በዲጂታል ዓለም ወረቀት ለምን ተወደደ?

ብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች በወረቀት ዋጋ ውድነት ምክንያት ከገበያ ውጭ ሆነዋል። ፀሐፊዎች በወረቀት ዋጋ ውድነት ምክንያት መጽሐፍ ማሳተም እየቻሉ አይደለም። የጋዜጣና መጽሔት መሸጫ ዋጋ ሲጨመር አንባቢው ለመግዛት ይቸገራል። መጽሐፍ አሳትሞ ለመሸጥ ከመሸጫ ዋጋው ይልቅ የማሳተሚያ ዋጋው ሊበልጥ ይችላል።

ስለዚህ መጽሐፍ ማሳተም የሚችለው ባለሀብትና ባለሥልጣን ብቻ ነው ማለት ነው። ባለሀብት ደግሞ መጽሐፍ የሚጽፍበት ጊዜ የለውም። መጽሐፍ ለመጻፍ የሚያስችል ማህበራዊና ተፈጥሯዊ ዕይታ የለውም። ባለሥልጣንም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ነክ ነገሮችን ካልሆነ በስተቀር ማህበራዊና ተፈጥሯዊ የሆኑ ዕይታዎችን የማየት ዕድሉ የተገደበ ነው።

የአብዛኛውን ሕዝብ ስሜት ሊገልጽ የሚችል የማህበረሰቡን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የሚያዩት፣ ተፈጥሮን በእግር እየተንቀሳቀሱ የሚመሰጡባት፣ ከአረቄ ቤት እስከ ባለኮከብ ሆቴል ያሉ ገጠመኞችን… የማየትና የመስማት ዕድል ያላቸው የድርሰት ተሰጥዖ ያላቸው ጥበበኞች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ገንዘብ የላቸውም። ስለዚህ አገሪቱ ሀሳብ አልባ ልትሆን ነው ማለት ነው። ሀሳብ ማለት የግድ ሳይንሳዊና ፖለቲካዊ ጽንሰ ሀሳብ ብቻ አይደለም። የሰዎች አዳዲስ ዕይታዎች፣ ፍልስፍናዎች፣ የሕይወት ውጣ ውረድ ገጠመኞች፣ የዘመን ትውስታዎች… የአንዱ ለአንዱ መዳረስና መተዋወቅ አለባቸው። እነዚህ ሰዎች ግን ድሃዎች ናቸውና ጽፈው ማሳተም አይችሉም። ማሳተም እንደማይችሉ ስለሚያውቁ የመጻፍ ወኔያቸውም ይቀዘቅዛል።

የጋዜጦችና መጽሔቶች አማራጭ አለመኖር ነገሮችን ሁሉ በግለሰቦች ስሜት ላይ ብቻ ለተመሰረተው ማህበራዊ ሚዲያ ያስረክባል። የተቋማዊ አሰራር ባህል ይበላሻል። ተጠያቂነትና ተቋማዊ ኃላፊነት ስለማይኖር አሉቧልታና ሀሰተኛ መረጃ ይበዛል። የንባብ ባህል ይጠፋል። ወጣቱ ትውልድ የማህበራዊ ገጾች ሰለባ ይሆናል። ማህበራዊ ገጾች ደግሞ በባህሪያቸው ጥድፊያ የሚበዛባቸው ናቸው። ረጃጅም ነገር ለማንበብ አያስችሉም። የገጽ መጠናቸው ውስን ስላልሆነ በስስት እየሮጡ ለማየት ያስገድዳሉ። በወጣትነት ዕድሜ ደግሞ ሁሉን ነገር ለማየት መጓጓት ያለ ነው። ስለዚህ ነገሮችን በጥልቀት የሚያይ ትውልድ አይፈጠርም ማለት ነው። በጥልቀት ማሰብ የሚቻለው ጠለቅ ያሉ ነገሮችን ማንበብ ሲቻል ነው። በጥልቅ የሚያስብና የሚያሰላስል ትውልድ አልተፈጠረም ማለት የተማረ አልባ አገር እናስረክባለን ማለት ነው።

የንባብ ባህልን ለማዳበር እንደ አብርሆት ቤተ መጽሐፍ አይነት ግዙፍና ማራኪ ቤተ መጽሐፍ ተገንብቷል። ቤተ መጽሐፉ ግን በቀደመው ዘመን የተጻፉ ብቻ የሚነበቡበት መሆን የለበትም። አዳዲስ መጻሕፍት፣ ጋዜጦችና መጽሔቶችም የሚገኙበት መሆን አለበት። የቀድሞዎችን ብቻ ለማንበብ ከሆነ ቤተ መጽሐፍ ሳይሆን ቤተ መዘክር ሆነ ማለት ነው። የኢንተርኔት መጠቀሚያ ብቻ መሆን የለበትም። እንደዚያ ያማረ፣ የሚመስጥ እና ፀጥ ያለ ግርማ ሞገስ ያለው ቤተ መጽሐፍ የኢንተርኔት መጠቀሚያ ብቻ ሊሆን አይገባም። ኢንተርኔት የትም ሆኖ መጠቀም ይቻላል።

አዳዲስ መጽሐፎች በብዛት ይታተሙ ዘንድ፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች አማራጭ የሚዲያ አይነቶች ይሆኑ ዘንድ፣ በአጠቃላይ የንባብ አብዮት ይፈጠር ዘንድ መንግሥት በወረቀትና የማተሚያ ግብዓቶች ላይ ያለውን ቀረጥ መላ ሊለው ይገባል። የንባብ ባህል ባልዳበረበት ማህበረሰብ ውስጥ ወረቀትና የማተሚያ ግብዓት እንደ ቅንጦት መታየት የለበትም፤ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

