ኢትዮጵያ የብዙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት የሚከበሩባት ሀገር ናት። በክርስትና እምነት ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸው የጥምቀትና የመስቀል ደመራ በዓላትን መጥቀስ ይቻላል። በእስልምና እምነትም እንዲሁ የተለያዩ በዓላት አሉ። ከዚህ ባሻገር በሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ የሚከበሩ እንደ ሲዳማ ፊቼ ጨምበላላ ዓይነት ታላላቅ በዓላት አሏት። እነዚህ የማይዳሰሱ በዓላት የቱሪስት መስህብ በመሆን ለሀገሪቱ የሚያበረክቱት የኢኮኖሚ ፋይዳ ትልቅ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ከእነዚህ በዓላት መካከል በዩኔስኮ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት አካል የሆነውና በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በትልቅ ደረጃ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል አንዱ ነው።
የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከሚከበሩ በዓላት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዝ ክብረ በዓል ነው። በዓሉ የሚከበረው የክረምት ወቅት አልቆ የፀደይ ወቅት በሚጀምርበት ወቅት ነው። የዝናብ፣ የጎርፍ እና የጨለማን ወቅት አሻግሮ ለፀደዩ ብርሃን ላዳረሰ አምላክ ምስጋና ማቅረብ ላይ ያተኩራል ማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ የኢሬቻ በዓል በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ በብዙዎች የሚከበር በሕዝብ ቁጥር ተወዳዳሪ የሌለው በዓል ነው። ይህ ማለት የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የመላ ጥቁር አፍሪካውያን ታላቅ በዓል እየሆነ ስለመምጣቱ ማሳያ ነው።
የኢሬቻ አጀማመር በገዳ አቆጣጠር (አንድ ገዳ 7 ዓመት ከ8 ወር ወይም 8 ዓመት) የሚቆይ ሲሆን፤ ያ ሲሰላ ኢሬቻ ከ6 ሺህ 660 ዓመት በፊት የተጀመረ እንደሆነ አዋቂዎች ይናገራሉ። የገዳ ሥርዓት ባለበት፤ የኦሮሞ ሕዝብ በሚገኝበት ሁሉ ኢሬቻ አለ። በዓሉ ዋቄፈና ከተባለውና ከጥንቱ የኦሮሞ ሕዝብ እምነት የፈለቀ እንደሆነም ይጠቀሳል።
የማኅበረሰብ ባሕላዊ መሪዎች የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው (ዋቃ) ምስጋናውን ለማድረስ የኢሬቻ በዓልን ያከብራል ይላሉ። ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው። ሕዝቡ ክረምቱ በማለፉ በኢሬቻ ቀን ምስጋናውን ለፈጣሪ ያቀርባል። በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ መስከረም ላይ ይገናኛል። ሕዝቡም ክረምቱን በፈጣሪ ፍቃድ የሞላው ውሃ ጎድሎ ከዘመድ አዝማድ አገናኝን ብሎ ምስጋናውን ለፈጣሪ ያቀርባል።
የኦሮሞ ሕዝብ የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ሲወጣ እንደ ሳር ወይም አበባ ያሉ እርጥብ ነገሮችን በእጁ ይዞ ይወጣል። የእዚህ ትርጉምም ‹‹ ፈጣሪያችን ሆይ አብቦ ፍሬ ያፈራው፤ አንተ ያጸደቅከው ነው። ለዚህም እናመስግንሃለን’ በማለት እርጥብ ነገር ተይዞ ይወጣል›› ሲሉ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ።
