ምርታማነትን በማሳደግ የሚገለጸው የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ውጤታማ ጉዞ

የሰው ልጅ በምድር ሲኖር ሊሟሉለት ከሚገባቸውና የግድ ከሆኑ መሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል አንዱና ቀዳሚው ምግብ ነው። ምክንያቱም በሰው ልጅ በልቶ የማደር እና ያለማደር እውነት ውስጥ የሚገለጡም፣ የሚመጡም በርካታ የሰውነትም የክብርም ጉዳዮች አሉ።

በሰው ልጅ በልቶ ማደር ውስጥ ዕድገት አለ፤ ጤና አለ፤ አምራችነት አለ፤ የአካልና የአዕምሮ ሚዛን መጠበቅ አለ። ከዚህ በተቃራኒው በሰው ልጆች በልቶ አለማደር ወይንም በምግብ ራስን አለመቻል ውስጥ፣ የጤና መቃወስ አለ፤ የአካልና አዕምሮ ሚዛን መዛባት አለ፤ ከአምራችነት ይልቅ የሰው እጅ ተመልካችነት አለ፤ ክብረ ነክነት አለ።

ይሄ እውነት እንደ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሕዝብና ሀገር ጭምር የሚገለጥ ነው። ምክንያቱም በልቶ ማደር ያልቻለ ግለሰብ ግለሰባዊ ክብርና ሌላም ጉዳዩን ትቶ ለምግብ ሲል የሌሎችን እጅ መመልከቱ አይቀሬ ነው። በልቶ ማደር ያቃተው ቤተሰብና ማኅበረሰብም እንደዚሁ። ይሄው ሃቅ በሕዝብና ሀገር ደረጃም የሚገለጽ ሲሆን፤ ችግሩ በዚህ ደረጃ ከፍ ብሎ የሚገለጽ ነው።

ምክንያቱም፣ ራሱን መመገብ ያልቻለ ሕዝብ የሌሎች ሕዝቦችን ደጅ መጥናቱ አይቀሬ ነው። ሕዝቦቹን መመገብ ያቃተው ሀገርም እንዲሁ የሌሎች ራሳቸውን መመገብ የቻሉ ሕዝቦችን ሀገር በር ማማተሩ የግድ ነው። ይሄ ሂደት ደግሞ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ክብሩን፤ ሀገርም እንደ ሀገር ሉዓላዊነቱን ቸል እንዲል ያስገድዳል።

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንም በዚህ ረገድ በአንድ በኩል አቅምን አሟጦ ባለመሥራት፤ በሌላ በኩል በተፈጥሮ አደጋዎች (ድርቅና ጎርፍን በመሳሰሉ) ምክንያቶች አያሌ ችግሮችን፤ አያሌም ፈተናና ጫናዎችን አሳልፈዋል። የበርካቶችን ደጅ ጠንተው፣ የብዙዎችን በር አማትረው ፊት ተነፍገዋል፤ አልያም ለድጋፍ ከተዘረጉ እጆች ጀርባ ያሉ ጣልቃ ገብነትን እንደ አመጣጣቸው ለማስተናገድ ተገድደዋል።

ይሄን መሰሉ ድጋፍ ታከክ የሆነ የእጅ ጥምዘዛ፣ የሉዓላዊነትና ክብር ጉዳይ ታዲያ በዚህ መልኩ ሀገርን እያሳፈረ፣ ዜጎችንም አንገት እያስደፋ መቀጠል ስለሌለበት፤ ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ይሄን ችግር ለመቀልበስ በሰፊው ተሠርቷል። ይሄም ኢትዮጵያ ያላትን መልክ እና ዘርፈ ብዙ አቅም በመለየት፤ ኢትዮጵያውያንም የሚያመላክትና የሚያስተባብራቸው ካገኙ ምንም አይነት ነገር መፈጸም የሚችል ኅብረት እንዳላቸው በመገንዘብ የተጀመረ ነበር።

እንደታሰበውም በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተጻፈበት ውጤት ተገኘ። በዚህም ስንዴ ከራስ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተቻለ። የሩዝ ፍላጎትንም በራስ አቅም መሸፈን ተቻለ። በፍራፍሬም ቢሆን ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትም፣ ለውጪ ገበያም ማድረስ ያስቻለ ውጤት ተገኘ። በቡና፣ ሻይ ቅጠልና ቅመማ ቅመምም የተመዘገበው ውጤት እጅጉን የሚያኮራ ሆነ።

በማሽላ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቅባትና ቅመማቅመም፣ በስንዴ፣ በእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ፣ በአጠቃላይ በአዝዕርት፣ በጥራጥሬ፣ በቅባትና ሌሎችም የግብርና ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙና መልከ ብዙ ተግባራት፤ ዛሬ ላይ በምግብ ራስን ለመቻል እና የክብርም፣ የሉዓላዊነትም ጥያቄን ለመመለስ ከሚደረገው ጥረት የተሻገረ ውጤት እየታየባቸው ያሉ ናቸው።

ምክንያቱም እነዚህ ተግባራት ዘርፈም፣ መልከም ብዙ መሆናቸው በአመጋገብ ሥርዓታችን ላይ የተመጣጠነ ምግብን ለማግኘት የሚያስችሉ ናቸው። ይሄ የተመጣጠነ የምግብ ሥርዓት ደግሞ ካልተቆራረጠና ዘላቂነት ካለው ምርታማነት ጋር ሲደመር፣ እንደ ሀገር እውን እንዲሆን ለሚጠበቀው የምግብ ሉዓላዊነት ግብ መድረስ መስፈንጠሪያ አቅም ይሆናል።

ምክንያቱም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራው በአንድ በኩል በዓይነት፤ በሌላ በኩል በብዛትና ቀጣይነት ባለው ምርታማነት የታጀበ ነው። ተግባሩም ከምግብ ዋስትና የላቀ፤ የምግብ ሉዓላዊነት መንገድን በጥሩ መነሳሳትና ውጤት ታጅቦ እንዲጀመር እድል የሰጠ ነው።

በመሆኑም በአንድ በኩል ምርታማነትን በማሳደግ፤ በሌላ በኩል የተለያዩ የምርት አይነቶችን የማምረት ሂደቱ ላይ እየታየ ያለው ከፍ ያለ ውጤት፤ ከምግብ ዋስትና ባሻገር ላለው የምግብ ሉዓላዊነት ጉዞ መሳካት ትልቅ አቅም ነውና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል!

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You