የኢሬቻ በዓልን በሰላም!

ከአዲስ ዓመት መግቢያ አንስቶ እስከ አሁን በሀገሪቱ በርካታ የአደባባይ በዓላት ተከብረዋል፤ እየተከበሩም ነው። በዚህም በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አዲስ ዓመታቸውን፣ ሌሎች ደግሞ የመስቀል ደመራ በዓልን በደማቅ ሥነ ሥርዓት አክብረዋል።

እነዚህ በዓላት በአደባባይ የሚከበሩና ከፍተኛ የሕዝብ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው ናቸው። በበዓላቱም ላይ ከሕፃናት አንስቶ እስከ አዛውንት፣ በሀገር ውስጥ ከሚኖሩት ውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ። በእዚህ ላይ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ ሀገር ጎብኚዎችም በዓላቱን ሲሉ ወደ ሀገሪቱ ይመጣሉ። እነዚህ ጎብኚዎች አዲስ አበባን ብቻ የሚጎበኙ አይደሉም፤ በዓላቱ በሚከበሩባቸው የተለያዩ ክልሎች ይሄዳሉ።

ይህ ኢትዮጵያውያን ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ጭምር እየተንቀሳቀሱ ቤተሰቦቻቸውን የሚጠይቁበት፣ የሚደግፉበት፣ በአጸፋው እነሱም የሚመረቁበት ወቅት፣ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ ፋይዳውም ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል።

ሀገሪቱም እነዚህ በዓላት ያላቸው ማህበራዊ ፋይዳ በሚገባ እንዲታይና ለሀገራዊ ጥቅም እንዲውል በተለይ ለቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ከፍተኛ ፋይዳ በመገንዘብ በትኩረት እየሠራች መሆኑ ይታወቃል። በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ በትኩረት እየሰራች እንደመሆኗ ይህ ወር ለዘርፉ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ታምኖበትም በስፋት እየተሰራ ነው።

የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ሀገራቸውን እንዲያውቁ፣ የውጭ ቱሪስቶች ሀገሪቱን እንዲጎበኙ እና የሀገሪቱ አምባሳደር እንዲሆኑ ይፈለጋል፤ በጉብኝታቸው ከፍተኛ ሀብት የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑም ከዚህ ሀብት ለመጠቀምም ጽኑ ፍላጎት አለ፤ ፍላጎት ብቻም ሳይሆን ከዚህ እምቅ ሀብት ለመጠቀም በርካታ ተግባሮች እየተከናወኑ ናቸው። ይህ ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲሰፋም የጉብኝታቸው ቆይታ የተራዘመ እንዲሆን ይፈለጋል፤ ይህ እንዲሆንም በስፋት እየተሠራም ነው።

እነዚህ በዓላት ያለ ምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲከበሩ ማድረግ ይጠበቃል። ለዚህም ነው መንግሥት ሁሌም በዓላቱ ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ ልዩ ዝግጅት እያደረገ ሲሠራ የቆየው፤ እየሠራ የሚገኘውም።

ለዚህም ነው የመስቀል ደመራ በዓልን ጨምሮ እስከ አሁን በክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የተከበሩት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአዲስ ዓመትና የመስቀል በዓላት በሰላም ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ ማድረግ የተቻለው።

ብዝሀነት መልኳም ልኳም በሆነባት ኢትዮጵያ እነዚህ በዓላት ያለ ምንም የጸጥታ ችግር መከበር መቻላቸው መንግሥት ምን ያህል በሰላም ላይ እየሠራ መሆኑን በሚገባ ያመለክታል። መንግሥት በተለያዩ በዓላት ወቅትም ይህንን ያደርጋል። የመስከረም ወር ግን ከእነዚህ በዓላት ወቅቶች ይለያል፤ በዚህ ወር አንድ እና ሁለት በዓላት ብቻ አይደሉም የሚከበሩት፤ በርካታ በዓላት ናቸው። እነዚህ በዓላት ሁሉ ያለ ምንም የጸጥታ ችግር መከበራቸው መንግሥት ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ምን ያህል እየተጋ መሆኑን ያረጋግጣል።

መንግሥትን ይህን ሲያደርግ የጸጥታ ኃይሎችን ብቻ ይዞ አይደለም፤ የሰላሙ ባለቤት ነው ብሎ በጽኑ የሚያምንበትን ሕዝብ ለእዚህ ዓላማ በማሳለፍም መሆኑ ይታወቃል። የበዓላቱ በሰላም መከበር ሲታሰብ ሕዝቡ የበዓሉም የሰላሙም ባለቤት እንደመሆኑ በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ሰርቷል ብሎ መግለጽ ይቻላል።

ይህ ለሰላም ያለ ቁርጠኝነትና ሰላምን የመጠበቅ ተሞክሮ በቀጣይ ሳምንት የኦሮሞ ብሔረሰብ ፈጣሪውን በሚያመሰግንበት የእሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔና በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ እንዲሁም በመላ ኦሮሚያ ክልልና በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች እንዲሁ እንደሚደገም ይጠበቃል።

ይህንንም በዓል በሰላም ያለ ምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገዋል። ሕዝቡም ይህ ለሁለት ቀናት የሚከበር በዓል ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር አስተዋጽኦ በማድረግ በኩል የማይተካ ሚና እንዳለው ይገነዘባል።

የበዓሉ ታዳሚዎች ከመላ ሀገሪቱ እንዲሁም ከውጭ ሀገሮች ወደ አዲስ አበባና ቢሾፍቱ በመንቀሳቀስ በዓሉን የሚያከብሩ እንደመሆናቸው በተለያዩ አካባቢዎች ጉዞ በሚያደርጉባቸው ወቅቶች እንዲሁም በበዓላቱ ወቅቶች የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት በሚንቀሳቀሱባቸው ሥፍራዎችና በሚያደርጓቸው የቆይታ ወቅቶች ሁሉ ሰላማቸው እንዲጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም ሕዝቡ በየደረጃው ካለው የአስተዳደር መዋቅር እንዲሁም ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ይህን ኃላፊነቱን መወጣቱን ማጠናከር ይኖርበታል።

የበዓላቱ በሰላም መከበር ፋይዳው ብዙ ነው። አንዱ በዓላቱ በተለመደው አግባብ ከተለመደውም አግባብ በላይ በድምቀት እንዲከበሩ ማስቻል ነው። ሌላው ደግሞ እነዚህ በዓላት ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ነው። የሀገር ገጽታ የሚገነባበት አንዱ መንገድ መሆኑም ይታመናል። እነዚህና ሌሎች የበዓላቱ መከበር ዓላማዎች በሚገባ እንዲሳኩ ዋናው መሳሪያ ሰላምና ሰላም ነው። በዓላቱ ያለ ምንም የጸጥታ ችግር የተከበሩበት ሁኔታ በዚህ ሳምንት በሚከበረው የእሬቻ በዓልም ላይ መደገም ይኖርበታል!

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You