አዲስ አበባ፡- ለትውልድ መልካም እሴትን ያሻገሩ አረጋውያንን ማክበርና ፍቅር መስጠት ሀገር ወዳድነት ነው ሲል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረጋውያንና ቤተሰብ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለሀገር በየተሠማሩበት ሃላፊነት ሃላፊነትን በመወጣት ብዙ ውለታ የሠሩ ፤ ለትውልድ መልካም እሴትን ያሻገሩ አረጋውያንን ማክበርና ፍቅር መስጠት ሀገር ወዳድነት ነው።
አረጋውያን ለሀገር ብዙ ውለታ ውለዋል፤ የዋሉትንም ውለታ መዘከር፤ ማከበርና ፍቅር መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል።
አረጋውያን የተሰጣቸውን ሃላፊነት በመወጣት መልካም እሴት ለትውልድ ጥለው አልፈዋል፤ ለጣሉትና ለሰሩት መልካም ሥራ ክብራቸውንና መብታቸውን ማከበርና አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ፍቅርና ክብር ለአረጋውያን መስጠት የዜጎች ግዴታ ነው፤ ለእነሱ ክብርና ፍቅር መስጠት ሀገርን መውደድ ነው፤ ሀገርን የሚወድ ማንኛውም ዜጋ መልካም እሴት የሰጡትን አባቶች መደገፍ አለበት ሲሉም አብራርተዋል።
አረጋውያንን ደስተኛ ማድረግ መልካምነት ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ መልካምነት ደግሞ የኢትዮጵያውያን ባህል በመሆኑ በዚሁ እሴት የመደገፍ ሥራ መሥራት ተገቢ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ምንም ጧሪና ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንን ለመደገፍ ራሱን የቻለ ሥርዓት እየተዘረጋ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በበጎ ፍቃድ በማህበር ተደራጅተው የአረጋውያን ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ማዕከላትን፣ ግለሰቦችን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ይበልጥ እንዲጠናከሩና እንዲስፋፉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ጠቁመዋል።
አረጋውያንን ለመደገፍ በጎ ፍቃድ ሥራ የተሠማሩ የተለያዩ ማህበራትን የማበረታታትና አስፈላጊውን ግብዓት የማሟላት ሥራ እየሠራ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
አረጋውያን በመደገፍ ለትውልድ መልካም እሴትን የማተላለፍ ሥራ እየተሠራ ነው፤ በድጋፉም የመሥራት አቅም ያላቸውን ጉልበት የማይጠይቁ ሙያዊ ነገሮችን እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር፤ ጡረታ የወጡትንም በሙያቸው ተደራጅተው አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመድን ፈንድ ፅህፈት ቤት በማቋቋም አረጋውያንን የመደገፍ ሥራ እየሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።
በስጋጃና መሰል ሙያዎች በርካታ አረጋውያንን የማሳተፍ ሥራ እየተሠራ ነው፤ በተለያዩ ሙያዎች አረጋውያንን ለማሳተፍ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ተጠናክሮም ይቀጥላል ሲሉ ጠቁመዋል።
በየክልሎች ምንም የገቢ ምንጭ የሌላቸው አረጋውያንን የገቢ ምንጭ የሚያገኙበት የሥራ እድል በመፍጠር የነፍስ ወከፍ ገቢ የሚያገኙበት መንገድ የመፍጠር ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አረጋውያንን በፋይናንስና በቴክኒክ መደገፍ፤ መሥራት ለሚችሉት የሥራ እድል መፍጠር ለሀገር ሁለተናዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ለአረጋውያን እየተደረገ ያለው በፋይናንስ የመደገፍ፤ የማቋቋም፣ ምቹ የሥራ እድል የመፍጠር ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው፤ ተጠናክሮም ይቀጥላል ሲሉ ጠቁመዋል።
የዓለም አረጋውያን ቀን በጋምቤላ ክልል ‹‹ ክብርና ፍቅር ለአረጋውያን›› በሚል መሪ ቃል በዓለም ለ34ኛ፤ በኢትዮጵያ ለ33ኛ ጊዜ በትናትናው ዕለት ተከብሮ ውሏል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም