የማዳመጥ ሃይል

“ብዙ ከማውራት ብዙ መስማት” የሚል ጥሩ አባባል አለ። ይህ አባባል ያለምክንያት አልተነገረም። ብዙ ማውራት ትርፉ አድማጭን ከማሰልቸት ውጪ ብዙ ትርፍ ስለማይገኝበት ነው። ብዙ ማውራት ቁም ነገር ከማስጨበጥ ይልቅ ፍሬከርስኪ ወሬ ብቻ የሚደሰኮርበት ነው። ብዙ ማውራት ዝም ብሎ እንደቁራ መለፍለፍ ነው። ብዙ ማውራት አድማጭን ማሰልቸት ነው። ብዙ ማውራት ብዙ ለማዳመጥ ዝግጁ አለመሆን ነው። ስለዚህ “ብዙ ከማውራት ብዙ ማድመጥ” ይሻላል ይባላል ።

ምክንያቱም ብዙ የሚሰማ ሰው ብዙ ቁም ነገር ይጨብጣል። ብዙ የሚሰማ ሰው የሰዎችን አንደበት በቀላሉ በማየት ስሜታቸውን በቀላሉ የመረዳት ብቃት አለው። ብዙ የሚሰማ ሰው ሥነ ምግባር ያለው ነው። ብዙ የሚሰማ ሰው ብዙ አያወራም ወይም አይለፈልፍም። ካወራም ቁጥብ ሆኖና አድማጭን በማያሰለች መልኩ ነው። የሚያወራውም ወሬ ቁም ነገር ያለው ነው። ከዚህ አንፃር ብዙ የሚሰማ ሰው ጥቂት እያወራ ብዙ በመስማት ብዙ ያተርፋል።

ይህ ብዙ በሚያወሩና ብዙ በሚሰሙ ሰዎች መካከል ያለ ሰፊ ልዩነት ነው። ይህ ሲባል ግን ብዙ የሚያወራ ሰው ምንም አይሰማም ማለት አይደለም። በተመሳሳይ ብዙ የሚሰማ ሰው ምንም አይናገርም ማለት አይደለም። ልዩነቱ ብዙ የሚያወራ ሰው ብዙ ለመስማት ዝግጁ አለመሆኑ ነው። ብዙ የሚሰማ ሰው ደግሞ ጥቂት እያወራ ብዙ መስማቱ ነው፡፡

እዚህ ላይ ታዲያ በመስማትና ማድመጥ መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል። መስማት ማንም ይሰማል። ቁም ነገሩ ተናጋሪው በአንድ ሃሳብ ላይ ሲናገር ሰሚው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እያዳመጠ ነው የሚለው ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ሲሰማ ለሚወራው ነገር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰማም ላይሰማም ይችላል። እያዳመጠ ከሆነ ግን ሙሉ ጆሮውን ሰጥቶ ጉዳዩን በጥሞና እያዳመጠ ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ አንድ ሰው አንድን ነገር እየሰማ ከሆነ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እያዳመጠ ስላልሆነ በቀኝ ጆሮው ሰምቶ በግራው ሊያፈሰው ይችላል። ሙሉ ትኩረቱን ሰጥቶ በሁለቱም ጆሮዎቹ ነገሩን እያዳመጠ ከሆነ ግን ይህ ሰው ጥሩ አድማጭ ነው ሊባል ይችላል።

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ አድማጭ መሆን ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ መረዳት የሚያስፈልገው። ብዙ ከማውራት ብዙ መስማት ብቻ ሳይሆን ብዙ ከማውራት ጥሩ አድማጭ መሆን የሚያስፈልገውም እዚህ ላይ ነው። ምክንያቱም ጥሩ አድማጭ ሲኖር መግባባት ይኖራል። ጥሩ አድማጭ ሲኖር መስማማት ይኖራል። ጥሩ አድማጭ ሲኖር ችግርን መፍታት ይቻላል። ጥሩ አድማጭ ሲኖር መረዳዳትና መተጋገዝ ይኖራል፡፡

ብዙ ጊዜ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአካባቢ፣ በማህበረሰብ፣ በህብረተሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ የሚከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች የሚፈጠሩት ባለመደማመጥ ነው። አላስፈላጊ ንትርኮች፣ ጭቅጭቆችና መቋሰሎች መንስኤያቸው አለመደማመጥ ነው። በተለይ እንደሀገር ዛሬ ለደረስንበት አለመግባባትና የሃሳብ ልዩነት መደማመጥ አለመቻል ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። እስከዛሬ በመሃከላችን የተፈጠሩ የእርስበርስ ግጭቶችና ጦርነቶችም ያለመደማመጥ ውጤቶች ናቸው። በግለሰብ ደረጃ እርስ በርስ የሚያነታርከንና የሚያጋጨንም ይኸው አለመደማመጥ ነው።

