“ኢሬቻ ማዕከሉ ምስጋና እና ሰላም ነው” ፕሮፌሰር ተሰማ ተኣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር

ግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ለሚጠጋ ዘመን ሳይታክቱ አስተምረዋል። በተለይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ብዙዎቹን እየቀረጹ ለትውልድ እውቀታቸውን ሳይሰስቱ አሸጋግረዋል። የእርሳቸው ተማሪ የነበሩ በርካቶች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ልክ እንደ እርሳቸው ሁሉ በማስተማር ላይ ይገኛሉ። አሁንም በሙሉ ጥንካሬ የሁለተኛ እና ሶሰተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በማስተማርም በማማከር ላይ ይተጋሉ። የዛሬው የዘመን እንግዳችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ተሰማ ተኣ።

እንግዳችን ፕሮፌሰር ተሰማ፣ ተወልደው ያደጉት በአሁኑ አጠራር ምስራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ አካባቢ በምትገኝ ጃቶ በምትባል ቀበሌው ውስጥ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አንድ ብለው የጀመሩት በመካነ ኢየሱስ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ በዚያም ከአንድ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸው ተከታትለዋል፡፡

በወቅቱ አባታቸው ሲያስተምሯቸው የነበረው በየሶስት ወሩ (ተርሙ) እየከፈሉ ሲሆን፣ ይከፈል የነበረውም ሶስት ብር ነበር። አባታቸው የልጃቸውን ትምህርት ቅቡልነት ያስተዋሉት ገና በለጋ እድሜያቸው ነውና ብላቴናው ተሰማም አባታቸውን አላሰፈሩም፤ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የደረሱት የአንደኛነትን ማዕረግ ሳይለቁ ነው። እንግዳችን የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠንቅቀው እዚያው ነቀምት ከተማ ወደሚገኘው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት በማቅናት ከሰባተኛ እስከ አስረኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ተማሩ።

ከአስረኛ ክፍል በኋላ ያቀኑት ወደ ሐረር ከተማ ሲሆን፣ የመምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመግባት የመምህርነትን ኮርስ ተከታትለዋል። ለሶስት ዓመት ያህልም አስተምረው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመማር በ1962 ዓ.ም ገቡ። ይሁንና በወቅቱ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመጨረስ የወሰደባቸው ጊዜ ሰባት ዓመት ነው፤ ምንም እንኳ በአራት ዓመት ውስጥ ሊጠናቀቅ የተገባው ቢሆንም፤ አንድ ዓመት ዩኒቨርሲቲውን ማገለልገል እና ሁለት ዓመት ደግሞ የእድገት በኅብረት ዘመቻ ስለነበር የማጠናቀቂያ ጊዜው ሊራዘም ግድ ብሏል። እንዳጠናቀቁ ግን የመመረቂያ ጽሑፋቸው በመመረጡ በዚያው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እንዲያገለግሉ ሆነ። በመጀመሪያ ሲያስተምሩ የነበረው በዕደማሪያም በሚባል ትምህርት ቤት 11ኛ እና 12ኛ ክፍልን ሲሆን፣ እዚያ ሲያስተምሩ ቆይተው በወቅቱ ትምህርት ቤቱ በመዘጋቱ እንደየትምህርት ክፍላቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲያስተምሩ ተደረገ። እርሳቸውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የታሪክ መምህር ሆነው ማስተማር ቀጠሉ፡፡

ለታሪክ ክፍለ ትምህርት የበቁ መምህራን ያስፈልጋሉ መባሉን ተከትሎ በሀገር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ ትምህርት በሁለተኛ ዲግሪ የመማር እድል አግኝተው ተመረቁ። በዚያም ለሁለት ዓመት ካስተማሩ በኋላ ለሶስተኛ ዲግሪ ወደ አሜሪካ ሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ አቅንተው በዚያው በታሪክ መስክ በመማር የዶክተሬት ዲግሪያቸውን ተቀበሉ። ወደ አዲስ አበባም ተመልሰው ማስተማራቸውን ተያያዙት። ለሶስት ዓመት የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ሆነውም አገልግለዋል። በትምህርት አስተዳደርም አስር ዓመት አቅማቸውን ሳይሰስቱ ሰርተዋል።