በበዓሉ ተሳትፎ ሰፊ ድርሻ ካላቸው አካላት መካከል ወጣቶች በቀዳሚነት ታጣቀሽ ናቸው፤ ወጣት ገመቹ አሕመድ ከበዓሉ ተሳታፊና አስተባባሪ ከሆኑ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። እርሱ እንደሚናገረው፤ የኦሮሞ ሕዝብ ገዳ የሚበል የሃይማኖት፣ የአስተዳደርና የዕርቅ መሰል እሴቶችን ይዞ የኖረ ሕዝብ ነው። ከዚህ ውስጥ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ ጌታውን የሚያመሰግንበት ሥርዓት አንደኛው ነው ይላል።
የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚከበር የሚገልጸው ወጣት ገመቹ፤ የመጀመሪያ ኢሬቻ ቱሉ የሚል ስያሜ ያለውና በተራራ ላይ የሚከበር መሆኑን ይናገራል። ሌላኛ በወንዝ ዳር የሚከበረው ኢሬቻ መልካ እንደሆነ ያስረዳል። በተራራ ላይ የሚደረገው ኢሬቻ በጋውን በሰላም አሰልፈናል ክረምቱ ደግሞ የሰላም ይሁንል ተብሎ ለፈጣሪ አደረ የሚሰጥበት ኩነት ነው ይላል።
በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ወጣቶች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚገልጸው ገመቹ፤ በበዓሉ በቅድሚያ ልጃገረዶች፣ በመቀጠል አባ ገዳዎች በሶስተኛ ደረጃ ወጣቶች ሆነው ወደ ወንዝ ‹‹መሬሆ›› እያሉ ስወርዱ፤ ወጣቶች ወይም ቄሮዎች ኃላፊነት አለባቸው። እንደ ወጣቱ ገለፃ፤ በዓሉ ያለ አንዳች ኮሽታ ከየትኛውም ፖለቲካዊና መሰል ጉዳይ ነፃ ሆኖ የሕዝብ በዓል እንደመሆኑ እሴቱን ጠብቆ ፈጣሪውን ብቻ በሚያመሰግንበት መንገድ ተከብሮ እንዲያልፍ ወጣቶች መወጣት ያለባቸው ሚና ትልቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር በአዲስ አበባ፣ በሸገር ከተማና በቢሾፍቱ በተለያዩ አደረጃጀቶች ተደራጅተው የሶስቱም ከተማ ወጣቶች አንድ ላይ በመሆን እየሰሩ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ገመቹ በኢሬቻ በዓል አገልግሎት ላይ የሚውሉ ማንኛቸውም ነገሮች ባሕልና እሴቱን ጠብቀው እንዲከበሩ በወጣቶች የሚዜሙ የባሕል ጨዋታዎች ሳይቀሩ ተሰንደው ዝግጅት ተደርጎ የባሕል ቡድን ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተለያዩ ሀገራት የበዓሉ ታዳሚ ለመሆን የሚመጡ እንግዶች የበዓሉን ምንነትና ታሪክና እሴት እንዲያውቁ የማስተዋወቅ ሥራ ለመሥራት ወጣቶች የኢሬቻ አምባሳደር ሆነው ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተዋል ያለው ወጣት ገመቹ፤ በደህንነት በኩል በበዓሉ ከሚያዙ ጽሑፎች ኢሬቻን ብቻ የሚገልጹ እንዲሆኑ፣ የሚያዝ ባንዲራ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እውቅና ያለው ባንዲራና የአበገዳ ባንዲራ እንዲሆን በዚህ አግባብ ወጣቶች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግሯል።
በሸገር ከተማ አስተዳደር ስር የሚከበሩ ሁለት የኢሬቻ በዓላት አሉ። በሰበታና ቡራዩ የሚከበሩ ሌሎች የኢሬቻ በዓላትም አሉ። ይህ ማለት በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ ከሚከበሩ በዓላት ጋር አንድ ላይ ትልቅ ኩነት ሆነው የሚያልፉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ በሰላም ተከብረው እንዲያልፉ በየደረጃው ያለው ወጣት በየአካባቢው ተደራጅቶ ተወያይቶ የበዓሉን ዕለት እየጠበቀ እንደሆነ ወጣት ገመቹ ገልጿል።
ኢሬቻ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ባሕል እየሆነ መጥቷል የሚለው ወጣቱ፤ የዓለም ጥቁር ሕዝብ የራሱ የሆኑ እሴቶች ሃይማኖቶች፣ መተዳደሪያ ሕጎች አሉት። ኢሬቻ ከዚህ አንፃር ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው ይላል። ማንኛውም ሰው ኢሬቻ ለማክበር ከመሄዱ በፊት ለአምላኩ ምስጋና ከመቅረቡ በፊት ሰው ሁሉ መታረቅ አለበት። ኢሬቻን ማክበር የሚቻለው እርስ በእርስ ሰላም አውርዶ፤ ሆድ ንፁህ ሆኖ ከቂምና በቀል ወጥቶ ነው የሚለው ወጣት ገመቹ፤ ይህ እንደ ሀገር ሰላምን ለማውረድ ዕርቅን ለማስተማር ትልቅ ዋጋ ያለው በዓል መሆኑን ያስረዳል።
ይህንን በዓል ደግሞ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አውቀው የእራሳቸው አድርገው ተቀብለው ማክበር አለባቸው ብሏል። በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የባሕልና የሳይንስ ተቋም (UNESCO) ተመዝግቦ ዓለም አቀፍ ጥበቃ ማግኘት እንዲችል መሥራት እንዳለባቸው ተነግሯል።
የኢሬቻን ትላልቅ ዕሴቶች ለዓለም ማስተዋወቅ እንዳለ ሆኖ፤ በበዓሉ ላይ የተደረጉ የስም መጥፋት ሥራዎች ትክክለኛውን የኢሬቻ ምንነት በማጉላት ማስተካከል ያስፈልጋል ብሏል። ወጣት ገመቹ እንደገለፀው፤ በዓሉ ያለው አንድምታ መልካም ብቻ እንደሆነ ሁሉም ግንዛቤ እንዲኖረው መሥራት ያስፈልጋል።
በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው በዓሉን ለማክበር ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው ባዶ እጁን አይደለም። የሚመጣው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይዞ ነው የሚለው ወጣት ገመቹ፤ ይህንን ገንዘብ አዲስ አበባ ላይ ለአገልግሎት ያውለዋል። ይህ ለከተማዋ ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም ነው ብሏል። ስለዚህ የአዲስ አበባ ሕዝብ ኢሬቻን ብቻ ሳይሆን ሌሎች በዓላትም በከተማዋ እንዲከበሩ ተባባሪ መሆን አለበት ብሏል።
ወጣት ከድር እንዳልካቸው የኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ነው። እርሱ እንደሚናገረው፤ ኢሬቻ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል ሲሆን፤ የሰላም ምልክት ተደርጎም ይወሰዳል ይላል። ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ሰማይና ምድርን ለፈጠራ አምላክ ምስጋና የሚያደርስበት በዓል ነው። ከዘመን ወደ ዘመን ለሻጋገረ አምላክ ምስጋና ያቀርባል። የሚመጣውን ዘመንም አምላክ የብራ አድርግልን ብሎ ጸሎቱን ለፈጣሪ ያቀርባል ይላል።
ወጣት ከድር እንደሚናገረው፤ በዚህ በዓል የወጣቶች ኃላፊነት ትልቅ ነው። እንደ ክልል በበዓሉ ዙሪያ ከሁሉም የወጣት አደረጃጀቶች ጋር የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ውይይት ተደርጓል። በዓሉ የሕዝብ ሆኖ ከበዓልነት ባፈነገጠ መልኩ ችግርና ሁከት ለመፍጠር የተዘጋጁ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ፤ ወጣቶች ይህንን አውቆ አካባቢያቸውን በንቃት መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁሟል። ከኦሮሚያ ከአራት ሚሊየን በላይ ወጣቶችን በዚህ ጉዳይ ላይ በማወያየት በዓሉ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንደተሰሩ ተናግሯል።
በዓሉ ምንም መሰናክሎች ሳይገጥሙት በሰላም እንዲጠናቀቅ ልዩ ዝግጅት እንደተደረገ የተነገረው ወጣት ከድር፤ በየአካባቢ ካሉ ወጣቶች ተመልምለው ወጥተው በየደረጃው ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ተደርሷል። ከአዲስ አበባ፣ ከሸገር ከተማ ወጣቶችን በመመልመልና ውይይት በማድረግ በአዲስ አበባ የሚከበረው የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ከፀጥታ ስጋት ነፃ ሆኖ እንዲከበር ዝግጅት ተጠናቋል ብሏል። በቢሾፍቱም እንዲሁ ወጣቶች ተደራጅተው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ ክብረ በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጎ መጠናቀቁን ተናግሯል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ በሸገር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች “በፎሌ” በመደራጀት ስለምን ለማስጠበቅ ሥራዎች እንደተሰሩ የሚናገረው ወጣት ከድር፤ ከየአካባቢው ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ወጣቶች ደግሞ በዓሉ በሰላማዊ መልኩ እንዲከበር የየድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የጋራ መግባባት ለመፍጠር ተሰርቷል። ከወጣቱ ባሻገር በአጠቃላይ ሕዝቡ በዓሉ የኦሮሞ ሕዝብ የምስጋና በዓል እንጂ የየትኛውም ቡድን የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ መድረክ እንዳልሆነ ተገንዝቦ፤ ሁሉም የበዓሉ ታዳሚ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ይጠበቃል ብሏል።
ኢሬቻ በአዲስ አበባ ብቻ በሚሊየን የሚቆጠሩ ስዎች ተገኝተው የሚያከብሩት በዓል ነው የሚለው ወጣት ከድር፤ ይህ ትልቅ ፌስቲቫል በምንም ሁኔታ በሚፈጠሩ አሉታዊ ነገሮች መጠልሸት የለበትም ለከተማዋ ተጨማሪ ጥቅምና ውበት ሆኖ ተከብሮ ማለፍ አለበት። ይህንኑ ወጣቱ በደንብ ተገንዝቦ ያለ ምንም ችግር በዓሉ እንዲከበር እራሱ በዓሉን በሰላም ማክበር ይጠበቅበታል ብሏል። በሌላ በኩል ደግሞ በበዓሉ ሰርጎ በመግባት ሁከትና ግርግር በመፍጠር በዓሉን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል ካለ ደግሞ በንቃት በመጠበቅ ለኢሬቻ በዓል ድምቀት የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነ ተነግሯል።
በዓሉ የሚከበረው አባ ገዳዎች ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰራት ነው። ግልፅ የሆነ መመሪያ ደግሞ ከአባገዳዎች ተሰጥቷል፤ ወደ በዓሉ ማንኛውም ሰው ሲመጣ ኢሬቻን ለማክበር እንጂ ሌላ ዓላማ ይዞ መምጣት የለበትም ብሏል። ይህንን ወጣቱ በውል ተረድቶታል የሚለው ወጣት ከድር፤ ይህ ማለት በዓሉ ላይ ይዞ መገኘት የተፈቀደውንና የተከለከለውን ነገር በደንብ መገንዘብ እና ይዞ መምጣት የለበትም የተባለውን ነገር ይዞ መምጣት የለበትም ብሏል።
የኦሮሞ ባሕል የሚያስተምረው መከባበርን አንድነትን ፍትህን ነው የሚለው ወጣት ከድር፤ በበዓሉ የሚገኙ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክር መልኩ በአንድነት ማክበር ይጠበቅባቸዋል። ኢሬቻ ሰላም ዕርቅና ፍቅርን የሚሰብክ ነው ካለ በኋላ፤ ይህንኑ እሴቱን በጠበቃ መልኩ ለማክበር መዘጋጀት ተገቢ እንደሆነ ገልጿል።
ወጣቶቹ በመጨረሻ ባስተላለፉት መልዕክት የኦሮሞ ሕዝብ ቱባ ባሕል ከሚገለጽባቸው ሁነቶች አንዱ የሆነው የኢሬቻ በዓል ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱን ከፍ ማድረግ በሚቻልበት መልኩ እንዲከበር ወጣቶች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተናግረው፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ የተለመደ እንግዳ ተቀባይነቱን በማሳየት በዓሉን ለማክበር እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም