የገበሬው ማሳ፣ ተራራው፣ ሸንተረሩ፣ ሸለቆውና ሜዳው አረንጓዴ ነፍስ ዘርቷል። የመሬቱ አረንጓዴ ቀለም ቀልብን ይማርካል፤ የነፋሱ ሽውታ ከአረንጓዴው ልምላሜ ጋር ልብን በሀሴት ይሞላል። ገበሬው በማሳው ላይ በሬዎቹን ጠምዶ የ100 ሚሊዮን ህዝብ የዕለት ጉርስ ለማሟላት ወጣ ውርድ እያለ ያርሳል። ክረምቱ ሞቅ እያደረገ ዝናብ በመጣል ለምርቱ ምቹ ሆኗል።
ሴቶችና ወጣቶች በኩትኳቶና በአረም በአረንጓዴው መሬት ላይ ጉብጥ ብለው ከምድር ጋር የሚያወሩ ይመስላል። ቅጠላቸው ሰፍቶ በውበት ያሸበረቁትን በቆሎ፣ ዘንጋዳና ማሽላም ይኮተኩታሉ፤ አረሞችን ያርማሉ።
ህፃናት በአረንጓዴው መስክ ላይ ፍየሎችን፣ በጎችና ከብቶችን ይጠብቃሉ። በክረምቱ ጸጋ ሳር ያገኙት ክብቶቹ ውበትም፣ ውፍረትም ጨምረው ይታያሉ። በጥቅሉ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ክረምቱ ህይወት ዘርቷል።
በገበሬው መንደር በፈጣሪ ጸጋ የሚፈለገው የተሟላ ቢሆንም ሰው ሰራሽ ጉድለቶች መፈጠ ራቸውን ይናገራሉ። ገበሬው የሚቀርብለት ምርጥ ዘርና የማዳበሪያ እጥረት እንደገጠማቸው ይናገራሉ።
በኦሮሚያ ክልል የኦሞናዳ ወረዳ እርሻቸውን ሲያከናውኑ ያገኘናቸው አርሶ አደር ነዚፍ አባጎጃም፤ አላህ ክረምቱን ለግብርና ምቹ አድርጎታል። የሰው ሰራሽ ችግር ግን ለግብርና እንቅፋት ሆኖብናል ይላሉ።
አርሶ አደሩ እንደሚሉት የዘር አቅርቦት እጥረትና የጥራት ችግር አለብን። በዘር ችግር ምክንያት የመዝሪያ ጊዜያቸው ወደኋላ ቀርቷል። ቆይቶም መጥቶ ሊዳረስ አልቻለም። በዚህም ከብቶችን ጭምር በመሸጥ ከግለሰቦች ገዝተው በመዝራታቸው ላልተፈለገ ወጭ ተዳርገዋል።
በተለይም በመንግሥት የመጣው ዘር በነቀዝ የተበላ በመሆኑ ከተዘራም በኋላ በአንዳንድ ቦታ ሳስቷል። በዚህም የተነሳ ከተጠበቀው ምርት ቅናሽ ሊኖረው እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
ከምርጥ ዘር በተጨማሪ የዩሪያ ማዳበሪያ በወቅቱ ያለመቅረብና እጥረት አለ። በዋናነት በቆሎ፣ ጤፍና በርበሬ እንደሚዘሩ የሚያነሱት አርሶ አደር ነዚፍ ክረምቱ ለምርት የሰጠ ቢሆንም የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ችግር የሚፈልጉትን ግብርና ለማከናወን እንቅፋት መሆኑን በማንሳት ቁጭታቸውን ይገልፃሉ።
በደቡብ ክልል በእርሻ ማሳቸው ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሙዘይን መሀመድም እንደ አርሶ አደር ነዚፍ ተመሳሳይ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ችግር ያነሳሉ። “መሬታችን ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ስለለመደ ከዚህ ውጭ ብንዘራም ለፍቶ መቅረት ነው።” ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ መንግሥት በወቅቱ መንግሥት ግብዓት ባለማቅረቡ በምንፈልገው ልክ አላዘመርንም ይላሉ።
የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አስማረ ጃራ፤ በአገሪቱ አልፎ አልፎ በሚፈጠሩ ግጭቶች በክልልና በዞን ደረጃ እጥረት አለ። በምርጥ ዘር መቅረብ ከሚገባው 25 በመቶ አልቀረበም። 25 በመቶ እጥረት ከያዝነው እቅድ አንፃር እንጂ ያለው እጥረት እስከ 40 በመቶ ይደርሳል። በተለይም የበቆሎ ዘር ችግር አለ። ከዚህም በተጨማሪ የዩሪያ ማዳበሪያም በዞን ደረጃ 70ሺ ኩንታል የሚደርስ እጥረት መኖሩን ይናገራሉ።
አርሶ አደሩ ከማሳ ዝግጅት አንፃር ቀድሞ ተዘጋጅቷ። ክረምቱም ለመኸር ሥራ ጥሩ ነው። አርሶ አደሩም ምርታማ ለመሆን እየተረባረበ ነው። ያሉትን ጉድለቶችን ተረባርበን በማሟላት ውጤታማ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙ ኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ብርሃኑ፤ በማበጠሪያ፣ በዘር አሰባሰብ እና በተለያየ ችግር ምክንያት አርሶ አደሮች የሚፈልጉትን ዘር በወቅቱ ሙሉ በሙሉ አለመቅረቡንና ክፍተቶች እንዳሉ ያምናሉ።
በተለይም በከፍተኛ ደረጃ የበቆሎ ዘር የሚሰበሰ ብባቸው አካባቢዎች በኦሮሚያና ቢኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በነበረው ግጭት ምክንያት ምርጥ ዘር በወቅቱ አልተሰበሰበም። ይህን በመገንዘብ ቀድመን ለአርሶ አደሩና ለህዝብ አሳውቀናል። አርሶ አደሩ ተመሳሳይ ምርት ያላቸውን ተኪ ዘር እንዲጠቀም በመምከር የመፍትሄ ሃሳብ አስቀምጠናልም ይላሉ።
በዓመቱ የተያዘው እቅድ 2 ሚሊዮን ክንታል ምርጥ ዘር ሲሆን፤ አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ዘር በወቅቱ ተሰራጭቷል። ክፍተት ያጋጥማል ተብሎ በታሰበባቸው ዘሮችም 600ሺ ኩንታል በልዩ ሁኔታ ምርጥ ዘር ተገዝቶ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ለበጀት ዓመቱ የታቀደው የማዳበሪያ አቅርቦት መጠን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሆን፤ በዕቅዱ መሰረት ሙሉ በሙሉ ተገዝቶ አገር ውስጥ ገብቷል። ከዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሃያ አምስት ሽህ ሜትሪክ ቶን የሚሆነው ለክልሎች እየተከፋፈለ ይገኛል። ሌላው በወደብ ላይ ሲሆን፤ በቅርቡ ተጓጉዞ ዘግይተው ለሚታረሱ ሰብሎች እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
በአቅርቦት ደረጃ የማዳበሪያ ችግር አለመኖሩን ያነሱት አቶ አለማየሁ፤ ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ የስርጭት መጓተት ሊኖር እንደሚችል አምነው፤ አርሶ አደሮች ካላቸው የማዳበሪያ ፍላጎት ጉጉት ቀድመው ለመውሰድ ስለሚያስቡ የማዳበሪያ እጥረት እንዳለ በማሰብ መሆኑን በመጥቀስ በተጨባጭ ግን ለመዝራት የሚያግዳቸው የማዳበሪያ እጥረት እንደሌለ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። ክልሎችም ቶሎ ዘር በሚዘሩ አካባቢዎች ማዳበሪያውን በማዛወር ጭምር በቂ ማዳበሪያ እያቀረቡ መሆኑንም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2011
አጎናፍር ገዛኸኝና ይበል ካሳ