እንግዳችን፣ በግላቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር በመሆን ለሕትመት ያበቋቸው መጻሕፍት አሉ፤ ከእነዚህም መካከል “Documents of Wollega History” ተጠቃሽ ሲሆን፣ ይህም የመረጃ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። በሜጫ ኅብረተሰብ ላይ ያጠነጠነ መጽሐፍ ጽፈው ጀርመን ሀገር አሳትመዋል። “The West­ern Oromo and The Ethiopian State to 1941” በሚል ርዕስ ያሳተሙ ሲሆን፣ ገና አልተመረቀም። የዛሬው እንግዳችን በርካታ አርቲክሎችንም ጽፈዋል። እኛም እኚህን ጉምቱ የታሪክ ምሁር የኢሬቻን ባሕል አስመልክተን የዛሬው የዘመን እንግዳችን አድርገን አቅርበናቸዋል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ የታሪክ ምሁር ኢሬቻ ምንድን ነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር ተሰማ፡– የኢሬቻ መሰረት የት? መቼ? እንዴት እንደጀመረ ማወቅ በጣም እስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ኅብረተሰብን ማወቂያ አንዱ መንገድ ቋንቀቋውን ማጥናት ነው። ይህም ሲጠና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቋንቋ ቤተሰቦችን ማጤን ተገቢ ነው፤ እነዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙና የሚነገሩ ትልልቆቹ የቋንቋ ቤተሰቦች አራት ሲሆኑ፣ እነርሱም ሴሜቲክ፣ ኦሞቲክ፣ ኩሸቲክና ናይሎ ሳህራ ናቸው። አራቱም የመጡት ከአፍሮ ኢሽያቲክ የቋንቋ ቤተሰብ ሲሆን፣ እነዚህ ቋንቋዎች በምስራቅ አፍሪካም ጭምር የሚነገሩ ናቸው፡፡

የኩሽ ቋንቋ ቤተሰብ ከሆነው ውስጥ የኦሮሞን ማኅበረሰብ ስንወስድ ትልቁና ዋነኛው ነው። የኩሽ ማኅበረሰብ በታሪክ ሲጠና ከክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው የዓባይ ሸለቆን ይዞ እስከ ግብጽ ድረስ በመዝለቅ ነው። ከዚህም የተነሳ ኩሽ ብዙ ዓመት ግብጽን ያስተዳደረ ነው። ወደ ሌላውም ክፍለ ዓለም የተሰራጨ ማኅበረሰብ ነበር። ይኸውም የኩሽ ግንድ በኢትዮጵያም በብዛት የሚገኝ ነው፡፡

ኦሮሞ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ በኩሽ ማኅበረሰብ ውስጥ ትልቁን ቦታ ይዞ የዘለቀና ዓባይ ሸለቆ ውስጥ የኖረ ነው። በወቅቱ ዓባይ የራሱ ስም ያለው ሲሆን፣ ይኸውም በተለይም ወደ ሐረርጌ አካባቢ ባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች “ሞርሞር” በመባል የሚታወቅ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንዳሉት የኦሮሞ ማኅበረሰብ ኢሬቻን ማክበር የጀመረበት ትክክለኛውን ጊዜ ለማወቅ ቢከብድም፤ የሚከበረው መቼ እና እንዴት ነው?

ፕሮፌሰር ተሰማ፡- የኩሽ ማኅበረሰብ ይኖር የነበረው በ”ሞርሞር” ሸለቆ ውስጥ በመሆኑ ኢሬቻ የሚባለውን ነገር በወንዙ “Riverbank” ላይ በየዓመቱ ሲያከብር የነበረ እንደሆነ በታሪክ ይነገራል። በየቦታው የተሰራጩት የኩሽ ዝርያዎችም በሌሎቹም የአፍሪካ ሀገራት እንዲሁ ያከብራሉ። በዚህ አከባበር ውስጥ ኦሮሞ ከኩሽ ግንድ ውስጥ ዋናው ስለነበረ የራሱ የሆነ የገዳ ሥርዓት ያለው ነው። ኦሮሞ የኑሮውን ሁኔታ (ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና ማኅበራዊውን) ሁሉ የሚያንጸባርቀው በገዳ ሥርዓት ውስጥ ነው። ከሥርዓቱ ውስጥ ትልቁ ባሕል ደግሞ ኢሬቻ ነው። የኢሬቻ ባሕል ደግሞ ጠለቅ ያለ እና ለየት ያለ ምስጢር ያለው ነው። ከሌላው ሕዝብ ጋር መስተጋብር መፍጠር የሚቻለው በኢሬቻ አማካይነት ነው።

ኢሬቻን በአጭር ጊዜ በውስን ሃሳብ መግለጽ አይቻልም። ኢሬቻ ጽንሰ ሃሳቡም ሰፊ ሲሆን፣ የሚከበረውም በዓመት ሁለቴ ነው። አንደኛው “ኢሬቻ መልካ” የሚባል ሲሆን፣ እሱም ውሃ ሕይወት ስለሆነ በወንዝ ወይም በኩሬ ዳር ውሃን መሠረት አድርጎ የሚከበር ነው። ሁለተኛው “ኢሬቻ ቱሉ” የሚባል ሲሆን፣ ተራራ፤ ከሌላው የመሬት አቀማመጥ ከፍታ ያለው ስለሆነ የኦሮሞ ማኅበረሰብ በተራራ ላይ ተገኝቶ እግዚአብሔርን (ዋቃን) የሚጠራበት ስፍራ ነው። ዋቃ ከፍተኛ ኃይል ያለው፣ በየቦታው የሚገኝ፣ ሰማይና ምድርን የፈጠረና በውስጡም ያሉትን የፈጠረ አምላክ ሲሆን፣ የሚያመልኩትም እሱኑ ነው። የሚሉትም “ዋቃ ቶኪቻ” (Waaqa tokichaa) ነው፡፡

“ዋቃ ጉራቻ” ሲሉ፣ እግዚአብሔር ጥቁር ነው ለማለት ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር ንጹህ ነው ለማለት ነው። ከቀለማት መካከል ጥቁር ቀለም ግልጽና ንጹህ ነው ተብሎ በእነርሱ ዘንድ የሚታመን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ “ውሃ” ሕይወት የሚሰጥና ትልቅ ቦታ ያለው ነው። እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑትም በዚያ ደረጃ ነው።

ክረምት ሲመጣ ጥሩ ዝናብ እንዲሰጣቸው በዚያ ላይ ይለማመናሉ። ተራራው ላይ ወጥተው ዝናብ እንዲዘንብ ለዋናው የዝናብ ጊዜ መሸጋገሪያ እንዲሆናቸው እግዚአብሔርን ይማጸናሉ። ዋናው ክረምት ከሰኔ ጀምሮ ስለሚዘንብ እርሻ ያለው ወደ እርሻው ይሰማራል። ከብት የሚያረባው እንዲሁ ነው።

ክረምቱ በዝናብ የታጀበ በመሆኑ ወንዞች ይሞላሉ፤ ከዚህ የተነሳ ኅብረተሰቡ እርስ በእርስ እንደ በጋው መገናኘት አይችልም። ዘመድ ለዘመድም መጠያየቅ አይችልም። ከዚህ የተነሳ የክረምቱን ጊዜ የጨለማ ጊዜ ብለው ያምናሉ። ምንም እንኳ እርስ በእርስ እንደልብ መገናኘት ባይችሉም በተሰጣቸው ዝናብ መሰረት ሥራቸውን በአግባቡ የሚከውኑበት ጊዜ ነውና ወደ በጋው ለመሸጋገር ተስፋ ያደርጋሉ።

ዝናቡ ካበቃ እና የወንዙ ሙላት ካለፈ በኋላ ከያሉበት ወጥተው እርስ በእርስ የሚገናኙት በኢሬቻ በዓል ላይ ነው። ኢሬቻን ለማክበር ወደ ስፍራው ከመሄዳቸው አስቀድሞ ከሁለት ሳምንት በፊት የሚያደርጉት ዝግጅት አለ፤ ይህ ዝግጅት ልብን ንጹህ ማድረግና እርስ በእርስ ተጣልተው ከሆነ መታረቅ ላይ የሚያተኩር ነው፤ ምክንያቱም ቂም ቋጥሮ ወደ ኢሬቻ መሄድ አይቻልም።