ልዩነታችን ውበታችንና የአንድነት ቀለማችን ሆኖ ሳለ በጎሳ፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካና በሌሎችም ጉዳዮች ተቻችሎ ከመኖር ይልቅ እርስበርስ የምንጋጨው ከልዩነታችን ይልቅ በጋራ በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ መነጋገርና መደማመጥ ባለመቻላችን ነው። በመካከላችን እርስ በርስ መደማመጥ ቢኖር ምነኛ መስማማት በነበረ። ግለሰቦች እርስበርሳቸው ቢደማመጡ ምነኛ በተግባቡና ያሉባቸውን ችግሮች በፈቱ። ማህበረሰብ ከማህበረሰብ ተቀራርቦ ቢያወራና አርስበርስ ቢደማመጥ ምን ያህል በሰላም ተስማምቶ በኖረ። እንደሀገር ደግሞ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩነታቸውን ወደጎን ትተው አንድ በሚያደርጋቸው እሴቶች ላይ ቢነጋገሩና ቢደማመጡ ሀገራችን ምንኛ ዓለም በቀናባት።

ርግጥ ነው ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ካሏቸው ድንቅ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ሌሎች አስደናቂ ማህበረሰባዊ እሴቶች ጋር ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር ናት። ይህ መልካም ባህል በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ደርሶ አሁንም ቀጥሏል። ነገር ግን ደግሞ ይህን ባህል የሚነቀንቁ አደገኛ አዝማሚያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መታየት ጀምረዋል። መልካም የሚባሉ የኢትዮጵያውያንን እሴት የሚሸረሽሩ ሁኔታዎች እያቆጠቆጡ መጥተዋል።

ለነዚህ ችግሮች መከሰት እንደምክንያት የሚጠቀሱ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም መደማመጥ አለመቻል ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። የሚገርመው በኢትዮጵያ ከጫፍ እስከጫፍ የሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸው ድንቅና ያለተበረዘ ተደማምጠው ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት ባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች አሏቸው። ሆኖም እኔ አውቅልሃለው ባዮችና ራሳቸውን እንደተራማጅ ፖለቲከኛ የሚያዩ ሰዎች/በሰላማዊና በዴሞክራሲ መንገድ ፖለቲካቸውን የሚያራምዱትን አያካትትም / ይህን ኢትዮጵያን በራሳቸው መንገድ ተነጋግረውና ተደማምጠው ችግሮቻቸውን ለማለፍ የሚያደርጉትን ጥረት ለማደናቀፍ እየሞከሩ መሆናቸው ያሳዝናል።

ሆኖም እነዚህ ሰዎች የትኛውንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ዓላማቸው አሁንም አልተሳካም። ኢትዮጵያውያን አኩሪ የመነጋገርና መደማመጥ ባህላቸው አሁንም ቀጥለዋል። ይህ የመነጋገርና ተደማምጦ ችግርን የማለፍ ባህል አይነኬ መሆኑን አስመስከርዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን አሁንም እርስበርሳችን መነጋገር፣መደማመጥና መግባባት ይጎለናል። ምንም እንኳን በግለሰቦች መካከል ያለመደማመጥ ችግር ያለና ተፈጥሯዊ ባህሪ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ተራና አሉባልታ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ንትርክርኮችና አለመደማመጦች ይታያሉ። ዛሬም ድረስ በቀላሉ መፍታት በሚቻሉና ትርጉም አልባ በሆኑ ብሎም ውጤት በሌላቸው ጉዳዮች ላይ ጭቅጭቆች ይታያሉ ።

ፖለቲካ በፈጠረው የሃሳብ ልዩነት በጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ዘርና ቋንቋ መከፋፈል መጥቷል፡፡ አንዱ የሌላኛውን ቋንቋ ማንቋሸሽና መዝለፍ ይታያል፡፡ በተለይ ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም የጥላቻ ንግግሮችን የሚያደርጉ በዝተዋል፡፡ መቀመጫቸውን በውጪ ሀገራት አድርገው እዚህ በሰላም አርፎ የተቀመጠውን ሰው የጥላቻ ንግግር በመስበክ አንዱን ከአንዱ በብሄር፣ ቋንቋ ዘር የሚያጋጩ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህን የማጋጨት መንገድ በመጠቀም ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የሚጣጣሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህ አይነቱ መንገድ የማይጠቅም መሆኑን ተረድተው በንግግርና በመደማመጥ ፍላጎታቸውን ማሳካት ይችላሉ፡፡

በብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መካከልም ባለመደማመጥ የሚከሰቱ ቦታን፣ድንበርንና ሌሎችንም ምክንያቶች መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ይታያሉ፡፡ እንደነዚህ አይነት ግጭቶች በአብዛኛው ብሄር ብሄረሰቦቹ ባሏው ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት የሚፈቱ ናቸውና የሌሎች ሰዎች ጣልቃ ገብነት ያስፈልገውም፡፡ ቁጭ ብለው ከተነጋገሩና ከተደማመጡ ችግሮቻቸውን በቀላሉ መፍታት ይችላሉ፡፡ ዋናው ነገር ይህን ክፍተት አይተው ጉዳዩ ሌላ መልክ እንዲይዝ ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች እጃቸውን ይሰብስቡ፡፡

ፖለቲከኞችም ቢሆኑ ያለመግባባታቸው ዋነኛው ሚስጥር አለመደማመጣቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በልዩነቶቻቸውና በሃሳቦቻቸው ዙሪያ አይደማመጡም፡፡ አንዱ የሌላኛውን ሃሳብ አያዳምጥም፡፡ ምን አልባትም እኮ ከአንዱ የፖለቲካ ፓርቲ የተሻለ ሃሳብ ሌላኛው ጋር ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን በንግግርና በመደማመጥ ሊያምኑ ይገባል፡፡

እንደሀገርም ዘላቂ ልማትና ሰላም ማረጋገጥ ከተፈለገ ቁጭ ብሎ መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ አንዱ የሌላኛውን ሃሳብ ሊያደምጥ ይገባል፡፡ አንዱ የሌላኛውን ፍላጎት መረዳት ይኖርበታል፡፡ በመደማመጥ ውስጥ ብዙ ነገር አለ፡፡ በመደማመጥ ውስጥ ጥሩ ውጤት አለ፡፡ ስለዚህ እንደሀገር አሁን ለገጠመን የሰላም መደፍረስና አለመግባባት ትልቁ መድሃኒት መደማመጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሀገር አቀፍ ደረጃ የጀመረው ምክክር ልዩነት ያላቸው ፖለቲከኞች፣ የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ የወሰዱ ሰዎች፣ በመንግሥት ጥርስ የነከሱ ሰዎች፣ ቂመኞች፣ ኩርፈኞችና ሌሎችም ቁጭ ብለው ለመመካከር በር የሚከፍትላቸው ነው።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ግጭቶችን ፣ አለመግባባቶችን፣ እርስ በርስ መጠላላቶችን፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን፣ ጦርነቶችንና ሌሎችንም ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ነው። የምክክር ኮሚሽኑ እነዚህን ችግሮች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እስካሁን በተጓዘችበት የታሪክ ጅረት ውስጥ እስካሁን በዜጎች መካከል በልዩ ልዩ መልኩ የተፈጠሩ ቅራኔዎችንም ጭምር ለመፍታት ታላሚ ባደረገ መልኩ ነው የተቋቋመው ።

በዚህ ሀገራዊ የምክክር ሂደት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሴቶች ወጣቶች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የተገለሉ የማህረሰብ ክፍሎች፣ ራሳቸውን የሚገልፁበት መተዳደሪያ ያላቸው አካላት፣ መምህራንና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ለዚህም የታሳታፊነት መስፈርቶችን ኮሚሽኑ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ተባባሪ አካላት ሆነው ይሠራሉ፡፡ ከዚህ እንፃር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ያስቀመጠው ምቹ ሁኔታ ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከዚህ በፊት የነበሩባቸውን አለመግባባቶች፣ ግጭቶች፣ መቋሰሎች፣ የተዛቡ ትርክቶችንና ሌሎችንም ችግሮቻቸውን ቁጭ ብለው በመነጋገርና በመደማመጥ ለመፍታት የሚያስችል ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ መደማመጥ ከግለሰቦችና ከቤተሰብ የሚጀምር ከመሆኑ አኳያ ሁሉም በንግግርና መደማመጥ በማድመጥ ሃይል ሊያምን ይገባል።

አስናቀ ፀጋዬ

 አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You