የማዕድን ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ቢሆንም፣ ሀገሪቱ ያላትን የማዕድን ሀብት ለይቶ አውቆ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውልና በሥርዓት እንዲመራ ከማድረግ አኳያ ብዙ እንዳልተሰራ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ዋንኛው ዘርፉን በሥርዓትና በተቀናጀ መልኩ ለመምራት የሚችሉ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች አለመኖራቸው መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እንደ ሀገር ዘርፉ ብዙም ያልተሰራበት እንደመሆኑ ልምድ ያካበቱ ብዙ ባለሙያዎች አለመኖራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ያሉትም ቢሆኑ በጽንስ ሃሳብ የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር ለመለወጥ ሲቸገሩ ይስተዋላል። የባለሙያው የብቃት ክፍተት ዘርፉ ባለሙያ እንዳይደገፍ ያደርገዋል፤ ይህም ክፍተቶች እንዲፈጠሩና ወጥ የሆነ የአሰራሩ ሥርዓት እንዳይኖር ምክንያት ይሆናል። ችግሩን ከሥር መሠረቱ ለመፍታት ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጀማሪዎቹ ልምድና ተሞክሮ እንዲቀስሙ ማድረግ ላይ የሚሰራ የሙያ ማህበር እንዲኖር የግድ ይላል።
የኢትዮጵያ ጂኦሳይንስ ማዕድን ምህንድስና ማህበር የተቋቋመውም በማዕድን ዘርፉ አንጋፋና ጀማሪ ባለሙያዎችን በአንድነት አሰባስቦ የሚይዝ የሙያ ማህበር መኖሩ ለዘርፉ እድገት ወሳኝነት ያለው መሆኑ ስለታመነበት ነው።
ዶክተር ታረቀኝ ታደሰ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ የኢትዮጵያ ጂኦሳይንስ ማዕድን ምህንድስና ማህበር ፕሬዚዳንት እና በጂኦሎጂና በማዕድን ዘርፍ አማካሪም ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ የጂኦሳይንስ ማዕድን ምህንድስና ማህበር የተመሰረተው እ.ኤ.አ 1992 ነው። አብዛኛዎቹ የማህበሩ አባላት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች /በሥነ ምድር፣ በጂኦሎጂ ፣ በሃይድሮሎጂ፣ በማዕድን ፍለጋ እና በመሳሰሉት/ ላይ የሚሰሩ ናቸው። ማህበሩ በተለያዩ የሥነ ምድር ሙያዎች የሰለጠኑ፣ የተማሩ፣ በማዕድን ቁፋሮ ዲዛይን /ማይኒግ ኢንጂነሪንግ/ እንዲሁም በውሃ ላይ በአጠቃላይ በሥነ ምድር ጥናት የሚሰሩ ሳይንቲስቶችን፣ ተመራማሪዎችን፣ አስተማሪዎችንና ምሩቃንን አቅፎ ይዟል።
ማህበሩ በዋናነት የሙያ ማህበራትን ብቃት ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ሲሰራ ቆይቷል። ስልጠናዎችን መስጠት፣ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ኮንፍረንሶችን በማዘጋጀት ጥናታዊ ጽሑፎች እንዲቀርቡ በማድረግ ለዘርፉ ግብዓትና ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎችን ይሰራል። መንግሥትም ሆነ የዘርፉ ኃላፊዎች የሚያስፈልጓቸው ሙያዊ ጉዳዮች ሲኖሩ በሥነ ምድር ጥናት አንጋፋና የረጅም ዓመታት ልምድ ያላቸው ብዙ ባለሙያዎች ስላሉት ልምዳቸውንና እውቀታቸውን ያጋራል፤ ያማክራል።
ማህበሩ በሙያው ረጅም ዓመታትን ያገለገሉትንም ሆነ አዲስ ተመራቂ ተማሪዎችን ያካተተ በመሆኑ ስለሙያው ጥቅም፣ እድገትና ሙያው ለሀገር እያበረከተ ስላለው አስተዋጽኦ እና በማዕድን፣ በውሃ እና በኮንስትራክሽን ዘርፎች የሚሰሩ ሥራዎችን በተመለከተ ባለሙያዎቹ ያላቸውን እውቀትና ልምድ ማካፈል ያስችላል። በተለይ የምድር ሀብትን የሚጠቀሙ ማንኛቸውም ዓይነት ዘርፎች ሀብቱን በተገቢው መልኩ በትክክል ጥቅም ላይ እንዲውል በምርምር የተገኙ ውጤቶችን በማሳወቅ ትክክለኛ ሥራ እንዲሰራ የባለሙያዎችን አቅም የመገንባት ሥራዎችንም እንደሚሰራ ይናገራሉ።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የማህበሩ አባላት ባለሙያዎች በመሆናቸው በሁሉም ዘርፎች በተለያየ ቦታዎች ይሰራሉ። ለአብነት በማዕድን ሚኒስቴር፣ በማዕድን ቁፋሮ በተሰማሩ የግል ኩባንያዎች፣ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ ባለሙያዎችን ያካተተ ነው። ማህበሩ ሥራዎች ጥራታቸውንና ብቃታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ አቅም የመገንባትና የማማከር ተግባር ያከናውናል። መንግሥት በዘርፉ የፖሊሲ አጀንዳዎች ሲያስፈልገው አጥንቶ በማቅረብ የተሻለ አሰራር እንዲኖር ያደርጋል። ሙያው በትክክል ለሀገር ጥቅም እንዲውል ለማድረግ የሚያስችሉ ሙያዊ ምክረ ሃሳቦችን ይጠቁማል።
በሌላ በኩል ለማህበሩ አባላት ሰልጠና በመስጠት ያበቃል፤ ሥራዎች ላይ በማወያየትና ጥራታቸው ከፍ እንዲል ማድረግ እና የመሳሳሉ ተግባሮችን ያከናውናል። ለአብነትም የጥናት ውጤቶች እንዲታተሙና ለሕዝቡም ሆነ ለሳይንቲስቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ያደረጋል። ጥሩ ተሞክሮ ይሆናሉ ተብለው የተለዩትን አሰራሮች በመውሰድ ሥራ ላይ የሚውሉባቸውን ሁኔታዎች ያመላክታል።
‹‹ማህበሩ ዘርፉ ብቃት ያለውን ሙያተኛ እንዲጠቀምና ባለሙያውም በተሻለ መልኩ ለሀገር ጥቅም እንዲሰጥ ለማድረግ እየሰራ ነው›› የሚሉት ዶክተር ታረቀኝ፤ በማዕድን ዘርፉም ሆነ በሁሉም የሥነ ምድር ሙያዎች የሰለጠኑ ባለሙያዎች የሙያ ብቃት እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። ለእዚህም የተሻለ ቴክኖሎጂ በማፈላለግ ባለሙያዎች የሚጋሩበትን ሁኔታ በመፍጠር በየዘርፉ ጥሩ እንዲሰራ የማብቃት ተግባሮችን ያከናውናል ይላሉ።
ማህበሩ በፖሊሲም ሆነ በስትራቴጂ እና በሌሎች ሙያዊ ጉዳዮችም የማማከር ሥራን ይሰራል ሲሉ ጠቅሰው፣ የማማከር ሥራው በተለይ በመንግሥት ደረጃ የሚሰጥ ከሆነ በምን መልኩ መሥራት ይቻላል በሚለው ላይ አንጋፋ ባለሙያዎች እንዲወያዩበት በማድረግ የደረሱበት ግኝት በሰነድ ተዘጋጅቶ ለጠየቀው አካል እንደሚቀርብም ይገልጻሉ።
የማህበሩ አባላት በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ እንደመሆናቸው የሰለጠኑ፣ የተመረቁና የሚመራመሩ (ከየዩኒቨርሲቲዎች፣ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ከግሉ ዘርፉ የተውጣጡ) ባለሙያዎች ያሉበት መሆኑን ያመላክታሉ። አባላቱ ሥራዎችን በመመልከት ምን እየተሰራ ነው? ምንስ ጎድሏል የሚሉ ጉዳዮችን በማየት ሙያዊ እይታቸውን የሚሰጡበት መሆኑንም ይገልጻሉ።
እንደ ዶክተር ታረቀኝ ገለጻ፤ በአሁን ወቅት በየክልሉ ለማዕድንም ሆነ ለውሃ ፍለጋ የቁፋሮ ሥራዎች እየተካሄዱ ቢሆንም፣ እነዚህ ሥራዎች ሲሰሩ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባል። በየክልሉ ካሉት ሙያተኞች አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። በዚህም የተነሳ መሬት ላይ ባለው ሥራ በሙያው ብዙም የበቁ አይደሉም፤ ማህበሩ ለወጣቶቹ በማዕድን ፍለጋ፣ ቁፍሮና የምርት ፈቃድ አሰጣጥ አሰራሮች ላይ ስልጠና ይሰጣል። ስልጠናው በየክልሉ ያሉ ባለሙያዎች ዘርፉን በብቃት በመምራት እንዲሰሩ እና የሥራውን ትክክለኝነት ማረጋገጥ እንዲችሉ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው። ማዕድን ሲቆፈር አካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ብክለት እንዴት መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስተካከል ይቻላል በሚለው ጭምር ስልጠና በመስጠት አብሮ መሥራት የሚቻልበት ሥርዓት መዘርጋት ያስችላል። በተለይ አቅም የመገንባት ሥራዎች ላይ በትኩረት ይሰራል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ቦታዎች ላይ በሚባል ደረጃ ለማዕድናት ፍለጋ በሚል በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ቁፋሮ እየተካሄደ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ታረቀኝ፤ ቁፋሮው ሥርዓት እንዲይዝ፣ ሕጋዊ እንዲሆን፣ አካባቢን እንዳይበክል ለማድረግ፣ ቁፋሮው በመካሄዱ አካባቢው ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ዓለም አቀፍ ተሞክሮና ልምድ ምን ይመስላል በሚለው ላይ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ስልጠና የሚሰጥበትና በዘርፉ የተሻለ ተግባር ማከናወን የሚያስችል ተግባር የሚከናወንበት ሁኔታ እንዳለም አብራርተዋል።
‹‹የሙያ ማህበሩ ለአሥር ዓመታት ያህል በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እምብዛም እንቅስቃሴ አላደረገም። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን በአዲስ መልኩ ሥራ ለመጀመር አዲስ አመራር ተመርጦ በተደራጀ መልኩ መሥራት ተጀምሯል ሲሉም ገልጸዋል። በባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ መካሄዱን ጠቅሰው፣ በመድረኩም ከክልሎች፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች የተውጣጡ 350 ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል። ማዕድን ዘርፍ ያሉት ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ምንድን ናቸው? በሚሉት ዙሪያ ውይይት መደረጉን አስታውቀው፣ ግኝቱንም በሰነድ በማዘጋጀት ለመንግሥት አካላት ለማቅረብ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የማህበሩ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል።
በማዕድን ዘርፍ ከታዩት ችግሮች መካከል አንዱ ተደርጎ የተነሳው የአቅም ውስንነት ነው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የአቅም ውስንነቱ በማዕድን ዘርፉ በተለይ በየክልሉ፣ በየዞኑ እና በየወረዳው ያለውን ባለሙያ ማብቃትን እንደሚፈልግ አመላክተዋል። ማህበሩም ወጥ የሆነ አስራር እንዲሰራና በማዕድን ዘርፉ የሚከናወኑ ተግባሮች መንግሥት ያስቀመጠውን ግብ እንዲያሳኩ ለማድረግ፣ በእውቀትና በሥርዓት ተመርቶ የሀገር ኢኮኖሚ እንዲደግፍ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚሰሩም አመልክተዋል።
በተመሳሳይ ከኢንዱስትሪ ጋር በመሥራት የማዕድን ግብዓት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች አቅም ማደግ ይጠበቃል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ 80 በመቶ ያህሉ ኢንዱስትሪዎች የማዕድን ግብዓቶች የሚጠቀሙ ናቸው። የማዕድን ግብዓት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ምን ያህል ናቸው? ግብዓቶቹን በደንብ እንዲጠቀሙ ምን መደረግ አለበት? ሌሎች ለምን ግብዓቶቹን አልተጠቀሙም? ከውጭ የሚገባውን የማዕድን ውጤትስ በሀገር ውስጥ እንዴት መተካት ይቻላል? በሚሉት ላይ በማህበሩ በኩል ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከውይይቱ የተገኙ ግብዓቶች ደግሞ ተጠናክረው እንዴት ሥራ ላይ ይዋሉ? የሚለው ደግሞ ዲዛይን እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ማህበሩ በዘርፉ ለተሰማሩ አምራቾች እድገት የሚሆነውን አቅጣጫ በማሳየት ሙያዊ ድጋፍ ይደረጋል ሲሉም አመልክተው፣ በኢንዱስትሪው፣ በማዕድን ዘርፉም ሆነ በውሃው ዘርፎች ብቃት ካለው ባለሙያ ጋር በተያያዘ ያለውን ክፍተት በመለየት ክፍተቱን ለመሙላት የስልጠና እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። በዘርፎቹ የተሻለ አሰራር እንዲመጣ ለማድረግ የሚያከናውነው ይህ ተግባር ሀገር ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ገቢ ለማሳደግ እንደሚረዳም አስረድተዋል።