ኢሬቻ የሚከበረው ሥርዓትን ተከትሎ ነው። ፊት ለፊት የሚሄዱት ሴቶች ናቸው። ቀጥሎ ሃዳ ስንቄዎች ናቸው። ከእነርሱ በመቀጠል አባ ገዳዎች ይከተላሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካለማወቅ የተነሳ ይመስለኛል ይህን ሥርዓት ሲያፋልሱ ቆይተው ነበር። ዲስፕሊኑን የሚጥሱ ነበሩ፤ ነገር ግን አሁን አሁን እያስተካከለ ነው።

ኢሬቻ፣ ሥርዓቱ የሚመዘዘው ከገዳ ሥርዓት ውስጥ ነው፤ የገዳ ሥርዓት ደግሞ ማንንም የማይነካ ነው። በገዳ ውስጥ ተቋማት አሉ። ለምሳሌ ጉዲፈቻ እና ሞጋሳ ተጠቃሽ ናቸው። ለምሳሌ ጉዲፈቻ ልጅን ማሳደግ፣ ማብላትና ማጠጣት እንዲሁም እንደ እራስ አድርጎ ማየት ነው። ሞጋሳም እንደዚያው ነው። እነዚህን የመሰሉ መልካም እሴቶች ያሉት ቢሆንም ሥርዓቱን በተመለከተ የውሸት ትርክት የሚፈጥሩ አሉ፤ ይሁንና ለሀሰተኛ ትርክታቸው ዋቢ ሊሆናቸው የሚችል አንድም ነገር የለም፤ አይገኝምም። በተለይ ደግሞ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የሚጻፈው ነገር ሲታይ እኔ የተናገርኩትንም ጭምር አዛብተውና በፈለጉት ዓይነት መንገድ አጣምመው ተጠቅመው መረጃ ያስተላልፋሉ።

አዲስ ዘመን፡- የኢሬቻ እሴቶች ምንድን ናቸው? የሚተላለፍበት ጉዳይ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ተሰማ፡– ዋናው ነገር ኢሬቻ ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚቀርብበት ነው። ኢሬቻ የአንድነትም ተምሳሌት ነው። ውሃ ሕይወት መሆኑን የሚያንጸባርቅ ጭምር ነው። ምክንያቱም በየቋንቋውና በየባሕሉ የተለያየ እምነት አለ፤ የተለያየም ባሕል አለ። አንድ ሰው በእምነቱ ክርስቲያንም ሆነ እስላም ሊሆን ይችላል። ይሁንና እምነት ሌላ ነው፤ ኢሬቻ ደግሞ ሌላ ነው። ኢሬቻ እንደ ባሕል ሰውን የሚያቀራርብ፣ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ የሚያገናኝ ነው። ለምሳሌ በቀድሞው አደረጃጀታቸው በደቡብ ክልል የነበሩ ብሔረሰቦች ኢሬቻን ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ጋር ለማክበር ይመጣሉ፤ አሁንም ይመጣሉ። ምክንያቱ ደግሞ የኩሽ ነገዶች ስለሆኑ ነው። ኢሬቻ የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን የሌሎችም በመሆኑ በአቃፊነቱ የሚታወቅ ነው፡፡

በኢኮኖሚ ደረጃ ኢሬቻ ትልቅ ድርሻ አለው፤ ሰዎች የሚገናኙበት ስለሆነ መሸጥና መለወጥም በዚያው አብሮ ያለ ነው። በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ሃሳብ በመለዋወጡ ረገድም ሚናው ጉልህ ነው። አንዱ ዘንድ የሌለው መረጃ ወደሌላው ዘንድ የሚተላለፍበትም ቦታ ነው።

ኢሬቻ፣ ተስፋ የሚሰነቅበትም ጊዜ ነው። ሰዎች ክረምቱን ከወንዝ ሙላት፣ ከንፋስ፣ ከውሽንፍር፣ ከዶፍ ዝናብ እንዲሁም ከጎርፍ ላዳናቸውን እግዚአብሔር (ዋቃ) ምስጋና አቅርበው ወደፊቱ ደግሞ መልካም ጊዜ እንዲሆንላቸው ተስፋ የሚያደርጉበትም ጭምር ነው። ክረምቱ አልፎ የዘሩት አዝርዕት ፍሬ እንዲሰጥ በአምላካቸው ተስፋ የሚጥሉበት ነው።