ብዙ ሰዎች ‹‹ዘመኑ የዲጂታል ነው›› ሲሉ ይሰማል። በተደጋጋሚ ስንለው እንደቆየነው የዲጂታሉ ዓለም እንኳን እንደ ኢትዮጵያ አይነት ታዳጊ አገር የሥልጣኔ ጫፍ ላይ ናቸው በሚባሉት አገራትም ብዙ የቴክኒክ ችግር ያጋጥመዋል። መረጃን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ የዲጂታሉ ዓለም ላይ ብቻ መንጠልጠል አስተማማኝ አይደለም። የሆነ ጊዜ፣ የሆነ ቀን ውድመት ሊያጋጥመው ይችላል። ቀላል፣ ምቹ እና ቀልጣፋነቱ አከራካሪ አይደለም። እሱ ላይ ብቻ መተማመን ግን አስተማማኝ አይሆንም፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ስናየው ደግሞ በአዲስ አበባ ደረጃ እና በወጣቶች ብቻ አይደለም መለካት ያለብን፤ በቦታም ሆነ በዕድሜ ምክንያት ኢንተርኔት የማይጠቀሙ አሉ። 600 ገጽ መጽሐፍ በኮምፒውተር ማንበብ ለወጣትም ቢሆን ለጤናም ተስማሚ አይደለም። የበይነ መረቡ ዓለም በባህሪው ለአጫጭር ነገሮች ነው። ለመዝናኛ ነገሮች ነው።

የሚገርመው እኮ ‹‹ከመምህሩ ደቀ መዘምሩ›› መሆናችን ነው። የበይነ መረቡን አማራጭ በፈጠሩት አገራት ወረቀት አልቀረም። መጻሕፍት፣ ጋዜጣና መጽሔቶች ይታተማሉ። በሠለጠኑት አገራት ወረቀት አልቀረም፤ ታዲያ እኛ ምን ስለሆነ ነው የወረቀትን ነገር እንዲህ እንደ ቀላል ያየነው? እውነት ይህን ያህል የዲጂታል ተጠቃሚ ሆነን ነው? አይመስለኝም፤ ሰነፎች ስለሆንን ነው።

‹‹አሜሪካን ፔፐር አሶሴሽን›› ባለፈው ዓመት ባወጣው ዝርዝር ሐተታ፤ ወረቀት በዚህ በዲጂታል ዘመን ተፈላጊነቱ እንደቀጠለ ነው። በተለይም ድምጽ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች እና ለዓይነ ሥውራን አሁንም አማራጩ ወረቀት ነው። ደረሰኝ የመሳሰሉት ሰነዶች ዛሬም በወረቀት ናቸው። በዲጂታል ያሉ አማራጮች ድንገተኛ ስረዛ (delete) እያጋጠማቸው ነው። ይህን የሚለው የዓለም ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ውስጥ ያለው ማህበር ነው። ውሎች ዛሬም እየተደረጉ ያሉት በወረቀት ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ዓይነ ሥውራን እየተማሩ ያሉት ለመንካት በሚመቸው ወረቀት ነው። የዲጂታሉ ዓለም ለጊዜው ለእነርሱ ምቹ አይደለም።

የማህበሩ ሰነድ፤ 25 በመቶ የሚሆነው የአሜሪካ ገጠራማ ክፍል የብሮድ ባንድ ተጠቃሚ አይደለም ይላል። በዚህም ምክንያት ወረቀት በብዛት መመረትና መሰራጨት አለበት ብሎ ይመክራል። የጉግል ፈጣሪው ላውረንስ ኤድዋርድ ፔጅ አገር የሆነችው አሜሪካ እንዲህ ካለች፤ ታዲያ እኛ ማን ስለሆንን ነው ወረቀትን እንዲህ የናቅነው? 25 በመቶ የሚሆን ኢንተርኔት የማይጠቀም ሕዝብ አለኝ የምትለው አሜሪካ ወረቀት በብዛት ይሰራጭ ስትል፤ 80 ምናምን በመቶ አርሶና አርብቶ አደር ይዘን ወረቀትን እንደ ዋዛ ማየት ነበረብን?

በዲጂታል ዘመን ወረቀት መወደዱ ሊገርም ይችላል። አማራጭ ሲኖር፣ በብዙ መገልገያዎች ወረቀት ሲቀር፣ መርከስ እንጂ መወደድ አልነበረበትም። ምናልባት ግን ማምረቱ ላይ ትኩረት ስላልተሰጠ ይሆናል። መወደዱ ግን የሚያሳየው ተፈላጊነቱን ነው። ባደጉት አገራት ሳይቀር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ነው።

ወደ አገራችን ዓውድ ስናመጣው ደግሞ ወረቀት አሁንም በጣም የሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ ነው። አባቶች በካፌዎች አካባቢ ሲቀመጡ በአጠገባቸው የሚያልፈው ሎተሪ የያዘ ወጣት ብቻ ይሆናል ማለት ነው። ጋዜጣና መጽሔት እያቀያየሩና እያማረጡ አያነቡም ማለት ነው። ወረቀት ለውል እና ለደረሰኝ ብቻ መሆን የለበትም። በተለይም ለንባብ ባህላችን መዳበር የግድ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ለጊዜው የተሻለው መፍትሔ የወረቀትና የማተሚያ ግብዓቶች ላይ ማሻሻያ ማድረግ ነውና ይታሰብበት!

ዋለልኝ አየለ

 አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You