አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በተጠናቀቀው የ2011 በጀት ዓመት በምዝገባ ምክር፣ በመረጃና ተያያዥ አገልግሎቶች ለ31ሺ 950 ተገልጋዮች አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ። በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ካቀደው 17 ነጥብ 89 ሚሊዮን ብር መካከል 15 ሚሊዮን 291ሺ 705 ብር ገቢ መሰብሰቡንም ገለፀ።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርምያስ የማነብርሃን የጽሕፈት ቤቱን የ2011 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ፣ ጽሕፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት (ፓተንት)፣ በግልጋሎት ሞዴል፣ በኢንዱስትሪ ንድፍ፣ በአስገቢ ባለቤትነት (ፓተንት)ና በኮፒ ራይት ምዝገባ ለአመልካቾች የባለቤትነት የምስክር ወረቀት ሰጥቷል። የዘንድሮው አገልግሎትም ከ2010 የበጀት ዓመት አገልግሎት ጋር ሲነፃፀር በ13 ሺ 523 ብልጫ አለው።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ ጽሕፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ ሦስት ሺ 245 የንግድ ምልክቶችን መዝግቧል። ከነዚህም መካከል አንድ ሺ 980 ያህሉ የውጭ አገራት የንግድ ምልክቶች ሲሆኑ፣ በጽሕፈት ቤቱ ምዝገባ የተከናወነላቸው የአገር ውስጥ የንግድ ምልክቶች ቁጥራቸው መሻሻል እያሳየ ቢሆንም፤ አሁንም ድረስ ዝቅተኛ የሆነው በንግድ ምልክቶች ምዝገባ ረገድ ባለው የግንዛቤ ውስንነት ምክንያት ነው።
ከጽሕፈት ቤቱ ዓላማዎች መካከል አንዱ የቴክኖሎጂ ሽግግርን መደገፍ በመሆኑ ከዓለም አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር 11 የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ እንዲሁም የምርምር ተቋማት የየራሳቸውን የቴክኖሎጂ ድጋፍ ማዕከላትን እንዲያቋቁሙ ድጋፍ አድርጓል።
‹‹ጽሕፈት ቤቱ ከሰበሰበው ገቢ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው ከንግድ ምልክት ምዝገባ የተገኘ ነው። በበጀት ዓመቱ ከተመዘገቡት የንግድ ምልክቶች መካከል አብዛኞቹ የውጭ አገራት የንግድ ምልክቶች ናቸው። የአገሪቱ አንዳንድ ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም የምጣኔ ሀብቱ መቀዛቀዝ ከንግድ ምልክቶች ምዝገባ በሚገኘው ገቢ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ በማሳደሩ በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ በታቀደው ገቢ ላይ መጠነኛ የአፈፃፀም ጉድለት እንዲኖር አድርጓል›› ብለዋል።
ጽሕፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ሰጥቶ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ዓለም አቀፍ ግንኙነቱን የማስፋት ተግባር አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ኤርምያስ፣ በበጀት ዓመቱ ከቻይና ብሔራዊ አእምሯዊ ንብረት ድርጅት የስልጠናና አቅም ግንባታ ድጋፎችን ማግኘቱን ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከአውሮፓ ፓተንት ቢሮ ጋር በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በስልጠናና በሰው ሀብት ልማት እንዲሁም በፓተንት መረጃዎች አያያዝ ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረሙንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የአእምሯዊ ንብረቶች በቂ የሕግ ጥበቃ እንዲያገኙ የማድረግ፣ ግንዛቤን የማሳደግ፣ አእምሯዊ ንብረት በባሕል፣ በንግድና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለአገር ሁለንተናዊ ልማትና እድገት አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ምቹ ሁኔታ የመፍጠር እንዲሁም በአእምሯዊ ንብረት ጉዳዮች ላይ በሕግና በፖሊሲ መንግሥትን የማማከር ዓላማዎችን ይዞ የተቋቋመ ድርጅት ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2011
አንተነህ ቸሬ