የኢሬቻ እሴት ጉልበት ነው። ክንደ ብርቱ ነው፤ በአፋን ኦሮሞ (Irree) ይባላል። ኢሬቻ ኃይል ነው። ምክንያቱም ሕዝቡ ከያለበት ተሰብስቦ ወደምስጋና ማቅረቢያ ስፍራ ሲገናኝ ከፍተኛ ኃይል ነው። ማንም ሊመልሰው የማይችል ኃይል ነው። ኃይሉ ግን ለክፋት የተሰለፈ ሳይሆን ለምስጋና፣ ለወንድማማችነትና ለአንድነት ነው።

ዋቄፈና ክርስቲያንን አይጠላም፤ ክርስቲያንም ዋቄፈናን አይጠላም፤ እስልምና ዋቄፈናን አይጠላም፤ ዋቄፈና እስልምናን አይጠላም።

ኢሬቻን የምንወስደው እንደ ባሕል ነው። በአንደኛው አርቲክሌ ላይ እንዳሰፈርኩት ዋቄፈና እስላምና ክርስቲያን አንድ ላይ የተቀበሉበትም ምክንያት እግዚአብሔር አንድ ነው ስለሚሉ ነው። እግዚአብሔር አንድ ነው፤ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ ናቸው።

በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ውስጥ እንደሚለው ደግሞ “እኔ አባቴ ውስጥ እንደምኖር፤ አባቴም በእኔ ውስጥ ይኖራል። እናንተም በእኔ ውስጥ ትኖራላችሁ፤ አባቴ ውስጥም ትኖራላችሁ፡፡” ይላል።

እኔ ደግሞ የተማርኩት በመካነ ኢየሱስ ሚሽን ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፤ በመሆኑም ያደግኩት መዝሙር እየዘመርኩና ቃል እየተካፈልኩ ነው። የኖርኩትም እግዚአብሔርን እያመሰገንኩ ነው። በወቅቱ ያስተምሩኝ የነበሩ እነዚያ ሚሲዮናውያን በቤታችን ኢሬቻ በሚከበርበት ወቅት ወደቤታችን ይመጡ እንደነበር አስታውሳለሁ። ስለሆነም ኢሬቻ ከሌላው እምነት ጋር የማይጣረስና የማይናናቅ ነው። መስተጋብሩም ትክክለኛ የሆነ የባሕልን ሁኔታ የሚያከብር ነው። መጽሐፉም እንደሚለውም፤ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ነው።

የኢሬቻ በዓል ከወላጆች ወደ ልጆችና ልጅ ልጆች መተላለፍ ያለበት የባሕል እና ወግ ሥርዓት ነው። ሥርዓቱ ደግሞ የሰላም ነው። ኢሬቻ ማዕከሉ ምስጋና እና ሰላም ነው። ኢሬቻ ሞራል ነው። ኢሬቻ የመከባበር ባሕል ነው። ትልልቅ ሰዎች የሚከበሩበትና ከፍታውን የሚይዙበት ነው። በሥርዓት ውስጥ ፎሌዎች ጠባቂዎች ናቸው። በኢሬቻ ውስጥ ተንኮል የለም፡፡

የኢሬቻ ባሕል ሥርዓት ያልተከተለ ሆኖ ቢሆን ኖሮ በራሱ በኦሮሞ ማኅበረሰብ አማካይነት ይጠፋ ነበር። ለሺዎች ዓመታት ሲከበር የመጣ ሥርዓት፤ ተንኮል፣ ሰውን የመርገምና የማጥፋት ዓላማን በውስጡ ይዞ ቢሆን ኖሮ ዛሬ በአደባባይ በደመቀ መልኩ አናየውም ነበር። ትርክቱ ይህን ተከትሎ ቢሆን ኖሮ ኦሮሞ ራሱ ያጠፋው ነበር። ነገር ግን ኢሬቻ ምስጋና፣ አንድነትና ወንድማማችነት ያለው በመሆኑ በየዓመቱ እንዲመጣ ይፈለጋል፤ ለዚህም ደግሞ ኢሬቻ አድራጊዎች ዘንድ “መሬ…ሆ! መሬ….ሆ…!” እየተባለ ይዜማል። እንዲህም ሲባል በየዓመቱ ተመልሰህ ና እንደማለት ነው። በመሆኑም በየዓመቱ ተመልሶ እንዲመጣልን እንናፍቃለን። እኛም ኢሬቻን ለማክበር የምንዘጋጅ ሲሆን፣ ለልጆቻችንም እናስተምራለን። እንዲቀጥልም እንሻለን።

አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ አካላት ኢሬቻ ምስጋና የሚቀርብበት ባሕል መሆኑን ባለመረዳት ከባዕድ አምልኮ ጋር ሲያያይዙት ይሰማል፤ ኢሬቻውን የሚፈጽሙ አካላት ወደ ወንዝ “መልካ” ሄደው ለምለም ሳር ይዘው የሚፈጽሙት ሥርዓት ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ተሰማ፡- አስቀድሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ውሃ ሕይወት ነው፤ ለምለም ሳር (Co­qorsa) የሚባል አለ። ይህ የሳር ዓይነት የመልማትም ምልክት ነው። የማደግም ምልክት ነው። የመስፋትም ምልክት ነው። ሳሩንና አደይ አበባን ይዘው ውሃ እየነከሩ ለሌሎችም ውሃውን ያፈናጥቁታል። ለምሳሌ ቀሳውስቱ በጥምቀት ወቅት ውሃ ወደ ምዕመኑ ይረጫሉ፤ በኢሬቻ ባሕልም ልክ እንደዚያው የለመለመውን ሳር ውሃ በመንከር ይረጫሉ። ይህ የሚያሳየው ውሃ ሕይወት መሆኑን ለማመላከት ነው። ውሃ የብልጽግናም ምልክት ስለሆነ ነው። የመኖርም ምልክት ነው። በእጃቸው ይዘው የነበረውን ለምለም ሳር ለምልክት ይሆን ዘንድ እዛው ያደርጉታል እንጂ ምንም ዓይነት የባዕድ አምልኮ የለበትም፡፡

ይህ አባባላቸው ደግሞ በታሪክ ላይ ያልተመሰረተ እና በጥናት ያልተደገፈ ነው። ፈጣሪ ሆይ ሲሉ የሚያመሰግኑት እግዚአብሔርን (ዋቃ)ን ነው እንጂ ወንዙን አይደለም። ወንዙን የፈጠረው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ምስጋና የሚያቀርቡት ወንዙን ለፈጠረው ለእግዚአብሔር ነው። ሳሩንና አበባውን ጨምሮ ሕይወት ያለውንም ሆነ የሌለውን ነገር የሰጣቸውን እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ እንጂ ፍጥረትን አይደለም።

የለመለመውን ሳር ውሃ ነክረው የሚያፈናጥቁት ለምስጋናቸው ምልክት ይሆን ዘንድ ነው። ምስጋናቸውም ሆነ ጸሎታቸው እርጥብ እንዳይጡ ነው። ውሃ ደግሞ ሰውንም ከብትን ማኖር የሚችል የሕይወት መሰረት ነው ለማለት እና ያንን የሕይወት መሰረት የሰጠው እግዚአብሔር ስለሆነ ደጋግመው እሱኑ የሚያመሰግኑበት ሥርዓት ነው። ለሚቀጥለው ደግሞ ጥሩ ምርት እንዲያገኙ ይጸልያሉ። በጥቅሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚያቀርቡበት ሥርዓት ነው፡፡

አንዳንዶች እጃቸውን በሌሎች ላይ ጭነው ሲጸልዩ ወይም ደግሞ መስቀል ሲያሳልሙ ውክልናው እግዚአብሔርን በማሰብ መሆኑ የሚታወቅ ነው እንጂ ባዕድ አምልኮ እንዳልሆነ ሁሉ ኢሬቻም በሥርዓቱ ውስጥ እግዚአብሔር የሚመሰግንበት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ የቱሪዝም ምንጭ እንዲሆን ከማን ምን ይጠበቃል?

ፕሮፌሰር ተሰማ፡- ኢሬቻ በመንግሥት/በነገሥታት ደረጃ እንዳይከበር የተደረገበት ጊዜ ሁሉ ነበር። አጥኚዎች ኢሬቻ ጥንት ሲከበር የነበረና ንጹህ የሆነ ባሕል እንደመሆኑ ለጥናት ይጠቀሙበታል። ቱሪስቶች ደግሞ በጥናት የተደገፈውን እንደ ኢሬቻ ዓይነት ባሕል ለማየት ይጓጓሉ። እንደሚታወቀው በኢሬቻ ባሕል ላይ የሚታየው የተለያየ ዓይነት አልባበስ እና የተለያየ ዓይነት የምግብ አቀራረብ ነው፤ ከዚህም ባሻገር አዳዲስ የባሕል እቃም ይስተዋላል። ከዚህ የተነሳ የቱሪስቶችን ቀልብ ይስባል። ቱሪስት ይህን ባሕል ለማየትም ለመታደምም ወደ ሀገራችን ስለሚመጣ ቱሪዝሙን ከፍ አደረገው ማለት ነው። ከዚህ የተነሳ ኢሬቻ ትልቅ የቱሪዝም ምንጭ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ደግሞ ለባሕሉ ባለቤትም ለሀገራችንም ጠቀሜታው የጎላ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በኢሬቻ የአከባበር ሥርዓት ውስጥ ምስጋና ለ“ዋቃ ጉራቻ” ይሰጣል፤ አንዳንዶች “ዋቃ ጉራቻ”ን በስያሜው ብቻ ከሌላ ነገር ጋር ያያይዙታልና እርስዎ “ዋቃ ጉራቻ” ምን ማለት እንደሆነ ትርጉሙን ቢገልጹልን?

ፕሮፌሰር ተሰማ፡- “ዋቃ ጉራቻ” ንጽህናን አመላካች ነው። “ጉራቻ” ሲባል ጥቁር ማለት ነው፤ ጥቁር ደግሞ የተከበረ መሆኑን አመላካች ነው። እግዚአብሔርን ጥቁር ነው የሚሉበት ምክንያት የእግዚአብሔርን ንጽህና ለማሳየት ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ መንፈስ ስለሆነም የሚታይ አይደለም። ጥቁር ነገር ወይም ጨለማን መጨበጥ አይቻልም። ምስጢራዊ ነው። ስለዚህም አምላክ ሁሉም ቦታ ያለ ነው። ምንጊዜም ሊደረስበት የማይችል እና ልዕለ ኃያል የሆነ ነው ለማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኢሬቻን ታላቅ እሴት የጋራ እና አካታች ለማድረግ ከማን ምን ይጠበቃል? በተለይ በታሪክ ምሁራን አካባቢ ያሉ አካላት ምን ማድረግ አለባቸው?

ፕሮፌሰር ተሰማ፡– አንዳንድ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የኢሬቻን ባሕል ካልሆነ ነገር ጋር ሲያያይዙት ይስተዋላል፤ ይህ ደግሞ ባሕሉን የሁሉም ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ሚና የሚጫወት ነው። በመሆኑም የኢሬቻ ባሕል ባዕድ የሆነ አምልኮ እንደሌለበት ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

በተለይ ሚዲያ ትልቅ አቅም ያለው እንደመሆኑ ትክክለኛውን ሁኔታ ለሕዝብ ማድረስም ይጠበቅበታል። በተለይ አንዳንድ አካላት ኢሬቻን በተመለከተ አዛብተው የሚጽፉና የሚናገሩ በመሆናቸው ያንን ሐሰት የሆነውን ትርክት በማስተካከል ወደ ታዳሚያኑ ማድረስ ተገቢ ነው እላለሁ። ትክክለኛውን የኦሮሞ ባሕል የሆነውን ኢሬቻ በመግለጽ ተገቢውን መረጃ በማድረሱ በኩል የበኩላቸውን ቢወጡ መልካም ነው። ይህ የኢሬቻ ባሕል እስከ ዛሬ ድረስ መዝለቅ የቻለው ጥሩና መልካም የሆኑ እሴቶች ስላሉት ነው።

ኦሮሞ በባህሪው አቃፊ ነው፤ ሌላውን ማኅበረሰብ የሚገፋ አይደለም። በጉዲፈቻ እና በሞጋሳ የኖረ ሕዝብ ነው። የገዳ ሥርዓትንም የሚከተል እንደመሆኑ በውስጡ ትልልቅ ተቋማት ያለው ነው። ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር ያለውም ኅብረት ዛሬ የመጣ ሳይሆን ቀድሞውም የነበረ ነው። ስለዚህ ኦሮሞ የሚያከብረው የኢሬቻ ባሕል እግዚአብሔርን ከማመስገን ውጭ በተቃራኒው የቆመ አይደለም። ሁሉም የየራሱ እምነት አለው፤ ባሕል ደግሞ የጋራ ነው። ባሕል ተወራራሽ ነው። ሁሉም ይህን ባሕል ከኦሮሞ ጋር ለማክበር አብሮ ቢመጣ የሚጣረስ ነገር አይኖረውምና ኑና አብረን እናክብር እላለሁ። ምክንያቱም ኢሬቻ ለአንድነት፣ ለሰላምና መልካም ለሆነ ነገር ሁሉ ቀናዒ የሆነ ባሕል ነው። ኢሬቻ የሚያመሰግነውና ተስፋ የሚጥለው በእግዚአብሔር (ዋቃ) ላይ ነው፡፡

ስለዚህ የሚጽፈውና የሚያስተምረው ምሁር ሁሉ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፤ ግን ደግሞ ያልሆነ ነገር በመጻፍ ሕዝብን ማሳሳት ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ ለሥራቸው ትክክለኛ ዋቢ ስለማይኖር ተዓማኒ አይሆኑም እላለሁ። ኢሬቻ ውስጥ ውሸት የለም። በመንፈስ ሆነው የሚያመሰግኑት እግዚአብሔርን (ዋቃ)ን ነው። ኢሬቻ በጣም የበለጸገ ባሕል ስለሆነ መጠላት የለበትም። ደግሞም የኦሮሞ ብቻ ነው ተብሎ መገፋትም የለበትም። ጉዳዩን ፖለቲካ ለማድረግ የሚሹ አካላት ግን የሉም ማለት አይቻልም።

በመጨረሻም ማስተላለፍ የምፈልገው፤ በአሁኑ ወቅት እየተከበረ ያለው ኢሬቻም ሆነ ወደፊትም እየተከበረ የሚቀጥለውና ወደ ልጅ ልጆች የሚተላለፈው ኢሬቻ በሰላማዊ መንገድ፣ በንጽህና፣ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የየበኩሉን እንዲወጣ የሚል መልዕክት ነው። በዚህ በሚከበረው ክብረ በዓል ላይ የሚታደመው ሕዝብ ለሰላም ተምሳሌት መሆንም ይጠበቅበታል፤ በሰላሙ ዙሪያ ለሌሎችም አርዓያ መሆን መቻል አለበት እላለሁ። የበዓሉ ታዳሚ የሆኑት ወጣቶች፣ ጎልማሶችም ሆኑ አረጋውያን እንደየእድሜያቸው ሁኔታ እርስ በእርስ መከባበር ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ደግሞ ወጣቶቹ ክብር ለሚገባቸው ታላላቆቻቸው ክብር እየሰጡ ዲስፕሊናቸውን ጠብቀው በዓሉ ያለምንም እንከን ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የየድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡

በተለይም ደግሞ “ባሕላችሁ ባሕሌ ነው” በሚል መንፈስ ኢሬቻን ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች ክብር መስጠትን መዘንጋት የለባቸውም። እንግዶቹ በሚያዩት የተሟላ ዲስፕሊን በየዓመቱ ለሚመጣው የኢሬቻ በዓል እንዲገኙ የሚያደርጋቸው ነውና በዚህ በኩል ድርሻችሁን መወጣት ይጠበቅባችኋል እላለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ፕሮፌሰር ተሰማ፡- ስለሰጣችሁኝ እድል እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

Recommended For You