አዲስ አበባ፡- አገሪቱ ከአቅሟ በላይ ተበድራ በርካታ ፕሮጀክቶችን በመጀመሯና በውስብስብ አሰራሮች ምክንያት ታሞ የነበረው ኢኮኖሚ መዳን መጀመሩን መንግሥት አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊዎች ትናንት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ አገሪቱ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች በርካታ ብድር በመውሰድ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምራለች።
ነገር ግን በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት ባለማጠናቀቋ የአገሪቱ ብድር ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት እስከ 31 በመቶ ደርሷል። ከዚህም በተጨማሪ የነበረው ፖሊሲ ችግር የነበረበት በመሆኑ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ እንደነበርና መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች ከችግሩ መውጣት መጀመሩን ገልጸዋል።
የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ መኮንን፤ ኢኮኖሚው ታሞ፤ የታቀደውን የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሳያሳካ አገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቷት ነበር። ከፍተኛ የዕዳ ክምችት ፈጥሯል። የማይጣጣም የወጪና ገቢ ተከስቷል። ከፍተኛ ማትጊያ ሲደረግባቸው የነበሩት ዘርፎችም ውጤት አልነበረባቸውም። በአጠቃላይ ቀደም ሲል ተይዞ የነበረው መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ አልተቻለም ብለዋል።
መንግሥት የታመመውን ኢኮኖሚ ለማስተ ካከል ከፍተኛ ግምገማ በማካሄድ ከበሽታው እንዲያገግም ተደርጓል። አብዛኛውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመንግሥት ሲካሄድ የነበረውን አቅ ጣጫ በመንግሥትና በግሉ የሚሰራው ተለይቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። መንግሥት የግሉን ሴክተር ለመደገፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራ እንዲያከናውን አቅጣጫ ተሰጥቶ ሥራ ተጀምሯል።
ምቹ ሁኔታም ለመፍጠር መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማቆም ነባሮቹ እንዲያልቁ የማድረግ ሥራዎች አከናውኗል። በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉትን ችግ ሮች ዘርዝሮ በመለየት ሥራ ተጀምሯል። የህግ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው።
የማትጊያ ስርዓቱን ለማስተካከል በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር በማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። አዳዲስ የኢኮኖሚ ምንጮችን የመለየትና ተጀምረው በትናንሽ እንቅፋት የቆሙ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዋል። ኢኮኖሚው ከበሽታው እየዳነ መሆኑን የሚያሳየው የፕላን ኮሚሽን ባደረገው ግምገማ 9ነጥብ2 በመቶ እንደሚያድግ ትንበያ ሰጥቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ፤ የግሉ ዘርፍ የሥራ ዕድል እንዲፈጥርና በኢኮኖሚው ውስጥ ዋና ተዋናይ እንዲሆን 40 የሚሆኑ የህግና የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አንስተዋል።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያወጧቸው መረጃዎች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ በአፍሪካ ኢንቨስትመንት ከሚስቡ አምስት አገራት መካከል አንዷ ናት። አገሪቱ ካላት ህዝብና እምቅ ሃብት አንፃር ገና ብዙ መስራት አለብን። ይህንን ለማሳካት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በአገሪቱ ያለውን የሰላም ዕጦት ለመቅረፍ ለዜጎች ሥራ ፈጥሮ ወደ ሥራ ማስገባት ዋና መፍትሄ ነው። ይህን ለማድረግ መንግሥትና ህዝብ መተባበር አለበት። ሥራውን የሚፈጥረውም መንግሥት ሳይሆን የግሉ ዘርፍ ነው። ከመንግሥት የሚጠበቀው ለዚህ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