚድሮክ ወርቅ ጋር የተያያዘው ጉዳይም በጥናት የሚመለስ ነው ብሏል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ቡርቃቱ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ እስከ አሁን የማዕድን ልማት ሥራውን አቋርጦ የወጣ ኩባንያ የለም፤ ሆኖም የወጡም ካሉ ምክንያታቸው የተለያየ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ አልሚዎች ማዕድን እናገኝበታለን ብለው ባሰቡት ቦታ ላይ ማዕድን ካላገኙ ሊወጡ ይችላሉ፤ ሥራው ተስፋ እንዳለው እያየ ግን አቋርጦ የወጣ ኩባንያ የለም። ሆኖም ከፀጥታ አንጻር ባለፈው የተከሰቱ ሁለት አደጋዎች ነበሩ፤ ሰዎችም ሞተውበታል ፤ በዚህ ሁኔታ ያቋረጡ ይኖራሉ።
ሚኒስትሩ ባሳለፍነው የበጀት ዓመት የማዕድን ፍለጋና ፍቃዶችን መስጠትና የነዳጅ ስምምነቶችን ለመፈራረም መታቀዱንና በዚህም 24 ፍቃዶችን በመስጠት ከእቅድ በላይ ክንውን መመዝገቡን ገልጸዋል። ይህም የሚያሳየው አገሪቱ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ ኩባንያዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተነሳሽነትና ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸውም መሆኑንም አብራርተዋል።
በዚህም 4 ነጥብ 95 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያለው ኢንቨስትመንት መመዝገቡን ገልጸው፤ ይህ ደግሞ ጥሩ የሆነ የማዕድን ኢንቨስትመንት ወደ አገሪቱ እየመጣ መሆኑን ያመላክታል። በቀጣይም ብዙ ጥያቄዎች እየቀረቡ በመሆኑ እየተጣራ ፍቃዱ በሚሰጥበት ጊዜ ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ ሊያበረክት የሚችለውን ሚና በአግባቡ ይወጣል ብለዋል ።
በተመሳሳይ በነዳጅ በኩል ዘንድሮ አዳዲስ ስምምነቶች አልተፈራረምንም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ምክንያቱ ደግሞ ኩባንያዎች በውጭ አገር ሂሳብ ለመክፈት ስለፈለጉና ፤የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ባለመፍቀዱ ስምምነት ማድረግ አለመቻሉን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን የተዘጋው በቀረበበት የህዝብ ቅሬታ እንጂ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ ይዘት እንደሌለው ሚኒስትሩ ገልጸው፤ የማህበረሰብን ጤና የመጠበቅ ግዴታችንን እየተወጣን ነው ብለዋል።
በወቅቱ የቀረበውን አቤቱታ በመመርኮዝ ኩባንያው ለአጭር ጊዜ ሥራውን አቋርጦ ሁኔታው ይጣራ የሚል ውሳኔ ተላልፎ የነበረ ቢሆንም አንድ ዓለም አቀፍ አማካሪና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ሆነው ባካሄዱት ሰፋ ያለ የአካባቢ ምርመራ ኩባንያው ሳይከፈት ረዘም ያሉ ጊዜያት አልፈዋል። ይህም ቢሆን ግን የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው ኩባንያው የሚጠቀመው ኬሚካል ለጤና ችግር የሚያጋልጥ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የማዕድን ኩባንያው በዚህ ሁኔታ ሥራውን በማቆሙ በርከት ያሉ የሥራ እድሎች ታጥተዋል፣ ያስገባ የነበረው የውጭ ምንዛሪም ቀርቷል ፤ ሆኖም ይህን መሰል ችግር ሲያጋጥም በየትኛውም ዓለም ጥቅምን ወደ ኋላ በመተው ህብረተሰብን ማስቀደም ግዴታ ነው ፤ ወደፊትም ቢሆን የማዕድን ልማት ለአካባቢና ለህዝብ ጤና ጉዳት በማያደርስ መልኩ እየተሰራ መሆኑን የማረጋገጥ ሥራ መስራት ያስፈልጋል፤ይህ እንደ አሰራርም የሚዘረጋ እንደሚሆን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2011
እፀገነት አክሊሉ