‹‹እንደ ሀገር በዘርፉ ብዙ የተማረ የሰው ኃይል እየተመረቀ ቢሆንም፣ የሰው ኃይሉ በትምህርት ሥርዓቱ በጽንስ ሃሳብ ይበልጽግ እንጂ በተግባር የበለጸገ ግን አይደለም›› ሲሉ ጠቅሰው። በተግባር ያልበለጸገው ሲሰራም ሆነ ሲመራ መቸገሩ እንደማይቀር አስታውቀዋል። ተመራቂዎቹ በጽንሰ ሃሳብ የጨበጡትን እውቀት ሥራ ላይ ማዋል እንዲችሉ በልምድ ከተካኑ ባለሙያዎች ጋር መሥራትና ልምዱን መቅሰም እንዳለባቸው አስታውቀዋል። ‹‹ለዚህም ነው እንደዚህ ዓይነት የሙያ ማህበር እንዲኖር የሚያስፈልገው›› የሚሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ ማህበሩም የዘርፉ ባለሙያዎች በሙያና በአሠራር ሥርዓቱ እንዲካኑ፣ የተማሩትን በተግባር እንዲተረጉሙ ለማድረግ እና ግር የሚላቸው በማጥራት የተሻለ እንዲሰሩ የሚረዳ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት እንዳሉት፤ የማዕድን ዘርፍ አሁን ላይ የሀገር ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምሰሶ ተደርጎ ትኩረት ያገኘበት ጊዜ ነው። መንግሥትም የሚደግፉ ስለሆነ ዘርፉ ይህንን እድል ተጠቅሞ ብቃት ያለው ባለሙያ እንዲኖርና የአሠራር ሥርዓቱ ተሻሽሎ በግሉ ዘርፍ ሆነ በመንግሥት ረገድ የሚሰሩ ሥራዎች የመገምገም ብቃት ማደግ ይጠበቅበታል። በተለይ የግል ዘርፉ ሥራዎች አብዛኛውን ጊዜ አዋጭነት መሀከል የሚያደርጉ እንደመሆናቸው ሥራዎቹ በትክክል መሥራታቸውን መገምገም የሚችል ብቃት ያለው የመንግሥት አካል ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል በዘርፉ የግል ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲቻል መረጃዎችን አሰባስቦና አጠናክሮ በየጊዜው የተደራጀ መረጃ የማቅረብ አቅም መፍጠርም ይጠበቃል። መረጃዎች በማዕድን ሚኒስቴርና በጂኦሎጂ ኢንስትቲዩት ተደራጅተው በደንብ ተጠናክረው መገኘት አለባቸው። ላብራቶሪ ተደራጅቶ ማዕድናቱ በትክክል ተለይተው የግል ባለሀብቱ እንዲያለማቸው መደረግ ይኖርበታል። በዚህ መልኩ ሲሰራ ደግሞ ማዕድናትን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ከማግኘት ጎን ለጎን ሀገሪቷን በደንብ ሊያሳደጉ የሚችሉ ማዕድናትን ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት በሚሆኑት ላይ መሰራት አለበት።
የኢንዱስትሪ ግብዓት ማዕድናትን በሀገር ውስጥ በማምረት ለህብረተሰቡ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ ‹‹ወደ ውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኙ ማዕድናት እንዳሉ ሆነው በሀገር ውስጥ ማዕድናትን እያመረት መጠቀም መቻል አለብን ሲሉ ያስገንዝባሉ። ማዕድናቱ ለፋብሪካ ግብዓት ሆነው የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚኖሩበትም አመልክተዋል። ይህም በመንግሥት እየተሰራበት ቢሆንም ይበልጥ ማደግና ማጎልበት እንዳለበት ተናግረው፣ ለዚህም ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ተከትሎ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ለማድረግ መሟላት ያለባቸው ሁሉ እንዲሟሉ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል። በተለይ በመንግሥት በኩል የማዕድናት ምርመራንና የመስክ ዳታ ስብሰባ ጨምሮ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚቻልባቸው ግብዓቶች እንዲኖሩ ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የግሉ ዘርፍም ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ጥራት ያለው ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል ይላሉ።
በዘርፉ ትላልቅ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ እድሉን በመስጠት ኢንቨስትመንቱ እንዲጠናከር በመሥራት የባለሙያውን አቅም በመገንባት፣ ቴክኖሎጂና ግብዓቶችን በማሟላት ከተሰራ የማዕድን ዘርፉ የኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ ማለት ይችላል ሲሉ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታረቀኝ ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም